ኢትዮጵያ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ የምታገኘውን ገቢና ወጪ በአግባቡ መጠቀም ሲገባቸው ኃላፊነታቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች፣ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
መርማሪ ቡድኑ ሰኞ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ባቀረበው የምርመራ ሥራ እንደገለጸው፣ መንግሥት በ2006 ዓ.ም. የኅብረተሰቡን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት 656,613.55 ቶን ስኳር ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል፡፡ ኃላፊዎቹ ስኳሩ ከመርከብ ጂቡቲ በሚራገፍበት ወቅት፣ ተከታትለው መቆጣጠር ሲገባቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ባለመውሰዳቸው የ13,800,000 ብር ጉድለት መድረሱን አስረድቷል፡፡
ኃላፊዎቹ ከግዥ መመርያው ውጪ ደረቅ ወደብን ከባቡር መስመር ጋር በማገናኝት ‹‹አመርትነት›› ለተባለ የቻይና ኩባንያ ለድሬዳዋ ደረቅ ወደብ 69 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሞጆ ደረቅ ወደብ 39 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ውል መፈራረማቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ኃላፊዎቹ ለዚሁ የቻይና ኩባንያ በተደጋጋሚ ለአሥራ አንድ ጊዜያት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሥራ በመስጠት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ለቦርድ ሳያሳውቁ ክፍያ መፍቀዳቸውንም መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡
በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚሠሩት ስምንት ተጠርጣሪ ኃላፊዎች የዘጠኝ መርከቦች መጠባበቂያ ወጪ 1.5 ሚሊዮን ብር መሆኑን የሚያውቁ ቢሆንም፣ 3.8 ሚሊዮን ብር ያላወራረዱ መሆናቸውንም መርማሪው ጠቁሟል፡፡
ከደረቅ ወደብ የኮንቴይነር ማንሻ ሳይበላሽ ተበላሽቷል በማለት በሰዓት ሁለት ሺሕ ብር በቀን 16 ሺሕ ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲከፈል መደረጉንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የድርጅቱ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ የ250 ሚሊዮን ብር ኮንቴይነር ግዥ ያላግባብ ለመፈጸም ሦስት ሚሊዮን ብር ጉቦ መደራደራቸውን ቦርዱ ስለደረሰበት ግዥው እንዲሰረዝ ማድረጉንም ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
እንደ መርማሪ ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት ኃላፊዎቹ ለሞጆ ደረቅ ወደብ የተለያዩ ፎርክ ሊፍቶችን ገዝቶ መሥራት ሲቻል፣ በኪራይ እንዲሠራ በማድረግ በአንድ ዓመት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማውጣታቸውንና ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የግዥ ጥያቄ ሳያቀርቡና ቦርዱ ሳይፈቅድ 25 ፎርክ ሊፍቶችንና ስምንት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ለተለያዩ የመስተንግዶ አገልግሎቶች ለዓመት የሚመድበውን በጀት በማባከን 14 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መጠቀማቸውን መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሞጆ ደረቅ ወደብ መታሸግ የነበረበትን የደንበኞች ንብረት ጂቡቲ እንዲታሸግ በማድረግ 470 ሚሊዮን ብር መንግሥት እንዲያጣ ማድረጋቸውንና ከ1,500 በላይ ወጣቶች ሥራ አጥ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ለማወቅ መቻሉን አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም የስድስት ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉንና መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው የጭነት አስተላላፊነት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ በስተቀር፣ የሰባት ተጠርጣሪዎች የተከሳሽነት ቃል ለመቀበል፣ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ የማነጋገር ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድቷል፡፡ መኖሪያ ቤታቸውንና ቢሮአቸውን በመበርበርም፣ ከምርመራ ሥራው ጋር የሚገናኙ በርካታ ማስረጃዎችን መስብሰቡንም አክሏል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ ተጠቃለው የተሠሩ የኦዲት ሪፖርቶች ማሰባሰቡን፣ ሌሎች የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለፎረንሲክና ለሚመለከታቸው ተቋማት ለማስመርመር መስጠቱን አስረድቷል፡፡
የ15 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ከኦዲት ሪፖርቱ ጋር በተገናኘ የአምስት ኦዲተሮችን የሙያ ምስክርነት ቃል መቀበልና ከበርካታ ተቋማት ማለትም ከባንኮች፣ ከተቋሙ የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች፣ ከኢንፎርሜሽን፣ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲና ከሌሎችም ተቋማት ሰነዶችን ማሰባሰብ እንደሚቀረው በመግለጽ ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ መርመሪ ቡድኑ እየገለጸ ያለው አገራዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለና እነሱ የሚመለከቱ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩት በእሳቸው ደመወዝ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ደመወዛቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዲለቀቅላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውና እሳቸውም የዋስትና መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው የጠየቁት ተጠርጣሪ፣ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡
የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሲሳይ አባፈርዳ ደግሞ፣ ‹‹በመርማሪ ቡድኑ የተነገረኝ የተጠረጠርኩበት ጉዳይና በችሎቱ ለፍርድ ቤቱ የተነገረው አይገናኝም፤›› ብለዋል፡፡ ሲያዙም እንዳልተነገረቸውና በፍርድ ቤቱ ደግሞ የማይመለከታቸውና ያልሆነ ነገር እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን በመጠቆም፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
የተጠረጠሩባቸው አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በመርማሪዎች ተገልጾላቸው ማብራርያ መስጠታቸውን በመናገር ከመርከብ ግንባታ (ግዥ) ጋር በተገናኝ ግን እሳቸውን የሚመለከት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ተከትሎ የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ናቸው፡፡
የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች ዓለም አቀፍ የውል ስምምነቶች ከመሆናቸውም አንፃር አንድም የግል ባህሪያት የሌሉዋቸው መሆናቸውን ለመርማሪዎች የገለጹ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ተለውጥው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት 31 ዓመታት ከጀማሪ መሐንዲስነት እስከ ኃላፊነት ሲሠሩ መቆየታቸውን የገለጹት ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ፣ ከ7,000 ዶላር እስከ 10,000 ዶላር እየተከፈላቸው ወይም ባሁኑ ምንዛሪ እስከ 150,000 ብር ሊከፈላቸው የሚችለውን ደመወዝ ትተው ከመርከብ የወረዱት አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ካላቸው ቅን አስተሳሰብ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ለአገራቸውም በርካታ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያስገኙ ጥናቶችንና ፕሮጀክቶችን በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዳደረጉ፣ መንግሥት ጭምር እንደሚያውቅ አስረድተዋል፡፡
ምርመራው እንዲቀጥልና እውነቱ እንዲወጣ የእሳቸውም ፍላጎት መሆኑን በመግለጽ ምንም እንኳን ፌዴራል ፖሊስ በጥሩ ሁኔታ ይዟቸው ቢገኝም ከባድ የሆነ የኩላሊት ሕመምና የደም ግፊት ስላለባቸው፣ በበቂ ዋስትና ከአገር እንዳይወጡ ጭምር ዕግድ ተጥሎባቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
የጂቡቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ታዬ ደግሞ፣ ቤተሰቦቻቸው ከእሳቸው ደመወዝ ውጪ ምንም የሚተዳደሩበት ገቢ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የታገደባቸው ደመወዝ እንዲለቀቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሚሠሩበትና ከቤታቸው ብዙ ሰነዶች እንደተወሰዱባቸው ገልጸው፣ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
እሳቸው የተቀጠሩት በ2006 ዓ.ም. የገላን ወደብ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደሆነ የተናገሩት ተጠርጣሪ፣ በአሁኑ ጊዜ የሞጆ ደረቅ ወደብ ሥራ አስኪያጅ ሌላ መሆናቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ወንጀል ተፈጽሟል የሚልበት ጊዜና እሳቸው የተቀጠሩበት ጊዜ ስለማይገናኝ፣ የታሰሩት በሌሉበትና በማይገናኙበት መሆኑን ጠቁመው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡትና መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ የጭነት አስተላላፊነት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራም በጠበቃቸው አማካይነት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ሌሎች ኃላፊዎች ከተጠረጠሩበት ጋር በተገናኘ መሆኑን አስታውሰው፣ ንፅህናቸውን ስለሚያውቁና ከሥራ በስተቀር በመርማሪዎች በሚነገረው የጥፋት መጠን የሚናወጡ ባለመሆናቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት እውነቱ እንደሚረጋገጥ በማመናቸው፣ በውጭ አገር ሆነው ጉዳዩን የሰሙት ቢሆንም መጥተው እጃቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከአገር ይወጣሉ ወይም የሚያደርሱት ችግር አለ ሊባል ስለማይችል፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ጠይቀዋል፡፡
መርማሪው ፖሊስም ጥያቄው ከአገር ይወጣሉ ወይም ያመልጣሉ ሳይሆን፣ የምርመራ ሰነዶችን ስለሚያጠፉና ምስክሮችን ስለሚያባብሉ ዋስትና ሊፈቀድላቸው አይገባም የሚል መሆኑን አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ በሰጠው ትዕዛዝ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ እንዳልተቀበለ አስታውቋል፡፡ ደመወዝ ሊከለከል ስለማይገባ የታገደ ደመወዝ እንዲለቀቅና መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በተፋጠነ መንገድ በመሥራት በ12 ቀናት ውስጥ ማጠናቅቅ እንዳለበት አስታውቆ ለመስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
