ናንካይ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተሰኘ የቻይና ኩባንያ በጋምቤላ ክልል በደለል ወርቅ ምርት ሊሰማራ ነው፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የአነስተኛ ደረጃ ደለል ወርቅ ማዕድን ማምረት ፈቃድ ለናንካይ ማይኒንግ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የወርቅ ማዕድን ልማት ስምምነቱ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የናንካይ ማይኒንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ኬሺንካ ናቸው፡፡
ሚኒስቴሩ ለናንካይ ማይኒንግ የሰጠው የማዕድን ልማት ፈቃድ ኩባንያው በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አኝዋ ዞን፣ አበቦ ወረዳ፣ ሲሪ ወንዝ አካባቢ 2.04 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ የደለል ወርቅ (Placer Gold) ለማምረት የሚያስችለው እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ለወርቅ ልማት ፕሮጀክቱ 50.3 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደመደበና በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት 210 ኪሎ ግራም የደለል ወርቅ እንደሚያመርት ገልጿል፡፡ ኩባንያው ወደ ሥራ ሲገባ ለ57 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
የወርቅ ልማት ስምምነቱ ለሁለት ዓመት እንደሚፀናና የፈቃድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ ዕድሳት ጊዜ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊታደስ እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስረድቷል፡፡
የደለል ወርቅ በአብዛኛው በወንዞች ዳርቻ በቀላል ቴክኖሎጂ የሚመረት ሲሆን፣ ወርቅ አዘል ድንጋዮች ተፈጭተው በውኃ በመምታት ደቃቅ ወርቅ ተለይቶ ይወጣል፡፡ የደለል ወርቅ በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎች በባህላዊ መንገድ ይመረታል፡፡
በዓለም ባንክ የተካሄድ ጥናት በአምስቱ ክልሎች ከአንድ ሚለዮን በላይ በባህላዊ ወርቅ አምራቾች እንዳሉና በዓመት ከዘጠኝ ቶን በላይ ወርቅ እንደሚያመርቱ ይጠቁማል፡፡ በባህላዊ አምራቾች የተመረተው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርብ ቢሆንም፣ ገሚሱ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚጓዝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ምርት የተሰማራው ብቸኛው ኩባንያ ሚድሮክ ጎልድ ለገንደንቢ በሚገኘው ወርቅ ማውጫ በዓመት 3.5 ቶን ወርቅ እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ ከለገደንቢ በተጨማሪ ሚድሮክ ጎልድ በመተከል አካባቢ ባካሄደው መጠነ ሰፊ የወርቅ ፍለጋ ሥራ ከፍተኛ መጠን ያለው የጽንሰ ወርቅ (Primary Gold) ያገኘ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ኢዛና ማይኒንግ ሌላው የከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ምርት ፈቃድ የተሰጠው ኩባንያ ነው፡፡ ኢዛና ማይኒግ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ኒውሞንት ከተሰኘ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር በሽርክና ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለማምረት በሒደት ላይ ነው፡፡
ሌላው ከፍተኛ ወርቅ ምርት ፈቃድ የተሰጠው ከፊ ሚኒራልስ የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ በምዕራብ ወለጋ ቱሉ ካፒ አካባቢ የወርቅ ማምረቻ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
አገሪቱ ከወርቅ ኤክስፖርት በዓመት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታገኝ የነበረ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ መውረድና የሕገወጥ ወርቅ ዝውውር በመስፋፋቱ ምክንያት ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ ወደ 230 ሚሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡
