ከጥር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከእስር ለማምለጥ ከዶ/ር ፍቅሩ ማሩና ከተለያዩ እስረኞች ጋር ሲወያዩ የከረሙ ታራሚዎ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ቂሊንጦ ጊዜያዊ የተከሳሾች ማረፊያ ቤትን በማቃጠልና የ23 እስረኞችን ሕይወት አጥፍተዋል የተባሉ 121 እስረኞች ተከሰሱ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ለስምንት ወራት ሴራ ሲጠነስሱ ከርመዋል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ፣ ኢብራሒም ካሚልና ሸምሱ ሰዒድ የተባሉት እስረኞች ሌሎቹ እስረኞች ‹‹የዱርዬው ቡድን›› በመባል በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በተቋቋመው ቡድን ውስጥ እንዲታቀፉ ሲያወያዩ ነበር፡፡ ለማረሚያ ቤቱ ፖሊስ መረጃ ያቀብላሉ ብለው የጠረጠሯቸውን እስረኞች በማረሚያ ቤቱ በሚገኝ ፌሮ ብረትና ማንኛውም ቁሳቁስ ነገር ደብድበው በማቁሰልና በመግደል እንዲቃጠሉ ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ በተለያዩ የወንጀል ድርጊት ተከሰው ክሳቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ሲሆኑ፣ በ2008 ዓ.ም. መጨረሻዎቹ ወራት ላይ ተከስቶ የነበረውን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተላላፊ በሽታ ምክንያት፣ ማረሚያ ቤቱ ለአንድ ቀን ከታራሚ ቤተሰቦች ምግብ እንዳይገባ በመከልከሉ ሳቢያ ቡድኑ እስረኞቹን በማስተባበር የማረሚያ ቤቱን ምግብ እንዳይበሉ አድማ ማስመታቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ከጥር ወር ጀምሮ ለስምንት ወራት ‹‹ከእስር እናመልጣለን›› የሚል ዕቅድ ነድፈው ሲያሴሩ መቆየታቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ማረሚያ ቤቱ ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከውጭ ምግብ እንዳይገባ መከልከሉን ምክንያት በማድረግ ቃጠሎውን መፈጸማቸውን፣ እስረኞችን በአሰቃቂ ሁኔታ በፌሮ ብረትና በተለያዩ ቁሳቁሶች ደብድበው በመግደል እንዲቃጠሉ ማድረጋቸውን በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው 121 እስረኞች በጋራና በተናጠል በመሆን የዱርዬው ቡድን የሚሠራውንና የሚያደርገውን ሚስጥራዊ እንቅስቃሴ ለማረሚያ ቤቱ ፖሊሶችና ኃላፊዎች ይናገራሉ በማለት የጠረጠሯቸውን 23 እስረኞችን (ስማቸው ተጠቅሷል) ቀጥቅጠው በመግደል፣ በማረሚያ ቤቱ ቀድመው በእሳት የተቀጣጠሉ የዞን ሰባት ሁለት መኝታ ቤቶች ውስጥ በመጣል እንዳቃጠሏቸው ክሱ ያብራራል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ሦስት ክሶችን በቅጽል ስሙ ዊዚ በሚባለው ያሬድ ሁሴን ላይ የመሠረተ ሲሆን፣ ሌሎች ስምንት ክሶችን በጋራ አድርጎ መሥርቷል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች (121) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀናለ) እና 539 (1ሀናሐ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል መፈጸማቸውንና ለዚህም ድርጊት በዋናነት የሚወያዩት ከዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ ከማስረሻ ሰጤና ከሌሎችም እስረኞች ጋር በመመካከር መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል ቴዎድሮስ ዳንኤል፣ ብስራት አበራ፣ አራጋው ሞገስ፣ የአብስራ ብርሃኑ፣ ዳዊት በላይነህ፣ ገብረ ሚካኤል ገብረ ሥላሴ የተባሉ ተከሳሾች ከጥር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በማረሚያ ቤቱ ከዶ/ር ፍቅሩ፣ ከማስረሻ ሰጤና ከሚስባህ ከድር ጋር ዕቅድ በመያዝና ለማስፈጸም የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ‹‹የዱርዬው ቡድን››ን ማቋቋማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ (121) በቡድኑ ሥር አባል እንዲሆኑ በማድረግና ሌሎችንም እንዲያደራጁ፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ አመፅ በመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ 500,000 ብር እንደተሰጣቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ ገንዘቡ የተሰጣቸው ለፖሊስ መረጃዎችን የሚያቀብሉ እስረኞችን እንዲገድሉ መሆኑንም ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ እስረኞችን በማደራጀት በመዘጋጀት ላይ እያሉ አተትን ምክንያት በማድረግ የተከሳሾች ቤተሰቦች ምግብ እንዳያስገቡ ማረሚያ ቤቱ ሲያሳውቅ፣ ዱርዬው ቡድን እስረኞችን በመሰብሰብ የማረሚያ ቤቱን ውሳኔ እንዲቃወሙና ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አመፅ በማስነሳት ድርጊቱ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡
ተከሳሾቹ በተናጠል፣ በጋራና በቡድን በመሆን በማረሚያ ቤቱ ላይ በፈጸሙት የእሳት ቃጠሎና የሰው መግደል ወንጀል የ23 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት ሊወድም መቻሉን ክሱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም 121 ተከሳሾች በፈጸሙት ከባድ የሰው መግደልና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ቂሊንጦ ጊዜያዊ እስረኞች ማረፊያ ቤትን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በማቃጠል በተጠረጠሩ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ 38 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ የአዲስ ካርዲዮቫስኩላር ማዕከል መሥራችና ባለድርሻ ናቸው፡፡ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የሙስና መዝገብ ተከሰው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
