የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለበዓል የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት ችግር የለም ቢልም፣ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መደብሮች በረዣዥም ሠልፎች ተጨናንቀው ሳምንቱን አሳልፈዋል፡፡
በተለይ ዘይትና ስኳር ለመሸመት በከተማው የሚገኙ 141 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በከፈቷቸው መደብሮች ረዣዥም ሠልፎች ተስተውለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2003 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለበዓሉ በከተማው ለሚገኙ ሸማች ማኅበራትና ዩኒየኖች 6.3 ሚሊዮን ሊትር ዘይት መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡ ስኳርም እንዲሁ 87,100 ኩንታል ተሠራጭቷል፡፡
‹‹አቅርቦቱን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአቅርቦት ችግር የለም፤›› ሲሉ አቶ ገመቺስ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሸማቾች ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በተሰጣቸው ኮታ መሠረት ዘይትና ስኳር ለመሸመት ረዣዥም ሠልፎችን ሲጠብቁ ሰንብተዋል፡፡
አንድ ቤተሰብ ዘይትና ስኳር ኮታ የተፈቀደለት ስለሆነ ሦስት ሊትር ዘይት በ85 ብር፣ አምስት ኪሎ ስኳር ደግሞ በ95 ብር ሒሳብ ሲሸምት ነበር፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሸማቾች እንደገለጹት፣ የዘይትና የስኳር ዋጋ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መደብሮች ቅናሽ አለው፡፡ ነገር ግን አለቀ ሊባል ስለሚችል ሁሉም ሸማች የድርሻውን ለማግኘት ለመሠለፍ ተገዷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ከኢንዱስትሪ ምርቶች በተጨማሪ በዓሉን በሚመለከት፣ በከተማው የሚገኙ የሸማቾች ማኅበራትን በክልል ከሚገኙ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በማገናኘት ግብይት እንዲፈጽሙ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
በተለይ ሽንኩርት፣ የዕርድ ከብቶች፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ጤፍ፣ ዱቄት ለማኅበራትና ለዩኒየኖች መሠራጨታቸውን አቶ ገመቺስ ተናግረዋል፡፡ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በከፈቷቸው 127 ሉካንዳ ቤቶችም ቢያንስ አምስት አምስት የዕርድ ከብቶች ለበዓሉ መቅረባቸው ተመልክቷል፡፡
አቶ ገመቺስ በሰጡት መግለጫ፣ በዓሉን በማስመልከት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ቢሮው ቁጥጥር እያደረገ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
