Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

$
0
0

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ላለፉት አሥር ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡

 

ዶ/ር ጌታቸው ኃላፊነታቸውን የለቀቁበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ ከግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ፣ የዶ/ር ጌታቸውን መልቀቅ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ሥልጠና ላይ በመሆናቸው ዝርዝሩን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ፣ ዶ/ር ጌታቸው ያቀረቡትን መልቀቂያ እንደተቀበለና በምትካቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መሾሙ ታውቋል፡፡

መንግሥት በመላ አገሪቱ አምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር አውታር ዝርጋታ ተግባራዊ ለማድረግ ከጠነሰሰ ጊዜ ጀምሮ፣ ዶ/ር ጌታቸው ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኅዳር 1999 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 141 ኮርፖሬሽኑን በይፋ ሲያቋቁም፣ ዶ/ር ጌታቸው መዋቅሩን ከመዘርጋት አንስቶ ፕላኑን እስከ ማውጣት ድረስ ያሉ ሥራዎችን መርተዋል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታትም በተለይ የአዲስ አበባ (ሰበታ)-ጂቡቲ፣ የአዋሽ-መቐለና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከመሩዋቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ የአዲስ አበባው ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ዶ/ር ጌታቸው ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ-ጂቡቲ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሙከራ ላይ እያለ ዶ/ር ጌታቸው ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፡፡

48.9 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ የሚንቀሳቀሰውና ለአሥር ዓመታት በእሳቸው የተመራው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የሥራ አፈጻጸሙን የሚያደንቁት የመኖራቸውን ያህል የሚተቹትም በርካታ ናቸው፡፡

ትችት አቅራቢዎች ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሰውም ሆነ የተሽከርካሪዎች መሸጋገሪያ በበቂ ደረጃ ሳያካትት መገንባቱ ለትራፊክ መጨናቀቅ ምክንያት ሆኗል የሚለው አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ -ጂቡቲ ባቡር መስመር ሲገነባ የደረቅ ወደብ፣ የጂቡቲ ወደብና የነዳጅ ማከማቻ መሠረተ ልማቶችን ታሳቢ አለማድረጉን ያክላሉ፡፡

የሥራ አፈጻጸሙን መልካምነት የሚገልጹ አካላት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ ገና አሥር ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱ በባቡር መሠረት ልማት ግንባታ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን ከዳር ማድረስ መቻሏን በበጎ ጎኑ መታየት አለበት ይላሉ፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ጥረት ቢደረግም፣ ጥረቱ ሊሳካ አልቻለም፡፡

 

Standard (Image)

የሒልተን ሆቴል ሠራተኛ ማኅበር የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው አለ

$
0
0

 

በሒልተን ሆቴል አስተዳደርና በሠራተኞች ማኅበር መካከል የተፈጠረው ውዝግብ አሁንም መቀጠሉንና በአባላቱ ላይ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የሠራተኛ ማኅበሩ አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ማኅበሩ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ በሆቴሉ አስተዳደር ላይ ያለውን ቅሬታ በዝርዝር ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ከሠራተኞች የሥራ ደኅንነት፣ ዕድገት፣ እንዲሁም ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዙ ችግሮች እንዳሉና ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ከሳምንት በፊት የሆቴሉ አስተዳደርና የሠራተኛ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ከማካሄድ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሁለቱም ባለመስማማታቸው ጠቅላላ ጉባዔው ሳይከናወን ቀርቷል፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እና ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም አበበ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ፈቃድ እንዲሰጠው መጠየቁንና የሆቴሉ አስተዳደርም ጥያቄውን ተቀብሎ ፈቅዶ ነበር፡፡

ነገር ግን የሆቴሉ አስተዳዳር ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆቴሉ የሰው ኃይል ዳይሬክተር ወ/ሮ አዳኑ ታፈሰ በተጻፈ ደብዳቤ፣ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ስብሰባ መሰረዙን አስታውቋል፡፡

በደብዳቤው መሠረት የስብሰባ ፈቃዱ የተሰጠው ለሆቴሉ ሠራተኞች ብቻ ነበር፡፡ ማኅበሩ ግን በስብሰባው ላይ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት አካላት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የቱሪዝም፣ ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ማኀበራት ፌዴሬሽን የጋበዘ ስለሆነ፣ ይኼንን ማስተካከል ካልተቻለ የተሰጠው የስብሰባ ፈቃድ ይሰረዛል፡፡

‹‹መጀመርያ ስብሰባው ሲፈቀድ የምናውቀው ስብሰባው ሠራተኛው ብቻ በተገኘበት እንደሚካሄድ እንጂ ሌሎች አካላት እንደሚገኙ አልነበረም፤›› ሲሉ የሆቴሉ ኃላፊ ክላውዝ ስቴነር በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ይኼ ሆን ተብሎ ሠራተኛው በነፃነት እንዳይናገርና በደሉን እንዳይገልጽ የተደረገ ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ የማኅበሩ ኃላፊዎች ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ማክሰኞ ዕለት ማኅበሩ በሰጠው መግለጫ ሥራ ላይ እያሉ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች በአግባቡ እረፍት ማግኘት እንዳልቻሉ ለአብነት ተገልጿል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ በቤት አያያዝ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት ወ/ሮ ፍቅርተ ገብረ ወልድ ከደረጃ ወድቀው በእጃቸውና በወገባቸው ላይ ጉዳት ቢደርስባቸውም፣ እረፍት ማግኘት ሲገባቸው ሥራ ገበታ ላይ እንዲገኙ እየተገደዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆቴሉ አስተዳደር ለወ/ሮ ፍቅርተ የተጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹ግለሰቧ ከሥራ ውጪና በሥራ ላይ እያሉ ወድቀው ጉዳት ስለደረሰባቸው ተገቢው የሕክምና ፈቃድ ቢሰጣቸውም የጤንነታቸው ሁኔታ መሻሻል ባለመቻሉ ፈቃድ እየተሰጣቸው በሥራ ላይ ከሚገኙባቸው ቀናት ይልቅ የማይገኙባቸው ስለሚያመዝን፣ በዚህ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን ለዘለቄታው መወጣት እንደማይችሉ በግልጽ ያረጋግጣል፤›› ይላል፡፡

በዚሁ ደብዳቤ ከነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሦስት ጊዜ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው እኚሁ ግለሰብ ተገልጾላቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሠራተኞችም ሥራ ላይ እያሉ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በግድ እንዲሠሩ እየተደረጉ መሆናቸውን የማኅበሩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረውና በአሁኑ ጊዜ 630 ሠራተኞች የሚያስተዳድረው የሒልተን ሆቴል መነሻ ደመወዝ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  600 ብር ነበረ፡፡ የመጨረሻው የደመወዝ እርከን ደግሞ 6,853 ብር ነው፡፡ ከደመወዝ እርከን ጋር በተያያዘ ሠራተኞቹ ባነሱት ጥያቄ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከ15 በመቶ እስከ 25 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ይኼ ማስተካከያ ለሠራተኞች የማይጠቅምና እነሱም እንዳልተስማሙበት የማኅበሩ አመራሮች ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሆቴሉ ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ወጥ የሆነ አሠራር የለውም ይላል፤›› ማኅበሩ፡፡ ‹‹መሰብሰባችንም መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው፤›› ሲሉም አቶ አብርሃም ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የሒልተን ሆቴል ኃላፊ ክላውዝ ስቴነር፣ እስካሁን ከሠራተኞች መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግል የመጣላቸው ጉዳይ የለም ብለዋል፡፡

ከደመወዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ በተገቢው መንገድ እየሠራ እንደሆነና እስካሁንም የተደረገው በቂ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩ አመራሮች ግን ጥያቄያቸው በአግባቡ ምላሽ ካላገኘ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ለአቤቱታ እንደሚሄዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው የታሰሩ ተከሰሱ

$
0
0

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 1/2009ን ተላልፈዋል በሚል ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉትና ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ የነበሩት፣ የቀድሞ አንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ ኤልያስ ገብሩ (ጋዜጠኛ) ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ አዋጁን በመተላለፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 1/2009 አንቀጽ 2(1) እና (2)ን መተላለፋቸውን፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ካዲስኮ አካባቢ ተይዘው ሲፈተሹ፣ አቶ ዳንኤል ጥቁር ህዋዌ ሞባይል ስልክ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በጋዜጠኝነት ለበርካታ ዓመታት የሠራው አቶ ኤልያስ ደግሞ ሳምሰንግ ሞባይል ይዞ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡

በአቶ ዳንኤል ሞባይል ስልክ ውስጥ ‹‹ተማምሏል ጎንደር›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ቪዲዮ፣ የግንቦት ሰባት አመራሮች ምሥልና ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ መገኘቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 12(1)ና መመርያ ቁጥር 1/2009 አንቀጽ 2(3) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ አቶ ዳንኤል፣ የኢሳት ቴሌቪዥንን ፕሮግራሞች ቪዲዮና ለቴሌቪዥን ጣቢያው የሰጡትን መግለጫ ሪፖርት በስልካቸው ውስጥ መገኘቱን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም አቶ ዳንኤል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸውን ድርጊቶች ተላልፈው በመገኘታቸው፣ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ማድረግ ወንጀልና የሽብርተኛ ድርጅቶች ሚዲያዎችን መከታተልና ሪፖርት ማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አቶ ኤልያስ ሲፈተሽ በተገኘው የሳምሰንግ ሞባይሉ ውስጥ የኢሳት አመራሮች ምሥሎች፣ የሽብርተኛ ድርጅቶችን ሐሳብ የሚገልጹ ጽሑፎችና ምሥሎች መገኘታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ሌላው በሞባይሉ ውስጥ የተገኘው፣ ‹‹መለስ ብዙኃኑን የማጥፋት ሴራ፣ ትግሬን ታላቅ የማድረግ ቅዥት፣ ፀረ አማራ፣ የሁሉም ድክመት ተጠያቂ አማራ ነው ብሎ የሚያስብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተባብሮ ቡናን ብቻ ባለመሸጥ ማዕቀብ ቢጥል ለመቀሌ ዘይት መግዣና ለሕዝባችን ጥይት መግዣ… በመቸገር የሚንበረከክ ወያኔ እናያለን…›› የሚል መጣጥፍ መገኘቱን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ጎንደር በወራሪው ሕወሓት ሠራዊት ተወረረች…፣ ትምህርት ከድል በኋላ፣ በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደባችሁ ተማሪዎች እንዳትሄዱ…›› የሚሉና የትግራይ ክልል ከድሮው የሰፋ መሆኑን የሚያሳይ የካርታ ምሥልና ይዞታ መገኘቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም መቻቻልንና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር በመፈጸም ወንጀልና ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት በማድረግና በማስተዋወቅ ወንጀል ክስ መመሥረቱን ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በጠበቃቸው አማካይነት ባቀረቡት ተቃውሞ አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ክልከላና የቅጣትን መጠን ማስቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሕግ መርህ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይም ሆነ ማስፈጸሚያ መመርያም ላይ የተቀመጡ አንቀጾች የያዙት በአዋጁ የተከለከሉትን መተላለፍ እንደማይቻል ብቻ የሚገልጹ መሆኑን ተከሳሾቹ ገልጸው፣ በማመሳሰልና በማቀራረብ (አናሎጂ) አንድ ሰው ሊከሰስ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ሌላው በአዋጁ መመርያ 1/2009 አንቀጽ 2(1) እና (2) ስር የነበሩት ክልከላዎች በመመርያ ሁለት ቀሪ የተደረጉ በመሆናቸውና ሕግ ወደኋላ ሄዶ ሊሠራ ስለማይችል ሊከሰሱ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

ክልከላ ወንጀል ካለመሆኑም ሌላ፣ እነሱ ደግሞ የተከለከሉትን ተላልፈዋል በሚል ከስድስት ወራት በላይ ስለታሰሩ በነፃ ሊሰናበቱ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠይቀው፣ ‹‹ተከሳሾች ሕግ ጠቅሰው ስለተከራከሩ ምላሻችንን በጽሑፍ እናቅርብ›› በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ለግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

እንደ አዲስ ለመቋቋም የመንግሥትን ውሳኔ የሚጠባበቀው የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ በሠራተኞች ፍልሰት መቸገሩን አስታወቀ

$
0
0

 

  • የመስክ ተሽከርካሪዎች እጥረት በሥራዬ ላይ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል

ከተመሠረተ 71 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ፣ እንደ አዲስ ለመቋቋም ከስያሜ ጀምሮ ለውጥ የሚያደረግበትን ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ለማፀደቅ እየተጠባበቀ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሠራተኞች ፍልሰት እዳስቸገረው አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሐመድ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ለመሥራት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል 600 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጠናና የሥራ ልምድ ያካበቱ 250 ሠራተኞቹ ወደ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ፈልሰውበታል፡፡ በቀሩት 350 ሠራተኞች የሚጠበቁበትን ሥራዎች ለመፈጸም ቢታገልም፣ ያሉትንም ለማቆየት የሚቻልባቸውን ማሻሻያዎች ማድረግ ግድ እንደሚል አቶ ሱልጣን አሳስበዋል፡፡

ከሚለቁት ሠራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ በሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ዝቅተኛነት ምክንያት ለመልቀቅ እንደሚገደዱ በተደረጉ ውይይቶች ወቅት መረዳታቸውን ያስታወቁት አቶ ሱልጣን፣ ይሁንና ሁሉም ሠራተኞች ግን ተመሳሳይ ሥራ ወደሚሠሩና ከኤጀንሲው የተሻለ የደመወዝ ስኬልና ጥቅማ ጥቅም ወዳላቸው የመንግሥት ተቋማት ይሄዳሉ ብለዋል፡፡ እንደ ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እና እንደ ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ያሉ መሥሪያ ቤቶች ከኤጀንሲው ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚያከናውኑ ቢሆኑም፣ ከካርታ ሥራዎች ይልቅ ከፍተኛ የደመወዝ ስኬል ስላላቸው ሠራተኞች እየለቀቁ እንደሚሄዱ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ኤጀንሲው ተመጣጣኝ የደመወዝ ስኬል እንዲኖረው የሚያስችል ጥናት አጥንቶ ለመንግሥት ማቅረቡንም አቶ ሱልጣን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲው ለመስክ ሥራ የሚያስፈልጉትን ተሽከርካሪዎች በበቂ መጠን ማግኘት ካለመቻሉም በላይ፣ ያሉትም ቢሆኑ አብዛኞቹ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ጫና ውስጥ እንደከተቱት ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ሱልጣን ማብራሪያ፣ ተቋሙ ካሉት 20 የመስክ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 15 ያህሉ 30 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ የተቀሩት አምስቱም ቢሆኑ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ችግሮቹን በመቅረፍ ዓለም የሚገኝበት ዘመናዊ የካርታ፣ የቅየሳ፣ የሪሞት ሴንሲንግ ሥራዎችን በማጠቃለል ዘመናዊ የመልከዓ ምድር መረጃዎችን (ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን) በጥራትና በቅልጥፍና ለማቅረብ ከስያሜ ጀምሮ የአደረጃት ለውጥ ለማድረግ የሚያስችለውን የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለማፀደቅ እየተጣበቀ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ኤጀንሲው ተጠሪ ለሆነበት ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አቅርቦ እንደታመነበትና የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያፀድቀው አቶ ሱልጣን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

85 በመቶ የአገሪቱን ክፍሎች የሚሸፍን 1፡ 50,000 መሥፈርት ካርታን ወደ 1፡25,000 ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ ያስታወቀው ኤጀንሲው፣ በአሁኑ ወቅት በአናሎግ ደረጃ የነበሩ የአገሪቱን ካርታዎች ወደ ዲጂታል መቀየር እንደቻለም አስታውቋል፡፡

ከ71 ዓመታት በፊት በአሜሪካ መንግሥት እገዛ የተመሠረተው ኤጀንሲው ለመመሥረቱ ምክንያት የሆነውም በዓባይ ሸለቆ ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ የጥናትና የቅየሳ ሥራዎች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ አሜሪካውያኑ ኤጀንሲው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የሚያበቃውን የቅየሳና የካርታ ሥራ እንደሠሩም ይነገራል፡፡ ይሁንና በ1973 ዓ.ም. በአዋጅ በመቋቋም፣ በ1980 ዓ.ም. የተቋቋመበት አዋጅ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚሁ አግባብ ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀው የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ፣ በ2003 ዓ.ም. ባደረገው ጥናት መሠረት ማሻሻያዎች ሊደረጉለት እንደሚገባ አስታውቆ ነበር፡፡

የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት የልዩ ተግባር፣ ጠቅላላ መሠረታዊ ካርታዎችን ማምረት፣ የቅየሳ መቆጣጠሪያ ነጥቦችን ማስፋፋት፣ በተለያየ ወቅት የተነሱ የአየር ፎቶግራፎችንና የሳተላይት ምሥሎችንና ሌሎችንም ምርቶችና አገልግሎቶች እያቀረበ ይገኛል፡፡

 

 

Standard (Image)

በዱከም የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ሊገነባ ነው

$
0
0

 

  • ዘንድሮ ለ3.4 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል

  የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ከአዋሽ በመቀጠል በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ዱከም አካባቢ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ሊገነባ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንተርፕራይዙ የነዳጅ ዴፖ ግንባታ ለማካሄድ ከኦሮሚያ ክልል አሥር ሔክታር መሬት ተረክቧል፡፡

በአዋሽ አካባቢ ቀደም ሲል 100 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር መጠባበቂያ ነዳጅ የሚይዙ ዴፖዎች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ በዚሁ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለዕለት ተዕለት ተግባር የሚውል 36 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር የሚይዝ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ግንባታ  እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የአዋሽ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ግንባታው ከ90 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ በቀጥታ ከባቡር ነዳጅ መቀበል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ ግንባታው ያለበትን ደረጃ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዴፖ ግንባታ በጥልቀት እንደሚካሄድ አቶ ታደሰ ገልጸው፣ በዱከም የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ለመገንባት ፕሮጀክት መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት በዱከም ሊገነባ ለታቀደው ዴፖ የዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት እንደሚካሄድና ይህም ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ግንባታ እንደሚገባ አክለዋል፡፡

ባቡሩ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምር አገሪቱ የምታስገባውን 60 በመቶ ያህል ነዳጅ እንደሚያጓጉዝ የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ በ2009 ዓ.ም በአጠቃላይ 3.4 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ ወደ አገር እንደገባና እንደሚገባ፣ ለነዳጅ ግዥና ለተያያዥ ክንውኖች ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገ አቶ ታደሰ አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ የባቡር መስመሩ ግንባታ ከተገባደደ በኋላ ዘግይቶም ቢሆን ከሆራይዘን ወደብ ጋር የባቡር መስመሩን ለማገናኘት የሚያስችል ግንባታ እየተጀመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነዳጅ በባቡር ማመላለስ አዋጭ ቢሆንም፣ ከአዲስ አበባ (ሰበታ) እስከ ጅቡቲ ድረስ ያለው 756 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር በሚገነባበት ወቅት፣ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ግንባታ ቀደም ብሎ አለመታሰብን የሚያመላክቱ አሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል የባቡር መስመሩ ግንባታ ሲካሄድ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖና አብዛኛውን የኢትዮጵያ ነዳጅ የሚገባበትን የጂቡቲ ሆራይዘን ወደብ ከባቡር ሐዲዱ ጋር እንዲገናኝ አለመደረጉ ነው፡፡

አንድ የባቡር ዋገን (ሞተር) 36 ፉርጎዎችን የመጎተቱ አቅም እንዳለው አቶ ታደሰ ገልጸው፣ አንድ ዋገን 70 ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚይዙትን ያህል ነዳጅ የማጓጓዝ አቅም አለው ብለዋል፡፡ ‹‹አንድ ፉርጎ 80 ሺሕ ሊትር ሲይዝ፣ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ ግን 45 ሺህ ሊትር ይይዛል፤›› በማለት የባቡርን አዋጭነት ጠቁመዋል፡፡

Standard (Image)

የቻይና ፕሮጀክቶች ከ111 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ተገለጸ

$
0
0

 

እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው የቻይና መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረገ ባለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለ57,555 ቋሚና ለ53,669 ጊዜያዊ፣ በአጠቃላይ ለ111,224 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተጠቆመ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የቻይና ባለሀብቶች በ674 ፕሮጀክቶች ላይ በመሰማራት ከ3.86 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ እያፈሰሱ ነው፡፡

ሁለቱ አገሮች በንግድ ዘርፍ ለመተባበር የሚያስችል ስምምነት እ.ኤ.አ በ1996 የተፈራረሙ መሆኑን አቶ መለስ አስታውሰው፣ የንግድ ምጣኔውም እ.ኤ.አ. በ2004 357 ሚሊዮን ዶላር የነበረው እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 6.37 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሁለቱ አገሮች የንግድ ምጣኔ በየዓመቱ በአማካይ 22.2 በመቶ እያደገ ነው ብለዋል፡

ኢትዮጵያና ቻይና የልማትና የቴክኒክ ትብብር የተፈራረሙት እ.ኤ.አ. በ1971 እንደሆነ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ የትብብር ዓይነቱና ስትራቴጂያዊ አጋርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ብድር የመስጠት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የገለጹት አቶ መለስ፣ ቻይና ከወለድ ነፃ ብድርና ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን በገበያ ዋጋ የንግድ ብድር ወደ መስጠት እየተሸጋገረች በመሆኑ ኢትዮጵያም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆናለች ብለዋል፡፡

ከቻይና በተገኘው የልማት ዕርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህም መካከል የወረታ-ወልዲያ መንገድ፣ የዕድገት የክር ፋብሪካ፣ የሃሬ መስኖ ልማት፣ የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ግንባታ፣ የኮል ፎስፌት የማዳበሪያ ፋብሪካ ማቋቋሚያ ጥናት፣ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ፣ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥናት፣ የወሎ ሠፈር-ጎተራ መንገድ ግንባታ፣ የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የማሽነሪ ግዥ፣ የግብርና የቴክኒክና የሙያ ትምህርት የቁሳቁስ ዕርዳታ፣ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ተጠቃሾች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 13 ቀን 2017 ጀምሮ በቻይናና በሌሎች የእስያ አገሮች መሥራችነት እ.ኤ.አ. በ2012 የተቋቋመው ‹‹ኤዥያ ኢንፍራስትራክቸር ኢንቨስትመንት›› አባል በመሆኗ፣ ባንኩ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆንላት ተገልጿል፡፡

በቅርቡ ቻይና ተካሂዶ በነበረው ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› ፎረም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በቆይታቸው ቻይና ውስጥ ከሚገኙ 17 ታላላቅ ኩባንያዎች ጋር የአንድ ለአንድ ውይይቶችን በማካሄድ፣ ስለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ገለጻና ማብራሪያ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Standard (Image)

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ ለአዳዲስ በረራዎች ፈቃድ ተጠየቀ

$
0
0

 

  • መንግሥት ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርቧል

በሳዑዲ ዓረቢያ ያለሥራና ያለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የትራንስፖርት ችግር መኖሩ ተጠቆመ፡፡ ኢትዮጵያዊያኑን በፍጥነት ለመመለስም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለአዳዲስ በረራዎች ፈቃድ ተጠይቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንዲሁም ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ በሚደረገው የአውሮፕላን በረራ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያንን የዕፎይታ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት፣ የትራንስፖርት ችግር ማጋጠሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ እንዳስታወቁት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ እንዲመለሱ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ዜጎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ካጋጠሙት እንቅፋቶች መካከልም የትራንስፖርት ችግር አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንዲሁም ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረውን በረራ ለመጨመር፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፈቃድ እንደተጠየቀ አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡ የዕፎይታ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ዜጎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፈቃደኛ በሚሆንበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ጅዳ፣ ከአዲስ አበባ ጂዛንና ከአዲስ አበባ ሪያድ አዳዲስ በረራዎች እንደሚጀመሩ አስረድተዋል፡፡ ከማጓጓዙ ጋር በተያያዘም የሚካሄደው የትኬት ሽያጭ በትኬት ጽሕፈት ቤቶች ብቻ ውስን ስለነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ ሲባል በሪያድ፣ በጂዳና በጂዛን የሚገኙ የኮሙዩኒቲ ጽሕፈት ቤቶች የትኬት አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ያስቀመጠችው ጊዜ ገደብ ከሃያ ቀናት ያልበለጡት በመሆኑ፣ ዜጎችን በመመለስ ጥረት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የብሔራዊ ዜጎች አስመላሽ ግብረ ኃይል ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ጥረት የበለጠ ለማፋጠን በአንድ አምባሳደር የተመራ በአጠቃላይ 12 ዲፕሎማቶችን የያዘ ልዑካን ቡድን ወደ ሪያድና ጂዳ እንደተላከ አቶ መለስ ጠቁመው፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ዜጎችን በመመለስ አገራዊ ተልዕኮ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም ዜጎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ክልሎች እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ የኦሮሚያ፣ የአማራና የደቡብ ክልሎች ሃያ የሚሆኑ ኃላፊዎችን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለቅስቀሳ ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራው ዜጎችን አስመላሽ ግብረ ኃይል፣ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመሄድ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራቱ ተጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያው ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሳይንገላቱ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡበት ጉዳይ ላይ የመከረ መሆኑን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ዓመት በላይ እልህ አስጨራሽ ምክክርና ድርድር በኋላ በኢትዮጵያና በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታት መካከል የተፈረመው የሥራ ሥምሪት ስምምነት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዋና ጭብጦች ናቸው ከተባሉ ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሲሄዱ፣ በሁለቱ መንግሥታት በኩል ሊሟሉ የሚገባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሄዱ የሚያደርገውን ይህንን ስምምነት ጨምሮ እስካሁን የተፈረሙ ስምምነቶች አራት እንደሚያደርሰው አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ከኩዌት፣ ከኳታርና ከዮርዳኖስ ጋር ስምምነቶች መፈረማቸውን አስታውሰዋል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብታቸው በሕግ ተከብሮ እንዲኖሩ ማድረግና አሠሪውም ሆነ ሠራተኛው ኮንትራቱን እንዲያከብር በስምምነቱ ላይ ተገልጿል ብለዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ በገቡ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ላይ በደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳትና እንግልት ምክንያት መንግሥት የጉዞ ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ‹‹የአፍሪካ አገሮች፣ የኅብረቱ ሊቀመናብርትና ሠራተኞች ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ዕጩአቸው አድርገው እስከ መጨረሻ በመደገፋቸውና የእስያ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የካሪቢያንና የአውሮፓ አገሮች ድምፃቸውን ለእሳቸው በመስጠት ላደረጉት ትብብር መንግሥት ታላቅ ምሥጋና ያቀርባል፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን ጥቅም ለማስከበር ከተለያዩ አካላት ጋር ተባብራ እንደምትሠራ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ በዓለም አቀፍና በበይነ መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ ያላትን ውክልና ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አክለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች አገራቸውን ወክለው በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲወዳደሩ በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የውክልና ቦታዎችን አዘጋጅቶ በማቅረብ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ተደማጭ በማድረግና የአፍሪካን አጀንዳም በማራመድ መድረክ የተጠናከረ ሥራ ወደፊት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡  

Standard (Image)

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አደረጃጀት በአሜሪካ አማካሪ ኩባንያ ሊጠና ነው

$
0
0
  • የልማት ድርጅቶች የትርፍ ድርሻ ውሳኔ አላገኘም

 

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሰኔ 2008 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 916 ሲቋቋም ተጠሪነታቸው ለሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሆኖ፣ የኮርፖሬት አስተዳደርና የፋይናንስ አፈጻጸማቸውን ብቻ እንዲከታተል ኃላፊነት ከወሰደባቸው ግዙፉ መንግሥታዊ ኮርፖሬሽኖች ጋር የሥልጣን መደራረብ በመፈጠሩ፣ ይኼንን የሥልጣን መደራረብ የሚያስቀር ጥናት እንዲያካሂድ ታዋቂው የአሜሪካ አማካሪ ኩባንያ መኬንዚ ተቀጠረ፡፡

ለሌሎች ሚኒስቴሮች ቀጥታ ተጠሪ ሆነው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የኮርፖሬት አስተዳዳርና የፋይናንስ አፈጻጸም ክትትልና ድጋፍ የሚደረግላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ናቸው፡፡

እነዚህ ግዙፉ ኮርፖሬሽኖች ተጠሪነታቸው ለሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በመሆኑ፣ በሥራ አመራር ቦርድ የሚመሩ ናቸው፡፡ የኮርፖሬት አስተዳዳርና የፋይናንስ አፈጻጸማቸው ደግሞ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ይካሄዳል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥራውን በሚያካሂድበት ወቅት የኃላፊነት ወሰን እየተደራረበ በመሆኑ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ ይኼ አሠራር ሊስተካከል እንደሚገባ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገር ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያልሞላውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ በድጋሚ አሠራሩን ለማስተካከል ተወስኗል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ረዳት ኃላፊ አቶ አሰበ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአሜሪካው ኩባንያ መኬንዚ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት፣ አጠቃላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አደረጃጀት ምን መሆን እንዳለበት አጥንቶ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

‹‹ምክንያቱም ኮርፖሬሽኖቹ ተጠሪነታቸው ለሁለት መሥሪያ ቤቶች መሆኑ ችግር ፈጥሯል፤›› ሲሉ አቶ አሰበ ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካው ኩባንያ ከአደረጃጀት ጥናት በተጨማሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርን የሚመለከቱ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ባወጣው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ይኼንን ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የቻይና፣ የህንድ፣ የሲንጋፖርና የቬትናም ልምዶች በማየት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋቸውን ለመንግሥት  ፈሰስ ከማድረግ ይልቅ፣ ራሳቸውን ለማሳደግ እንደሚያውሉት ዕቅድ ተይዟል፡፡

‹‹የልማት ድርጅቶች ለመንግሥት ታክስና የትርፍ ድርሻ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ የትርፍ ድርሻ ክፍያው ግን አብዛኛው በገንዘብ ሚኒስቴር የሚወሰን ሲሆን፣ መጠኑ የተለያየ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች እንደ ተጨባጭ ሁኔታቸው በማስላትና ዕቅዳቸው ላይ በመመሥረት እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን የትርፍ ድርሻ ክፍያ ራሳቸው ሥራ ላይ እንዲያውሉት ይደረጋል፤›› የሚለው ሚኒስቴሩ ያወጣው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የሌሎች አገሮችን ልምድ ጠቅሶ፣ ‹‹በኢትዮጵያ በኩልም አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በጋራ ይሠራል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

በተለይ በመንግሥት ሥር እንዲቆዩ የተደረጉ ስትራቴጂካዊ ኮርፖሬሽኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ ሆነው እንዲሠሩ፣ ትርፋቸውን ለብሔራዊ ግምጃ ቤት ፈሰስ ከማድረግ ይልቅ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ እንደሚገባ ዕቅዱ ያስረዳል፡፡

የቀድሞ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቢያንስ 20 በመቶ ትርፋቸውን ራሳቸው እንዲጠቀሙ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ እስካሁን  በመቆየቱ፣ ኤጀንሲው በሚኒስቴር ደረጃ ከተዋቀረም በኋላ በትልቅ ዕቅድ ይህንኑ ሐሳብ አሻሽሎ አቅርቧል፡፡

ነገር ግን በትርፍ ድርሻ ፈሰስ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ውሳኔ ያልተሰጠበት በመሆኑ፣ አማካሪ ድርጅቱ መኬንዚ ይኼንኑ ጉዳይ ጨምሮ እንደሚያጠና እና የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

Standard (Image)

በኦሮሚያ ክልል ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጻሕፍት ክለሳ ሊደረግባቸው ነው

$
0
0

 

በኦሮሚያ ክልል ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ከአምስት ዓመት በላይ በሁለተኛ ቋንቋነት ሲያገለግሉ የነበሩ የተማሪዎች አማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ክለሳ ሊደረግባቸው መሆኑ ታወቀ፡፡

ሰሞኑን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በክልሉ ይሰጥ የነበረው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የተማሪዎችን የአማርኛ ቋንቋ ክህሎት በተገቢው ሁኔታ የማያጎለብትና የማያዳብር ሆኖ በመገኘቱ እንዲሻሻል ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ባገኘው ድጋፍ የአዲሶቹ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ አራት ክፍሎች ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ሊያዘጋጅ ነው፡፡ የመጻሕፍቱ ብዛት ሦስት ሚሊዮን ሲሆን፣ የኅትመትና የሥርጭት ጨረታ አውጥቶ ሰነዱ በመሸጥ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስካሁን ድረስ ከአሥር በላይ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት የጨረታ ሰነዱን እንደገዙ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የጨረታ ሰነዱ ሽያጭም እስከ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በረሶ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በክልሉ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የማንበብና የመጻፍ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ በክልሉ ያሉ የቋንቋ ማስተማሪያ መጻሕፍት ላይ ክለሳ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እንደ  ኃላፊው ገለጻ፣ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ከቀላል ፊደል ጀምሮ የማንበብና የመጻፍ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሲባል አዲስ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ቶላ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት አዲሶቹ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተማሪዎች እጅ እንደሚገቡ ገልጸው፣ የተከለሱትን አዳዲስ የቋንቋ መጻሕፍት ለማስተማር ሲባል በክረምት ወቅት ከ63 ሺሕ በላይ መምህራን ሠልጥነው ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል፡፡

Standard (Image)

በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የቀረበው ክስ እንዲሻሻል ብይን ተሰጠ

$
0
0

 

 ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ በዋና ወንጀል ላይ ተካፋይ በመሆን፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን በመተላለፍና የሐሰት ወሬዎችን በማውራት ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር  መረራ ጉዲና፣ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ መሠረት ክሱ እንዲሻሻል ፍርድ ቤት ዓርብ ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ብይን ሰጠ፡፡

ዶ/ር መረራ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ በመቃወም ያቀረቡትን አቤቱታና ዓቃቤ ሕግ የሰጠውን ምላሽ የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከተከሳሽ ጋር ክስ የቀረበባቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ክሶችን ዓቃቤ ሕግ እንዲያሻሽል ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ ኢሳትና ኦኤምኤን ሕጋዊ ድርጅቶች መሆን አለመሆናቸው ተገልጾ መቅረብ አለበት፡፡ ድርጅቶቹ ሕጋዊ ከሆኑ በየትኛው አገር እንደሚገኙ፣ መቼና እንዴት እንደተቋቋሙ ተገልጾ መቅረብ አለበት፡፡ በመሆኑም ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ዶ/ር መረራ በዕለቱ ማለትም ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠበቆቻቸው አማካይነት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ተከሳሹ ባቀረቡት አቤቱታ ከቀረቡባቸው ክሶች ጋር የደረሱዋቸው ማስረጃዎች፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን የተከተሉ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ባልተከሰሱበት በሽብርተኝነት አዋጁ መሠረት የቀረቡ በመሆናቸው፣ ተስተካክለው እንዲደርሱዋቸው እንዲታዘዝላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ አቤቱታው መቅረብ የነበረበት ቀደም ብለው ካቀረቡት የክስ መቃወሚያ ጋር መሆን አስታውቆ ተቀብሏቸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ የሚያቀርበውን ክስ ለመቀበልና ተከሳሹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

 

Standard (Image)

የኢንተርኔት መቋረጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እያወከ ነው

$
0
0

 

በዳዊት እንደሻው

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ኢንተርኔት በመቋረጡ፣ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

ከአሁን ቀደም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በነበረው ቀውስ፣ መንግሥት ኢንተርኔት እንዲቋረጥ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በየዓመቱ ከሚደረገው የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሥጋት መንግሥት ኢንተርኔት አቋርጧል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ፈተና በመሰረቁ ኢንተርኔት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ ፈተናው ተሰርቆ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቀድሞ መለቀቁ ለኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ 246,452 የሚሆኑ የ12ኛ እና 1,029,782 የሚሆኑ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸው አይዘነጋም፡፡

ዓምና መንግሥት ለፈተና ዝግጅት 250 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ፈተናው ተሰርቆ ከወጣ በኋላ ሌላ ፈተና ለማዘጋጀት ተገዶ ነበር፡፡ እስካሁን ከፈተናው መሰረቅ ጋር ተያይዞ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በመንግሥት በተወሰደ ዕርምጃ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገ በመሆኑ፣ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር መፍጠሩ ታውቋል፡፡

‹‹እኛ የምናውቀው ኢንተርኔቱ ሙሉ በሙሉ አለመቋረጡንና የተወሰደውም ዕርምጃ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ነው፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰይድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት መቋረጡ ከማኅበራዊ ድረ ገጾች አልፎ የኮምፒዩተርና የሞባይል ስልክ ተገልጋዮች ዘንድ ደርሷል፡፡

የንግድ ተቋማት፣ ባንኮች፣ የመረጃና ቴክኖሎጂ ተቋማትና የጉዞ ወኪሎች በዚህ የኢንተርኔት መቋረጥ ተጠቂ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል ሞደርን ኢትዮጵያ የተባለ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ከሳይበር ጋር በተያያዙ ሥራዎች  የሚታወቀው ድርጅት ይገኝበታል፡፡

ይህ ድርጅት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጀቶች ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ በኢንተርኔት መቋረጥ ሳቢያ አጋር ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት ያከናውኑት የነበረውን ሥራ አቋርጠው ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንደሄዱ፣ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡

‹‹ይኼ ለእኛ በጣም የሚያናድድ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሆቴሎች በዚህ የኢንተርኔት መቋረጥ ተጠቂ ሲሆኑ፣ በችግሩ ምክንያት በኢንተርኔት የሚደረግ የመኝታ አገልግሎት ቡኪንግ ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደ 25 በመቶ የሚጠጋው የሆቴል ቡኪንግ በኢንተርኔት የሚከናወን ነው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሆቴላቸውም ሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሆቴል አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በመረጃ ፍሰቱ ላይ በተፈጠረው መቋረጥ እነዚህን ሁሉ ነገሮች መሥራት አልቻልንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክሬዲት ካርድ የሚደረጉ ክፍያዎችን፣ የሆቴሉን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ክፍያዎችን፣ እንዲሁም  በተለያዩ የሥራ ክፍሎች መካከል የሚደረጉ የመረጃ ልውውጦችን ማከናወን እንደተቸገሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ለአገሪቱ ገጽታ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፤›› ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንዳየው ኢንተርኔት ከተቋረጠ ጀምሮ ከሒልተን ሆቴል በስተቀር በአብዛኞቹ ሆቴሎች ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሒልተን ሆቴል ኢንተርኔት መጠቀም በሚፈልጉ ደንበኞች ተጨናንቆ ተስተውሏል፡፡

ይህ የኢንተርኔት መቋረጥ የተከሰተው ሆቴሎች በአስቸኳይ አዋጁና በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ወደ 380 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳጡ በገለጸ በሳምንታት ውስጥ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተቋረጠው ኢንተርኔት እንደ ራማዳና ካፒታል የመሳሰሉ ሆቴሎች ላይ ከሁለት ቀናት በኋላ መሥራት እንደጀመረ ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል፡፡

 ከዚሁ ከሆቴል ሥራ ጋር በተያያዘ የጉዞ ወኪሎች የችግሩ ተጠቂ ሲሆኑ፣ በአብዛኛው በኢንተርኔት የሚሰጡ አገልግሎቶች ተቋርጠውባቸዋል፡፡

ከተመሠረተ ሁለት ዓመት የሆነው ጁመያ የጉዞ ወኪል 26 ሠራተኞች ቀጥሮ የሚያሠራ ድርጅት ሲሆን፣ በዚሁ ችግር በሳምንት በአማካይ የሚደረጉ ከ60 እስከ 80 የሆቴል ይያዝልን ጥያቄዎች ቆመዋል ይላል፡፡ ‹‹አሁን ምን ያህል እያጣን ነው የሚለውን መግለጽ ቢከብድም፣ ነገር ግን እየሠራን እንዳልሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ሲሉ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ኤደን ሳህሌ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ባንክ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ሥራቸው እየተስተጓጎለባቸው ነው፡፡ የገንዘብ ማስተላላፊያ ስዊፍት፣ ከወጪና ከገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ የባንክ ሥራዎች መስተጓጎላቸውን የባንክ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ከገንዘብ ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የግል ባንኮች የሎተሪ ወይም የሽልማት ዘመቻ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎች በአጠቃላይ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ መቋረጡን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ደንበኞች ገንዘብ ሲላክላቸው በእኛ ባንክ በኩል እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ሽልማት ብናዘጋጅም፣ ሰሞኑን ግን ይህን ማድረግ አልቻልንም፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባንክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ሎተሪ ይኼን የሽልማት ዘመቻ እንድናደርግ ውስን የጊዜ ፈቃድ ቢሰጥንም፣ በቀጣይ ሳምንታት ግን ምንም ማድረግ እንደማንችል ተገንዝበናል፡፡ ለዚህ ዘመቻ ብዙ ወጪ ብናወጣም የኢንተርኔት መቋረጥ ልፋታችንን መና አስቀርቶታል፤›› ሲሉ እኝሁ ኃላፊ አክለዋል፡፡

በኢንተርኔት ሳቢያ መቋረጥ ከገቢና ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ባንኮች ሥራቸውን ማከናወን እንደተሳናቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይኼ ማለት በቀላል አማርኛ  ገቢና ወጪ ንግድ ቆመ ማለት ነው፤›› ሲሉ አንድ የግል ባንክ የመረጃና የቴክኖሎጂ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊ ድረ ገጽን ስንዘጋ ተማሪዎችን ከሚፈጠረው አለመረጋጋት ለመጠበቅና ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲወስዱ ነው፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡    

Standard (Image)

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ

$
0
0

 

  • መንግሥት ከ8.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል ተብለዋል

በቅርቡ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ብድር ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ደርቤ አስፋው ሁሪሳ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የብድር ክፍል ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ ኅዳር 12 ቀን 1992 ዓ.ም.፣ ሚያዝያ 12 ቀን 1992 ዓ.ም. እና ሚያዝያ 12 ቀን 1993 ዓ.ም. በተደረጉ ሦስት ውሎች ከተለቀቀ ብድር ጋር በተያያዘ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ብድሩን የወሰደው ናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑን፣ የተፈቀደለትን 35 ሚሊዮን ብር ብድር የሚመጥንና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 27 ቀበሌ 01 ውስጥ በካርታ ቁጥር 0270 የሚታወቀውን ንብረት ዋስትና አስይዞ እንደነበር፣ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ተበዳሪው ማኅበር በውሉ መሠረት ግዴታውን ባለመወጣቱ አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመያዣነት የተረከበውን ንብረት በጨረታ እንዲሸጥ ማድረጉንም ፖሊስ ገልጿል፡፡ በመያዣነት በተያዘው ግቢ ውስጥ ሌላ ንብረት ስለመኖሩ የባንኩ መሐንዲስ አስተያየት የሰጠ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው አቶ ደርቤ ግን አስተያየቱን ችላ በማለት ያልተገመተና በጨረታው ያልተካተተ ንብረት፣ ንብረቱን ለገዛው አካል እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መንግሥት ሊያገኝ የነበረውን 8,545,640 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውንና በፈጸሙት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ቀሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስረድቶ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ደርቤ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በተገለጸው የሥራ ኃላፊነት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ይሠሩ ነበር፡፡ በ1992 ዓ.ም. ግን በባንኩ ውስጥ አልነበሩም፡፡ ያልተገመተና ያልተሸጠ ንብረት አስተላልፈዋል የተባሉት ለአቢሲኒያ ባንክ መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ተላለፈ የተባለው ንብረት የናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ንብረቶቹ ቢገመቱ ኖሮ ንግድ ባንክ ሸጦ 8,454,640 ብር ያገኝ ነበር ተብሎ የቀረበባቸው ክስ እንዴት ከዓመታት በኋላ ሊነሳ እንደቻለም እንዳልገባቸው ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንትና የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ካለባቸው ኃላፊነትና ለአገርም ካደረጉት ትልቅ አስተዋጽኦ አኳያ የፍርድ ሒደቱን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ግን ከመሥሪያ ቤቶች የሚሰበስባቸው ሰነዶች እንዳሉ ገልጾ፣ በዋስ ቢወጡ ሰነድ ሊያጠፋ እንደሚችሉ በማስረዳት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም መርማሪው ቃል ለመቀበልና ሰነድ ለመመርመር ስድስት ቀናት እንደሚበቁት በማስታወቅ፣ ለግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት አቶ ደርቤ ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ አልፎታል፡፡

Standard (Image)

ብሔራዊ ባንክ የወጋገን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሹመት አፀደቀ

$
0
0

በዳዊት እንደሻው

ወጋገን ባንክ አቶ ደሳለይ እንበዛ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሾሙለት ያቀረበውን ጥያቄ ብሔራዊ ባንክ አፀደቀ፡፡ አቶ ደሳለይ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የአገልግሎት ክዋኔ ዘርፉን ይመራሉ፡፡

በሹመቱ መሠረት አቶ ደሳለይ ከአሁን በፊት በቦታው የነበሩትን አቶ አሰፋ ተፈራን ይተካሉ፡፡ ከአሁን ቀደም ቦታውን ሲመሩት የነበሩት አቶ አሰፋ፣ ከአንድ ወር በፊት ከቤተሰብ ጋር በተያያዙ የግል ምክንያቶች መልቀቃቸው ታውቋል፡፡

አቶ አሰፋ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ሹመታቸውም ወጋገን ባንክ አጠቃላይ የአስተዳደር መዋቅረ ለውጥ ካደረገ በኋላ የመጣ ነው፡፡

የአስተዳደር መዋቅር ለውጡ ዲሎይት በተባለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ከተደረገ ጥናት በኋላ የመጣ ሲሆን፣ የመዋቅር ለውጡም ድሮ ያልነበሩ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታዎችን አስተዋውቋል፡፡ በዚህም መሠረት የኮርፖሬት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የአገልግሎት ክዋኔ፣ እንዲሁም የድጋፍ ዘርፎች በምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲመሩ ተዋቅረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ባንኩ ሁለት የምክትል ፕሬዚዳንት ቦታዎች እንደነበሩት ይታወሳል፡፡

አሁን የተሾሙት አቶ ደሳለይ ከአሁን ቀደም በባንኩ የተለያዩ ኃላፊነቶች ለአሥር ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ለባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የብድር ግንኙነት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡

በተጨማሪም የወጋገን ሽሬ እንዲሁም ተክለ ሃይማኖት (አዲስ አበባ) ቅርንጫፍ ኃላፊ ሆነው በተለያዩ ጊዜያት ሠርተዋል፡፡

በ30ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል የሚገኙትና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ደሳለይ አሁን ባገኙት ሥልጣን መሠረት የዓለም አቀፍ ባንኪንግን፣ የቅርንጫፎችንና ከብድር ጋር የተገናኙ ሥራዎችን በዋናነት ይመራሉ፡፡

በ1990 ዓ.ም. መጀመርያ በ16 ባለአክሲዮኖች በ30 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተመሠረተው ወጋገን ባንክ፣ በሰኔ 2008 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት መሠረት የተከፈለ ካፒታሉ 1.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በአሁን ወቅት ባንኩ 2,349 የአክሲዮን ባለቤቶች አሉት፡፡ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን በአሁኑ ወቅት እየገነቡ ከሚገኙት ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ፣ እስካሁን ለዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ግንባታ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ውጪ አውጥቷል፡፡

አብዛኛው ሥራ የተጠናቀቀለት የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

 

Standard (Image)

አወዛጋቢው የታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዢ ጨረታ በሁለት ኩባንያዎች አሸናፊነት ተጠናቀቀ

$
0
0

በዳዊት እንደሻው

ለወራት ሲያወዛግብ የነበረውና የታብሌት ኮምፒዩተሮችንና የኤሌክትሪክ ኃይል ማጠራቀሚያ (ፓወር ባንክ) ለመግዛት ሲካሄድ የነበረው ጨረታ፣ በመጨረሻ ሁለት ኩባንያዎች በ663.7 ሚሊዮን ብር አሸናፊ ሆነው እንዲያቀርቡ ሊደረግ ነው፡፡

በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችንና 125 ሺሕ ፓወር ባንኮችን ለመግዛት ሲከናወን የነበረውን ጨረታ፣ በመጨረሻ ሁዋዌና ሊኖቮ የተባሉት ድርጅቶች አሸንፈዋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ጨረታውን ለማሸነፍ ከሰባት ኩባንያዎች ጋር የተወዳደሩ ሲሆን፣ በመጨረሻም አሸናፊ ሆነው ሊወጡ ችለዋል፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን በመወከል በግዥና በብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት ከስድስት ወር በፊት የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ በመጀመሪያው ዙር ሰባት አቅራቢዎች መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በቴክኒክ ግምገማው ላይ በተጫራቾች በቀረበው ቅሬታ ጨረታው ተሰርዞ ዳግም አቅራቢዎች እንዲጋበዙ ተደርጓል፡፡

በሁለተኛው ዙር ወደ አሥራ ስምንት የሚጠጉ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ የተጋበዙ ቢሆንም፣ ዘጠኝ የሚሆኑት ሊሳተፉ ችለዋል፡፡ በጨረታው መጓተት ምክንያት ዕቃዎቹ ይቀርባሉ የተባለበት የጊዜ ገደብ ሊዘገይ ችሏል፡፡ መጀመርያ በነበረው ዕቅድ መሠረት ዕቃዎቹ በግንቦት 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቢታሰብም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 አገልግሎቱ በመጨረሻ ባደረገው የቴክኒክ ግምገማ ሌኖቮና ሁዋዌ ወደ ፋይናንስ ዙር እንዲያልፉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ በተመሳሳይ ወደ ፋይናንስ ግምገማ እንዲያልፍ ተደርጎ የነበረው ባክ ዩኤስኤ ተሰናብቷል፡፡ ይህ ኩባንያ እንዲወድቅ የተወሰነው ሌኖቮ አቅርቦት በነበረው ቅሬታ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት በመጀመርያው ዙር ባክ ዩኤስኤና ሁዋዌ ወደ ፋይናንስ ዙር እንዲያልፉ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ለመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ሌኖቮን ጨምሮ ቴክኖ የተባለው የአገር ውስጥ ኩባንያ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ቦርዱም ከሌኖቮ በስተቀር ሌሎች ያቀረቡትን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል፡፡

ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ሁዋዌና ሌኖቮ ወደ ፋይናንስ ግምገማው እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡ በውሳኔውም መሠረት ሁዋዌና ሌኖቮ የታብሌት ኮምፒዮተሮችንና ፓወር ባንኮችን ለማቅረብ ለእያንዳንዳቸው ዋጋ አቅርበዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በላይ በፈጀው የፋይናንስ ግምገማም፣ አገልግሎቱ ሁለቱ አቅራቢዎች ከሰጡት ዋጋ ዝቅተኛውን ተቀብሏል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ታብሌት ለማቅረብ 141.7 ዶላር የቀረበ ሲሆን፣ ለአንድ ፓወር ባንክ ደግሞ 15 ዶላር ቀርቧል፡፡ ይህ ዋጋ ዕቃዎቹን እስከ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ድረስ ለማቅረብ የተሰጠ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አንድ ታብሌትና ፓወር ባንክ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝበት ፒያሳ ድረስ ለማድረስ 15.75 ብርና 14.63 ብር የትራንስፖርት ዋጋ ጠይቀዋል፡፡ በቀረበው አነስተኛ ዋጋ መሠረት ሁለቱ ኩባንያዎች ዕቃዎቹን እንዲያቀርቡ መወሰኑን፣ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

አቅራቢዎቹ የሚያቀርቡዋቸው ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንደሚሆኑና ክፍያውን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንደሚሸፍነው ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱ ለሁለቱ ኩባንያዎች ታብሌት ኮምፒዩተሮችን እኩል እንዲያቀርቡ የጠየቀ ሲሆን፣ ፓወር ባንኮቹን በተመለከተ ለሌኖቮ 63 ሺሕ ፓወር ባንኮችን፣ እንዲሁም ሁዋዌ ደግሞ 53 ሺሕ ፓወር ባንኮችን እንዲያቀርብ ዕድሉን ሰጥቷል፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች ከአገልግሎቱ ጋር ከሰባት የሥራ ቀናት በኋላ ኮንትራት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡ ለደኅንነትም ሲባል የታብሌቶቹ ባትሪዎች ሲቀርቡ እስከ 30 በመቶ ብቻ እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ ከአሁን ቀደም ኤጀንሲው ለዋናው የሕዝብ ቆጠራ ዝግጅት እንዲረዳው የሙከራ ቆጠራ ባለፈው ዓመት የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም 220 የሚሆኑ የተመረጡ ቦታዎች በታብሌት ኮምፒዩተሮች የታገዘ ቆጠራ ተደርጎላቸዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም ኅዳር ወር ላይ እንደሚደረግ ለሚጠበቀው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መንግሥት ሦስት ቢሊዮን ብር ገንዘብ የመደበ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ወጪው 40 በመቶ የሚሆነው በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ይሸፈናል፡፡

አገሪቱ ከዚህ በፊት የመጨረሻውንና ሦስተኛውን ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡ በዚህም ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 73.8 ሚሊዮን መድረሱ ይታወሳል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ 100 ሚሊዮን ይጠጋል እየተባለ ነው፡፡

 

Standard (Image)

ኢትስዊች በዘጠኝ ወራት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ አንቀሳቀሰ

$
0
0

 

በአንድ ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤቲኤሞች ገንዘብ ለማውጣት በሚያስችለው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት አማካይነት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2.19 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ማንቀሳቀስ መቻሉ ተገለጸ፡፡

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት አገልግሎቱን ከጀመረ አንድ ዓመት ከሞላው ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የባንክ ተገልጋዮች በደንበኝነት ካልተመዘገቡበት ባንክ ኤቲኤም ላይ 2.19 ቢሊዮን ብር ያወጡት 5.89 ሚሊዮን በሆኑ ምልልሶች ነው፡፡  

የካርድ ተጠቃሚዎች ከራሳቸው ባንክ ውጪ ባለ ኤቲኤም የመጠቀም ልምድ እያደገ ስለመምጣቱ የሚያሳይ መሆኑን የሚጠቁመው መረጃው፣ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በስተቀር 17ቱም ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት ባለቤት በመሆን የካርድ አገልግሎቶች በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ያስረዳል፡፡  

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤም ካርድ የያዙ ደንበኞች ከሌሎች ባንኮች ኤቲኤሞች ገንዘብ ማውጣት ባለመቻላቸው የተፈጠረው የአገልግሎት መስተጓጎል ባይኖር፣ በዚህ ዘመናዊ አገልግሎት የሚጠቀሙና ሊንቀሳቀስ የሚችለውም የተገልጋዮች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን ይችል እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ በተለይ በአገሪቱ ካሉት አራት ሺሕ ከሚደርሱ ኤቲኤሞች ውስጥ ከ1,800 በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆናቸው፣ የባንኩ ካርድ በሌሎች ኤቲኤሞች ላይ ባለመሥራቱ በኢትስዊች በኩል ሊቀንቀሳቀስ የሚችለውን የገንዘብ መጠን አሳንሶታል ተብሏል፡፡ ይህ ወደ ሁለት ወራት ገደማ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካርድ በሌሎች ባንኮች ኤቲኤሞች ላይ ያለመሥራት ችግር፣ ባለፈው ሳምንት ተቀርፎ አገልግሎት ጀምሯል፡፡

ኢትስዊች ለዚህ ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ማዕከል ሆኖ ለሚያካሂደው አገልግሎት በእያንዳንዱ ዝውውር 0.25 ሳንቲም ገቢ የሚያገኝ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2.1 ቢሊዮን ብር በማንቀሳቀስ 5.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ ኢትስዊች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች በአክሲዮን ያቋቋሙት ኩባንያ ሲሆን፣ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል ነው የተመሠረተው፡፡

በቦርድ የሚመራው ይህ ተቋም እስከዚህ ወር መጀመሪያ ድረስ የኩባንያው ቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲመሩ የቆዩት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና ነበሩ፡፡ በቅርቡ በተደረገ አዲስ ምርጫ ግን አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ኢጣፋ የቦርድ ሊቀመንበርነት ቦታውን ተረክበዋል፡፡ 

Standard (Image)

የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የ1.9 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ከውጭና ከአገር በቀል ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ

$
0
0

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በ2009 በጀት ዓመት በዕቅድ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል የግዢ ሒደታቸው የተጠናቀቁና 1.9 ቢሊዮን ብር የሚፈጁ ስድስት ፕሮጀክቶችን፣ በውጭና በአገር በቀል ተቋራጮች ለማከናወን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የባለሥልጣኑ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ አገር በቀል ተቋራጭ ከሆኑት ጣናና አሰር ሥራ ተቋራጮች፣ እንዲሁም ከቻይናው ሲጂሲና ዣንግዚ ሥራ ተቋራጭ ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ወጪያቸው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት እንደሚሸፈን የተገለጹት ፕሮጀክቶች ለገዳዲ የጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ልማት ፕሮጀክት፣ የጨፌ ክፍል ሁለት ፍሳሽ ማጣሪያ ግንባታ ፕሮጀክት፣ አዳዲስ የፍሳሽ ቅብብሎሽ ጣቢያ ግንባታና የነባር ጣቢያዎች ማሻሻያ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አቶ ተስፋለም ገልጸዋል፡፡

ክፍል ሁለት የለገዳዲ ጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ልማት ፕሮጀክት በቀን 86 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ በማምረት በሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱ በ2008 ዓ.ም. የተጀመረና 1,598,997,097 ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ እስከ 2012 በጀት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አቶ ተስፋዓለም ገልጸዋል፡፡ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮውን አገር በቀሉ ተቋራጭ ጣና ሥራ ተቋራጭና የቻይና ኩባንያዎች ኩንዙ፣ ሲጂሲና ዣንግዚ እያከናወኑት መሆኑንም አክለዋል፡፡ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ግንባታ ቁጥጥር የሚያደርገው ደግሞ የውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በሦስት ዋና ዋና የፍሳሽ ማዕከል እንደምትከፈል የገለጹት አቶ ተስፋዓለም፣ 100 ሺሕ ሜትር ኩብ የማጣራት አቅም ያለው ቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ፣ 80 ሺሕ ሜትር ኩብ የማጣራት አቅም ያለው ምሥራቅ ፍሳሽ ማጣሪያና 85 ሺሕ ሜትር ኩብ ማጣራት የሚችለው አቃቂ ፍሳሽ ማጣሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአቃቂ ፍሳሽ ማጣሪያ በሁለት ንዑስ ተፋሰስ ተከፍሎ ደቡብ አቃቂ ንዑስ ክፍልና አቃቂ ጨፌ ንዑስ ተፋሰስ እንደሚባሉ የጠቆሙት አቶ ተስፋዓለም፣ 60 ሺሕ ሜትር ኩብና 25 ሺሕ ሜትር ኩብ ፍሳሽ ማጣራት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ አቃቂ ጨፌ ፍሳሽ ማጣሪያ 120 ሺሕ ለሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ዘመናዊ የፍሳሽ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው በዋነኛነት የቦሌ፣ የአቃቂና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

 በቀን 12,500 ሜትር ኩብ ፍሳሽ ማጣራት እንደሚችል የተጠቆመውን አቃቂ ጨፌ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት፣ 218,701,833 ብር እንደሚፈጅና ሲጂሲ የሚባለው የቻይና ኩባንያ ሲገነባው፣ ሱሬካ የተባለው የፈረንሣይ አማካሪ ድርጅትና ጁንኮል የሚባል አገር በቀል አማካሪ ድርጅት በጣምራ እንደሚቆጣጠሩት አስረድተዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ የተገለጸው የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ደግሞ 26 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ተገልጿል፡፡ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታው 55,041,603 ብር እንደሚፈጅ ተጠቁሟል፡፡ አዳዲስ የፍሳሽ ቅብብሎሽ ጣቢያ ግንባታና ነባር የፍሳሽ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች ፕሮጀክቶችም በ2008 በጀት ዓመት መጀመራቸውንና በ2011 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደሚጠናቀቁ አቶ ተስፋዓለም ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

መንግሥት የጥጥ ምርት ለማስፋፋት ለውጭ አልሚዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ሊያቀርብ ነው

$
0
0

- የዘረመል ጥጥ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው በሰፊው እንደሚውል ይጠበቃል

- የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሰኔ መጨረሻ ግንባታቸው ያልቃል ተብሏል

በአገሪቱ የተገነቡትም ሆኑ እየተገነቡ ለሚገኙ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ማምረቻዎች የሚያስፈልጋቸውን የጥጥ አቅርቦት ለማሟላት፣ መንግሥት ለውጭ አልሚዎች ሰፋፊ እርሻዎችን ለማቅረብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና የምርት እንቅስቃሴ የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው፣ በአገሪቱ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻነት የተገነቡትም ሆኑ እየተገነቡ የሚገኙ አራት ፓርኮች ከፍተኛ የጥጥ ምርት አቅርቦት ችግር እንደሚያጋጥማቸው ይታሰባል፡፡

የአገር ውስጥ የጥጥ ምርትም ሆነ ጥራት አስተማማኝ ባለመሆኑም ምክንያት ከውጭ ለሚመጡ አልሚዎችም ጭምር የቦታ ጥያቄ እየቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ከወዲሁ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለማልማት የሚፈልጉ የውጭ ኩባንያዎች መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፣ በአገሪቱ በጥራትም በአቅርቦት ብዛትም ችግር አለበት የተባለውን የጥጥ ምርት በሰፋፊ እርሻዎች ለማምረት ጥያቄ እያቀረቡ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ጂያንሱ ቴክስታይል የተባለ የቻይና ኩባንያ፣ የፈትል ጥጥ ለማምረት የሚያስችለውን ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሥር የውጭ ኩባያዎችም እዚሁ ጥጥ በማምረት ለመጠቀም ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡ ሁዋፋንግ፣ ውሺ፣ ጂያንዚ ሰንሻይን፣ ኤቨረስት የተባሉትን ጨምሮ የቻይናና የታይዋን ኩባንያዎች የመንግሥትን ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ውሺ የተባለው ትልቅ ኩባንያ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን በሰፊው ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ ይዞታው ከሚያመርታቸው ውስጥ ለአሜሪካው ታዋቂ የፋሽን ኩባንያ ፊሊፕ ቫን ሒውሰን (ፒቪኤች) የሚያቀርባቸው እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም በላይ መንግሥት በዘረመል ጥጥ እንዲመረት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝና በዚህ ሳቢያ የአገሪቱን የጥጥ ምርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚቻል መታመኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ የዘረመል ጥጥ በሰፊው እንዲመረት ለማድረግ በማሰብ፣ የቤተ ሙከራና የመስክ ላይ ምርምሮች ተገባደው ወደ መደበኛ እርሻ ለመግባት የሚያስችሉ ዕርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የውጭ ጥጥ አምራቾች ጥያቄ ማቅረባቸው የአገር ውስጥ አምራቾችን፣ የመዳመጫ ፋብሪካዎችን በአቅራቢነትና በጋራ አምራችነት እንዲሳተፉ ዕድሉን እንደሚፈጥርላቸው ያብራሩት ዶ/ር በላቸው፣ በጠቅላላው በአገሪቱ የአሥር ዓመታት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡

ከአምራቾች ባሻገር ሁለተኛ ደረጃ ግብዓት አቅራቢዎችና የምርት ገዥዎችም እየገቡ እንደሚገኙ ተጠቅሶ ከእነዚህ መካከል የፈረንሣይ ሻርጀ፣ እንዲሁም የጀርመን ራንግላር የሸሚዝና የሌሎችም ምርቶችን ግብዓቶች በኢትዮጵያ ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ ዴካትሊዮን፣ ቫንኒቲፌር እንዲሁም ኤችኤንድኤም የተባሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ገዥዎችም ምርት መረከብ መጀመራቸው እየተነገረ ነው፡፡

ይህ የተደረገው በአገሪቱ ሐዋሳን ጨምሮ ለኮምቦልቻ፣ ለመቐለ፣ እንዲሁም ለቦሌ ለሚ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስሪ ፓርኮች ግብዓት እንዲውል ለማድረግ እንደሆነ ያብራሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተገነቡ 52 ማምረቻ ሼዶች ውስጥ ከሚገኙ 16 ኩባንያዎች ውስጥ ስድስቱ ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ቀሪዎቹ አሥሮቹም ተከላ ጨርሰው በመጪው መስከረም ለመላክ ሙከራ መጀመራቸውንም እንዲሁ፡፡

መንግሥት እስካሁን ግንባታቸውን ካጠናቀቃቸው የቦሌ ለሚና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጓዳኝ በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ የመቐለና የኮምቦልቻ ፓርኮችን ግንባታ እንደሚያጠናቅቅም ይፋ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ፣ ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡም ተጠቅሷል፡፡ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱትሪ ፓርኮችም በመጪው ዓመት ታኅሳስ ወር ወደ ሥራ እንደሚገቡ ሲጠበቅ፣ በጠቅላላው 13 ፓርኮች በልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ዘርፍ ተደልድለው ግንባታቸው እየተካሄደ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከጨርቃ ጨርቅ ማምረቻዎቹ በተጨማሪ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአብነት ያህል ለመድኃኒትና ለመሳሰሉት ማምረቻነት እንደሚውል ተገልጿል፡፡

መንግሥት ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ብቻ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ በመመደብም በርካታ ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉት ግንባታዎች ኢትዮጵያ በአሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ የቀላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ የበላይነቱን እንድትቆናጠጥ ለማድረግ ያገለግላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ለአብነት ያህል ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ ይነገራል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች መብታችንን የሚጋፋ ድርጊት ተፈጸመብን አሉ

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ ወር 2017 ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን ሠራተኞች መልምሎ የቀጠረበት መንገድ የባንኩ ቋሚ ሠራተኞችን መብት የተጋፋ ነው ተብሎ ቅሬታ ቀረበበት፡፡ ባንኩ በበኩሉ አዳዲስ ሠራተኞችን የመለመለው የቋሚ ሠራተኞችን መብት ለመንካት ሳይሆን፣ ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ለመቅጠር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባንኩ ሕግ የጣሰ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ባንኩ የ‹‹ማኔጅመንት ትሬኒ ማስተርስ ቅጥር›› በማለት የፈጸመው የሠራተኞች ምልመላ ሕግ የጣሰና አድሏዊ አሠራር መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ‹ማኔጅመንት ትሬኒ› በማለት ባወጣው የማስተርስ ቅጥር ምልመላ ከ250 በላይ ቋሚ ሠራተኞችና 300 የሚሆኑ የውጭ ተወዳዳሪዎች መመዝገባቸውን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ ድርጊቱ የባንኩ አስተዳደር ከመሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ጋር ያደረገውን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የባንኩ አስተዳደር (ማኔጅመንት) እና የሠራተኛ ማኅበሩ ባደረጉት 12ኛው የኅብረት ስምምነት አንቀጽ 13፣ ‹‹ባንኩ አዲስ ሠራተኛ የሚቀጥረው በዝውውር ወይም በደረጃ ዕድገት ቦታውን የሚሸፍንና ተፈላጊውን መመዘኛ ማሟላት የሚችል ቋሚ ሠራተኛ ሲታጣ ብቻ ነው፤›› የሚል ቢሆንም፣ ስምምነቱን በማፍረስ ቅጥር መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

በባንኩ ውስጥ በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በልምድ ብቃት ያላቸው ሠራተኞች እያሉ፣ በተደረገው አዲስ ምልመላ ከውጭ ተወዳዳሪዎች 79 ሲቀጠሩ ከውስጥ ወይም ከቋሚ ሠራተኞች 21 ብቻ መወሰዳቸው እንዳሳዘናቸውም አስረድተዋል፡፡

ባንኩ የሠራውን ስህተት እንዲያርም ለፕሬዚዳንቱ አቶ በቃሉ ዘለቀ ቅሬታ ያስገቡ ቢሆንም ምላሽ ማጣታቸውን የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ጉዳዩ ዝም ተብሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡ የደረሰባቸው የመድልዎ አሠራር ለማስቆምና አስመርምሮ ተገቢው ውጤት ላይ ለመድረስ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለእንባ ጠባቂ ኮሚሽን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ግን ቅሬታቸውንና ጥቆማቸውን እንዳልተቀበላቸው ጠቁመዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው ሕግ ተጥሶ በመሆኑ የሚመለከታቸው የዴሞክራሲ ተቋማትና አስፈጻሚዎች የማያስቆሙት ከሆነ፣ መብታቸውን በሕግ ለማስከበር እንደሚገደዱም አክለዋል፡፡

ሠራተኞቹ ደረሰብን ለሚሉት በደል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ፣ የባንኩ የ‹ማኔጅመንት ትሬኒ› ፕሮግራም ከጀመረ ዓመታት እንደተቆጠሩ አስታውሰዋል፡፡ ባንኩ ሥራውን እያስፋፋና ተደራሽነቱን በብቃት ለመወጣት በቂና ጥራት ያለው የሰው ኃይል አዘጋጅቶ ማስቀመጥ ስላለበት፣ ይህንን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን የሚያደርገው ልዩ ለሆነ የሥራ ዓይነት ማስታወቂያ አውጥቶ ሳይሆን፣ ለሚከፍታቸው አዳዲስ ቅርንጫፎች በኃላፊነት የሚመድባቸውን ሠራተኞች ለማዘጋጀት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባንኩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አምስት ዓመታት የሥራ ዘመን በየዓመቱ አንድ መቶ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ በልሁ፣ የሚከፈቱትን ቅርንጫፎች ብቃት ያላቸው ሠራተኞች መምራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ለዚህም የራሱን ብቃት ያላቸው ሠራተኞች አዘጋጅቶና አሠልጥኖ መጠበቅ ስላለበት ያንን እያከናወነ መሆኑን በማስረዳት፣ ባንኩ ሕግ የተላለፈበት ምንም ዓይነት ድርጊት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ሠራተኞች አሠራሩን እያወቁ ሆን ብለው የማይሆን ነጥብ በማንሳት፣ ለሠራተኛውና ለባንኩ ደንበኞች ያልሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ እየተሯሯጡ ነው፤›› ሲሉም አውግዘዋል፡፡  

Standard (Image)

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት ተጠርጥረው ከታሰሩበት የሙስና ወንጀል በዋስ ተፈቱ

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፌንፊኔ ቅርንጫፍ የብድር ክፍል ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ከ16 ዓመታት በፊት ከተሰጠ ብድር ጋር በተገናኘ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል በመባል በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰረው የነበሩት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት በዋስ ተፈቱ፡፡

 

ፕሬዚዳንቱ አቶ ደርቤ አስፋው ሁሪሳ ከእስር የተፈቱት በ20,000 ብር የዋስትና ገንዘብ ነው፡፡ ግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና ተከልክለው ትዕዛዝ በተሰጠ በማግሥቱ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን ግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. አቶ ደርቤን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አቅርቦ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ ስድስት ቀናት ተፈቅደውለት ለግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ነገር ግን አቶ ደርቤ የዋስትና መብት ተነፍጓቸው በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ የተሰጠው ትዕዛዝ ተነስቶ፣ በማግሥቱ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በ20,000 ብር ዋስ መለቀቃቸውን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

ዋስትና በተነፈጋቸው በማግሥቱ የዋስትና መብት ሊፈቀድላቸው የቻለው ፖሊስ በመጀመርያው ቀን ዋስትና ያስከለከላቸው የምርመራ ሒደቱ ረዥም ጊዜ ይፈጅብኛል በማለቱ ቢሆንም፣ በአጭር ሰዓታት ውስጥ በማጠናቀቅና በማግሥቱ እንዲቀርቡ በማድረግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ዋስትና ቢፈቀድላቸው እንደማይቃወም በማስረዳቱ፣ እንደተለቀቁ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከአቶ ደርቤ ጋር ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት አቶ አበበ አጥናፉም በ20,000 ብር፣ አቶ ገብረ ፃድቅ ገብረ መድኅን በ12,000 ብር፣ አቶ ደረጀ ባዩ ደግሞ በ6,000 ብር ዋስትና መለቀቃቸው ታውቋል፡፡

አቶ ደርቤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታች ተነስተው በጂማ ዲስትሪክት በኃላፊነት ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት፣ እንዲሁም በኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትነት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

Standard (Image)

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተፈጥሯል

$
0
0
  • ለስምንት ሚሊዮን ተጎጂዎች 555 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

   ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ቡድን፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች አስቸኳይ የዕርዳታ ምግብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መፈጠሩን በይፋ አስታወቁ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ፣ በድርቁ አካባቢዎች ከመደበኛ ምግብ በተጨማሪ በተለይ ፅኑ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መፈጠሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ ደግሞ አሁን ያለው የአስቸኳይ ዕርዳታ ምግብ እንደሚሟጠጥ አስታውቋል፡፡

      በመግለጫው መሠረት ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በማሽቆልቆሉ ሳቢያ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ በድርቅ የተጎዱ ወገኖች የዕለት ዕርዳታ ጠባቂዎች ለፅኑ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ለአስቸኳይ ዕርዳታ የሚውል ምግብ መጠንም በአሳሳቢ ደረጃ መቀነሱ ተገልጿል፡፡

ከሐምሌ ወር ጀምሮ 500 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ግዥና ለትራንስፖርት እንደሚያስፈልግ፣ 55 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ድርቁ በከፋባቸው ቦታዎች ፅኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለደረሰባቸው ወገኖች በአስቸኳይ እንደሚፈለግ በመግለጫው ተካቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርቁ በስፋት በሚታይባቸው ደቡባዊና ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍሎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ መጠን በጣም ከፍ ማለቱን መግለጫው ጠቁሞ፣ ለዚህ መንስዔው ደግሞ የበልግ ዝናብ አነስተኛ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ 7.9 ሚሊዮን ዜጎች የዓመቱን የመጨረሻ ኮታቸውን የሚወስዱት በሰኔ ወር መጨረሻ በመሆኑ፣ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የችግሩ መጠን ሊሰፋ እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ዝናቡ በማነሱ ምክንያት የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 7.78 ሚሊዮን ማሻቀቡ ይታወሳል፡፡ ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት ወራት ሊጨምር እንደሚችል የተመድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ቀደም ለድርቁ ተጎጂዎች ያስፈልጋል የተባለው ዕርዳታ 948 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ አሁን ግን 550 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚፈለገው፡፡ ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በሚፈለገው መጠን እየተገኘ ባለመሆኑ፣ አሁንም የተጠናከረ ዕርዳታ መቅረብ እንዳለበት እየተጠየቀ ነው፡፡ በተለይ የዕለት ደራሽ ምግቦች፣ የተመጣጠኑ ምግቦችና ንፁህ የመጠጥ ውኃ አንገብጋቢ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ድርቁ የከፋባቸው ሥፍራዎች በጣም የራቁ በመሆናቸውና የውኃ ጉድጓዶችም በመድረቃቸው የውኃ እጥረት ፈተና መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ድርቁ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ የተለያዩ ሥፍራዎች 7.8 ሚሊዮን ዜጎችን ያጠቃ ሲሆን መንግሥት የውኃ፣ የምግብ፣ የጤናና የትምህርት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም የተለያዩ ሚኒስቴሮችን አቀናጅቶ በመሥራት ላይ መሆኑንና 98 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምግብ ለተረጂዎች ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ አሥር አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ጉብኝት አመቻችቷል፡፡ ‹‹ሆርን ኦፍ አፍሪካ ፓርትነርሺፕ ሚሽን›› የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው የልዑካን ቡድን ከሰኔ 1 ቀን እስከ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በሁለቱ አገሮች ለደረሰው አስከፊ ድርቅ ዕርዳታ ለማሰባሰብ የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ጉብኝት ያደርጋል ተብሏል፡፡

በልዑካን ቡድኑ ውስጥ አሥር የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች መካተታቸው ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ ከሐሙስ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዋርዴር ዞን ከከፍተኛ የአገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ጉብኝት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ ዋርዴር ዞን ኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ዞን በድርቁ ምክንያት በርካቶች ለአስቸኳይ ዕርዳታ ተጋልጠው፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል በቅርቡ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ የተፈናቀሉ 2,395 ሰዎች (475 ቤተሰቦች) አስቸኳይ የዕርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጓቸው ተገልጿል፡፡ በአምስት ቀበሌዎች ውስጥ ኗሪ የነበሩ ወገኖች ቤቶቻቸው በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው የቤት ዕቃዎቻቸው፣ ማብሰያዎቻቸው፣ ልብሶቻቸው፣ ምግባቸውና ምግብ ነክ ያልሆኑ ንብረቶቻቸው ወድመውባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 950 ተማሪዎች ደብተሮቻቸውና የመማሪያ መጻሕፍቶቻቸው ከጥቅም ውጪ ሆነውባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ለሦስት ወራት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና መቋቋም እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

 

Standard (Image)
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live