Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የአንበሳ አውቶቡስ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ኃላፊዎች ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

$
0
0
  • በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ የተያዙ ተጠርጣሪዎች 125 ደረሱ

ለበርካታ ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ በድሉ አሰፋን ጨምሮ፣ ስድስት ኃላፊዎች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ገልጾ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ያቀረባቸው የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ፋንታሁን፣ የቴክኒክ መምርያ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ላቃቸው፣ የየካ ቴክኒክ ቨርዥን መሪ አቶ ሙሔ አወል፣ የሸጎሌ ቴክኒክ ኬዝ ቲም መሪ አቶ መገርሳ ጌታቸውና የአውቶሞቲቨ ቨርዥን መሪ አቶ ደመላሽ ፈጠነ ናቸው፡፡

ተጠርጣዎቹ ድርጅቱን በመምራት ላይ እያሉ በ2006 ዓ.ም. ድርጅቱን መልሶ የማቋቋም ሥራ ሲያከናውን፣ ግብፅ ከሚገኝ ኢጅፕት ፓወር ከሚባል ድርጅት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የአንድ አውቶብስ ሞተር በነፃ እንደተሰጣቸው መግለጻቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በመቀጠልም አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም በስጦታ የተበረከተውን ሞተር በአንድ የዳፍ አውቶብስ ላይ ተገጥሞ እንዲሞከር ሲያደርጉ፣ ሞተሩ እንደማይሠራ ባለሙያዎች ለቴክኒክ ኮሚቴው መግለጻቸውንም መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ የሞተሩ ፍሪሲዮን እንዲሞከር ተጠይቆ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደማይሠራ የተገለጸ ቢሆንም፣ የቴክኒክ ኮሚቴው ግን በደረጃ አንድ መንገድ ላይ ባይሠራም በደረጃ ሁለትና ሦስት ላይ እንደሚሠራ በመግለጽ ሪፖርት ማቅረቡን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው ‹‹ሞተሩ ይሠራል›› የሚል ሪፖርት ቢያቀርብም፣ በማኔጅመንት በተደረገ ስብሰባ ሞተሩ እንደማይሠራ ተገልጾ እያለና ምንም ዓይነት ጥናት ሳይደረግ፣ ከግብፁ ኩባንያ ጋር በሦስት ዙር ግዢው እንዲፈጸም በመስማማት ስምምነት ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

ነገር ግን ተጠርጣዎቹ ውሉን በመጣስ በአንድ ጊዜ የ49 ዳፍ አውቶብሶች ሞተር ከኩባንያው በ33 ሚሊዮን ብር የግዢ ሥርዓት በመፈጸም፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቋል፡፡

እንደማይሠሩ እየተገለጸ የተገዙት ሞተሮች በዳፍ አውቶብሶች ላይ የተገጠሙ ቢሆንም፣ ባለመሥራታቸው ቆመው እንደሚገኙ መርማሪ ቡድኑ አስረድቶ ለጊዜው ለምርመራ መነሻ ያገኘው የምርመራ ግኝት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንና ብዙ እንደሚቀረው በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡

በሚደረገው ምርመራ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው በመግለጽ ምላሽ የሰጡት የቀድሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አሰፋ ናቸው፡፡ አቶ በድሉ እንደገለጹት፣ ከግብፅ ኩባንያ ጋር ተመሳጥረው እየተባለ የሚቀርበው ክስ ትክክል አይደለም፡፡ እሳቸው ከሁለት ዓመት በፊት በጡረታ በክብር ተሸልመው መሰናበታቸውን፣ ባለቤታቸው፣ ልጆቻቸውና እሳቸውም ሕመምተኛ መሆናቸውን አስረድተው፣ ጡረታ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በዕውቀታቸው ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በመሥራት ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሙስናን ለመከላከል በተቋሙ ብዙ መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለትምህርት እንዲሆን በማለት ለግላቸው የተሰጣቸውን ስጦታ እንኳን ለድርጅቱ ማበርከታቸውንና ይኼ አንዱ ማንነታቸውን የሚገልጽ መሆኑን በማስረዳት ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ ሁኔታ ዋስትና ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ግን ቀሪ ሥራዎቹን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ፣ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የአሥር ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶ ለመስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማና በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የተለያየ ኃላፊነት ላይ የነበሩ 18 ተጠርጣሪዎችን አቅርቦ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና በጥቅም በመመሳጠር የመንግሥትን ይዞታና የመንግሥትን ቤቶች በግለሰቦች ስም በማዛወር ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና የሞቱ ሰዎችን መጠቀሚያ በማድረግ በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡ የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰቡን፣ የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና በቀጣይም መረጃ ማሰባሰብና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው በማስረዳት 14 ቀናት እንዲፈቀደለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም የተያዙበት ጉዳይ ከእነሱ ጋር እንደማይገናኝና ሥራ ከለቀቁ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሆናቸው፣ የሠሩትም ተገቢና በሕጉ መሠረት መሆኑን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ነፍሰጡር በመሆናቸው በማረፊያ ቤት እንደተቸገሩ፣ የትምህርት ቤት መክፈቻ ወቅት በመሆኑ ልጆቻቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸውና ደመወዝና የባንክ ደብተር ስለተያዘባቸው ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ሰባት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለመስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰባት ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እያጠናቀቀ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንደተገነዘበ ገልጾ፣ ለጳግሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እንኳን ፖሊስ ፍርድ ቤትም ደመወዝ የማገድ ሥልጣን የለውም በማለት በአስተዳደር በኩል መፍትሔ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን 24 ተጠርጣዎችን ያቀረበው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ነው፡፡ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ታደለ ደመቀና የደረቅ ቆሻሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ ፋንታሁን  የምርመራ መዝገብ እስከ ቢሮ አስተዳደር ጸሐፊ ድረስ የተካተቱበት 24 ተጠርጣሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የተጠርጠሩትም በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው፣ በአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር በመረጋገጡ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጾ፣ ጉዳቱ የደረሰው ተገቢ ያልሆነና የአስተዳደሩን የፋናንስ መመርያ በመጣስ ግዢ በመፈጸም፣ ክፍያ በመፈጸም፣ ለሥልጠናና ለአበል በሚል ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመፈጸምና ሌሎችንም ወጪዎች በማውጣት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት በመግለጽ 14 ቀናት እንዲፈቅድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም ድርጊቱ በየግላቸው እንዲነገራቸው፣ የሠሩት ጥፋት እንደሌለና የወሰዱት አበል ሕጉን ያልተከተለ ነው ተብለው ተመላሽ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ የ53 ሚሊዮን ብር ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ድርሻው ምንና እንዴት እንደሆነ ማሳየት ተገቢ መሆኑን እንዳመነበት ጠቁሞ፣ መርማሪ ቡድኑ ለይቶና ድርሻቸው ምን እንደሆነ ገልጾ ለጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም.  እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ ከጠዋቱ 4፡50 ሰዓት ጀምሮ ያለማቋረጥ ከቀትር በኋላ 8፡30 ሰዓት ድረስ በመቆየቱ ስምንት ተጠርጣዎችን በአዳሪ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት የዕለቱን ችሎት አጠናቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ማክሰኞ ምሽት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኋን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ዕጣ ሳይደርሳቸው እንደደረሳቸው በማስመሰል አምስት ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለአምስት ግለሰቦች በማስተላለፍ የተጠረጠሩ ሰባት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት ኃላፊዎች መታሰራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የቤቶቹም ግምትም ከ2.3 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት ሥራ አስፈጻሚ፣ ሁለት የሥራ ሒደት መሪዎች፣ ሁለት ባለሙያዎችና አንድ ሠራተኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ረቡዕ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት 63 የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደሆኑ፣ በመንግሥት ላይ የ170 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ ተገልጿል፡፡ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ቁጥርም 125 መድረሱ ታውቋል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles