Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ብአዴን የአመራር ሽግሽግና ለውጥ እንደሚያደርግ አስታወቀ

$
0
0

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭትና የሕዝብ ጥያቄ በወቅቱ መመለስ የሚገባው መሆኑን ጠቅሶ፣ በአጠቃላይ በክልሉ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታና የአመራር ሽግሽግና ለውጥ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶችን በከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ዘንድ በመቀጠል፣ ከዞን እስከ ወረዳ በተዘረጉ የፓርቲ መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮችን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማወያየቱን ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

ከሁለት ሺሕ በላይ ከፍተኛ አመራሮች በተሳተፉበት ከፓርቲው ችግሮች መካከል ሥልጣንን የኑሮ መሠረት ማድረግ፣ ትምክህተኝነትና የውስጥ ዴሞክራሲ መላላት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

በተለይ ደግሞ በአመራሩ ችግር ሳቢያ ኅብረተሰቡ ያነሳውን የማንነትና የወሰን ፍትሐዊ ጥያቄዎችን በአግባቡና በተገቢው ጊዜ ያለመመለስ ድክመት፣ ብዙ ችግሮችን ያስከተለ መሆኑን መገምገሙን አስታውቋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው ችግር የሕዝብ ልጆች የሆኑ ወጣቶችና የሕግ አስከባሪ ኃይሎች በመሞታቸው ማዘኑን፣ በክልሉ በሚኖሩ ሰላማዊ የትግራይ ወንድምና እህቶች ላይ የደረሰው አሳዛኝ ጥቃት የአማራን ሕዝብ የማይወክል ነው ሲል ብአዴን ገልጿል፡፡

የትምክህት አስተሳሰብ የድርጅቱን የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ትጥቅ መላላትን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ገኖ በመውጣት፣ የድርጅትና የመንግሥት አቅምን ማዳከሙን ይገልጻል፡፡

የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታትና ወደፊት በፍጥነት ለመራመድ ጥልቅ ተሃድሶ ለማድረግ መዘጋጀቱን፣ ለዚህ ውጤታማነትም የአመራር ሽግሽግና ለውጥ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባወጣው መግለጫ በተመሳሳይ የአመራር ሽግሽግ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል በተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት የአማራና የትግራይ ክልል አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት ሁለቱን ክልሎች የሚመሩት ብአዴንና ሕወሓት መግለጫ ከማውጣት ያለፈ የአመራር ለውጥ አላካሄዱም፡፡ በተቃራኒው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በክልሉ ለተፈጠረው ችግር የአመራሮቹን ፈጣን ዕርምጃ አለመውሰድ በመገምገም፣ የፓርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንዲነሱ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡  

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles