በዳዊት እንደሻው
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርን ወደ ግል ይዞታ ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ ባወጣው ጨረታ፣ ሚሊቶ ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 225 ሚሊዮን ብር የመጫረቻ ዋጋ አቀረበ፡፡
በግንቦት 2009 ዓ.ም. ጨረታው ከወጣ በኋላ 19 ተጫራቾች የጨረታ ሰነዱን ቢገዙም፣ ሚሊቶ ብቻ የመጫረቻ ሰነዱን አስገብቷል፡፡
ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በተደረገው የጨረታ ሰነድ የመከፈት ሥነ ሥርዓት፣ ሸበሌ ትራንስፖርትን ለመግዛት ሚሊቶ ብቻ ፍላጎት ማሳወቁ ታውሷል፡፡
በሥሩ 350 ያህል ሠራተኞችና 100 የጭነት ተሽከርካሪዎች ያሉት ሸበሌ በትራንስፖርት በተደጋጋሚ ለሽያጭ ቢቀርብም፣ በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ጨረታዎች ያለ ስኬት ተጠናቀዋል፡፡
በዚህ ሳምንት የተከናወነው የጨረታ ሒደት ከተሳካ ገዥው ኩባንያ፣ የሸበሌ ትራንስፖርት ሠራተኞችንና አስተዳደሩን አብሮ ይረከባል ተብሏል፡፡
ተጫራቹ ኩባንያ ያቀረበው የፋይናንስና የቴክኒክ ፕሮፖዛል ተገምግሞ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኢሕደዴግ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በ1980ዎቹ አጋማሽ የፕራይቪታይዜሽንና የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ተብሎ የተቋቋመው የአሁኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ370 በላይ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ አስተላልፏል፡፡
