በድሬዳዋ ከተማ ዲፖ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከነዳጅ ማደያ አቅራቢያ የተነሳ እሳት በነዋሪዎች ከፍተኛ ድንጋጤ ቢፈጥርም፣ የነዳጅ ማደያውን ሳያቃጥል በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡
ሪፖርተር ከከተማዋ ፖሊስ ባገኘው መረጃ እሳቱ ረቡዕ መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ከማደያው ጋር ተያይዞ በተገነባው መጋዘን ተነስቶ፣ በንብረት ላይ ውድመት ቢያስከትልም፣ የነዳጅ ማደያው መትረፉን አመልክቷል፡፡
እሳቱ በድንገት ከተነሳ በኋላ በአቅራቢያው ባሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ በተደረገው ርብርብ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መከላከል መቻሉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በወቅቱ በሥምሪት ላይ የነበሩ የፖሊስ አባል አስረድተዋል፡፡
ለቃጠሎው መንስዔ ምን እንደሆነ ገና ተጣርቶ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ቃጠሎው በወቅቱ ከተከሰተው የኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን እሳቱ በመጋዘን ውስጥ የነበሩ የጎማ መጠገኛ መሣሪያዎችን፣ የተሽከርካሪ ባትሪዎችን፣ ኮምፕሬሰሮችንና መሰል ንብረቶችን ማውደሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ስትሆን፣ በአብዛኛው የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ቤቶች ተጠጋግተው የተገነቡባት በመሆኑ ለእሳት አደጋና መሰል ጉዳቶች የመጋለጥ አደጋዋ ሰፊ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በአብዛኛው ድሬዳዋ ከእሳት አደጋ ይልቅ በጐርፍ ተደጋጋሚ የጉዳት ሰለባ መሆኗን የቅርብ ታሪኮቿ ያመለክታሉ፡፡
