Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live

ከህንዱ ኮንትራክተር የተነጠቀው የመንገድ ሥራ ለቻይናው ኮንትራክተር ተሰጠ

$
0
0

ሲው በተባለው የህንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመገንባት ላይ የነበረውና ባለፈው ዓመት ግንባታው የተቋረጠው የሐዋሳ - ጭኮ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ፣ ለቻይናው ሲኖኃይድሮ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጠ፡፡

66 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ የነበረውን የዚህን የመንገድ ፕሮጀክት ሲገነባ የነበረው ሲው የተባለው የህንድ ኮንትራክተር ቢሆንም፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታውን ማካሄድ አልቻለም በማለት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኮንትራቱን ባለፈው ዓመት አቋርጦበት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የመንገድ ግንባታው ተቋርጦ ከቆየ በኋላ፣ ሥራውን በአዲስ ኮንትራክተር ለማከናወን በወጣ አዲስ ጨረታ ሲኖኃይድሮ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

የህንዱ ኩባንያ የዚህን መንገድ ግንባታ ለማካሄድ በጨረታ አሸናፊ ሆኖ የተረከበው በ2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ በውሉ መሠረት መሥራት አልቻለም ተብሎ ኮንትራቱ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ከጠቅላላ ግንባታው 33 በመቶ ያህሉን አጠናቆ ነበር ተብሏል፡፡

ውሉ ከተቋረጠ በኋላ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል  በመንገድ ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም አላቸው ተብለው የተለዩ አምስት የውጭ ኮንትራክተሮች ተጋብዘው ነበር፡፡  ከአምስቱ ኮንትራክተሮች ሲኖኃይድሮ የተሻለ ዋጋ በማቅረቡ ኮንትራቱን ተፈርሟል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ ይገባል ተብሏል፡፡

ይህ ድጋሚ ጨረታ እንዲካሄድ የተደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ነው ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ በባንኩ ብድር የሚከናወን በመሆኑ፣ ጨረታው ከመደበኛ የጨረታ ሒደት ወጣ ያለና በመንገድ ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም አላቸው የተባሉትን በመጋበዝ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ሲኖኃይድሮ በጅምር የቀረውን የሐዋሳ - ጭኮ መንገድ ገንብቶ ለማጠናቀቅ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 965 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በ2005 በጀት ዓመት ሲው ኮንስትራክሽን ይህንን ፕሮጀክት ለመገንባት አሸናፊ የነበረበት ዋጋ 960 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ዋጋ ግንባታቸው የተቋረጡ መንገዶች ወደ ሌላ ኮንትራክተር ሲተላለፉ ከቀድሞው የበለጠ ዋጋ እየጠየቁ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

 

 

Standard (Image)

በአምቦ የኦሕዴድ ኃላፊንና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ሊገድሉ ነበር የተባሉ ተከሰሱ

$
0
0

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል መሆናቸውና በአምቦ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ኃላፊንና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ የኦሕዴድ ኃላፊ አቶ ያሬድ ተሾመንና የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ምትኩ ቴሶን በቦምብ ለመግደል ሲከታተሏቸው ነበር የተባሉት ተከሳሾች፣ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማና በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ባቲ ሙለታ ዋቅጅራ፣ መስፍን መኮንን መርጋ፣ ታፈሰ ደበሌ፣ ተፈራ ሙለታ፣ ሸንተማ ቀንአ፣ አስፋው አበራ፣ ጉቱ ሶሪ፣ እንደገና በቀለ፣ ፈይሳ ለማና አስማረ በላይ የተባሉ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ጫካዎችን ለተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጊያ ማጥናታቸውን፣ ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ በጨጫመነ ኤርጋ ቀበሌ፣ ልዩ ቦታው ሳቃ ጮጴ ወይም ሺሾ የተባለውን ጫካም መምረጣቸውን አክሏል፡፡

በተለይ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ባቲ ሙለታ ዋቅጅራ የተባለው ተከሳሽ፣ በተመረጠው ጫካ ውስጥ ካምፕ በመመሥረት አባላትን በሴል በማደራጀትና ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት፣ ሌሎቹ ተከሳሾች የሽብር ተግባር ወንጀል እንዲፈጽሙ አመራር በመስጠት ከኦነግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ ተከሳሹ በሁለቱ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲያደርስ እንደገና በቀለ የተባለውን ሌላኛውን ተከሳሽ ከማሰማራቱም በተጨማሪ፣ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ለመለመላቸው የኦነግ አባላት ያስገዛ እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡ እሱን የመለመለው በውጭ አገር የሚገኝ አባገርቡ የተባለ የኦነግ አባል መሆኑን፣ እሱም በአጭር ጊዜ 20 ሰዎችን መመልመል በመቻሉ ጫካ ገብተው ሥልጠና በመውሰድ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለማስወገድ ተጨማሪ ዝግጅት ማድረጊያ 6,700 ብር በባንክ እንደላከለት ክሱ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የኦነግን ተልዕኮ ለማስፈጸም በመዘጋጀትና በመንቀሳቀሳቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ለተከሳሾቹ ክሱ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ በክሱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ለኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቶ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ታክስ ባለመክፈል ወንጀል የተከሰሱ በአዲሱ ሕግ ነፃ ሆነናል ሲሉ ተከራከሩ

$
0
0

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በተከሰሱበት የወንጀል መዝገብ ቁጥር 141352 ተካተው የነበሩትና ከተመሠረተባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል በነፃ የተሰናበቱት አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔርን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች፣ እንዲከላከሉ ከተበየነባቸው ታክስ አለመክፈል ወንጀል በቅርቡ የወጣው ሕግ ነፃ እንዳደረጋቸው ተከራከሩ፡፡

እነ አቶ ነጋ ክሳቸውን እያየው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እንዳመለከቱት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. በፀደቀው ‹‹የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008›› መሠረት፣ ታክስ አለመክፈል በወንጀል ያስጠይቅ የነበረው ድንጋጌ ቀሪ ሆኗል፡፡ በመሆኑም እነሱ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው፣ ድርጅታቸው ኦዲት ሲደረግ በሒሳብ አሠራርና መዝገብ አያያዝ ምክንያት ታክስ አልከፈሉም ተብሎ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በአዲሱ አዋጅ እንደተገለጸው፣ ታክስ ላለመክፈል ሆን ብለውና ለመሰወር አስበው መሆኑ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ክሱ ቀሪ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3) መሠረትም ክሱ ቀሪ ሆኖ በነፃ መሰናበት እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው በእነ አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች ተከሳሾች ላይ በተመሳሳይ ወንጀል መዝገብ ቁጥር 141352 በቀረበው የወንጀል ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሳሾችን እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሠረት፣ የተከሳሾችን የመከላከያ ዝርዝር ለመቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን ተከሳሾቹ ከተለያዩ ሥፍራዎች እንዲቀርቡላቸው የጠየቋቸው ማስረጃዎች ተሟልተው ያልቀረቡ መሆኑን በማስረዳት፣ በድጋሚ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት አግኝቶ፣ ዝርዝር ማስረጃቸውን ለታኅሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

የ10ኛ ተከሳሽ የአቶ ከተማ ከበደና የ18ኛ ተከሳሽ የኬኬ ኩባንያ ጠበቆች፣ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ከመቅረፀ ድምፅ ተገልብጦ በሲዲ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለደኅንነት ሲባል ሲዲው እንዳይሰጥ ከበላይ አካል ትዕዛዝ የተሰጠ ስለሆነ ሊሰጣችሁ አይችልም መባላቸውን በመጥቀስ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ በተጨማሪም ተከላከሉ በተባሉበት ጉዳይ ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ ከተሰጣቸው የቀረበባቸውን ክስ የመከላከል መሠረታዊ መብታቸው ውጪ የጠየቁት ሲዲ ሊነፈጋቸው እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል በአግባቡ እንዳልተካተተ ማመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን በመቅረፀ ድምፅ ከተቀዳው ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ጋር በማመሳከር የመከላከያ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው በምንም ምክንያት ሊታለፍ እንደማይገባ አስረድተው፣ ሲዲው ካልተሰጣቸው የመከላከያ ዝርዝር ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ክርክሩን ከሚያዳምጡ በችሎት ከተሰየሙ ዳኞች ውጪ በችሎት ያልተሰየሙ፣ ክርክሩን በአካል ያላዳመጡና ያልነበሩ ዳኛ ፍርድ ቤቱ በሚሰጣቸው ትዕዛዞች ላይ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ተብለው በስም እየተጠቀሱ የሚተላለፉት ትዕዛዞች፣ በፍርድ ቤቱ ላይ እምነት እንዳይኖር ጥርጣሬን የሚፈጥርና ከዳኝነት ሥራና ሥነ ምግባር ውጪ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተከሳሾች የመከላከያ ዝርዝር እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዳኝነት አካሄድ ላይ በተከሳሾች የቀረበውን ተቃውሞ ተቀብሎ ስህተቱ እንደማይደገም አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ በነፃ እንዲሰናበቱ ባቀረቡት አቤቱታና አልተሰጠንም ስላሉት የምስክሮች ቃል (ሲዲ) ላይ ዓቃቤ ሕግ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለታኅሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

ሞሮኮ በ3.7 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ በድሬዳዋ ልትገነባ ነው

$
0
0

- ፋብሪካው ኢትዮጵያን በማዳበሪያ ራሷን ያስችላታል ተብሏል

ሞሮኮ በኢትዮጵያ በጠቅላላ የ3.7 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚገመት የማዳበሪያ ፋብሪካ በድሬዳዋ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ፈጸመች፡፡

የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት፣ ቅዳሜ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር የ3.7 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካና ሌሎች በርካታ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ 44 አባላት የያዘው የሞሮኮ ቢዝነስ ቡድን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሞሮኮ ባለሀብቶች የራሳቸው ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነቡ የኢትዮጵያ መንግሥት መሬት በነፃ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡

የማዳበሪያው ፋብሪካውን የሚገነባው ድርጅት (ኦሲፒ አፍሪካ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙስጠፋ ቴራፕ ከስምምነቱ መፈረም በፊት እንደተናገሩት፣ በድሬዳዋ አካባቢ ለመገንባት የታሰበው ይኼው ፋብሪካ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ በ2022 ግንባታው ሲጠናቀቅም ፋብሪካው በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት ይችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ራሷን በማዳበሪያ ያስችላታል ተብሎ የተገመተው ይኼው ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፋብሪካ፤ እ.ኤ.አ በ2025 የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ሲደረግበት በአጠቃላይ በዓመት 3.8 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፋብሪካው ኢትዮጵያ በማዳበሪያ ራሷን እንድትችል ከማስቻል አልፎ ወደ ውጭ መላክ እንደሚያስችላት በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት ይኼው ፕሮጀክት ወጪው ሙሉ ለሙሉ በሞሮኮ የሚሸፈን ሲሆን፣ የፕሮጀክት ግንባታው ከኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግሥቱ የተፈጸመው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ሁለቱ አገሮች ሌሎች አምስት ስምምነቶችና የጋራ መግባባቶችም ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በምግብ ምርት፣ እንዲሁም በኢነርጂና በማዕድን ፍለጋ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ሞሮኮ ማዳበሪያና ሌሎች ተያያዥ ምርቶች በማምረት በአፍሪካ ግንባር ቀደም አገር ስትሆን፣ ኩባንያው በውጭ አገሮች ካከናወናቸው ግንባታዎች ትልቁ ፕሮጀክት መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ 

Standard (Image)

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሚመራ ልዑክ በሳዑዲ ዓረቢያ የሥራ ጉብኝት አደረገ

$
0
0

- በኤርትራ የተቋቋመው የሳዑዲ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አንዱ መወያያ ነበር

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ በመገኘት፣ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና የፀጥታ ጉዳይ ላይ መምከሩ ተገለጸ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተመራው የባለሥልጣናት ቡድን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያመራው እሑድ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

የዚህ ጉዞ ዓላማ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ሳዑዲ ዓረቢያ በኤርትራ በመሠረተችው ወታደራዊ ጦር ላይ መነጋገር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑክ ውስጥ የተካተቱት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ሱፊያን አህመድና ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያመራው በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳና አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ መሐመድ ቢን ናይፍ አብዱላዚዝ ጋር በፀጥታ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ውይይት የየመንን የውስጥ ቀውስ ለመቅረፍ በሳዑዲ የሚመራው የዓረብ አገሮች ጥምረት በኤርትራ ወታደራዊ ጦር ሠፈር መመሥረቱ ችግር የሌለው ቢሆንም፣ በዚህ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አማካይነት የኤርትራ መንግሥትና መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያገኘ ስለመሆኑ፣ ይህም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው ሥጋት እንደሆነ ማስረዳት አንደኛው ተልዕኮ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የኤርትራና ሶማሊያ ማዕቀብ ትግበራ አጣሪ ቡድን ኅዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በኤርትራ ያቋቋሙዋቸው የአየርና ኃይልና የባህር ኃይል ጦር ሠፈሮች ለኤርትራ መንግሥትና ወታደራዊ ኃይል አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን መረጃ እንዳለው፣ ይህም ሥጋት እንደፈጠረበት መጥቀሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ አባላት ዶ/ር አብርሃም ተከስተና አቶ ሱፊያን አህመድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን የሳዑዲ ኢንቨስተሮች በተለይ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ፣ እንዲሁም በቆዳ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ቢሰማሩ ሁለቱም አገሮች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማስረዳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Standard (Image)

ለአዳማ ከተማ ሴት ከንቲባ ተሾሙ

$
0
0

ከአዲስ አበባ በምሥራቅ አቅጣጫ 85 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው የንግድ ከተማ አዳማ፣ ሴት ከንቲባ ተሾመላት፡፡ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ከተሞች ታሪክ ብቸኛዋ ሴት ከንቲባ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

ባለፈው እሑድ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በሚገኘው አባ ገዳ አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡ የከተማው ነዋሪዎች አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የወ/ሮ አዳነችን ሹመት ይፋ አድርገዋል፡፡

በወቅቱ ብዙም ባልተለመደ መንገድ የሕዝብ አደረጃጀት ወደ ጎን ተደርጎ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ለስብሰባ የተጠሩ ሲሆን፣ ስብሰባውም በአማርኛ ቋንቋ ተካሂዷል፡፡

አዲሷ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የልማት ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ለማካሄድ የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡

‹‹የከተማውን ሕዝብ ችግር መስማት ያስፈልጋል፡፡ ለውጥን ታሳቢ በማድረግ ከሕዝብ ጋር በሚያግባባ መንገድ መገናኘት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የልማት በተለይም ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የመኖርያ ቤት አቅርቦትና የመሳሰሉ ችግሮች መንሰራፋታቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ወ/ሮ አዳነች የአዳማ ከተማ ከንቲባ የነበሩትን አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል ተክተዋል፡፡ ሌሎች የካቢኔ አባላትም መነሳታቸው ታውቋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ እንግሊዝ ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ባለፉት 18 ዓመታት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የጨፌ ኦሮሚያ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢም ናቸው፡፡

ወ/ሮ አዳነች ለስድስት ዓመት በቆዩበት የኦሮሚያ ልማት ማኅበር የሚያስመሰግን ሥራ መሥራታቸው ተገልጿል፡፡ በተለይ 700 ሺሕ አባላት የነበሩትን የኦሮሚያ ልማት ማኅበር የአባላቱን ቁጥር ወደ 6.2 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡

የኦሮሚያ ልማት ማኅበር የፋይናንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ሙላቱ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር የሕዝብን ችግር የሚፈታ ማዕከል አድርገውታል፡፡ 

Standard (Image)

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

$
0
0

ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ተነሱ፡፡

ባለፈው ዓርብ ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ፊርማ በወጣ ደብዳቤ፣ አቶ ኢሳያስ  ከፕሬዚዳንትነታቸው መነሳታቸው ተገልጾላቸዋል፡፡

‹‹የተነሳሁበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በትኩስ ኃይል እንዲመራ ለማድረግ ከሆነ ግን መነሳቴ መልካም ነው፤›› ሲሉ አቶ ኢሳያስ የተነሱበትን ምክንያት እንደማያውቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ የተነሱበት ደብዳቤ ዓርብ ከቀትር በኋላ እንዲደርሳቸው ከመደረጉ በፊት፣ ጠዋት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራ ስብሰባ ተካሄዶ እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ፣ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀና አቶ ኢሳያስን ጨምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በሚቀርቡ የእርሻ መሬቶች፣ እንዲሁም ብድርን በተመለከተ የተፈጠሩ ችግሮች ላይ በተሰናዳ ጥናት ላይ ለመነጋገር ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተቋቋመ ኮሚቴ በተካሄደው ጥናት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አፈጻጻም በመልካም ጎኑ መነሳቱን የተናገሩት ምንጮች፣ በስብሰባው ሒደት ግን አለመግባባቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የመጀመርያው ወራት በአገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ከማበብ ይልቅ ችግራቸው እየጎላ በመምጣቱ፣ ሙሉ ለሙሉ ለዘርፉ መሬትና ብድር እንዳይቀርብ ታግዷል፡፡

ይኼ ዕግድ ሊወጣ የቻለው በተለይ በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ የእርሻ ኩባንያዎች የተሰጠው መሬት የተደራረበ በመሆኑ፣ በሁለት ኩባንያዎች ተደራርቦ ለተሰጠ መሬት ሁለት ጊዜ ብድር መሰጠቱ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሙስና አመላካች ክስተቶች በመኖራቸው ነው ተብሏል፡፡

ይኼ ችግር እንዴት ሊፈጠር እንደቻለና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካይነት የተቋቋመው ኮሚቴ ጥናት አካሄዷል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ማሻሻያዎች ተደርገው የታገደው የመሬትና የብድር አሰጣጥ በድጋሚ ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ ሌሎች ነጥቦች የተነሱ ቢሆንም የችግሩ ማጠንጠኛ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር፣ የመሬት አሰጣጥ ሒደትና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ በዚህ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጣቸው ብድሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደ ባንክ መርህ በመስኖ ለሚካሄዱ ሜካናይዝድ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠት ይሻል፡፡ ነገር ግን መሬት አስተዳደር የዝናብ ጥገኛ ለሆኑ ፕሮጀክቶች ብድር እንዲቀርብ ፍላጎት አለው፡፡ መንግሥት በዝናብ ጥገኛ ለሆኑ ፕሮጀክቶችም ብድር እንዲቀርብ መመርያ በመስጠቱ ባንኩ ብድር ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ለተፈጠሩ ችግሮች የመሬት አሰጣጡ ችግር እንዳለበት አቶ ኢሳያስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መሬት ለአልሚዎች የሚቀርበው በሁለት መንገዶች ነው፡፡ የመጀመርያው የግብርና መሬት አስተዳደር ከክልሎች በውክልና የሚወስዳቸውን መሬቶች ለአልሚዎች ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ክልሎች በራሳቸው መንገድ ለአልሚዎች መሬት ያቀርባሉ፡፡

አልሚዎች ከእነዚህ አካላት የወሰዱትን መሬት ለማልማት አስፈላጊ መሥፈርቶች አሟልተው ሲቀርቡ ባንኩ ብድር ይሰጣል፡፡ በተደረገው ስብሰባ መልማት ላልቻሉ መሬቶች ተጠያቂ በሚሆነው አካል ማንነት ጉዳይ ላይ ሲሆን፣ ልማት ባንክ ለችግሩ ተጠያቂ የግብርና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከቀድሞ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪ፣ እንግሊዝ ከሚገኘው ዌልስ ዩኒቨርሲቲ በባንኪንግና ፋይናንስ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

በሥራው ዓለም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ22 ዓመታት ከኦፊሰርነት እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የሠሩ ሲሆን፣ የኤቲኤም አሠራርን ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንዳስተዋወቁ ይነገርላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የሠሩ ሲሆን፣ እሳቸው ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የተበላሹ ብድሮች እየቀነሱ መምጣታቸውና የቦንድ ሽያጭ ማስጀመራቸው ከሚጠቀሱላቸው ለውጦች ውስጥ ናቸው፡፡

Standard (Image)

ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ ብረት መጥፋቱ ተጠቆመ

$
0
0

- ኃላፊዎቹ ‹‹አልነበርንም አልሰማንም›› ብለዋል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የገዛው በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች የተጫነ ብረት፣ ከነተሽከርካሪዎቹ መጥፋቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ኢንተርፕራይዙ እያስገነባቸው ለሚገኙት የ40/60 የቁጠባ ቤቶች መሥሪያ የሚውል፣ በሚሊዮኖች ብር የተገዛ ብረት አቃቂ በሚገኘው የዋናው ሳይት መጋዘን የሚያከማች ቢሆንም፣ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነና መጠኑ ለጊዜው ያልታወቀ ብረት መጥፋቱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ መጋዘኑ የሄዱት ተሽከርካሪዎች ብረቱን ሳያወርዱ ወደ ሌላ ሳይቶች እንዲወስዱ በመጋዘኑ ኃላፊዎች መታዘዛቸውንና የመረካከቢያ ሰነድ ሳይለዋወጡ እንዳልቀሩ የገመቱት ምንጮች፣ በዕለቱ ወይም በማግሥቱ ማድረስ የነበረባቸው ቢሆንም የት እንደደረሱ አልታወቀም ብለዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከነብረቱ የተሰወሩት ወይም እንዲጠፉ የተደረገው፣ በተደራጀና በሚገባ በታሰበበት ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለ ምንጮች አክለዋል፡፡ ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎችና በተለያየ መንገድ ክትትል እየተደረገበት ስለሆነ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ይውላል የሚል እምነት እንዳለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከጫኑት ብረት ጋር ስለመጥፋታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ የኢንተርፕራይዙን የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዓባይነህን ሪፖርተር ጠይቋቸው፣ ‹‹እኛ ጅግጅጋ ሥራ ላይ ከርመን ገና እየተመለስን ነው፡፡ አልነበርንም፣ አልሰማንም፡፡ ሥራ አስኪያጁ አቶ ኃይሉ ቀንዓም አብረውኝ ናቸው፡፡ ምንም የሰማነው ነገር የለም፤›› በማለት ድርጊቱን ከመግለጽ ይልቅ መሸፈን መርጠዋል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ሲኖትራክ በፋብሪካው ትዕዛዝ መሠረት 150 ኩንታል ብረት የሚጫን ሲሆን፣ እዚህ አገር ግን እስከ 200 ኩንታል ብረት የሚጭኑበት አሉ፡፡ 15 ሲኖትራኮች ላይ ተጭኖ ጠፋ የተባለው ብረት በምን ያህል መጠን እንደተጫነ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ከፍተኛ መጠን እንደሚኖረው ግን መጠራጠር አይቻልም ሲሉ ባለሙያዎች ያክላሉ፡፡

የ40/60 የቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር መሠረት 39 ሺሕ ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተደረገው ምዝገባ 163 ሺሕ ነዋሪዎች ሲመዘገቡ፣ ከ13 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ክፍያ አጠናቀዋል፡፡ በቅርቡም የ1,292 ቤቶችን ዕጣ ለማውጣት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ባንኩ በራሱ ዕጣውን የሚያወጣው ከአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶቹን በመረከብ ነው፡፡  

 

 

Standard (Image)

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በመንገዶች ጥገና ተጠምዷል

$
0
0

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የተጎዱ መንገዶችን የመጠገን ዘመቻ ውስጥ የገባው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ባለፉት 51 ቀናት 159 ሺሕ ካሬ ሜትር ርዝመት ያላቸውን የከተማዋን መንገዶች ጥገና ማድረጉን ሲያስታውቅ፣ ለትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ከሆኑ አደባባዮች መካከል የ18 ማዞሪያ አደባባይን ከረቡዕ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማፍረስ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በበጀት ዓመቱ ዋነኛ ሥራውን በከተማው መንገድ ጥገና ላይ በማዋል፣ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንቅፋት የሆኑ የተጎዱ መንገዶችን በመጠገን ላይ ነው፡፡ በተለይ በቀለበት መንገዱ ላይ የነበሩ መንገዶችን አብዛኛውን ክፍል አጠናቋል፡፡

በሌሎች የከተማው አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው መንገዶችን በተለይ ሌሊት ሌሊት በሚያካሂደው ጥገና፣ እስካሁን ወደ 159 ሺሕ ካሬ ሜትር የተበላሹ መንገዶች መጠገናቸውንና የትራፊክ ፍሰቱን እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉ ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ጥገናዎች የተጨናነቀውን የከተማውን የትራፊክ ፍሰት ሙሉ ለሙሉ የሚፈቱ ባይሆንም፣ ችግሩን ለማቃለል የሚረዱ በመሆኑ የጥገና ሥራውን በቀሪው የከተማው ክፍል ባሉ መንገዶች ላይ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ በተለይ ለትራፊክ መጨናነቅ ዋነኛ ማነቆ ናቸው ተብለው በተለዩ መንገዶች ላይ ያሉ የጥገና ሥራዎችን ቀድሞ ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡ አሁን ደግሞ አደባባዮችን በማፍረስ ተሽከርካሪዎችን በትራፊክ መብራት እንዲስተናገዱ ወደሚያስችለው ሥራ እየገባ ነው፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት ባለሥልጣኑ ሊፈርሱ ይገባቸዋል ብሎ ከለያቸው 18 አደባባዮች ውስጥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ጀሞ በሚሄደው መንገድ የሚገኘውን ሚካኤል አደባባይን በማፍረስ ጀምሯል፡፡ አደባባዩ ከፈረሰ በኋላም የትራፊክ መብራት ተክሏል፡፡ በአደባባዩ ዙሪያ ተጨማሪ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ረቡዕ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ የ18 ማዞሪያ አደባባይን በማፍረስ፣ ተሽከርካሪዎች በትራፊክ መብራት እንዲስተናገዱ የሚያደርግ ሥራ እንደሚያከናውን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ለትራፊክ ፍሰቱ እንቅፋት የሆኑ 14 አደባባዮች በዙሪያቸው የሚገኙ ብልሽቶች ተጠግነዋል፡፡ ከፒያሳ ጀምሮ በቸርችል ጎዳና፣ በብሔራዊ ቴአትር፣ በአምስት ኪሎ፣ በካዛንችስና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የተበላሹ መንገዶችን በሦስት ቡድኖች በተዋቀረ ግብረ ኃይል የጥገና ሥራውን እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአምስቱ ቀናት ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ለጥገና ወጪ ተደርጓል፡፡ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለሚካሄዱ ጥገናዎች 270 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡

ቀሪዎቹን አደባባዮች በየተራ የማፍረሱ ሥራ እንደሚቀጥል የሚገልጹት የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ በቀጣይ ግን ዋና ዋና በሚባሉት አደባባዮች ላይ ተላላፊ መንገዶችን ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በ2009 በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው ጥገና ላይ በመሆኑ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታዎችን አቀዝቅዟል፡፡

 

Standard (Image)

እስራኤል የኤርትራ ስደተኞችን ወደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ሸኘች

$
0
0

ለዓመታት በእስራኤል በጥገኝነት የቆዩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ተሸኙ፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው የአፍሪካ ስደተኞች ውስጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሕጋዊ የመኖርያ ፈቃድ የተሰጠው ለአራት ሰዎች (0.7 በመቶኛ) ብቻ መሆኑን የአልጄዚራ ዘገባ ገልጿል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከ42 ሺሕ በላይ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞች እንደሚኖሩም አመልክቷል፡፡

በቅርቡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ማሻገሯን የሚጠቁመው ይህ ዘገባ፣ ስደተኞቹን ወደ ኪጋሊ (ሩዋንዳ) እና ካምፓላ (ኡጋንዳ) እንዲሸኙ ከመደረጉ በፊት ሦስት አማራጮች እንደቀረበላቸው ያስረዳል፡፡

አማራጮቹ በስደተኞች ካምፕ መቆየት፣ ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርና ወደ ኤርትራ ተገደው እንዲመለሱ መደረግ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ምርጫቸው ወደ ሦስተኛ አገር መሻገር ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እያንዳንዳቸው ሦስት ሺሕ ዶላር ይዘው ወደ ሁለቱም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተሸኙት ኤርትራዊያን ስደተኞች፣ ብዙዎቹ በሰሃራ በረሃ በማቆራረጥ ለወራት ተጉዘው እስራኤል ውስጥ ገብተው ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ የቆዩ ናቸው፡፡ አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ጥያቄ ቢያነሱበትም፣ የእስራኤል ባለሥልጣናት ይህ የተደረገው በስደተኞቹ ፍፁም ፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ነው ብለዋል፡፡

የቢቢሲና የአልጄዚራ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ስደተኞቹን ከእስራኤል ተቀብለው የሚያስተናግዱት ቀድመው ከአገሪቱ ጋር በገቡት ውል መሠረት ነው፡፡

የኡጋንደና የሩዋንዳ ባለሥልጣናት ቢክዱም የእስራኤል ሥነ ሕዝብና ኢሚግሬሽን ቃል አቀባይ ሰቢን ሃዳድ ከሁለት የአፍሪካ አገሮች ጋር ስደተኞችን ለማፈናቀል እስራኤል ስምምነት እንዳላት ተናግረዋል፡፡ የሚዲያዎቹ ዘገባ እንደሚለው፣ እስራኤል ከሁለቱ አገሮች ጋር ያደረገችው ስምምነት በምላሹ የጦር መሣርያ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡   

 

Standard (Image)

ለውስብስብ ችግሮች ተዳርገናል ያሉ የግብርና ኢንቨስተሮች ምሬታቸውን ገለጹ

$
0
0

በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተንሰራፍቶ የቆየውን ችግር በቅጡ ለመረዳትና መፍትሔ ለመስጠት አዲሱ የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር እያሱ አብረሃ፣ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠሩት ስብሰባ ባለሀብቶች ምሬታቸውን ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱ አዳዲስ ሚኒስትሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር እያሱ፣ በበርካታ ችግሮች የተተበተበው የግብርና ኢንቨስትመንት ያለበትን ደረጃ ለማወቅና መፍትሔም ለማበጀት ይህንን ስብሰባ ቢጠሩም፣ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሟቸው ስብሰባውን አቋርጠው ሄደዋል፡፡

በእሳቸው ምትክ ከአንድ ዓመት በፊት የተሾሙት የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር ስብሰባውን መርተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ 100 የሚጠጉ ከፌዴራል መንግሥት መሬት የወሰዱ የግብርና ኢንቨስተሮች የተገኙ ሲሆን፣ የመናገር ዕድል የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ቢሆኑም መፍትሔ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ እየመከነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ካሉት ችግሮች መካከል የመሬት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማት፣ የብድር አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

በመሬት አሰጣጥ በኩል የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውክልና የወሰደውን መሬት፣ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ለባለሀብቶች ይሰጣል፣ ያስተዳድራልም፡፡

ነገር ግን ኤጀንሲው በሰጠው መሬት ላይ ችግር ሲያጋጥም መፍትሔ እንዲሰጡ የሚጠበቁት ክልሎች ናቸው፡፡ ይህ አሠራር ለዘርፉ ማነቆ ሆኗል በማለት በስብሰባው ላይ ተነስቷል፡፡

የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲው በተለይ በጋምቤላ ክልል የሰጣቸው ቦታዎች መደራረብ የሚታይባቸው በመሆኑ ከፍተኛ ችግር አጋጥሟል፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት በዘርፉ ችግር እንዳለ አምነው፣ በተለይ በጋምቤላ ክልል በታችኛው መዋቅር የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ለዘርፉም ብድር እየቀረበ አለመሆኑን አቶ አበራ ጠቅሰው፣ የብድር አቅርቦት ግን የእሳቸውን መሥሪያ ቤት እንደማይመለከት አስረድተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሀብቶች በመጀመሪያ ደረጃ ኤጀንሲው በትክክል የማያስተዳድረውን የእርሻ መሬት ለምን ይሰጣል? ኤጀንሲው በሰጠው መሬት ላይ ችግር ሲፈጠር ክልሎቹ እንዲፈቱት መጠበቅ አግባብ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለግብርና ኢንቨስትመንት ብድር እንዳይቀርብ በደብዳቤ የጠየቀው መሬት አስተዳደር ኤጀንሲው ራሱ መሆኑን ባለሀብቶቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ቢያቆም እንኳ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ እንደመሆኑ፣ የታገደው ብድር አሰጣጥ እንዲጀመር ማድረግስ አልነበረበትም ወይ?›› በማለት አንድ ባለሀብት ጠይቀዋል፡፡

የጥጥ ኢንቨስትመንት የግብርና ሥራ ቢሆንም፣ የጥጥ ጉዳይን የሚከታተለው ዳይሬክቶሬት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እንዲገባ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት አዋጁ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሀብቶችን በመወከል የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሟሉ ያደርጋል የሚል ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ይህንን አድርጎ እንደማያውቅ ባለሀብቶች በምሬት ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ኢንቨስት ለማድረግ ቦታ የወሰዱ ኢንቨስተሮችም ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ኦሞ ለዓመታት መጠናቀቅ ያልቻለውና በአንድ ወቅት በመገንባት ላይ የነበረው የኦሞ ድልድይ በድጋሚ ችግር ውስጥ በመሆኑ፣ በጥልቀት ወደ እርሻ ሥራ መግባት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ እያሉ ግን የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲው ማስጠንቀቂያ ከሰጣቸው ኩባንያዎች መካከል ኦሞ ቫሊ፣ ዳሰኒ እርሻ፣ ዶ/ር ጠአመ እርሻ፣ ዳሰነች እርሻ፣ ጉቲት እርሻ ልማት ይገኙበታል፡፡

እነዚህ የእርሻ ልማት ድርጅቶች በራሳቸው ፋይናንስ በተወሰነ ደረጃ ሥራ እየሠሩ ቢሆንም፣ ድልድዩ ተጠናቆ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ሰጥቷቸው በስፋት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተስፋ ቢያደርጉም፣ ድልድዩ መጠናቀቅ ካለመቻሉም በላይ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ኤጀንሲው ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ማስጠንቀቂያ መጻፉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

የባለሀብቶቹን ቅሬታ የሰሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰዓዳ ችግሮቹን መረዳታቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ለባለሀብቶቹ ዕገዛ ለማድረግ የሚያስችለውን ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ቃል ገብተዋል፡፡

መንግሥት ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚመለከተውና በአጭር ጊዜም መፍትሔ እንደሚሰጥ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

በ11ኛው ዙር ዕጣ ከወጣባቸው ቤቶች ውስጥ የ7169 ቤቶች ዕድለኞች አለመቅረባቸው ተገለጸ

$
0
0

- በታኅሳስ የመጀመሪያ ሳምንት ዕጣ ይወጣባቸዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕጣ ካወጣባቸው ከ30,000 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ፣ ለ7,169 ቤቶች ዕጣ የወጣላቸው ግለሰቦች ሊቀርቡ አለመቻላቸውን የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ዕጣ የወጣባቸውን ቤቶች እስከ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ተሰጥተው መጠናቀቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ የውል መዋዋያ ቅጽ ከወሰዱ 29,465 ግለሰቦች ውስጥ 6,035 ቅጹን አለመመለሳቸውን፣ 1,134 ደግሞ ቅጽ አለመውሰዳቸውን የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት ሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. አስረድተዋል፡፡ 

በ11ኛው ዙር ዕጣ የወጣላቸው የሚስተናገዱት ወይም የሚያገኙት አገልግሎት በአዲስ አሠራር በአንድ መስኮት ማለትም ማንኛውንም ውል የሚፈጽሙት እንደ ቀድሞዎቹ ባለ ዕጣዎች በተለያየ ቦታ ሳይሆን በአንድ ቦታ መሆኑን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ዕጣ የወጣላቸው ሳይንገላቱ በአንድ ቦታ የሚያገኙትን አገልግሎት እስከ ታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ቀርበው እንዲፈጽሙ አሳስበዋል፡፡ ይኼኛው መግለጫና ማስታወቂያ የመጨረሻ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ከታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በራሳቸው ፈቃድ እንደተውት ተቆጥሮ እንደሚሰረዙ አስታውቀዋል፡፡

ቀደም ብለው እንደገለጹት፣ በግዳጅ ላይ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች አስገዳጅ የመንግሥት ሥራ ላይ የነበሩ ግን ማስረጃቸውን ይዘው ሲቀርቡ እንደሚስተናገዱ አስረድተዋል፡፡ 

Standard (Image)

ልማት ባንክ የብድር ፖሊሲውን በድጋሚ እንዲከልስ ታዘዘ

$
0
0

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፈው ዓመት ያሻሻለውን የብድር ፖሊሲውን በድጋሚ በመከለስ፣ በአበባና በፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን የተሻለ ብድር ተጠቃሚ እንዲያደርግ መታዘዙን ምንጮች ገለጹ፡፡

ትዕዛዙ የመጣው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ባንኩ በአበባና በፍራፍሬ ምርት ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን በዝቅተኛው የብድር ማስያዣ ምጣኔ እንዲያስተናግድ የሚያዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቀድሞ ሲገለገልበት የነበረውን የብድር ፖሊሲ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ አሻሽሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከባንኩ የኢንቨስትመንት ካፒታል ብድር ማግኘት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች 50/50 በሚባለው የብድር ምጣኔ እንዲስተናገዱ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ደግሞ ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረውን 70/30 ምጣኔ በማስተካከል 75/25 ምጣኔ እንዲስተናገዱ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሰሞኑን በሰጠው ውሳኔ መሠረት፣ በአበባና በፍራፍሬ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች በሌሎች ዘርፎች ከሚሳተፉ ኢንቨስተሮች በተለየ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያውያን በ75/25 የብድር ምጣኔ እንዲስተናገዱ ማዘዙን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚፈልጉ በአበባና በፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች የጠየቁትን የብድር መጠን 25 በመቶ ሲያስይዙ፣ 75 በመቶ ብድር እንዲያገኙ ውሳኔ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርየም ደሳለኝ የሚመራው የኢንቨስትመንት ቦርድ በአበባና በፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን የተሻለ ድጋፍ ለመስጠት የወሰነው፣ ዘርፉ በፈጠረው ከፍተኛ የሥራ ዕድል ምክንያት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የአበባና የፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ ዕድሜ ቢኖረውም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመጫወት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ በአበባና በፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የተያዙ እርሻዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የውጭ ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ በተለይም በገጠርና ከፊል ከተሞች ለሚገኙ ሴቶች ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ ሰፊ የአበባ እርሻ የያዘው አፋር ፍሎራ ለብቻው ለስድስት ሺሕ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም ይኼው ዘርፍ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኗል፡፡ በ2008 ዓ.ም. 275 ሚሊዮን ዶላር አስገብቷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢንቨስትመንት ቦርድ ከዚህ ውሳኔ አስቀድሞ በነበረው ሌላ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው 23 የአበባ እርሻዎች የአንድ ዓመት የታክስ እፎይታና የቀረጥ ነፃ መብት መወሰኑን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

Standard (Image)

የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛወሩ

$
0
0

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቱሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ፡፡

በኦሮሚያ ክልል አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ፊርማ ሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣ ደብዳቤ፣ አቶ አህመድ ቱሳ ለአምስት ዓመታት በኃላፊነት ከሠሩበት ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ተነስተው ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛውረዋል፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት ባለሁበት ቦታ እንድቆይ ቢፈልግም፣ የኦሮሚያ ክልል መዋቅሮችን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሶ እንድዛወር ተደርጓል፤›› ሲሉ አቶ አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ አህመድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩ ሲሆን፣ በኋላም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ኮርፖሬሽን፣ የደረቅ ወደብ አስተዳደርና የባህር ትራንዚት ባለሥልጣን አንድ ላይ ሆነው የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግለዋል፡፡

አቶ አህመድ የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን ውጤታማ እንደነበር ቢገልጹም፣ የማይስማሙ አሉ፡፡ እነሱም በአምስት ዓመት ውስጥ በርካታ ሙያተኛ ሠራተኞች ድርጅቱን መልቀቃቸውን፣ የደረቅ ወደቦችና የባቡር መስመር ሳይጣጣሙ መቅረታቸውን፣ የደንበኞች እርካታ መቀነሱንና የማኔጅመንትና የሠራተኞች ግንኙነት መዳከሙን ይጠቅሳሉ፡፡

በእነዚህ ነጥቦች ላይ የኢንተርፕራይዙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በነበሩበት ዘመን ግምገማ መደረጉን፣ ሰሞኑን በኦሮሚያና በፌዴራል መንግሥት መዋቅሮች በተካሄዱ ግምገማዎችም እነዚህ ነጥቦች ነጥረው መውጣታቸውን ያስረዳሉ ይላሉ፡፡

ነገር ግን አቶ አህመድ እነዚህን ክሶች አይቀበሏቸውም፡፡ አቶ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋይናንስን በተመለከተ በ2003 ዓ.ም. የመሥሪያ ቤቱ ገቢ አንድ ላይ ተደምሮ 4.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ግን ይህ ገቢ በአራት እጥፍ ጨምሮ 16.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል ሲሉም ያክላሉ፡፡

የመልቲ ሞዳል አሠራር በ2004 ዓ.ም. ሲጀመር በዓመት አሥር ሺሕ ኮንቴይነር የማንሳት አቅም ነበር፡፡ ነገር ግን በ2008 ዓ.ም. ኮንቴይነር የማንሳት አቅም 175 ሺሕ ደርሷል፡፡

የደንበኞች እርካታን በሚመለከት አቶ አህመድ ሲያስረዱ፣ በ2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደንበኞች እርካታን በሚመለከት ጥናት ተካሂዷል፡፡

በገለልተኛ ባለሙያዎች በተካሄደው በዚህ ጥናት 71.6 በመቶ የሚሆኑ ደንበኞች በድርጅቱ አገልግሎት እንደረኩ መግለጻቸውን በመጥቀስ፣ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ አቶ አህመድ የደንበኞች እርካታ የደረሰበትን ደረጃ አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ ወደቡ ሲጨናነቅና የትራንስፖርት እጥረት ሲያጋጥም ደንበኞች ሊማረሩ እንደሚችሉ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

 

Standard (Image)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የነበሩት አቶ ነዋይ ገብረአብ ጡረታ ወጡ

$
0
0

- አቶ መኮንን ማንያዘዋል የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ላለፉት 20 ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ነዋይ ገብረአብ ጡረታ መውጣታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡

አቶ ነዋይ በኢኮኖሚ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት (EDRI) ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይም ነበሩ፡፡

በጡረታ የተገለሉት አቶ ነዋይ ከአማካሪነት ቦታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸውም መነሳታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በምትካቸው የተሾሙት የቀድሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ቀጥሎም የመጀመሪያው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ መኮንን ማንያዘዋል መሾማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ መኮንን የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሆነው ቢሾሙም ገና የቢሮ ርክክብ አለመደረጉ ተረጋግጧል፡፡ የተቋሙ ሠራተኞች ሹመቱን በይፋ እንዳልሰሙ ተናግረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት አቶ ዕውነቱ ብላታ ደበላ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ አቶ ነዋይ ጡረታ ስለመውጣታቸው ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚሉ አደረጃጀቶች መቅረታቸውን ግን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች በሒደት ሌላ ቦታ ሊመደቡ እንደሚችሉ፣ ጊዜያቸውን የጨረሱ ደግሞ በጡረታ እንደሚሰናበቱ አክለዋል፡፡ 

Standard (Image)

ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል የአርማታ ብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች ተያዙ

$
0
0

- 101 ጥቅል ብረት በቁጥጥር ሥር ውሏል

መንግሥት በልዩ ፕሮግራም ከያዛቸው የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ ለሆነው የ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል፣ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ የአርማታ ብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

ወንጀሉን በዋናነት ያቀናበሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የግብዓት፣ ክምችትና ሥርጭት ሙያተኛ፣ ባለሀብቶችና ተባባሪዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አባላትና በሌሎች የፀጥታ ሠራተኞች ትብብር በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ባልደረባ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለእያንዳንዳቸው የሲኖትራክ ሾፌሮች 2,000 ብር ለመክፈል በመስማማት በ15 ሲኖትራኮች ጎፋ ከሚገኘው የኢንተርፕራይዙ ማዕከላዊ መጋዘን ባለ 8 የብረት ዓይነት 67 ጥቅልና ባለ 6 የብረት ዓይነት 34 ጥቅል፣ በድምሩ 101 ጥቅል ብረት እንዲጫን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ስማቸው ለጊዜው እንዲገለጽ ያልተፈለገ ባለሀብት በ15 ሲኖትራኮች የተጫኑትን ብረቶች ሰበታ አካባቢ ከሚገኘው ፋብሪካቸው ውስጥ እንዲወርድ ካደረጉ በኋላ፣ መርካቶ አካባቢ ለሚገኙ ግብረ አበሮቻቸውና ወደ አዳማ በሽያጭ እንዲሠራጭ ማድረጋቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ፖሊሶች ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት ትብብር፣ ከኢንተርፕራይዙ ወጥቶ የተበተነው የአርማታ ብረት ደብዛው ሳይጠፋ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡ የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ ለጊዜው ተሰውረው እንደነበር ምንጮች አክለዋል፡፡

ባለሀብቶቹን፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንና ብረቱን በአጭር ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ያዋለው ፖሊስ፣ የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ ለጊዜው ከተሸሸጉበት ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደ አዲስ አበባ እንዳመጣቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸውና ሌሎች ተባባሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎች እያደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ብረትም በኤግዚቢትነት ተይዞ በፖሊስ ልዩ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕትም ‹‹ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ ብረት መጥፋቱ ተጠቆመ›› በሚል ርዕስ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ 

Standard (Image)

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆኑ

$
0
0

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ጌታሁን ናና፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ የቀረበው ሹመት ፀደቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አቶ ጌታሁን የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ ሾሟል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ሹመቱን ተቀብሏል፡፡

አቶ ጌታሁን ከ20 ዓመታት በላይ በብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ላለፉት ስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ባህረ ባለፈው ሳምንት መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ እሳቸውን በመተካት የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ተብለው ተሰይመው ነበር፡፡

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የተሾሙት አቶ ጌታሁን፣ ከሦስቱ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ጌታሁን ከብሔራዊ ባንክ ውጪ በሌሎች የባንክ መደበኛ ሥራዎች ውስጥ አይታወቁም፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ከአቶ ኢሳያስ ባህረ በፊት አቶ ሞገስ ጨመረና አቶ ወንድወሰን ከበደ (አሁን የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት) በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ዳዊት ታዬ አስተዋጽኦ አድርጓል)

Standard (Image)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት ዘርፎችን በማደራጀት ሹመት ሰጡ

$
0
0

- አቶ ሱፊያን አህመድ - የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ

- ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ - የኢንዲስትሪ ዘርፍ አስተባባሪ

- አቶ ሙክታር ከድር - የመልካም አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጽሕፈት ቤታቸውን በማደራጀት አዳዲስ ሹመቶችን መስጠታቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አዲሱን ካቢኔያቸውን ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባዋቀሩበት ወቅት፣ ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሚል ስያሜ የተሰጡ ማዕረጎች እንደሚቀሩ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹አሁን የሚያስፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአንድ ጉዳይ የሚያማክር ሳይሆን፣ የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች አፈጻጸምን የሚከታተልና የሚያቀናጅ አደረጃጀት ይኖራል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ለረዥም ዓመታት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሱፊያን አህመድን በሚኒስትር ማዕረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አድርገው እንደመደቧቸው የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩትን ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን ደግሞ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የኢንዱስትሪ ዘርፍና የፋይናንስ ዕቅዶች ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ በማድረግ እንደመደቧቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሙክታርን፣ ከድር በሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ በማድረግ እንደመደቧቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር በአዲሱ አሿሿሚ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

Standard (Image)

የቀድሞ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኑ

$
0
0

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከመዋሃዳቸው በፊት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ኃይለ ኢየሱስ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መሰየማቸው ተገለጸ፡፡

ምንጮች እንደገለጹት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲዋሀዱ አቶ ኃይለ ኢየሱስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለወራት ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ፣ ኃላፊነታቸውን ለቀው በሥራ ገበታ ላይ እንዳልነበሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚንዳትና አማካሪ ሆነው እንዲያገለግሉ መሰየማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መዋቅር ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሲኖሩት፣ የአቶ ኃይለ ኢየሱስ ሹመት ባንኩ ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲኖሩት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበሩት   አቶ ጌታሁን ናና በፕሬዚዳንትነት እንደሰየሙለት ይታወሳል፡፡

 

Standard (Image)

የትግራይ ክልል በርከት ያለ ምሁራን የተካተቱበት አዲስ ካቢኔ አዋቀረ

$
0
0

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በአብዛኛው የዶክተርነት ማዕረግ ባላቸው ምሁራን አዲስ ካቢኔ ለማዋቀር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ያቀረቧቸውን ዕጩዎች አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ ስድስት አዳዲስ የቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል፣ እንዲሁም የክልሉን ዋና ኦዲተር ኮሚሽነር ሹመት ማፅደቁን ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓባይ ወልዱ ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ አራት ዋና ዋና መሥፈርቶችን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሕገ መንግሥቱን በማመን በቁርጠኝነት ተግባራዊ የሚያደርጉ፣ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዓላማ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂን በተመለከተ ሥልጠና የወሰዱ፣ በቂ ትምህርትና የሙያ ሥልጠና ዝግጅት ለተፈለገው ዘርፍ የሚስማማና የሚመች ልምድ ያላቸው፣ እንዲሁም ታማኝነትና ከሙስና የፀዱ መሆናቸው የመምረጫ መሥፈርቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ለቢሮ ኃላፊነት የተመረጡት ስድስቱም ተሿሚዎች በዶክትሬት ማዕረግ የሚጠሩ ሲሆን፣ ለሌሎች ተቋማት የተመረጡ ተጨማሪ ሦስት ተሿሚዎች በተመሳሳይ ማዕረግ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ 12 ተሿሚዎች ሹመታቸው ሲፀድቅ ሦስቱ በካቢኔው ውስጥ ቀድመው የነበሩ ሲሆኑ፣ በአዲሱ አወቃቀር የቢሮ ለውጥ ያደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡ ለቢሮ ኃላፊነት የተመረጡት ዶ/ር ኢንጂነር ገብረ መስቀል ካህሳይ  (የትምህርት ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር አትንኩት መዝገበ  (የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አንድ ዘርፍ ኃላፊ)፣ ዶ/ር ተስፋ ሚካኤል ገብረ ዮሐንስ (የውኃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር አብርሃ ኪሮስ  (የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር የትምወርቅ ገብረ መስቀል (የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ) እና ዶ/ር ሙሉጌታ ሀዱሽ (የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ) ናቸው፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር ፋና ሐጎስና አቶ አማኑኤል አሰፋ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተሹመዋል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ረዳኢ በርኼ ደግሞ የክልሉ የዋና ኦዲተር ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

የቢሮ ለውጥ ያደረጉ አመራሮችን በተመለከተ አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጎይቶም ይብራህ  የወጣቶች ጉዳይና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሲሾሙ፣ ዶ/ር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ የደቡባዊ ምሥራቅ ዞን አስተዳዳሪ ሆነዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ቀደም ብሎ በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ጉባዔ ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ ለስምንት ቀናት ስብሰባ አካሂደው ነበር፡፡ በወቅቱ የ15 ዓመታት ግምገማ በማካሄድ የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ ባለ አሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡

በመግለጫውም፣ ‹‹የያዝነው ሥልጣን በዋናነት ለሕዝብ አገልግሎት አላዋልነውም፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹ወጣቶች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱና በራሳቸው አመለካከት እንዳይራመዱ መደረጋቸውንና ለዚህም ሁሉ መነሻው ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆነ አካሄድ በመስፈኑ ነው፤›› ተብሎ ነበር፡፡ ‹‹በእነዚህና መሰል ምክንያቶች በድርጅቱና በሕዝቡ መካከል ለዘመናት የቆየው አንድነትና መተማመን በተለያዩ ደረጃዎች ተሸርሽሯል፤›› ሲልም ጉባዔው በመግለጫው ገልጿል፡፡  

በተመሳሳይ ቀደም ብሎ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ካቢኔ ማዋቀራቸው ይታወሳል፡፡

የክልሎቹ አዲሱ የካቢኔ መዋቅር በፌደራል መንግሥት ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ካደረጉት አዲስ የካቢኔ ሹምሽርና ሽግሽግ ጋር መመሳሰል ይታይበታል፡፡

ነገር ግን በክልል ደረጃ ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር የዋና አመራሮች ለውጥ አለመደረጉ ይታወቃል፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት ዋናና ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮችን በአዲስ ሲለውጥ፣ ቀደም ብሎም የክልሉን መንግሥት የሚያስተዳድረው ኦሕዴድም ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን እንዲሁ መለወጡ አይዘነጋም፡፡

Standard (Image)
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live