ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ፀባይ ክስተት ባስከተለው ድርቅ ሳቢያ ለተጎዱ 9.7 ሚሊዮን ዜጎች ዕርዳታ የሚውል እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 900 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ሰኞ ታኅሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እ.ኤ.አ. ከ2016 ሲነፃፀር በ44 በመቶ እንደሚቀንስ የገለጸ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋር ድርጅቶች በጋራ ባካሄዱት ዳሰሳ በአገሪቱ ምሥራቅና ደቡብ አካባቢዎች አዲስ የድርቅ ምልክቶች መታየታቸውን ጠቁሟል፡፡ ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ፣ 1.2 ሚሊዮን ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮችና አጥቢ እናቶች ተጨማሪ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
በኤልኒኖ አማካይነት በተከሰተው ድርቅና በተጓዳኝ በተከሰተው የተጠናከረ ጎርፍ በበሽታዎችና በተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሳቢያ 9.7 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ሕይወት መቃወሱ ተገልጿል፡፡ ከ9.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ እንደማያገኙ፣ 2.4 ሚሊዮን ቤተሰቦች ለከብቶቻቸው የመኖና የጤና ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተገምቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 300,000 ያህል ሕፃናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚገጥማቸው አጋር ድርጅቶች መተንበያቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. ለ2016 መጨረሻ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ክፍተት አሁንም እንዳለ መሆኑን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ በተለይ ለውኃ ወለድ ተቅማጥ በሽታ፣ ለእንስሳት ጤና ክብካቤ እገዛና ለምግብ ዕርዳታ አቅርቦት አስፈላጊው የገንዘብ መጠን ተሟልቶ እንዳልቀረበ አክሏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 ለሚካሄደው የምግብ አቅርቦት፣ የጤና፣ የንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ በህንድ ውቅያኖስ ላይ የታየው አሳሳቢ የአየር ፀባይ በአገሪቱ ምሥራቅና ደቡብ አካባቢዎች ድርቅ ያስከትላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ የመኸር ምርት ሊቀንስ፣ የእንስሳት መኖና የውኃ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ጽሕፈት ቤቱና ሌሎች አጋር ድርጅቶች መተንበያቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡
