Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

አሜሪካ ያልተቆራረጠ የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ አሳሰበች

$
0
0

- የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ሥራ ጀመረ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ ፒተር ቭሩማን፣ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ኢትዮጵያ የተሳካ ውጤት ለማግኘት እንድትችልና ለአሜሪካ ኩባንያዎችም ብቻም ሳይሆን ለመላው የንግድ ማኅበረሰብ ያልተቆራረጠ የኢንተርኔትና የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እንትድታቀርብ ጠየቁ፡፡

ጉዳይ ፈጻሚው ቭሩማን እንዳሳሰቡት መረጃ ገንዘብ በሆነበት ዓለም፣ የመረጃ ፍሰትን የሚያፋልሱ ሰንኮፎችን ማስወገድ እንደሚገባና ይልቁንም አስተማማኝነት ያለው፣ በየጊዜው የሚከፈትና የሚቋረጥ አገልግሎት ከማቅረብ ይልቅ፣ ወጥነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔትና የሞባይል ዳታ አገልግሎት ለኢንቨስተሮች መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ቭሩማን ይህን ያሉት የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ሥራውን በይፋ በኢትዮጵያ መጀመሩ በተበሰረበት ወቅት ነበር፡፡ ኅዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት መንግሥት አስተማማኝ የመረጃ ፍሰት እንዲሰፍን፣ የንግዱ ማኅበረሰብም የምናደርገው የግንኙነት መስተጋብር ያልተገደበ እንዲሆን የማገዝ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ከተከሰተው ተቃውሞና ሁከት ጋር በተያያዘ ኢንተርኔትና የሞባይል ዳታ አገልግሎትን ዘግቶ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ ቭሩማን ንግግራቸውን በቀጥታ ከዚህ የመንግሥት ዕርምጃ ጋር አገናኝተው ባይገልጹትም፣ የኢንተርቴትና የሞባይል ዳታ አገልግሎት የንግዱ ዘርፍ የጀርባ አጥንት ናቸው በማለት አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ ‹‹ጠንካራ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ መፍጠር ካስፈለገ ወጥነት ያለውና አስታማማኝ ኮሙዩኒኬሽን መፍጠር ያስፈልጋል፤›› ያሉት ቭሩማን፣ እነዚህ አገልግሎቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች በዓለም የፋናንናንስ ተቋማት አማካይነት የሚለኩበት ቁልፍ መመዘኛዎች በመሆናቸው፣ ለተጠቃሚዎች በአግባቡ ሊቀርቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የሚያሳስበውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ለማራዘሙ የሰጠው ምክንያትም፣ በአገሪቱ የኢንተርኔትም ሆነ የሞባይል ዳታ አገልግሎት አስተማማኝ ባለመሆኑ ምክንያት አገር ውስጥ የሚገኙ አሜሪካዊ ዜጎችን ጉዳይ እንደልብ መከታተል እንደሚያዳግተው በማሳሰብ ነበር፡፡ ይኸው የአገልግሎት መቆራረጥ ግን ከዜጎች ደኅንነት ባሻገር የኩባንያዎችን ህልውና አሳሳቢ እንደሚያደርገውም ጉዳይ ፈጻሚው ቭሩማን አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የአዕምሯዊ ንብረቶች ጥበቃ ትኩረት እንዲደረግበትና የፈጠራ መብቶችና ባለቤትነትም እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች ከግል ኩባንያዎች ጋር የሚወዳደሩበት ሜዳ ፍትሐዊ እንዲሆን የጠየቁት ቭሩማን የቢዝነስ ቪዛ፣ ታክስና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቶች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሚያስችል መንገድ እንዲሠራባቸው ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎችንና ግለሰቦች አባል መሆን የሚችሉበት የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት (አምቻም) ለአባልት የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች ጨምሮ ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስኮችም አስተዋውቋል፡፡ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው አገር በቀል ኩባንያዎች፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወይም ወኪል ድርጅት ወይም ኃላፊ የሚመራቸው ተቀማጭነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኩባንያዎች የአምቻም አባል መሆን የሚችሉባቸው መሥፈርቶች ተካተዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles