Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live

ኢትዮጵያን ለመጉዳት በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የተጠነሰሱ ሁለት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች መምከናቸው ተገለጸ

$
0
0
  • ለዳያስፖራ አባላት መኖሪያ የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት በፍጥነት እንዲያቀርብ ተጠየቀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ስድስተኛ ወራቸውን እያገባደዱ የሚገኙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የአፈጻጸጸም ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያቀረቧቸው ሁለት የውሳኔ ሐሳቦችን የያዙ ሰነዶች ላይ ውይይት ሳይካሄድ ማምከን መቻሉን ገለጹ፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፣ ስለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት በሌላቸው የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጠንሳሽነት ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሁለት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች ተዘጋጅተው ነበር፡፡

ከሰነዶቹ አንዱ በአሜሪካ ሴኔት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 432 እና በኮንግረሱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 861 ናቸው፡፡ እነዚህ የውሳኔ ሐሳቦችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ ሴናተሮች ጋር ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ውይይት በማድረጋቸው፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ የኮንግረስ አባላት ጋር በመገናኘትና የቀረቡትን የውሳኔ ሐሳቦች ለማጨናገፍ የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረትም ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦችን ያዘጋጁ የኮንግረስ አባላት ስለኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው ለማስረዳት በተደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ፣ ረቂቅ የውሳኔ ሰነዶቹ ውይይት እንዳይደረግባቸውና ነገሩ ባለበት ደረጃ እንዲቆም መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በመኮነን ለሦስት ጊዜያት ሊወጡ የነበሩ የውሳኔ ሰነዶች ላይ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ እንዳይወጡ ማድረግ እንደተቻለ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡  

ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2017 የኮንግረስ አባል በሆኑት ክሪስ ስሚዝ የተባሉ ግለሰብ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚያበላሽና ጉዳት የሚያደርስ ረቂቅ የውሳኔ ሰነድ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አዲስ የቀረበው ሰነድ “Supporting Respect of Human Right  Encouraging Inclusive Governance in Ethiopia” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ የተሳሳተ ግንዛቤን መነሻ አድርጎ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የቀረበና አግባብነት የሌለው መሆኑን የማስረዳት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ሰነዶች ‹‹Supporting Respect of Human Right Encouraging Inclusive Government in Ethiopia›› የሚል ተመሳሳይ ርዕስ ያላቸው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ ከነበረው ግጭትና ተቃውሞ በኋላ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2016 የቀረቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሰነዶቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በግጭቱ ወቅት መጠቁሙን፣ ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ተማሪዎችን ያላግባብ ማሰሩን፣ እንዲሁም ዜጎች ነፃነታቸውን እንዳይጠይቁ መገደቡን ያወግዛሉ፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ በድጋሚ እንዲያጤን ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኮሚኒቲ አደረጃጀቶች ጋር በመሆንም ሰነዱ እንዳይፀድቅ መራጭ በሆኑባቸው አካባቢዎች እንዲቃወሙ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በአገራቸው የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ የዳያስፖራ አባላት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል የቤቶች ዲዛይንና መነሻ ዋጋ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ቢያቀርብም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግንባታ የሚሆን መሬት መስጠት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የአደረጃጀት፣ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው ባለመከናወናቸው ፕሮግራሙን ማስጀመር አልተቻለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የሚያደራጅ፣ የሚመዘግብ፣ የቤቶቹን ግንባታ የሚከታተልና ሲጠናቀቁ የሚያስረክብ አደረጃጀት፣ እንዲሁም ቦታ የማዘጋጀት ሥርዓት በፍጥነት ሊዘረጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ላቀረበችው የሰላም ሐሳብ ላለፉት 12 ዓመታት በላይ በጎ ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ኢትዮጵያንና አካባቢውን ከማተራመስ ተግባር መታቀብ አለመቻሉን ዶ/ር ወርቅነህ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለማሳደግና በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጥናት ላይ በተመሠረተ ትንተና ለመምራት እንዲቻል፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ ለመንግሥት መቅረቡን አስረድተዋል፡፡  

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ልትከተል ያረቀቀችው ‹‹አዲስና ጥልቅ›› የተባለው ፖሊሲ ምን እንደሆነ ‹‹ፍንጭ ይስጡን›› በማለት አንድ የምክር ቤት አባል ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዶ/ር ወርቅነህ ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ሰነዱን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርበናል፡፡ ሚኒስትሮቹ ተወያይተውበት ሲያፀድቁት ወደ ፓርላማው የሚመጣና የሚፀድቅ ነው፤›› በማለት አልፈውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ መንግሥታቸው በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርግና ይህም ዘላቂ መፍትሔ ለኢትዮጵያ እንደሚያመጣ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

Standard (Image)

ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በኢትዮጵያ የሚከሰት ማንኛውም የደኅንነት ችግር ለሱዳንም ሥጋት ነው አሉ

$
0
0

 

- ሁለቱ አገሮች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ይመክራሉ

- በሱዳን ወደብ ለኢትዮጵያ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ተርሚናል ተሠርቶ ተጠናቋል

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አህመድ አል በሽር፣ በኢትዮጵያ የሚከሰት ማንኛውም የደኀንነት ችግር የሱዳንም ሥጋት መሆኑን ተናገሩ፡፡ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደት እንድትፈጥር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እየመከሩ ነው፡፡

ከመጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያለውን የሱዳን የልዑካን ቡድን መርተው የመጡት ፕሬዚዳንት  አል በሽር፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር እስከ ዛሬ የተፈራረመቻቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ወህደት ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በመምከር ላይ ናቸው፡፡

ጉብኝቱን በተመለከተ ሁለቱም መሪዎች በጋራ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት አል በሽር በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችል ማናቸውም ዓይነት የደኅንነት ሥጋት የሱዳንም እኩል ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጭፈራችን እንኳን ሳይቀር የትኛው የማናችን እንደሆነ መለየት ያስቸግረኛል፤›› በማለት የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ታሪካዊና ጥንታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጭብጨባ በታጀበው ንግግራቸው፣ ‹‹እኛ አንድ ነን፣ የአንዳችን ችግር የሌላችንም ሕመም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ግንኙነታችን ገደብ አይኖረውም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ አባባል ከሆነ፣ የኢትዮጵያንና የሱዳንን ደኅንነት ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ‹‹የአንዳችን ችግር የአንዳችን ሕመም መሆኑን እኛ መሪዎች አምነን ተስማምተናል፡፡ ይህንን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲፈጽሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገፉበታል ብዬ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ውህደት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ዘርፎችን ያጠቃለለ እንደሆነም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ፕሬዚዳንቱ ግብዣቸውን አክብረው ‹‹ወደ ሁለተኛ ቤታቸው›› ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አድንቀው፣ ሁለቱም መሪዎች አዲስ አበባና ካርቱም መመላለሳቸው የተለመደ ቢሆንም፣ የአሁኑ የተለየና ለሁለቱም ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ጉብኝት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይኼኛው ጉብኝት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መሆኑን አስታውሰው፣  በቅርቡ ከአዲስ አበባ - ካርቱም የአውቶብስ ትራንስፖርት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንት በሽር የሁለቱም አገሮች ደኅንነት የማይነጣጠል መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ሱዳንን ከኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመንገድና በንግድ የማስተሳሰር ጉዳይ የቆየ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ በሁለቱ አገሮች ስምምነት የተደረሰባቸውን በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ፣ የሁለቱ አገሮችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውህደትና መስተጋብር ለመፍጠር እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያናኘቸው የባቡር መስመር ግንባታ ጥናት ተጠናቆ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ወደብ ለኢትዮጵያ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነፃ ተርሚናል ማዘጋጀቱንም አመስግነዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱን ‹‹ወንድሜ›› በማለት ቅርበታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በሁለቱም አገሮች መካከል ለመፍጠር የታሰበው የኢኮኖሚ ውህደት በቀጣናው ላሉት የኢጋድ አባል አገሮች ብሎም ለአፍሪካ አገሮች ቁጥር አንድ አብነት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አል በሽር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ነፃ የሸቀጦች  ልውውጥና ነፃ የሰዎች ዝውውር በመጀመር የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን እንደሚሠራ ገልጸው፣ እስካሁን በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የተከናወነው ሥራ ከፍተኛ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን የታሰበው መጀመርያ የኢኮኖሚ ቀጥሎ ወደ ፖለቲካ ውህደት በማስፋት በአካባቢው አንድ የጋራ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለመ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣናው የሚታየውን ስደት፣ ድርቅና ረሃብ ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻልም አክለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡትን ያህል ወደ አስመራም የሚጓዙ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱት ወዳለው አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ኤርትራንም ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዝርዝር ውስጥ ከመግባት ግን ተቆጥበዋል፡፡ በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የጋራ ኮሚሽን፣ የቴክኒክ ኮሚቴና ዓቢይ ኮሚቴ የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ መሬት ለማውረድ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡

ሱዳን ከግብፅና ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን የምትሳተፍበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር አባል ስትሆን፣ በግድቡ ላይ የተጀመረው ድርድር ፍሬያማ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውጪ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስና የደኅንነት ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡

 

 

Standard (Image)

ከ4.7 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ ቡና ነጋዴዎች ተከሰሱ

$
0
0

     በሐሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ የቡና ላኪነት የንግድ ፈቃድ በማውጣትና ሐሰተኛ የውክልና ሰነዶችን በመጠቀም የብቃት ማረጋገጫ በመውሰድ፣ 223,846 ዶላር ወይም 4,702,506 ብር የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው ድርጊቱን በመመሳጠር የፈጸሙት አቶ አብዱልዋሀድ ሞሐመድ፣ ወ/ሮ ሉባባ ከሊልና አቶ ሸሪፍ ሱሌማን ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ በመመሳጠር ጉዳይ አስፈጻሚ ነው በተባለ ቴዎድሮስ ከበደ ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማውጣትና ሐሰተኛ የውክልና ሰነድ በማስያዝ፣ ከግብርና ሚኒስቴር የቡና ላኪነት ብቃት ማረጋገጫና ከንግድ ሚኒስቴር ንግድ ፈቃድ እንዲያወጣ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ለዚህ አገልግሎቱም 300 ሺሕ ብር እንደተከፈለው ተገልጿል፡፡

 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአብዱልዋሀድ ሞሐመድ ስም 200,000 ብር ገቢ በማድረግና ከግብርና ሚኒስቴር ገንዘብ በባንክ መኖሩን የሚገልጽ ደብዳቤ በማጻፍ፣ ቡናን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላቸው በማስመሰል፣ የተሳሳተ ግምት እንዲያዝ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በአንደኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልዋሀድ ስም በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ ገንዘብ በማስገባት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 694.7 ቶን ቡና ገዝተው ሳይልኩ መቅረታቸውንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተከሳሾች ከባድ የማታለል ወንጀል በመፈጸማቸው ክስ እንደተመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

Standard (Image)

በኢትዮ ቴሌኮም በተለያየ ኃላፊነት ላይ የነበሩ አራት ሠራተኞች በሙስና ተከሰሱ

$
0
0

በኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ሪጅን ቢዝነስ ፓርትነር ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ አራት በተለያየ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ ሠራተኞችና ሁለት ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ፡፡

ተከሳሾቹ የምዕራብ ሪጅን ቢዝነስ ፓርትነር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደቻሳ ነመራ፣ የትራንስፖርት ሱፐርቫይዘር አቶ ጉርሜሳ አብዲሳ፣ የትራንስፖርት ፍሊት ኢንስፔክተሮች አቶ ገመችስ ኃይሉና አቶ አሸናፊ ጌታሁን ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር  ተመሳጥረዋል የተባሉት ግርማ አስፋው የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ጥገና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ አስፋውና የሒሳብ ሠራተኛው አቶ ጴጥሮስ ታረቀኝ ናቸው፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን የትራንስፖርት ፍሊት ኢንስፔክተር የነበሩት ሦስተኛና አራተኛ ተከሳሾች፣ ከግርማ አስፋው የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ጋራዥ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ በተቋሙ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምና ግርማ አስፋው የከባድና የቀላል ተሽከርካሪዎች ጥገና መካከል በተደረገው የተሽከርካሪዎች ሰርቪስና ጥገና ውል የገቡ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ከውል ውጪ የክፍያ ሰነዶችን በማዘጋጀት ትክክለኛ ጥያቄ በማስመሰል ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሾቹ በተለያዩ ጊዜያት በድምሩ 1,152,106 ብር ከውል ውጪ ለጥገና አገልግሎት በመክፈል በመንግሥት ላይ ጉዳት በመፈጸማቸው፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡  

Standard (Image)

ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ልዩ ዕውቅና ሰጠ

$
0
0

ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ልዩ ዕውቅና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከፈተው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዓመታዊ ሲምፖዚየም፣ የድርጅቱ ልዩ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሥልጠና ፕሮግራም (Trainer Plus) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋምን በሙሉ አባልነት መቀበሉን አስታውቋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ፉንግ ሊዩ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው የሙሉ አባልነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቱን ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች 13 ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋማት፣ ኤርፖርቶችና የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ኮሎኔል ወሰንየለህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› የተሰኘው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥልጠና ፕሮግራም ሙሉ አባል ለመሆን ለሁለት ዓመት ያህል ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ባለሙያዎችን ወደ ውጭ በመላክ ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ እንዲሠለጥኑ አድርጎ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማፀደቁን ኮሎኔል ወሰንየለህ ተናግረዋል፡፡

የ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› ሙሉ አባል መሆኑ ባለሥልጣኑ በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን የሰው ኃይል ለማሳደግ እንደሚያስችለውና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአቪዬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሙሉ አባል በመሆናችን በሌሎች አገሮች የተዘጋጁና በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የፀደቁ 100 ያህል የሥልጠና መርሐ ግብሮች ወስደን መጠቀም እንችላለን፡፡ ከሌሎች ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናትና የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋማት ልምድ መቅሰም እንችላለን፡፡ እኛም ለራሳችን ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት እንችላለን፡፡ ለጎረቤቶቻችንም ሥልጠና በመስጠት ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያስችለናል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሊዩ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የባለሙያዎች እጥረት መኖሩን ገልጸው፣ ለሰው ኃይል ልማትና የሙያ ሥልጠና ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች ያለባቸውን የአቪዬሽን ባለሙያዎች እጥረት ችግር ለመቅረፍ በሥልጠናው ዘርፍ ድርጅታቸው የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶ/ር ሊዩ፣ ብቁ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ለማፍራት የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡  

ከ70 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የማሠልጠኛ ተቋም ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችና ቴክኒሺያኖች ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጂቡቲና የሶማሊላንድ ባለሙያዎችን ማሠልጠን ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ ቀደም ሲል የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› አባል ሆኗል፡፡ የአቪዬሽን አካዳሚው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደበበ እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ ከአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ ገንብቷል፡፡ አየር መንገዱ ላለፉት 50 ዓመታት ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የአቪዬሽን አካዳሚውን በማስፋፋት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ4,000 በላይ ባለሙያዎችን የማሠልጠን አቅም አለን፡፡ ከ1,000 በላይ የተለያዩ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በማሠልጠን ላይ እንገኛለን፡፡ የገነባነው የማሠልጠን አቅም ከራሳችን አልፈን የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የአቪዬሽን ባለሙያዎች ማሠልጠን የሚያስችለን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዓመታዊ ሲምፖዚየም በአፍሪካ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ አስተናጋጁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ ጉባዔውን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከፍተዋል፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአቪዬሽን አካዳሚና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል እንደሚጎበኙና በዚሁ ወቅት አየር መንገዱ ያስገነባቸውን ሦስት አዲስ የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋሮች እንደሚያስመርቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተመድ አካል የሆነው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1944 ቺጋጎ አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከ52 መሥራች አገሮች አንዷ ናት፡፡ ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን የሚቆጣጠር ነው፡፡ 

Standard (Image)

የከንቲባው ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በይግባኝ ተከላከሉ ተባሉ

$
0
0

ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ በፍቃዱ አሰፋ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ከተከሰሱበት ክስ በነፃ የተሰናበቱ ቢሆንም ምርመራ ላይ በነበረው ይግባኝ እንዲከላከሉ ፍርድ ተሰጠ፡፡

አቶ በፈቃዱና ከእሳቸው ጋር ተከሰው የነበሩትን አቶ አብርሃም ጌታቸው እንዲከላከሉ ፍርዱን የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው፡፡ ችሎቱ ፍርዱን የሰጠው የሥር ፍርድ ቤት አቶ በፍቃዱ ከተከሰሱበት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ወንጀልና ዋጋ ያለውን ነገር ያለ ክፍያ ወይም ያለ በቂ ምክንያት ማግኘት ወንጀሎች መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከተከሰሱበት ወንጀል በነፃ መሰናበታቸውን በመቃወም፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ነው፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ በፍቃዱ ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ግምቱ 8,551 ብር የሆነ ባለ 24 ካራት ስምንት ግራም ወርቅ ያለክፍያ መቀበላቸውን ገልጾ ክስ ያቀረበባቸው ቢሆንም፣ በሰነድም ሆነ በሰው ሊያስመሰክርባቸው ባለመቻሉ የሥር ፍርድ በነፃ ማሰናበቱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጾ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱም አፅንቶታል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአቶ በፍቃዱ ላይ በሥር ፍርድ ቤት አቅርቦባቸው የነበረው ሌላው ክስ፣ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ ለሥር ፍርድ ቤት ያስረዳ ቢሆንም፣ ተከሳሹ በወቅቱ ከነበሩበት የሥራ ኃላፊነት አንፃር ተፈጽሟል የተባለውን የወንጀል ድርጊት የሚያረጋግጥ የሰነድም ሆነ የሰው ምስክር ሊያስረዳባቸው እንዳልቻለ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡ ተከሳሹም ለአንድ ዓመት ያህል በማረሚያ ቤት ከቆዩ በኋላ ከእስር ተፈትተው ወደ ምድብ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ አቶ በፍቃዱ ወደ ሥራቸው ከተመለሱ ከአንድ ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በምክትል ኃላፊነት ከተሾሙ ከሁለት ወራት በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ከሁለት ዓመት በፊት ያቀረበው ይግባኝ ተመርምሮ አቶ በፍቃዱ በሥር ፍርድ ቤት በነፃ የተሰናበቱበትን አንደኛ ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ በመስጠቱ፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አቶ በፍቃዱም መከላከያ ምስክሮቻቸውን ከማሰማታቸው በፊት የተከሳሽነት ቃላቸውን፣ መዝገቡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ለተመለሰለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሰጥተዋል፡፡ አቶ በፍቃዱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ሥር ባሉ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ከ20 ዓመታት በላይ በታማኝነት ማገልገላቸውን ለፍርድ ቤቱ ካስረዱ በኋላ፣ እንዴት ለእስር እንደበቁም ገልጸዋል፡፡

ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድ ስብሰባ ሊመሩ ወደ ስብሰባ አዳራሹ እየሄዱ፣ ‹‹ከአገር ሊወጣ ነው›› የሚል መረጃ እንደደረሰው የገለጸላቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ወደ ቤታቸው ተወስደው ቤታቸው ሲበረበር የተገኘውና መርማሪዎቹ የተነገራቸው እንዳልተጣጣመላቸው የገለጹት አቶ በፍቃዱ፣ መርማሪው ‹‹ጠላት አለህ?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸውና ምንም ነገር ባለመገኘቱ ማዘኑን ጠቁመዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግዢ መመርያ ቁጥር 3/2002 ያለውና በምርመራ ወቅት በፌዴራል የግዢ መመሪያ መሠረት ሠርተፊኬሽን ላይ እንዲፈርሙ የተለያዩ የማስገደድ ጫናዎች የተፈጠሩባቸው ቢሆንም፣ አለመፈረማቸውን አክለዋል፡፡ የገረማቸው ነገር በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከሁለት ወራት በኋላ የቀረበባቸው ክስ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከሚውሉ ግብዓቶች ግዢ ጥራት ጋር የተገናኘና በሽልማት ካገኙት ወርቅ ጋር የሚገናኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሳሻቸው ዓቃቤ ሕግ ካቀረበባቸው ምስክሮች መካከል ሁለቱ ምስክሮች የመሥሪያ ቤታቸው የሕግ ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠቁመው፣ ከሁለቱም ጋር በሥራ ምክንያት የከረረ ፀብ እንደነበራቸው በመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጭምር የሚታወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸውን የክስ መዝገብ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ሊመልሰው የቻለው በሁለቱ ሰዎች ምስክርነት መሆኑን የገለጹት አቶ በፍቃዱ፣ እሳቸውና ሁለቱ የመሥሪያ ቤቱ የሕግ ባለሙያዎች አለመግባባት ላይ መሆናቸውን የመሥሪያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ኃላፊዎችም ጭምር እያወቁት፣ በበቀል የሰጡት የምስክርነት ቃል ትክክልና አሳማኝ ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡

ግዢ የተፈጸመው በመመርያው መሠረትና ጨረታ የወጣውም በአግባቡ መሆኑን የገለጹት አቶ በፍቃዱ፣ መንግሥት ካወጣው መመርያ ውጪ የተፈጸመ ግዢ እንደሌለ፣ ይህም ቢሆን እሳቸውን እንደማይመለከታቸው በተደጋጋሚ አስረድተዋል፡፡ ሁለቱ ምስክሮች እሳቸውን እንደሚበቀሏቸው በተደጋጋሚ ሲዝቱባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ያለምንም ምስክር ‹‹ቢሮው ገብቼ ነግሬውና አስጠንቅቄው ነበር›› የሚለው የምስክርነታቸው ቃል እንደ እውነት መወሰዱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

ለህሊናቸው የሚኖሩና በአንገታቸው ላይ ክር በማንጠልጠል ብቻ ሳይሆን የህሊና ክርስቲያን መሆናቸውን የተናገሩት አቶ በፍቃዱ፣ ኃላፊ በመሆናቸው መንግሥት ቤት ሲሰጣቸው ‹‹እኔ በማኅበር የሠራሁት ቤት አለኝ›› በማለት ቁልፍ መመለሳቸውን ጠቁመው፣ ገንዘብ ቢፈልጉና ሥልጣናቸውን ያላግባብ መጠቀም ቢፈልጉ ቁልፉን በወቅቱ እስከ 500,000 ብር ድረስ መሸጥ ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ መሆንን ሕዝቡ እንደ ሌላ ነገር ስለሚያየው ራሳቸውን ደብቀው ‹‹እዩኝ እዩኝ›› ሳይሉ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ በፍቃዱ፣ ‹‹እኔ ያጣሁት የፍርድ አምላክ ነው፡፡ እንዴት ውስጤን ላሳያችሁ? የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚሰጥ አንድ ዓመት የህሊና እስረኛ ሆኜ ከረምኩ፤›› በማለት ሳግና እንባ እየተናነቃቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው የተከሳሽነት ቃላቸውን አጠናቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የመከላከያ ምስክሮችን ከሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

የስድስት ወሯ ነፍሰ ጡር በሠራተኛዋ ተገደለች

$
0
0
  • ጡረተኛው ከሠራተኛቸው ጋር በዘመዳቸው ተገድለዋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውና የስድስት ወራት  ነፍሰጡር መሆኗ የተገለጸው የ29 ዓመት ወጣት ወ/ሮ ሔዋን ሳህሌ፣ በሠራተኛዋ በደረሰባት ድብደባ ተገደለች፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ ነዋሪ የነበረችው ወ/ሮ ሔዋን ትዳር ከመሠረተች ስድስት ወራት እንደሆናትና የስድስት ወራት ነፍሰጡር መሆኗን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በተጠርጣሪ ሠራተኛዋ ተደብድባ ግድያ የተፈጸመባት መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሠራተኛዋ የግጭታቸውን ምክንያት ገና በግልጽ ባትናገርም፣ ‹‹ተጋጨንና ገደልኳት›› በማለት በቁጥጥር ሥር በዋለችበት ወቅት ለፖሊስ መናገሯን በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡

ሠራተኛዋ ለቤት ውስጥ ማሞቂያ (ቺሚኒ) የተዘጋጀ ፍልጥ እንጨት በማንሳት፣ የሟችን ጭንቅላት ደጋግማ በመምታት ሕይወቷ እንዲያልፍ ካደረገች በኋላ በግቢው ውስጥ በሚገኝ ጢሻ ነገር ውስጥ የደበቀቻት ቢሆንም፣ አስከሬኗ በፖሊሶች ፍለጋ ወዲያው ሊገኝ ችሏል፡፡

ሠራተኛዋ ድርጊቱን እሷ እንዳልፈጸመች ለማስመሰል ያልታወቁ ሰዎች ግቢ  ገብተው እሷን ካፈኗት በኋላ ሟችን ይዘዋት እንደሄዱ ለመናገር ብትሞክርም፣ ፖሊሶች ግቢውንና ቤቱን ሲፈትሹ በቀላሉ ሊያገኟት እንደቻሉ ታውቋል፡፡ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት የሟች ባለቤት ከቀድሞ ባለቤቱ የወለደው የ13 ዓመት ልጅ በቤት ውስጥ የነበረ ቢሆንም፣ እየተጫወተ ስለነበር ድርጊቱን እንዳልሰማም ተጠቁሟል፡፡

ልጁ የሆነውን በወቅቱ አውቆ ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባትም ድርጊቱ እሱም ላይ ሊፈጸም ይችል እንደነበር የገመቱም አሉ፡፡ የወ/ሮ ሔዋን የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መካነ መቃብር መፈጸሙም ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሳምንት ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ የባንክ ሠራተኞች የኅብረት ማኅበር በሚባለው አካባቢ፣ የ50 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አቶ ተወልደ ገብረአምላክና ሠራተኛቸው ትህትና ውብሸት በቤታቸው ውስጥ በስለት ታርደው መገኘታቸው ታውቋል፡፡

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ የነበሩና ባሁኑ ጊዜ ጡረተኛ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ግድያውን የፈጸመባቸው አብሯቸው የሚኖር የ35 ዓመት ዘመዳቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ ወጣቱ ግድያውን ፈጽሞ በቤት ውስጥ የነበሩ ጌጣጌጥና ሞባይሎች ይዞ መሰወሩም ተገልጿል፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ፍለጋውን አጠናክሮ መቀጠሉም ታውቋል፡፡ 

Standard (Image)

የቻይና መንግሥት በአዳማ ለሚገነባው የማሽነሪዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ

$
0
0

በቻይና የሁናን ግዛትና በኢትዮጵያ መንግሥት የእሽሙር ሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) ስምምነት መሠረት፣ የቻይና መንግሥት በአዳማ ከተማ ሊገነባ ለታቀደው የማሽነሪዎችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንዲለቀቅ መፍቀዱ ተገለጸ፡፡

የቻይናው ኢምፖርትና ኤክስፖርት ባንክ (አግዚም ባንክ ኦፍ ቻይና) ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የተጠየቀውን ገንዘብ ለማበደር መፍቀዱን ተከትሎም፣ ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በተካሄደው የኢትዮ-ሁናን የኢንቨስትመንት ትብብር ፎረም ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮ-ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ወገን የኢንዱትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከቻይኖቹ ወገን ሻንግሻ ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኒካል ዲቨሎፕመንት ግሩፕ ኩባንያ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡ የፓርኩን ግንባታም የቻይናው ተቋራጭ ሲጂሲኦሲ ተረክቧል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ እንዳስታወቁት፣ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ፓርኩን ገንብቶ እንዲያስረክብ የተመረጠው የቻይናው ተቋራጭ ከመመረጡም በተጨማሪ፣ የቻይናው ባንክ ለፓርኩ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማበደር ተስማምቷል፡፡ በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ 250 ሚሊዮን ዶላር ተለቆ ግንባታ እንደሚጀመር አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቻይናውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስትሮችና የሌሎች አገሮች ባለሀብቶች እንዲገቡ መንግሥት ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

በአዳማ የሚገነባው ኢትዮ-ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ተግባሩ ልዩ ልዩ ማሽነሪዎችን ማምረት እንደሆነ ያስታወቁት፣ የኢኮኖሚ ውጤታማነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ኢንዱስትሪ ፓርኩ ትልልቅ አምራቾች የሚቀላቀሉት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፣ በቻይና ግዙፍ የሚባሉ አምራቾች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በመግባት ለማምረት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ፉቶን ሳኒ የተባለው የተሽከርካሪዎች አምራች ኩባንያ፣ ቲቢኢኤ ሳውዘርን ፓወር ትራንስሚሽን ኤንድ ዲትሪቢዩሽን ኢንዱስትሪ ግሩፕ ይገኙበታል፡፡ ከሁለቱ ኩባንዎች በተጨማሪም ሁናን ቻንጋኦ የተባለው ኩባንያም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በፓርኩ የሚገቡ የመጀመሪያዎቹ ኩባንያዎች ለመሆን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

122 ሔክታር መሬት የሚያካልለው የኢትዮ-ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ትራንስፎርመሮችን፣ የፉቶን ተሽከርካሪዎችን፣ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችንና የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች በማምረት እንደሚሠራ ሲጠበቅ፣ በኢትዮጵያና በቻይና መንግሥታት ድርሻ የሚተዳደር የሽርክና ተቋም ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሁናን ግዛት መካከል የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ቋሚ ኮሚቴ እንዲመሠረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከመፈረሙም በተጨማሪ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የሁናን ግዛት ኮሜርስ ዲፓርትመንት የመግባቢያ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ድርድር ሒደት ከሁለቱ ወገን በየተራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቻይናና በኢትዮጵያ እየተገናኙ ተነጋግረዋል፡፡ 

Standard (Image)

ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርድር ደንብ ላይ ተስማሙ

$
0
0
  • ከመድረክ በተጨማሪ ሰማያዊና መአሕድ ራሳቸውን አግልለዋል

ከጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ስምንት ዙር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ስምንተኛውን ዙር ውይይት ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያካሂዱ በዝርዝር የድርድር ደንቡ ላይ ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ መድረክ ሰማያዊና መአሕድ የሉበትም፡፡

ከሚፈለገው ጊዜ በላይ ዘግይቷል እየተባለ በሚተቸው ውይይት ፓርቲዎቹ አስቀድመው በተወሰኑ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መስማማት ችለው ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች ለመወሰን ባደረጉት ጥረትም በስምምነት ለመወሰን 12 ጉዳዮችን ለይተዋል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደርና የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል በአብዛኛዎቹ ላይ ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፣ ሁለት ጉዳዮች ግን ውይይቱን ባለበት እንዲረግጥ አድርገውት ነበር፡፡ እነዚህም በአብዛኛው በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በመድረክ የተነሱ ነበሩ፡፡ ሁለቱ አጀንዳዎች ውይይቱ ወይም ድርድር በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይደረግና ማን ያደራድር የሚሉ ነበሩ፡፡

ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ላይ በስድስት ዙሮች ከተሳተፈ በኋላ፣ በሰባተኛው ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፣ በዋና አደራዳሪነት አልያም ለብቻው በጎንዮሽ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከውይይቱ ራሱን አግልሏል፡፡

በተመሳሳይ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይም ይበልጥ አጨቃጫቂ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አደራዳሪ ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ኢሕአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች ግን ድርድሩን ተሳታፊ ፓርቲዎች በፈረቃ ሊያደርጉት እንደሚገባ አቋም ይዘው ነበር፡፡

ይህን ልዩነት ለማቻቻል ጥረት እየተደረገ እያለ ሰማያዊ ፓርቲና የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ የማይኖር ከሆነ በድርድሩ መሳተፍ እንደማይፈልጉ በመግለጽ፣ እንደ መድረክ ሁሉ ራሳቸውን አግለዋል፡፡

ነገር ግን ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ስምንተኛው ዙር ውይይት የተቀሩት ፓርቲዎች ሰፊ ጊዜ ወስደው ከመከሩ በኋላ ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል ሞክረዋል፡፡ በዚህም ፓርቲዎቹ ድርድሩን ያለነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ለማካሄድ ወስነዋል፡፡

በመርህ ደረጃ ድርድሩን ፓርቲዎቹ በፈረቃ እንዲመሩት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይሁንና ፓርቲዎቹ እንዴት አድርገው በፈረቃ ድርድሩን ይምሩት የሚለው ጉዳይ ተጨማሪ ውይይት ጠይቆ ነበር፡፡ በመጨረሻም ድርድሩን የሚመራ ኮሚቴ ከፓርቲዎቹ ተውጣጥቶ እንዲቋቋም ተስማምተዋል፡፡ የኮሚቴውን አባላት ቁጥር ለመወሰንና አባላቱን ለመምረጥ ለሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በዕለቱ ፓርቲዎቹ እስካሁን ያካሄዷቸውን ውይይቶች ቃለ ጉባዔ መርምረው ለማፅደቅም ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ፓርቲዎቹ የተደራዳሪ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር፣ የሚዲያ ሚና፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ የግብዓት አቅርቦትና የድርድሩ ስያሜ ላይ ተስማምተዋል፡፡ ድርድሩ ያለሚድያ በዝግ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ ድርድሩን የሚመራው ኮሚቴ ግን ድርድሩ ሲጠናቀቅ በጋዜጣዊ መግለጫ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ተገልጿል፡፡

ድርድሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲካሄድም ፓርቲዎቹ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ፓርቲዎቹ የመደራደሪያ ሰነዱን ‹‹የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አሠራር ደንብ›› በሚል ስያሜ አፅድቀውታል። በድርድሩ ወቅት የውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ተገኝተው ሒደቱን መታዘብ እንደሚችሉም ተስማምተዋል፡፡

ተሳታፊ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የድርድሩ ዓላማዎች ላይ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብና ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

የባህረ ሰላጤውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሥጋት በቅርበት ለመከታተል ኢትዮጵያ በኦማን ኤምባሲ ልትከፍት ነው

$
0
0

በየመን የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስታከው የባህረ ሰላጤው አገሮች የሚያካሂዱት ፖለቲካዊ ፍልሚያና ከቀጣናው ውጪ በሚታየው የመስፋፋት አዝማሚያ የተነሳ ሥጋት የገባት ኢትዮጵያ፣ ሁኔታውን በቅርበት ሆና ለመከታተል አዲስ ኤምባሲ በኦማን ልትከፍት መሆኑ ተሰማ፡፡

ኤምባሲውን በፍጥነት ለመክፈትም የባህረ ሰላጤው ቀጣና ውስጥ ከምትገኘው ኦማን የመንግሥት ባለሥልጣናት ይሁንታ መገኘቱን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የተደራጀ የሰው ኃይል መረጣ የተጠናቀቀ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ኦማን ሊያቀኑ እንደሚችሉ ምንጮች አክለዋል፡፡

የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ በየመን የተፈጠረው ቀውስና የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚኖረው ፖለቲካዊ አንድምታ ተጠይቀው ነበር፡፡

በየመን በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስና የለየለት ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከሰንዓ ለማስወጣት መገደዷን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ወቅታዊ መረጃ የማግኘት እክል እንደተፈጠረ አስረድተዋል፡፡  

‹‹ኤምባሲያችንን ከየመን ካስወጣን በኋላ በየመን አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተለይ ደግሞ በገልፍ አገሮችና በኢራን መካከል እየተካሄደ ያለውን የእጅ አዙር (Proxy) ጦርነት ለመከታተልና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ለመተንተን በቂ መረጃ በወቅቱ የማግኘት ችግር አጋጥሞናል፡፡ ይህንን ችግር በፍጥነት ለመፍታትና በቅርበት ለመከታተል አዲስ ኤምባሲ በኦማን ለመክፈት እየጣርን ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የዓረብ አብዮት በየመን መቀጣጠሉን ተከትሎ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ የተገደዱት ፕሬዚዳንት ዓሊ አብዱላህ ሳላህን በመተካት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሐዲን በመቃወም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በአሁኑ ወቅት መልኩን ቀይሮ የአልቃይዳ፣ የአይኤስ፣ የሒዝቦላህና የሁቲ አማፂያን የጦር አውድማ ሆኗል፡፡

በየመን የተቀሰቀሰው ውስጣዊ ቀውስም የፖለቲካዊ ኢስላም ፍልሚያ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፍልሚያውም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው በሱኒ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑት የባህረ ሰላጤው አገሮች ማለትም በሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ቤሩት፣ ኳታርና ኦማን ባንድ በኩልና የሺያ እስልምና ተከታይ በሆነችው ኢራን መካከል የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢራን በየመን የሚንቀሳቀሰውን የሁቲ አማፂያን በመሣሪያ እየደገፈች ሲሆን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው የዓረብ አገሮች ጥምረት አባል አገሮች ደግሞ የፕሬዚዳንት ሐዲ ደጋፊዎችን ለመርዳት የእግረኛ ጦራቸውን ወደ የመን ልከዋል፡፡ በተጨማሪም ከኤርትራ መንግሥት በኪራይ ባገኙት የአሰብ ወደብ የጦር ኃይላቸውን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ለፓርላማው ያስረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ አካባቢ ያለው ጉዳይ በሒደት እኛን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካን እየሆነ ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች ፍልሚያ ቀስ በቀስ ወደ ቀይ ባህርና ወደ ሶማሌላንድ እንዲሁም ወደ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች እየተሳበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢራንን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ምክንያት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት የባህር ኃይሉን በሶማሌላንድ ማስፈር የሚያስችለውን ስምምነት ከወራቶች በፊት ፈጽሟል፡፡ በሁለቱ መካከል የተደረገው ስምምነት እንደሚያስረዳው ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አከራይታለች፡፡ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የሶማሌላንድ መንግሥት በሰሜን በርበራ የሚገኘውንና ለኤደን ባህረ ሰላጤ ቅርብ የሆነውን አካባቢ ከሊዝ ነፃ ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲጠቀምበት ፈቅዷል፡፡

መረጃ በተጨማሪ እንደሚያመለክተው፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሶማሌላንድ የሚገነባውን ወታደራዊ የጦር ሠፈር ለሌላ ዒላማ መጠቀም አትችልም፡፡ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ተመሳሳይ ወታደራዊ የጦር ሠፈር የመገንባት ጥረት በኳታር በኩል መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

‹‹በባህረ ሰላጤው አካባቢ የበላይነትን ለመያዝ በኢራንና በዓረብ አገሮች መካከል የተጀመረው ፍልሚያ ቀይ ባህርንና የአፍሪካ ቀንድን እንዳይመርዝ በኢትዮጵያ በኩል ሥጋት አለ፤›› የሚሉት አንድ የውጭ ጉዳይ ባለሙያ፣ በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚገኘው የአሜሪካ ጦር ጥቃት የመሰንዘር ፈቃድ ሊሰጡ የቻሉት፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ እንቅስቃሴው በአሜሪካ ደኅንነት ላይም ሥጋት የሚፈጥር ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በየመንና በባህረ ሰላጤው የሚፋለሙት ሁለት ትልልቅ ኃይሎች ጉዳይ ከእኛ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ሲመዘን ምን ማለት ነው የሚለውን በቅርበት ሆነን መከታተል አለብን፤›› ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የኳታሩ አሚር ሼክ ታማም ቢን ሃማድ አል ታኒ ለይፋ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ዋነኛ የመወያያ አጀንዳቸው የአካባቢው ደኅንነት እንደነበር መንግሥት ገልጿል፡፡ 

Standard (Image)

የኳታር አሚር ታሚም አል ታኒ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የላቀ መተማመን ፈጥራለች አሉ

$
0
0

የኳታር ሼክ አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረችው መግባባትና መተማመን የላቀና ስትራቴጂካዊ እንደሆነ ተናገሩ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ሥልጣን የያዙት የኳታር አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ የአፍሪካን ምድር ሲረግጡ የመጀመርያቸው ሲሆን፣ ለአንድ ቀን በቆየ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮችና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክር የቴክኒክ ኮሚቴ ወደ ሚኒስቴር ደረጃ ከፍ እንዲል ወስነዋል፡፡ እንዲሁም  በሁለቱም የአገር መሪዎች ደረጃ መደበኛ ምክክር እንዲደረግበት መስማማታቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ከመሪዎቹ ውይይት በኋላ አቶ ዓለም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኳታር መንግሥትና ባለሀብቶች በተለይ በነዳጅ፣ በማዕድን ፍለጋና በታዳሽ ኃይል በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለኳታር አሚር ያቀረቡላቸውን ጥያቄ አሚሩ በሙሉ ልብ ተቀብለውታል፡፡

እንዲሁም ደግሞ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይ የእስልምና ታሪካዊ ማዕከላትን እንዲያበለፅጉ፣ በቱሪዝምና በሆቴል ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥያቄ እንደቀረበላቸው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ 24 ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፣ የኳታር መንግሥት ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ፓርኮችን ለማልማት ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ አሚሩ መናገራቸውን አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉብኝቱ በተለየ ዕይታ መታየት ያለበት ነው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 20 ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ደርሷል፡፡

ኳታር በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካና ደኅንነት ከፍ ያለ  ፍላጎትና ተሳትፎ ያላት ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር በነበራት የጠበቀ ግንኙነት ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2008 ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዋና አማካሪያቸው አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ዶሃ (የኳታር ዋና  ከተማ) በመሄድ የዲፕሎማሲ ሥራ መከናወናቸው ይነገራል፡፡ ይህንን የዲፕሎማሲ ሥራ ተከትሎ ከ11 በላይ ስምምነቶች በሁለቱ አገሮች መፈረማቸው አይዘነጋም፡፡  

የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ለአጭር ጊዜ እክል አጋጥሞት የነበረ መሆኑን ያስታወሱ አቶ መለስ ዓለም፣ በአሁኑ ወቅት ግንኙነታቸው በመተማመንና በመግባባት የላቀ ደረጃ መድረሱን አሚሩ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተፈረመ አዲስ ስምምነት ባይኖርም፣ ሁለቱ መሪዎች የአገሮቹ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ እንዲሆን በመወሰናቸውና ጉብኝቱ የተለየ ትርጉም እንደነበረው አቶ መለስ ዓለም አክለዋል፡፡ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በጋራ ተቀናጅተው ለመሥራት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡

በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኳታር ኤርትራ ከሱዳንና ከጂቡቲ ጋር ዕርቅ እንድትፈጥር ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችው ግንኙነት ሙቀት በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማስታረቅ ፍላጎት እንዳላት የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሕንፃ በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

$
0
0

የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሊያስገነባ ነው:: የሕንፃው መሠረት ድንጋይ ማክሰኞ ሚያዚያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በይፋ ተቀምጧል:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ
ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና ሌሎችም ተገኝተዋል:: ሕንፃው በቦሌ መንገድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ 4,882 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ 14 ፎቆች ይኖሩታል ተብሏል:: አረንጓዴ ተክሎች በሕንፃው አናት ላይ እንደሚኖሩ የሕንፃ ንድፍ (ዲዛይን) ያመለክታል:: የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሕንፃው ግንባታ ድርጅቱ የሚዲያ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም ያስችለዋል ብለው፣ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆንም እንደሚያግዘው ገልጸዋል::
የሕንፃው ግንባታ ዋጋና የሥራ ተቋራጩ ማንነት አልተገለጸም:: ከባለሥልጣናቱ በስተጀርባ የሚታየው የሕንፃው ንድፍ (ዲዛይን) ነው:: (ፎቶ በመስፍን ሰለሞን)

Standard (Image)

ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የኤክስፖርት ምርቶችን አገር ውስጥ አሽጎ መላክ ጀመረ

$
0
0

 

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን አገር ውስጥ አሽጎ መላክ ጀመረ፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለየብቻ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በማጓጓዝ፣ ወደቡ ላይ ምርቶችን በኮንቴይነር በማሸግ ኤክስፖርት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ይኼን አሠራር  በማስቀረት በቃሊቲ ጉምሩክ (ኮሜት) ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የኤክስፖርት ቡና በማሸግ መላክ ጀምሯል፡፡

ለዓመታት ይህ አሠራር በነበረበት በመቆየቱ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች የኤክስፖርት ምርቶችንና ኮንቴይነሮችን ለያይቶ ማጓጓዝን በተመለከተ መንግሥትን ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ አዲስ አበባ በሚገኘው ቃሊቲ ጉምሩክ ግቢ ውስጥ ቡናና የተለያዩ የግብርና ምርቶችን አሽጎ መላክ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የደረቅ ወደብና የተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ ‹‹ከዚህ በኋላም በሐዋሳና በሌሎች ከተሞች እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ፣ እንዲሁም በሞጆ ደረቅ ወደብ የኤክስፖርት ምርቶችን አሽጎ ለመላክ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ በ2001 ዓ.ም. ሥራውን በይፋ የጀመረውን የሞጆ ደረቅ ወደብ የኢትዮጵያ ዋነኛ የገቢና የወጪ ዕቃዎች ማዕከል (ሎጂስቲክስ ሀብ) ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ደሳለኝ የሞጆ ደረቅ ወደብን የኢትዮጵያ የሎጂስቲክ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው ግዙፍ ዕቅድ የዓለም ባንክ ቦርድ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ሰሞኑን 50 ሚሊዮን ዶላር በኢንተርፕራይዙ አካውንት ገብቷል፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ አረጋግጠዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ አሁን ካለበት 60 ሔክታር መሬት ወደ 140 ሔክታር የሚያሳድጉ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና የሥጋ ውጤቶችን ለማጓጓዝ አስፈላጊ የሆኑ የማቆያ ማቀዝቀዣዎች፣ ተርሚናሎችና መጋዘኖች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውታሮች ይገነባሉ ተብሏል፡፡

እነዚህ ግንባታዎች የሞጆ ደረቅ ወደብ ትኩረት አድርጎ ከቆየው ገቢ ንግድ ወደ ወጪ ንግድም እንዲያሰፋ እንደሚያደርጉት አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡  

 

 

Standard (Image)

ከወጣቶች አሥር ቢሊዮን ብር በጀት ተጠቃሚ ለመሆን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች ተመዘገቡ

$
0
0

 

የፌዴራል መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከበጀተው አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የ3.3 ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶች ምዝገባ ተካሄደ፡፡ ቤት ለቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶቹን መመዝገቡን፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡  

ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን የመለየት ሥራ በየክልሉ የቤት ለቤት ቅስቀሳና ግብረ ኃይል በማደራጀት እየተከናወነ ነው፡፡

እስከ መጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው ሥራ ፈላጊዎችን የመለየት ተግባር 3,337,983 ሥራ ፈላጊ ወጣቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከተመዝጋቢዎቹ ውስጥም 80,552 ያህሉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች ሲሆኑ፣ 211,788 የሚሆኑት ደግሞ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተመረቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተጠቀሰው አጠቃላይ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ላይ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡ ‹‹ሥራ ፈላጊዎችን የመለየቱ ተግባር የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት በየጊዜው የቁጥር መለዋወጥና የጥራት ችግር እያጋጠመ በመሆኑ፣ በቀጣይነት ማጣራት የሚጠይቅ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ሥራ ፈላጊ ወጣቶቹን ከመለየቱ ተግባር ጎን ለጎን የወጣቶች የልማትና የለውጥ ስትራቴጂ ሰነድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አደረጃጀቶችና አመራሮች፣ እንዲሁም ለወጣት አደረጃጀቶች ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ስትራቴጂ ሥራ ላይ ለማዋልም የተለያዩ የአሠራር ማዕቀፎች ማለትም የወጣቶች የልማት ቡድን አደረጃጀትና ሥምሪት ማኑዋል፣ የወጣቶችና የመንግሥት ፎረም ማደራጃ ማኑዋልና የወጣት አደረጃጀቶች ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት ማኑዋል መዘጋጀታቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የወጣቶች ጥያቄ የሥራ ዕድል ፈጠራ መሆኑ ቢታወቅም፣ በርካታ የተዛቡ አስተሳሰቦች በወጣቶችም ሆነ በየደረጃው በሚገኘው የአመራር ኃይላችን የሚታይ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሥልጠናው ያስፈለገበት ምክንያትም ይህንን ችግር ለማረም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶቹ ሊሰማሩባቸው የሚገቡ የሥራ መስኮችን ለመለየት እንዲያስችል፣ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት የቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ በመሬት አቅርቦት ረገድ የከተማ አስተዳደሮች በፍጥነት ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፀደቀው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በሥራ ፈጠራ መርሐ ግብሩ የሚታቀፉ ወጣቶች ዕድሜ ከ18 እስከ 34 ዓመት መሆን አለበት፡፡  

Standard (Image)

የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ማኅበር እንዳያመርትና እንዳያሠራጭ ታገደ

$
0
0

 

  • ማኅበሩ የደረጃዎችን ምልክት እንዳይጠቀም ዕግድ ተጥሎበታል

‹‹እኛ የሰማነውም ሆነ የደረሰን ነገር የለም››

አቶ ሀብቱ ሐጎስ፣ የአፋር ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ

     ከካባዳ ጨው አምራቾች ማኅበር ጥሬ ጨው በመረከብ፣ በማቀነባበርና አስፈላጊውን መሥፈርት በማሟላት ለምግብ የሚውል ጨው ለማቅረብ የተቋቋመው አፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ምንም ዓይነት ምርት ከማምረትም ሆነ ወደ ገበያ ከማሠራጨት መታገዱ ታወቀ፡፡

በማኅበሩ ላይ የዕግድ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማኅበሩ የሚያመርተው ጨው አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጨው ደረጃ መሥፈርትን ማሟላት ባለመቻሉ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ሥራው በምግብና መጠጥ ማምረቻ ድርጅቶች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለኅብረተሰቡ የሚቀርብ ምርት ደኅንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጾ፣ በዚሁ መሠረት ማኅበሩ የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ባለሙያዎቹን ወደ ማምረቻው ሥፍራ መላኩን አስታውሷል፡፡ የተላከው የባለሙያ ቡድን አስፈላጊውን የቅድመ ናሙና ምርመራ በማድረግ በማኅበሩ ላይ የተገኙ ክፍተቶች መኖራቸውን ከገለጸ በኋላ፣ ማኅበሩ ማስተካከያ ለማድረግ በመስማማት ጊዜያዊ የብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቶት እንደነበር በዕግድ ደብዳቤው ላይ አስታውሷል፡፡

ባለሥልጣኑ በሰጠው የማስተካከያ ቀነ ገደብ መሠረት በድጋሚ የቁጥጥር ሥራ ያደረገ ቢሆንም፣ ማኅበሩ እንዲያስተካክል የታዘዘውን ወይም በተስማማው ክፍተት ላይ ምንም ነገር አለመሥራቱንም እንደተገነዘበም ጠቁሟል፡፡ ሌላው ባለሥልጣኑ በዕግድ ደብዳቤው ላይ የጠቆመው፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በላከለት የላብራቶሪ ፍተሻ ማኅበሩ የሚያመርተው የጨው ምርት አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጨው ደረጃ መሥፈርትን እንደማያሟላ ነው፡፡ ድርጅቱ ለማኅበሩ ሰጥቶት የነበረውን በጨው ምርቱ ላይ እንዲለጥፍ ፈቅዶለት የነበረውን በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን አስገዳጅ ደረጃ እንደማያሟላ በመግለጽ የተሰጠውን ምልክት የመጠቀም ፈቃድ እንዲመልስ፣ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ማሳወቁንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከመጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ችግሮቹን እስከሚያተካክል ድረስ፣ ምንም ዓይነት ምርት ከማምረትም ሆነ ወደ ገበያ ከማሠራጨት መታገዱን አስታውቋል፡፡

የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ አቶ ሰኢድ ያሲን የተባሉ ባለሀብትና የካባዳ ጨው አምራቾች ማኅበር በጋራ ያቋቋሙት ድርጅት ቢኖርም፣ ለካባዳ ጨው አምራቾች በቂ ጥሬ ጨው ምርት እያቀረቡ ቢሆንም ተገቢው ክፍያ በወቅቱ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ማኅበሩን በማውገዝ ለአፋር ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር በፊርማ የተደገፈ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

ከባለሀብቱ አቶ ሰኢድ ጋር የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት መስማማታቸውን ያስታወሱት አምራቾቹ፣ አቶ ሰኢድ የአምራቾች ወኪል እንዲሆኑ እንጂ፣ ባለሀብቱ ገና በሒደት ላይ የሚገኘው ፋብሪካ ሳይመሠረት የካባዳን ሥራ በሙሉ እንዲረከቡ ባለመሆኑ የሚቃወሙ መሆኑን ለፕሬዚዳንቱ ባቀረቡት አቤቱታ አሳውቀዋል፡፡ በመሆኑም የአምራቾች ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ገልጸው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የማኅበሩን ህልውና ከአደጋ እንዲታደጉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

በባለሀብቱ አቶ ሰኢድ 51 በመቶና በካባዳ ጨው አምራቾ 49 በመቶ ለተቋቋመው አፋር የጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለ ቢሆንም፣ እስካሁን አምራቾች የሚቀበለውን ጥሬ የጨው ምርት የሚያቀነባብረውና አዮዲን የሚረጨው በ1998 ዓ.ም. 83 በመቶ የመንግሥት ልማት ድርጅት በሆነው ማዕድን ኮርፖሬሽንና 17 በመቶ ደግሞ የኤፈርት ድርጅት የሆነው ኢዛና በጋራ ያቋቋሙት የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ማሽን በኮሚሽን በመከራየት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ሐጎስን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ባለሥልጣኑ ምርት እንዳይመረትም ሆነ እንዳይሠራጭ ስለማገዱ የሰሙት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ግን የብሔራዊ ደረጃ ምልክት እንዳይጠቀሙ በማለት የጻፈው ደብዳቤ እንደደረሳቸውና ምላሽ መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአንድ ምርመራ ወይም በአንድ ጊዜ ናሙና ውጤት ላይ ይደርሳል የሚል እምነት ስለሌላቸው፣ ተከታታይ ናሙና በመውሰድ እንዲያረጋግጡ በደብዳቤ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ማኅበራቸው በሙሉ አቅም የሚሠራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀምበት የሚችለውን ያህል የጨው ምርት ማቅረብ የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መቀመጫው ካናዳ የሆነ ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የሚባልና አዮዲንን ጨምሮ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ለተጠቃዎች በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሱ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ሲሆን፣ ከአፍዴራና ከተለያዩ ሥፍራዎች እየተመረተ ለሕዝብ ስለሚደርሰው የጨው ምርት ምን መሆን እንዳለበት እየመከረ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ አብነት ተክሌ፣ ‹‹ጨው ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አዮዲን በጥብጦ በአካፋና በእጅ በመርጨት የሚበቃ አይደለም፡፡ አዮዲን በባህሪው ይተናል፡፡ በመሆኑም ጨው በደንብ ታጥቦ፣ ደርቆና ተፈጭቶ በዘመናዊ ፋብሪካ ከባለ አሥር እስከ 50 ኪሎ ግራም በአዮዲን ከተረጨ በኋላ ላሚኔትድ በሆነ ከረጢት መታሸግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችል ሰመራ ከተማ ዘመናዊ የጨው ማምረቻ ፋብሪካ መገንባቱን የሚያውቁ ቢሆንም፣ ሕዝቡን ለማዳረስ እየሠራ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአፋር ጨው ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት አዲስ የጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ የግል ማኅበር ከአቶ ያሲን ሰኢድና ከካባዳ ጨው አምራቾች ጋር ለመመሥረት የመሠረት ድንጋይ መጣሉ ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ አሁን ግን ባለድርሻዎቹ ቅሬታ እንዳደረባቸው በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ማሳወቀቻውን አስረድተዋል፡፡

ምንም ይሁን ምንም የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥታት ትኩረት በመስጠት ንፅህናውን የጠበቀ ጨው እንዲመረት በማድረግ፣ ለሕዝቡ ጤንነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አቶ ያሲን ሰኢድን ለማግኝት ሪፖርተር በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

 

Standard (Image)

ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ የአዲስ አበባ ሸማች ማኅበራት የበዓል ምርቶችን አቀረቡ

$
0
0

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ኑሮ ለማረጋጋት ያቋቋማቸውና ባለፉት ስድስት ወራት 2.7 ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱ 141 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለትንሳዔ በዓል (ፋሲካ) የሚሆኑ ምርቶች በሰፊው ማቅረባቸው ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ቀጥተኛ ክትትል ያደረገባቸውና ለበዓሉ የሚሆኑ 800 የዕርድ ከብቶች አፋር ክልል ከሚገኘው አዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ከብቶች በሸማቾች ማኅበራት ሥር ለሚገኙ ሉካንዳዎች ተከፋፍለዋል፡፡ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ በሚያስከፍሉ ልኳንዳዎች ሥጋ በኪሎ 92 ብር፣ በማያስከፍሉ ልኳንዳዎች ደግሞ 80 ብር በኪሎ የሚሸጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ አቶሬ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሳይቸገሩ በዓሉን እንዲያሳልፉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በበቂ ደረጃ እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡

‹‹ንግድ ቢሮ አዋሽ አርባ ከሚገኙ ከብት አደልበው ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ሸማች ማኅበራትን አስተሳስሯል፤›› ሲሉ አቶ ዲላሞ አስረድተዋል፡፡

ከከብት አቅርቦት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሸማቾች በክልል ከተሞች ከሚገኙ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር በማስተሳሰር የስንዴ ዱቄት፣ ዶሮዎች፣ ሽንኩርትና እንቁላል በሰፊው እንዲገበያዩ በመደረጉ የገበያ ዋጋ ንረት እንዳይከሰት መደረጉን አቶ ዲላሞ ተናግረዋል፡፡

ለክብረ በዓሉ ተፈላጊ ከሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል ዘይትና ስኳር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በድጎማ የሚቀርብ ዘይት በመላ አገሪቱ እንዲያከፋፍሉ ዘጠኝ መንግሥታዊ፣ የግልና የኢንዶውመንት ኩባንያዎች መመረጣቸው ተገልጿል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዘይት በማቅረብ ላይ የሚገኙት አልሳም ትሬዲንግ፣ አፋ ትሬዲንግ (ሆራይዘን ፕላንቴሽን)፣ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ፣ አማሬሳ ዘይት ፋብሪካና አለ በጅምላ ናቸው፡፡

የዘይት አቅርቦት በጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች አለ በጅምላ ተጠቃሚዎችን ማርካት ባለመቻሉ፣ በሆራይዘን ሥር የሚገኘው አፋ ትሬዲንግ ክፍተቱን እንዲሸፍን እየተደረገ መሆኑን አቶ ዲላሞ ጠቁመዋል፡፡

ስኳርን በሚመለከት ለአዲስ አበባ ከተማ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በወር 112 ሺሕ ኩንታል ይከፋፈላል፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት ባለመመጣጠኑ አቅርቦቱ 120 ሺሕ ኩንታል እንዲሆን መወሰኑን፣ የከተማው ንግድ ቢሮ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃና ግብይት ዋና የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉሸዋ በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የዱቄትና የዘይት ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሙሉሸዋ ገልጸዋል፡፡ ካለፈው ሳምንት በፊት በ116 ወረዳዎች የሚገኙ ማኅበራት ምርት እንደሌላቸው ገዢዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ አቶ ዲላሞ ቅሬታው ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን በአቅርቦት ሳይሆን በሥርጭት የሚያጋጥም ችግር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሳምንተ ህማማት ወቅት ግን ይህ ችግር የተፈታ መሆኑንና ንግድ ቢሮው የተለያዩ የቁጥጥር ቡድኖች አቋቁሞ እየተከታተለ ክፍተቶችን እየሞላ እንደነበረ አቶ ዲላሞ አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት 141 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 275 ሺሕ አባላት አሏቸው፡፡ ማኅበራቱ አገልግሎት የሚሰጡት ለአባላቶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ግብይት ለመፈጸም ለሚፈልጉ የከተማው ነዋሪዎች ጭምር ነው፡፡ ማኅበራቱ ለሁሉም ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑና አባላትን ማብዛት ባለመቻላቸው፣ ካፒታላቸውን በሚገባ ማሳደግ እንዳላስቻላቸው አቶ ሙሉሸዋ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ማኅበራት የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ለበዓሉ የሚሆኑ ምርቶች ግዥ ፈጽመውበታል፤›› ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሦስት የፕላስቲክ ፋብሪካዎችን አዘጋ

$
0
0

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹በካይ›› ያላቸውን ስስ ፌስታል የሚያመርቱ ሦስት የፕላስቲክ ፋብሪካዎች፣ ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ዘጋ፡፡ ለአንድ ፋብሪካ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

የተዘጉት ፋብሪካዎች የማምኮ ወረቀት ፋብሪካ እህት ኩባንያ ማምኮ ፕላስቲክ፣ የሸዋ ዳቦ እህት ኩባንያ ሸዋ ፕላስቲክና ፎም ፕላስቲክ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ደግሞ ደብሊውኤጂ ፕላስቲክ ፋብሪካ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከ0.03 ሚሊ ሜትር ውፍረት በታች ፕላስቲክ ማምረት በአገሪቱ በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

‹‹እነዚህ ሦስት ፋብሪካዎች ከዓመት በፊት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ ሊያስተካክሉ ስላልቻሉ እንዲታሸጉ ተወስኗል፤›› ሲሉ አቶ ፀጋዬ አረጋግጠዋል፡፡

ስስ ፌስታሎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ብክለት እየፈጠሩ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን የጠቆሙት አቶ ፀጋዬ፣ በተለይ ስስ ፌስታሎች ከ100 ዓመት በላይ ሳይበሰብሱ የሚቆዩ በመሆናቸው በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡

‹‹ከብቶች እየተመገቧቸው ለሞትና ለበሽታ እየተዳረጉ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ለዕይታ እጅግ ደስ የማይል ሁኔታ ፈጥረዋል፤›› በማለት አቶ ፀጋዬ አስረድተዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ ከተዘጉባቸው መካከል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ ባለሀብት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ የእሳቸው ፋብሪካ ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች በሚሰጧቸው መሥፈርት መሠረት የሚያመርት ነው፡፡ በዚህም ፋብሪካቸው ሊዘጋ አይገባም ብለዋል፡፡

ነገር ግን አቶ ፀጋዬ ሲመልሱ፣ ‹‹የአካባቢ ችግር ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡ እኛ አገር ውስጥ የሚመረት ምርት ድንበር ተሻግሮ እንዲበክል አይፈቀድም፤›› ብለዋል፡፡

ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ኩባንያ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ምርቱን ካላስተካከለ፣ ዕጣ ፈንታው እስከ ወዲያኛው መዘጋት እንደሚሆን የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ 

Standard (Image)

የኦሮሚያ ባለሀብት ሶደሬ ሪዞርትን ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው ያዙ

$
0
0

 

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የሚታወቁት አቶ ድንቁ ደያሳ፣ ሶደሬ ሪዞርትን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ገዙ፡፡ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ጋር በተደረገ የፊርማ ሥነ ሥርዓት እንደተገለጸው፣ መንግሥት የነበረውን 30 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በ90 ሚሊዮን ብር አቶ ድንቁ ገዝተዋል፡፡

ባለሀብቱ የአጠቃላይ ክፍያውን 35 በመቶ ቀድመው እንደከፈሉ ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ 35 በመቶ የሚሆነው ክፍያ ከተከፈለ የቆየ ቢሆንም፣ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ግን በአሠራር ክፍተቶች ምክንያት መዘግየቱ ተገልጿል፡፡

አቶ ድንቁና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ መሰለች ወዳጆ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢና ቀደም ሲል የቀድሞ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር አበራ ደሬሳ ተገኝተዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ሶደሬ ሪዞርት በመንግሥትና ዲኢኬ ኦሮሚያ ቢዝነስ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተያዘ ነበር፡፡ መንግሥት ከአሁን ቀደም ይዞት የነበረውን 55 በመቶ የሚሆን ይዞታ ከሰባት ዓመት በፊት ለዲኢኬ አስተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ 80 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ተከፍሏል፡፡

በወቅቱ ዲኢኬ በአቶ ድንቁ፣ አቶ ቀመር የሱፍ (ድምፃዊ) እንዲሁም አቶ ኤልያስ ኢብሳ ሥር የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ባለ አክሲዮኖች ተቀይረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ዲኢኬ በዋናነት በአቶ ድንቁ ሥር ሲሆን፣ ከድርጅቱ ሁለት በመቶ የሚሆነው በአቶ ድንቁ ባለቤት ወ/ሮ ሌንሳ ጳውሎስና በወላጅ እናታቸው ወ/ሮ ዳንሴ ግርሙ ይዞታ ሥር ይገኛል፡፡

አቶ ቀመር የሱፍና አቶ ኤልያስ ኢብሳ የሚፈለግባቸውን ክፍያ ስላልከፈሉ፣ ከአክሲዮን ድርሻ ባለቤትነት እንደወጡ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ጊዜ በአቶ ድንቁ ተገልጿል፡፡

በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ድንቁ 35 በመቶ የሚሆነውን ቀድመው ቢከፍሉም፣ የአክሲዮን ዝውውሩ የፀና የሚሆነው ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደሚሆን ወ/ሮ መሰለች ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ድርጅቱ አሁንም ድረስ ማስፋፊያ ላይ እንዳለና ትርፍ ማግኘት አለመጀመሩን ዶ/ር አበራ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ በውጭ ኦዲተር ሲረጋገጥ የሚታወቅ ይሆናል፤›› ሲሉ ወ/ሮ መሰለች በበኩላቸው መልሰዋል፡፡ በሶደሬ ሪዞርት የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንደቆዩና እስካሁን 800 ሚሊዮን ብር እንዳወጡ፣ አቶ ድንቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ማስፋፊያውን በስድስት ወራት ውስጥ ለመጨረስ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አቶ ድንቁ አክለዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ድንቁ፣ ከአሁን ቀደም የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ከመንግሥት ለመግዛት 606 ሚሊዮን ብር አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥትን ከሚያስተዳድረው ከብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ትስስር እንዳለው ለሚነገርለት ጥረት ኮርፖሬት በ765 ሚሊዮን ብር እንዲተላለፉ ተወስኗል፡፡

በ1950ዎቹ በመንግሥት እንደተመሠረተ የሚነገረው ሶደሬ በውስጡ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን ይዟል፡፡ ከመንግሥት እጅ ከወጣ በኋላም ሶደሬ የአሁን ስሙን ይዞ እንደሚቀጥል በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅት ሚኒስቴር ሒልተን አዲስ አበባን ጨምሮ ሁለት ሆቴሎችን በመንግሥት ሥር እንዲቆዩ ወስኗል፡፡ በአልኮል መጠጥ፣ በወረቀት፣ እንዲሁም በእርሻና በትራንስፖርት የተሰማሩ አራት ድርጅቶችን ወደ ግል እንዲተላለፉም ለይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው አፈጻጸም ሚኒስቴሩ 1.2 ቢሊዮን ገቢ በሥሩ ካሉ የልማት ድርጅቶች ማግኘቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚታወቁት አቶ ድንቁ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባለቤት ሲሆኑ፣ ከአሁን ቀደም ሴንትራል የጤና ኮሌጅን ከቀድሞው ባለቤቱ አቶ አብነት ግርማይ መግዛታቸው አይዘነጋም፡፡

 

Standard (Image)

ፓርላማው አራት የፌዴራል ዳኞችን ለማሰናበት የቀረቡለትን ሰነዶች ከድምፀ ተአቅቦ ጋር አፀደቀ

$
0
0

 

ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት ባለመቻልና ከፍተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት ፈጽመዋል የተባሉ አራት የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ስንብት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡ ከተለመደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በተለየ አጨቃጫቂ መሆኑ በተስተዋለበት የስንብት ውሳኔ ሐሳብ ብዙ ጥያቄዎች የተስተናገዱ ሲሆን፣ የውሳኔ ሐሳቡን አሥር አባላት በድምፀ ተአቅቦና አንድ አባል የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተውበታል፡፡

የስንብት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ዳኞች አንዱ አቶ ውሂብ ማሞ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ተሹመው ሲሠሩ መቆየታቸውን፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለፓርላማው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል፡፡

የውሳኔ ሐሳቦችን በንባብ ያቀረቡት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ ነበሩ፡፡

      የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ያደረገውን ስብሰባና የደረሰበት ውሳኔ በመጥቀስ፣ አቶ ውሂብ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት በሠሩባቸው ጊዜያት ፈጽመውታል የተባለውን ዝርዝር የዲሲፕሊን ጉድለት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሠረት የዲሲፕሊን ክስና ማስረጃ ቀርቦባቸዋል ከተባሉ ጥሰቶች ውስጥ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ዓቃቤ ሕግና የግል ተበዳይ በፍርድ ቤት በይግባኝ ችሎት ላይ ባልተገኙበት ውሳኔ አስተላልፈዋል የሚል ክስ በቅድሚያ ተጠቅሶባቸዋል፡፡ ክሱ፣ ‹‹የሥር ፍርድ ቤት ስምንት ዓመት የተወሰነበት እስረኛ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ተበዳይ ቀርባ ቃሏን ቀይራለች በማለት፣ የተበዳይዋን የምስክርነት ቃል በመቅረፀ ድምፅ ሳይኖር፣ በመዝገብ ሳይሰፍርና ዓቃቤ ሕግ ሳይቀርብ በመዝገብ ላይ ሆን ብለው ተበዳይዋ ቃሏን እንደቀየረች በማስመሰል፣ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ግራና ቀኝ ተከራካሪዎች ባልቀረቡበት ሁኔታ እስረኛው በነፃ እንዲለቀቅ አድርገዋል፤›› ይላል፡፡

እንዲሁም በልደታና በአቃቂ ምድብ ችሎቶች ተመድበው ሲሠሩ ከ62 መዝገቦች በላይ ‹‹በአየር ላይ በመቅጠርና በእንጥልጥል ለረዥም ጊዜ በቀጠሮ ሳይወስኑ በመቅረት›› የሚልም ይገኝበታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተጠቀሰባቸው ክስ የመንግሥትን ሥራን ካለማክበራቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ያለምክንያት በሥራ ገበታቸው እንደማይገኙ፣ በተለይም ከሰዓት በኋላ ሥራ ላይ እንደማይኖሩ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ተስፋዬ የውሳኔ ሐሳቡን በንባብ ካቀረቡ በኋላ ለተነሱላቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ከአስገድዶ መድፈር ጋር የተጠቀሰውን ክስ በተመለከተ ተደፋሪዋ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች የ13 ዓመት ታዳጊ እንደነበረች ገልጸዋል፡፡

በሌሎች ሦስት የውሳኔ ሐሳቦች ስንብታቸው እንዲፀድቅ ለምክር ቤቱ ጉዳያቸው የቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው የተሾሙ ሦስት ዳኞች፣ ተመሳሳይ የዲሲፕሊንና የሥነ ምግባር ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

እነዚህም ዳኞች ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር በዚሁ ምክር ቤት ሹመታቸው ፀድቆ ቃለ መሐላ ፈጽመው የነበሩት በድሬዳዋ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት አቶ ዳግም መርጊያ፣ በየካ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት ወ/ሪት ግሩም አጎናፍርና በአራዳ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት ወ/ሪት ምሕረት ብርሃኔ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው እነዚሁ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በሥራ ገበታ ባለመገኘት፣ በእጃቸው የነበሩ የመንግሥት ንብረቶች ሳያስረክቡና በፍርድ ቤቶች በቀጠሮ ላይ የሚገኙ መዛግብትን ጥለው በመሄዳቸውና ሕዝብን ለማገልገል የገቡትን ቃለ መሐላ ወደ ጎን በመተው፣ ‹‹የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም›› የሚሉ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

ነገር ግን ‹‹የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም›› በሚለው ላይ ሦስቱም ዳኞች አንድ ዓመት እንኳ ማገልገል ባለመቻላቸው በርካታ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ቀርበዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አቶ ተስፋዬ፣ ዳኞቹ በምርመራ ወቅት ሊገኙ አለመቻላቸውንና ከአገር መውጣታቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የዕለቱን የምክር ቤቱን ስብሳባ የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታየ ምናለ ጉዳዩ ግልጽ በመሆኑ ያንን ያህል ሊያከራክር ስለማይገባው፣ ወደ ድምፅ መስጠቱ መግባት ይሻላል የሚል ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን በተሰጡት ማብራሪያዎች ላይ ደስተኛ ያልመለሱት የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

ወ/ሮ ሽታዬ ብዛት ያላቸው ጠያቂዎች እጅ ሲያወጡ በቀረበው ውሳኔ ላይ ብቻ ተንተርሶ ወደ ማፅደቁ እንዲገባ ግፊት ያደረጉ ቢሆንም፣ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በመፈልፈል የምርመራ ሥራ ማከናወን የምክር ቤቱ ሥራ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ እዚህ ያለነው ነገሮችን እንዴት? ለምን? እያልን በጥልቀት ለመመርመር የሚያስችለን ሥልጣን ያለን አይመስለኝም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እኛ የወከልነው አካል ነው፡፡ መጣራት የሚገባውን የቤት ሥራም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን እሱ ይከታተላል፣ ያጣራል፡፡ እዚህ እናንተ የምታነሱዋቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ጉባዔው እየተከታተለ ያጣራል፡፡ እኛም በሪፖርት እንከታተላለን፤›› በማለት ወደ ውሳኔ እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አባላቱ ወደ ማጉረምረም ሲገቡ የአካሄድ ጥያቄ ያነሱት በምክር ቤቱ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ  አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ‹‹በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ብቻ ውሳኔ ሰጥተን ብንቀጥል፣ ሌሎች መነሳት በሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔም ሆነ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመሆን በዝርዝር እንዲታይ፣ በአቶ ተስፋዬ በኩል በሪፖርት ቀርቦላቸው ቢያዩት ይሻላል፤›› በማለት ወደ ማፅደቁ ቢገባ እንደሚሻል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የእሳቸውንም ሐሳብ ተከትሎ የውሳኔ ሐሳቡን ወደ ማፅደቁ ተገብቷል፡፡ በዕለቱ 320 የሚሆኑ የምክር ቤት አባላት መገኘታቸው የተመዘገበ ሲሆን፣ በድምፅ መስጠቱ ሒደት ግን በአብላጫ ድምፅ የውሳኔ ሐሳቦቹ ፀድቀዋል፡፡ አሥር አባላት ድምፀ ተአቅቦ ሲያደርጉ፣ አንድ አባል የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

የተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ከጉባዔው ሥልጣንና ተግባራት መካከል፣ በአንቀጽ 6(ሸ) ላይ ‹‹ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሚፀድቅ ድረስ ዳኞችን ከሥራ ማገድ ይችላል፤›› ይላል፡፡

 

Standard (Image)

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን አስጠነቀቀ

$
0
0

 

የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ክስ በተመሠረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ አዲሱ ቡላን ጨምሮ በ22 ግለሰቦች ላይ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው የድምፅ ማስረጃ ጋር በተያያዘ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን አስጠነቀቀ፡፡

ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ የሰጠው በተለይ የኮርፖሬሽኑ የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ እንደነበሩ ለተናገሩትና በቅርቡ ወደ ሌላ ክፍል መዛወራቸውን ለገለጹት አቶ ፀጋ ልዑል ወልደ ኪዳን ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሰዎች ምስክሮቹን አሰምቶ እንዳጠናቀቀና ተጨማሪ በኦሮሚኛና በእንግሊዝኛ የተቀረፀ የድምፅ ማስረጃ እንዳለው ካስረዳ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተርጉሞ እንዲልክ እንዲታዘዝለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ያልፈጸመው ደግሞ አቶ ፀጋ ልዑል በኃላፊነት የሚመሩት ክፍል ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ኮርፖሬሽኑ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ ተደራራቢ የሥራ ጫና እንዳለበት ሲገልጽ ፍርድ ቤቱ በሌላ አካል እንዲያስተረጉም ካዘዘ በኋላ፣ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ማክበር እንደልተፈለገ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ፍርድ ቤት የላከው ዋና ኃላፊውን ሳይሆን፣ የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ አቶ ፀጋ ልዑል ወልደ ኪዳንና ሁለት የተለያየ የሥራ ኃላፊዎች ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ማንነታቸውን ሲያረጋግጥ አቶ ፀጋ ልዑል የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ መሆናቸውን ሲናገሩ፣ ለምን ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ እንዳላከበሩ ተጠይቀዋል፡፡

ቀደም ባሉት ትዕዛዞች መሠረት ኮርፖሬሽኑ በእንግሊዝኛና በኦሮሚኛ የተቀረፁ የድምፅ ማስረጃዎችን አስተርጉመው ያላቀረቡት፣ ያሏቸው ተርጓሚዎች ጋዜጠኞች በመሆናቸውና ፕሮፌሽናል ስላልሆኑ ኃላፊነት መውሰድ ፈርተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለኃላፊዎች ያንኑ ገልጸው ሪፖርት ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ላሉት ትዕዛዞች በጽሑፍ የሰጠው ምላሽ ኃላፊዎች የሥራ ጫና እንዳለባቸው፣ በቂ ጊዜ እንደሌላቸውና ፍርድ ቤቱ በሌላ አካል እንዲያስተረጉም ማለታቸው አግባብ ስለመሆኑ ለአቶ ፀጋ ልዑል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው በተጻፈበት ወቅት እሳቸው ከኃላፊነታቸው ላይ ተነስተው እንደነበር ሲገልጹ፣ ‹‹ታዲያ አሁን ለምን መጡ?›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አስከተለ፡፡ ‹‹አሁን የመጣሁት ቀደም ብሎ አንተ ጉዳዩን ስለምታውቀው ሂድና አስረዳ›› የሚል ትዕዛዝ ከአለቆቻቸው ደርሷቸው መሆኑን አስረዱ፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመንግሥት አካል መሆኑን ኮርፖሬሽኑ እንደሚያውቅና በብዙ ባለሙያዎች የተሞላ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ አቶ ፀጋ ልዑል ‹‹የባለሙያ ችግር አለ›› በማለት የሰጡት ምላሽ አሳማኝ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ይህ ተራ ትዕዛዝ አይደለም፡፡ ተራ ነገር ተርጉሙ አልተባላችሁም፡፡ ፍትሕ እንዲቃለልና ተገቢ ትርጉም እንዲሰጥበት ነው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ በአንድ ፓራግራፍ ደብዳቤ እንደማይችል ምላሽ መስጠቱ ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት ባለማሰቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ዕርምጃ መውሰድ አላቃተውም፡፡ ያነበበ፣ የሠለጠነና ልምድ ያለው የሰው ኃይል ያለው ኮርፖሬሽን ይህንን ድርጊት ይፈጽማል የሚል እምነት ስለሌለው ነው፤›› ብሏል፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደግሞ የመንግሥት ትዕዛዝ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም አክሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የያዘው አዝማሚያ ጥሩ እንዳልሆነና የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በተደጋጋሚ እንደ ተራ ነገር ማየቱ ጥሩ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ ፍርድ ቤት የሚልከውን ትዕዛዝ ለሌላ አካል እንዲሰጥ ምላሽ ከመስጠት በፊት አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮችን ማስተዋሉ እንደሚጠቅም ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

አቶ ፀጋ ልዑል በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ መተባበር ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለበት፣ ወቅታዊና ተደራራቢ ሥራ ስለገጠመው፣ ባለሙያዎቹ አንድ ቀን አንድ ቦታ ሌላ ጊዜ ሌላ ቦታ ለሥራ ስለሚመደቡና የተሰጣቸው ጊዜ አጭር መሆኑን በመጠቆም ቀደም ብለው የተናገሩትን ‹‹ፕሮፌሽናሎች አይደሉም›› ያሉትን ለማረም ሞክረዋል፡፡ ወቅቱም የበዓል ወቅት መሆኑንም እንደ ማካካሻ ጠቁመዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠል የጠየቀው በዕለቱ አስተርጓሚ ይዘው ስለመምጣታቸው ቢሆንም፣ ምላሻቸው ‹‹አላመጣንም›› ሆኗል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እንዲተረጎም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው ጉዳዩ ጠንከር ያለ በመሆኑ እንደሆነ ሲያስታውቅ፣ አቶ ፀጋ ልዑል ቀጠል በማድረግ፣ ‹‹ጉዳዩ አንገብጋቢ ስለሆነ በቂ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ ከሕግ ጋር በተያያዘ ወደ ኮርፖሬሽኑ በርካታ ትዕዛዞች እየመጡ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ከአለቆቻችን ጋር ሊነጋገር ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

እንዲተረጎም የተፈለገው የኦሮሚኛ ድምፅ ትንሽ ስንኞች ያሉት የኦሮሚኛ ዘፈን ነው በሚል መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ እንግሊዝኛውም ቢሆን ያን ያህል እንዳልሆነ በመቁጠር የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎችም ሆኑ የበታች ሠራተኞች ጉዳዩን አቅልለው ባያዩት የተሻለ መሆኑን አስረድቷል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች አስተያየታቸውን ተጠይቀው የአቶ በቀለ፣ ደጀኔ፣ አዲሱና ጉርሜሳ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ለሦስት ጊዜ የሰጠው ትዕዛዝ አልተፈጸመም፡፡ ፍርድ ቤቱም የዕለቱ ቀጠሮ የመጨረሻና መቋጫ መሆኑን ቃል ገብቷል፡፡ የተቀጠረው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ቀርበው ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳልፈጸሙ እንዲያስረዱና ተርጓሚ ይዘው እንዲቀርቡ ቢሆንም አልቀረቡም፡፡ ኮርፖሬሽኑ የእኛ ተከራካሪ ባለመሆኑ ተወክለው ለመጡት ኃላፊዎች ምላሽ አንሰጥም፡፡ መጀመሪያውኑ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያቀርብ ሁሉንም ማስረጃዎች በፍርድ ቤቱ መሥሪያ ቋንቋ አስተርጉሞ ማቅረብ ነበረበት፡፡ ይህንንም የማረጋገጥ ኃላፊነት የፍርድ ቤቱ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ማዛናዊ ለማድረግ ፍርድ ቤቱ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ በዝምታ አልፈናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ተጨማሪ ቀጠሮ ሊሰጥ ስለማይገባ ማስረጃው ታልፎ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ ባሰማው ማስረጃ መሠረት ብይን እንዲሰጥ መታዘዝ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የሌሎቹም ጠበቆች ተመሳሳይ ተቃውሞ በማሰማት ተጨማሪ ቀጠሮ እንዳይሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በዚህ መሀል አቶ በቀለ ገርባ አቤቱታ እንዳላቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ‹‹ይህ ቀጠሮ ለምን ያህል ጊዜ እንደተቀጠረና እንደተራዘመ ለእናንተ እተዋለሁ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሦስተኛ አካል ሆኖ ገብቷል፡፡ የማይመለከታቸውን ከሚልክ አንድ ባለሙያ ቢልክ ይሻል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስንት ባለሙያዎች እንዳሉት እናውቃለን፡፡ ፕሮፌሽናል የለም መባሉ የሚያሳየው የሥርዓቱን ሁኔታ ነው፡፡ እኛ የምንታገለው ይህንን ሁሉ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት የሚመጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመውሰድ ሳይሆን ፍትሕ ለማግኘት ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡት በፈቃደኝነት ሳይሆን ተደብድበው በቃሬዛ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ‹‹በጣም አዝናለሁ›› ብለዋል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ስንት ነገር የሚሠሩበትን ጊዜያቸውን በአንድ ቀጠሮ ያለምንም ውጤት በመመላለስ እንዲያጠፉ መደረጉ፣ ሌላ የሕግ ባለሙያ ጫናውን በመፍራት እንዳይቀርብላቸው ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሌላው አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ደጀኔ ጣፋ ናቸው፡፡ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ እንኳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀርቶ በማንኛውም ሚዲያ ውስጥ የሚቀጠሩ ጋዜጠኞች የመጀመሪያ መለኪያ የቋንቋ ችሎታ ነው፡፡ በኮርፖሬሽኑ ያሉት ባለሙያዎች እየታወቁ፣ ወደ ፍርድ ቤት የማይመለከታቸውን ኃላፊዎች እየላኩ በሰው መጫወት ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ክስ ሲቀርብባቸው ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን በወቅቱ ማስረዳታቸውን አቶ ደጀኔ ገልጸው፣ እየተሰቃዩ ያሉት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ መሆኑን አክለዋል፡፡

የከሰሳቸው ዓቃቤ ሕግ ልጃቸው እንደሚሆንና እሳቸው የተማሩና ትልቅ ሰው መሆናቸውን ጠቁመው፣ ቢዋሹና ያልሆነ ነገር እያደረጉ ቢቀጥሉ ኖሮ በአሁኑ ጊዜ ሚኒስትር ወይም አምባሳደር ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለዴሞክራሲና ለነፃነት መከበር በመታገላቸው ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ዝም ብለው ክሳቸውን የሚከታተሉት ፍርድ ቤቱን አክብረው መሆኑን ገልጸው፣ እየሆነው ያለው ነገር ግን እያሳዘናቸው መሆኑን በመጠቆም ‹‹ወይ ይፍረድብን ወይም ይግደለን፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም እነሱም ግራ እየተጋቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ደጀኔ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሰጠውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤቱ ማገዱን አስታውሰው፣ እዚህ ግን የፍትሕ ሥርዓቱን ማንም ካድሬ እየተጫወተበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕዝብ እየጮኸ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ግራ ቢገባውም የሕዝብ ስቃይ ሊሰማው ይገባል ብለዋል፡፡

እሳቸው ብቻ ያረጁ መሆኑን ጠቁመው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን የ23 ዓመት ወጣቶች ማሰር ተገቢ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ‹‹ከኮርፖሬሽኑ የመጣችሁ ኃላፊዎች የምንነግራችሁ አብረን እንኑር፣ አንጠፋፋ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ፤›› ብለዋል፡፡ ከዓቃቤ ሕግ ጀርባም ያለውን እንደሚያውቁ የገለጹት አቶ ደጀኔ፣ ፍርድ ቤቱ ጠንከር ብሎ ዕርምጃ ቢወሰድ ለሚመጣበት ነገር ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከበስተጀርባው የሚቆም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የኮርፖሬሽኑን ተወካይ አቶ ፀጋ ልዑልን ‹‹ኃላፊ ነኝ ብለዋል›› በማለት በድጋሚ ካረጋገጠ በኋላ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልተፈጸመበትን ሁኔታ በሚመለከት ያስረዱት በቂ አለመሆኑንና በማስጠንቀቂያ እንዳለፈው ገልጾ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በድጋሚ ባይፈጸም በራሳቸው አቶ ፀጋ ልዑል ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመንገር፣ ኦሮሚኛውንና እንግሊዝኛውን የድምፅ ማስረጃ በይዘት ጭምር በመተርጎም በጽሑፍ እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ለጽሕፈት ቤት ገቢ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በላከው ትርጉም ላይ ጠበቆች እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሻቸውን እንዲያቀርቡ በማሳሰብ፣ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live