የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እያስገነባው ላለው የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ ምርት ለማስጀመር በ48 ሔክታር መሬት ላይ ተተክሎ ለምርት የደረሰ የሸንኮራ አገዳ፣ መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በወረደ የመብረቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ በእሳት ቃጠሎ መውደሙ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት 12፡45 ሰዓት ላይ ከፍተኛ ድምፅ ካለው ነጎድጓድ ጋር የወረደው መብረቅ፣ በኩራዝ አንድና ኩራዝ ሁለት ፋብሪካዎች ከለማው 13 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ በ48 ሔክታር ላይ ለምርት የደረሰ ሸንኮራ አገዳ ሙሉ በሙሉ አውድሟል፡፡
ለአራቱ ፋብሪካዎች ከ100 ሺሕ ሔክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ልማት እንደሚያስፈልግ ታስቦ ቦታው የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ሁለቱ ፋብሪካዎች እንደ ሌሎቹ በግንባታ ላይ ያሉ ፋብሪካዎች ሁሉ በጊዜያቸው ባለመጠናቀቃቸው 13 ሺሕ ሔክታር ብቻ እንደለማ አስረድተዋል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት ከአራት ሰዓት በላይ በተደረገ ርብርብ ተጨማሪ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ‹‹በእርግጥ የፋብሪካዎቹ ግንባታ ባለመጠናቀቁ እንጂ የአገዳው ምርት ቀደም ብሎ መፈጨት የሚገባው ነበር፤›› ብለዋል፡፡
የመብረቅ አደጋ በአካባቢው የተለመደ መሆኑን፣ በተለይ በዚህ ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ ወቅት ክስተቱ ተጠናክሮ ይታያል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ ዓይነቱ አደጋ በሸንኮራ አገዳ ምርት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ክስተት ባይሆንም፣ ያስከተለው ጉዳት ግን ከፍተኛ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጋሻው፣ ከዚህ ቀደም ያስከተለው ጉዳት የከፋ ባይሆንም በጣና በለስና በወንጂ የሸንኮራ ማሳዎች ላይ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አብዛኞቹ በሥራ ላይ ባሉ የስኳር ፋብሪካዎች ተመሳሳይ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ስለሚታወቅ፣ የራሳቸው የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ሲኖራቸው፣ ከታሰበላቸው ጊዜ በመዘግየት ግንባታው ያልተጠናቀቁት የኦሞ ኩራዝ 1፣ 2፣ 3 እና 4 የአደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች እንደሌሉዋቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በደቡብ ኦሞ ኩራዝ በሚባለው ሥፍራ አራት ፋብሪካዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ግንባታቸውን አጠናቆ ለማስረከብ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቀድሞ ውል ቢገባም ማጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ ከኩራዝ አንድ ውጪ ሌሎቹ ሦስት ፋብሪካዎች ለቻይና ኮንትራክተር ተሰጥተው በግንባታ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በአሁኑ የመብረቅ አደጋ ጉዳት የደረሰበት የሸንኮራ አገዳ በ2006 ዓ.ም. የተተከለ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከእነዚህ አራቱ ፋብሪካዎች ኩራዝ 1 እና ኩራዝ ሁለት የያዝነው ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ይጠናቀቃሉ ተብሎ በመንግሥት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ፋብሪካዎች ደግሞ ገና በመጀመሪያ የግንባታ ደረጃ ላይ በመሆናቸው እስከ 2014 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቁ በዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡
