- ለአቃቂ ቃሊቲ መንገድ ግንባታ የዲዛይን ለውጥ ሊደረግ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በአደረጃጀቱ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረጉን ይፋ አደረገ፡፡ ለውጡንም ተከትሎ የአመራር ለውጦችን በማካሄድ የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊዎችም መነሳታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የከተማዋን የመንገድ አገልግሎት ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ የመዋቅር ተደርጓል፡፡ የመዋቅር ለውጡ ካካተታቸው ውስጥ ቀድሞ በአንድ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው አሠራር፣ ወደ አራት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆች እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በርከት ያሉ አዳዲስ የሥራ ክፍሎች የተከፈቱ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸውም በዳይሬክቶሬት እንደሚመሩ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
ከአንድ ወደ አራት ብዛታቸው ያደገው ምክትል ሥራ አስኪያጆችም በዋናነት የየራሳቸውን የሥራ ዘርፍ ያስተባብራሉ ተብሏል፡፡ እነዚህም የመንገድ ሀብት አስተዳደር፣ የምህንድስና ጨረታ፣ ኮንትራትና የጥናት ክፍል፣ በራስ ኃይል የመንገድ ግንባታና የሰው ኃይልና የፋይናንስ አስተዳደር ናቸው፡፡
ከባለሥልጣኑ ኃላፊነት የተነሱ ግለሰቦችን አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ በርካታ የሥራ ክፍሎች በአዲስ ሠራተኞችና አመራሮች እንዲተኩ መደረጋቸውንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ባለሥልጣኑ በአንድ ማዕከል የነበረውን አሠራሩን ወደ አምስት ዲስትሪክቶች በማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜናም ባለሥልጣኑ በቅርቡ እንደሚያስገነባቸው ከሚጠበቁ መንገዶች መካከል የአቃቂ-ቃሊቲ-ቂሊንጦ መንገድ አንዱ ነው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ተዘጋጅቶ የነበረውን ዲዛይን እንደገና ለማሻሻል ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
ከቻይና ኢግዚም ባንክ በተገኘ 102.7 ሚሊዮን ዶላር ብድር ባለሥልጣኑ በሁለት ምዕራፍ ከሚያስገነባቸው መንገዶች አንዱ ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ የሚገኘው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ በቡልቡላ እስከ ቂሊንጦ አደባባይ ያለው መንገድ ነው፡፡
ነገር ግን ከቃሊቲ እስከ ቱሉ ዲምቱ የሚገኘው መንገድ ቀደም ብሎ የተሠራለት ዲዛይን ቢኖርም፣ በኋላ በርካታ የአገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶች የተገነቡ በመሆናቸው፣ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ የዲዛይን ለውጥ እንደሚደረግለት ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የዲዛይን ማሻሻያው በስድስት ወራት ውስጥ ሊጠናቀቀ እንደሚችል፣ ኢንጅነር ሀብታሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
