Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ኢትዮጵያ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የውሳኔ ሐሳብ ያለተቃውሞ ፀደቀ

$
0
0

 

  • ግብፅ ድጋፏን ሰጥታለች

በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 72ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጉባዔ ላይ፣ ኢትዮጵያ ራሷ አዘጋጅታ ያቀረበችው የውሳኔ ሐሳብ ያለምንም ተቃውሞ መፅደቁ ተነገረ፡፡ አጀንዳው ሰላም ማስከበርን የተመለከተ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም ከኒውዮርክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በተገቢው ስትወጣ ከመቆየቷ በላይ የወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነቷን ተጠቅማ ያቀረበችው አጀንዳ ያለተቃውሞ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የፀደቀው የሰላም ማስከበር አጀንዳ 2378/2017 የውሳኔ ሐሳብ ሆኖ መመዝገቡንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበችው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አማካይነት ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በተጠያቂነት፣ በግልጽነትና በውጤታማነት ላቅ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አጀንዳውን ማቅረቧ፣ ውይይቱን መምራቷና ማዘጋጀት ልዩ አጋጣሚ ተደርጎ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይኼ ስኬት በባለብዙ ወገን መድረኮች እንደተገኘ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የሰላም ማስከበር አጀንዳ አራት የማሻሻያ ሐሳቦች መቅረባቸውን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ የመጀመርያው የማሻሻያ ሐሳብ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከሌሎች ተግባሮች መነጠል የለበትም የሚል እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹አባል አገሮች ግጭት ከመከሰቱ በፊት በመከላከል ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤›› ብለዋል፡፡

በመከላከል ዲፕሎማሲ ላይ በመመርኮዝ ወደ ግጭት ለሚያመሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ እንደደረሱ አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው የማሻሻያ ሐሳብ የቅንጅት ሥራ እንደሆነ ገልጸው፣ የሰላም ማስከበር ተግባር በተመድ ብቻ ሊከናወን እንደማይችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ግጭቶች ዓይነታቸው በፊት ከነበሩት እየተለዩ እንደመጡ፣ ለዚህ ደግሞ ሳይንሳዊ የሆነ ዘዴ በመጠቀም በጋራ መፍታት ተገቢ እንደሆነ መሪዎች መስማማታቸውን አክለዋል፡፡

የግጭቶች ተዋናዮች ዓይነታቸውና መጠናቸው እየተቀያየረ ከመምጣቱ አኳያ፣ በተመድና በአኅጉራዊ ድርጅቶች መካከል ትብብር እንደሚያስፈልግ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ መሪ ተዋናይ እንደሆነች ያወሱት ቃል አቀባዩ፣ በአሁኑ ወቅት ከ12 ሺሕ በላይ የሰላም አስከባሪ አባላት አሰማርታ ግዳጇን እየተወጣች እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ሦስተኛው የማሻሻያ ሐሳብ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚል እንደሆነ ጠቅሰው፣ በየትኛውም አገር በሚካሄድ የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ተጠቂዎች ሴቶች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመድ ምሥረታ ጊዜ ጀምሮ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ላደረገችው አስተዋፅኦ ዕውቅና መስጠት አለብን ማለታቸውን ጠቁመው፣ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮቬንኮ ደግሞ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ሒደት በወርቅ የተጻፈ ታሪክ አላት ማለታቸውን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት በመራችው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ የአራት አገሮች ፕሬዚዳንቶች፣ አንድ ምክትል ፕሬዚዳንትና አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች መገኘታቸውን አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

ይኼ ጉባዔም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ትልቅ ስኬት የምታስመዘግብበት እንደሆነ አቶ መለስ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጉባዔው ለተገኙት የተለያዩ አገሮች መሪዎችና ተወካዮች ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡

ይኼ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላቀረበችው የውሳኔ ሐሳብ ግብፅ ድጋፍ መስጠቷ ታውቋል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በኢትዮጵያ የቀረበውን የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የማሻሻያ ውሳኔ ሐሳብ መፅደቅ መደገፋቸውን የግብፁ አልሃራም ጋዜጣ አረጋግጧል፡፡ ይህም የተመድን ተልዕኮ ለማሳካት፣ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ መንግሥታት ፀጥታ በደፈረሰባቸው አካባቢዎች የሚያደርጉትን ሚና መተካት ሳይሆን፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ያካተተ አጠቃላይ ስትራቴጂና ዕቅድ በመንደፍ ግጭቶችን መፍታት አለበት ማለታቸው ተገልጿል፡፡ የችግሮችን ምንጭ ለማወቅና ለመፍታት ለሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ብቻውን አማራጭ መሆን የለበትም ብለው፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ለሁሉም ቀውሶች ብቸኛ መፍትሔ ስላይደሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሲቪሎችን ከጥቃት መከላከል ሁሉንም ወገን እንደሚመለት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles