Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ሕወሓት የሥልጣን ሽግሽግ እንደሚያደርግ አስታወቀ

$
0
0

-  የኦሮሞ አርሶ አደሮች ያሉባቸውን ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ኦሕዴድ እንደሚፈታ ገለጸ

የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአራት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ የሥልጣን ሽግሽግ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

ሕወሓት በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ወደኋላ የሚመልሱ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የአመራር ጉድለቶች መኖራቸውን በጥልቀት መገምገሙን አስታውቋል፡፡

‹‹ለፍትሕ ብሎ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ መልካም አስተዳደር ልናሰፍንለት አልቻልንም፤›› በሚለው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፣ ወጣቱ ተደራጅቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የተሰጠው ዕድል ደካማ እንደነበር ገልጿል፡፡

ሥልጣንን ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅምና ክብር መጠበቂያ አድርጐ መውሰድ የሁሉም ችግሮች ምንጭ መሆኑንም ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ በጠባብነት የሚገለጽ ባይሆንም፣ ምልክቶቹ መታየት መጀመራቸውን በተለይ የጐጠኝነት አስተሳሰብ ጐልቶ የሚታይ ችግር መሆኑንና ቀጣይ ትግል ካልተደረገ አደጋ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ያሉትን ችግሮች ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የአመራርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን መንደፉን የሚገልጸው የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ፣ የተጠያቂነት መርህን መሠረት በማድረግ የሥልጣን ሽግሽግና ማስተካከያ በማድረግ ማዕበላዊ እንቅስቃሴ እንደሚለኩስ ገልጿል፡፡

ዋናና ምክትል ሊቀ መናብርቱን ከሥልጣን ያነሳው ኦሕዴድ በበኩሉ፣ ለስድስት ቀናት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮችን በአዳማ ሰብስቦ ሲያካሂድ የነበረውን ውይይት መስከረም 15 ቀን 2009 ዓ.ም. አጠናቋል፡፡

ከ500 በላይ የሚሆኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን በወቅታዊ የክልሉ ፖለቲካዊ ቀውሶች ዙሪያ ያነጋገሩት ሰሞኑን የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት አቶ ለማ መገርሳና ምክትል ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው፡፡

ውይይቱን ያስተባበረው የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በከር ሻሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችና የፓርቲውን ተሃድሶ አስመልክቶ ለመላው የአገሪቱና የክልሉ ሕዝቦች መግለጫ ይሰጣሉ፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት ውይይት በክልሉ ለተነሳው ግጭትና ተቃውሞ መነሻ በአርሶ አደሩ በኩል ከመሬት ጋር ተያይዞ ሊፈቱለት ያልቻሉ ችግሮች እንደሆኑ መገለጹ ታውቋል፡፡

ኦሕዴድ ከመሬት ጋር የተያያዘው ችግር በጥናት ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንደሚፈታው ገልጿል፡፡

የተማሩ ወጣቶች ሥራ አጥነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን የገለጸው ኦሕዴድ፣ እነዚህንና ሌሎችንም ያለ ተስፋ መቁረጥ ታግሎ እንደሚያጠፋቸው አስታውቋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በመጠቀም የውጭና የውስጥ ኃይሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ኦሕዴድን ከሥልጣን ለማውረድ የያዙት ዕቅድ አይሳካም ብሏል፡፡  

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles