Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ከቻይና የሚገኙ ብድሮች ከመፅደቃቸው በፊት የአገሪቱ ብድር የመክፈል አቅም እንዲታይ የፓርላማ አባላት ጠየቁ

$
0
0

ከቻይና የሚገኙ አዳዲስ ብድሮች ከመፅደቃቸው አስቀድሞ የአገሪቱ ብድር የመክፈል አቅም እንዲታይ የፓርላማ አባላት ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የፓርላማ አባላቱ ጥያቄውን ያቀረቡት ሐሙስ ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. መንግሥት በቅርቡ የተፈራረማቸው የብድር ስምምነቶች እንዲፀድቁ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት ነው፡፡

ጥያቄውን ያስነሱት የብድር ስምምነቶች የተፈረሙት ከቻይና ኤክስፖርትና ኤምፖርት (ኤግዚም) ባንክ ጋር ሲሆን፣ ለአዲስ አበባ የመንገድ ግንባታና ለኃይል አቅርቦት መስመሮች ማሻሻያ የሚውሉ ናቸው፡፡

የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብረሃ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አማኑኤል ገለጻ፣ አንደኛው ብድር 230 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን፣ ዓላማውም ዕድሜ ጠገብ የሆነውን የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መረብ አሻሽሎ ለመገንባት ነው፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው ጠቅላላ ገንዘብ 274.1 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘው 230 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ብድር የሰባት ዓመታት የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ20 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን፣ ሁለት በመቶ ወለድና ጥቅም ላይ ባልዋለው ገንዘብ ላይ በዓመት 0.25 በመቶ የግዴታ ክፍያና ባንኩ ብድሩን ለሚያስተዳድርበት ደግሞ 0.25 በመቶ የክፍያ ግዴታን ይጥላል፡፡

ሌላው ብድር 102.7 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዓላማውም ከቃሊቲ የቀለበት መንገድ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ላለው መንገድና ከቃሊቲ የቀለበት መንገድ በቡልቡላ እስከ ቂሊንጦ አደባባይ ላለው መንገድ የሚውል ነው፡፡

የመንገዱ አጠቃላይ ወጪ አራት ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከቻይና የተገኘው ብድር 50 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ አቶ አማኑኤል አብራርተዋል፡፡ ይህ መንገድ 11.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረውና መንገዱ በሁለቱም አቅጣጫዎች ስምንት መስመር (ሌን) እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

ብድሩን ለመመለስ የአምስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ 20 ዓመታት መፈቀዱን፣ እንዲሁም በዓመት 2.6 በመቶ ወለድና ብድሩን ለማስተዳደር ለባንኩ 0.50 በመቶና በተመሳሳይ 0.50 በመቶ ጥቅም ላይ ባልዋለው ብድር ላይ ይከፈልበታል፡፡

አቶ አማኑኤል አብረሃ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ጀምበል ቻምበር አስማማው የተባሉት የምክር ቤቱ አባል፣ ወለዱ ጠንከር ያለ መሆኑንና የመክፈያ ጊዜው አጭር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ብድር ከመፅደቁ አስቀድሞ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የአገሪቱ ብድር የመክፈል አቅምን እንዲገመግም ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዘለቀ መሐሪ የተባሉ ሌላ የምክር ቤቱ አባልም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የብድር ስምምነቱ በተለይ የመንገድ ግንባታውን አስመልክቶ መንግሥት ኮንትራቱን የሚሰጠው ለቻይና ኩባንያ እንደሆነ፣ ባንኩ በቅድሚያ ሳያውቀው ከቻይናው ኩባንያ ጋር ውል ማቋረጥም ሆነ የውል ስምምነቱን ማሻሻል እንደማይቻል ይጠቁማል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትን ጥያቄ የተቀበሉት የምክር ቤቱን የዕለቱ ስብሰባ የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ናቸው፡፡ የብድር ስምምነቱ የአባላቱ ጥያቄ ታክሎበት ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles