የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሚስተር ቶም ማሊኖስኪ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ለመነጋገር ረቡዕ ታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተገለጸ፡፡
ረዳት ሚኒስትሩ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ከሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራት ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው የሚዲያ ጥቆማ ያመለክታል፡፡
ረዳት ሚኒስትሩ የአሜሪካ መንግሥትን ወክለው እንደሚመጡና የሚያንፀባርቁትም የመንግሥታቸውን አቋም በመሆኑ እንጂ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቀባይነት የሌላቸው ግለሰብ እንደሆኑ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
በዋናነት የሚጠቀሰው ምክንያት ደግሞ ግለሰቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን በኃላፊነት ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ፣ መንግሥት በጠላትነት የሚፈርጀው ሒውማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ አመራር ሆነው ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ በመሆናቸው ነው፡፡
የቀድሞው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ከመነሳታቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ሒውማን ራይትስ ዎችን ተችተው ነበር፡፡
የውጭ ሚዲያ ወኪሎች የሒውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርቶች መነሻ አድርገው ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ነው አቶ ጌታቸው ትችቱን የሰነዘሩት፡፡
‹‹ሒውማን ራይትስ ዎች መታረም የማይችል አጥፊ ነው፡፡ ሁልጊዜ ጥፋተኝነትን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሸከም ሥራው ያደረገ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም መታረም የማይችል አጥፊ ብቻ ሳይሆን ፍፁም ውሸታም ድርጅት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
ሚስተር ማሊኖስኪ ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የነበረውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሚዲያዎች ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዴሞክራሲና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ሆኖ የሕዝቦችን ፍላጎት ካላስተናገደ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡
