Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ዳንጎቴ የከረጢት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

$
0
0

-  500 የጭነት ተሽከርካሪዎች ሊያስመጣ ነው

 

በኢትዮጵያ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ የከፈተው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪ በ19 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻ ሊገነባ ነው፡፡

 

የከረጢት ማምረቻው የሚገነባው ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፊት ለፊት በሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚገኘው በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር ከተማ አቅራቢያ ከአዲስ አበባ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋብሪካው እስካሁን የሲሚንቶ ከረጢት ከናይጄሪያ በማስመጣት ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ ይህን የፋብሪካ ግብዓት በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን በማኔጅመንቱ በመወሰኑ፣ በዓመት 120 ሚሊዮን ከረጢት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በ19 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ በ2009 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ መስፍን፣ ግንባታው በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ በመጋቢት 2009 ዓ.ም. ምርት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

ከፋብሪካው ምርት ውስጥ 35 በመቶ ለዳንጎቴ ሲሚንቶ የሚቀርብ ሲሆን፣ የተቀረው 65 በመቶ ለሌሎች የአገር ውስጥ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሽያጭ ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 20 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡ የራሱ የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻ ያለው መሰቦ ብቻ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፕሮጀክቱ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በሁለተኛ ዙር የሚገነባው የከረጢት ፋብሪካ ለስኳር፣ ለማዳበሪያና ለእህል መያዣ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች እንደሚያመርት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ በሰኔ 2007 ዓ.ም. ተመርቆ ወደ ምርት የገባው ዳንጎቴ ሲሚንቶ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ አምርቶ በመሸጥ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገባት ችሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. 2.3 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ አምርቶ ለመሸጥ አቅዷል፡፡

‹‹ምርታችን ከፍተኛ ጥራት ያለው በመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ ኩባንያው ምርት በጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የ32 በመቶ የገበያ ድርሻ ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ለክልል ገበያዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የሚናገሩት አቶ መስፍን በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በጋምቤላ ክልሎች ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ለኤክስፖርት ገበያ ትኩረት በመስጠት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ወደ ሰሜን ኬንያ በመላክ ላይ ይገኛል፡፡ በሙከራ ደረጃ ወደ ሰሜን ኬንያ 10,000 ቶን ያህል ሲሚንቶ ተልኮ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ከጥቅምት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በየወሩ 10,000 ቶን ሲሚንቶ በመላክ በወር አንድ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሰሜን ኬንያ ውስጥ እስከ 200 ኪሎ ሜትር በመዝለቅ ገበያውን በመቆጣጠር ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ መስፍን፣ ዋጋ ሰብሮ በመግባት የኬንያን ገበያ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡ የድርጅቱ የማምረቻ ወጪ አነስተኛ መሆንና የራሱን ትራንስፖርት የሚጠቀም በመሆኑ፣ በኬንያ ያሉ ተወዳዳሪዎቹን በምርት ጥራትና በዋጋ ማሸነፍ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከኬንያ በተጨማሪ የጂቡቲ፣ የሶማሌላንድና የደቡብ ሱዳን ገበያዎችን ማጥናቱን፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም ከሰፈነ ጥሩ ገበያ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ፋብሪካው ለጀመረው የኤክስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኬሚካልና ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት ኩባንያው የኤክስፖርት ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉለት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዳንጎቴ ሲሚንቶ የአገር ውስጥ ገበያውን ለማስፋፋትና የኤክስፖርት ገበያውንም ለማጠናከር እንዲያስችለው 500 ዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪዎች ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የግዥ ጥያቄው ናይጄሪያ ለሚገኘው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪ ዋና መሥሪያ ቤት ቀርቦ በጐ ምላሽ መገኘቱን የጠቀሱት አቶ መስፍን፣ ተሽከርካሪዎቹ በ2009 ዓ.ም. ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ በአሁኑ ወቅት 443 ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪዎች አሰማርቶ በማሠራት ላይ ይገኛል፡፡

ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ የሚነገርላቸው ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ፣ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ለማካሄድ ፍላጐት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያን ገበያ የገመገመው ዋናው መሥሪያ ቤት በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማስፋፊያ ሥራ እንዲያከናውን ስምምነት ላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡ 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሁለተኛ ፋብሪካ በ600 ሚሊዮን ዶላር እንዲገነባ ተወስኗል፡፡

አቶ መስፍን ‹‹የዕቅድ ጉዳይ ካልሆነ ሁለተኛ ፋብሪካ መገንባት አስፈላጊነት ታምኖበታል፤›› ብለዋል፡፡ ዳንጎቴ ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሲሚንቶ በተጨማሪ በድንጋይ ከሰልና በፖታሽ ማዕድን ምርት ለመሰማራት ፍላጐት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles