- የኦሞና የነጭ ሳር ፓርኮች ድንበር በዚህ ዓመት ይከለላል ተብሏል
በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 872 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ቱሪስቶች ብቻ መገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በባህልና ቱሪዝም መስኮች ዙሪያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፓርላማ ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም፣ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን እየሳበ መሆኑንና የበለጠ ቢሠራበት አገሪቷ በሃይማኖት መጻሕፍት እንደምትገለጸው የቱሪዝም ገነት መሆን እንደምትችል ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባዔ ላይ ብቻ፣ ከ800 በላይ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ብቻ 223,032 ቱሪስቶች በኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ በምርምርና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
አንድ ቱሪስት በቀን ምን ያህል ወጪ ያወጣል? የሚል ራሱን የቻለ ዓለም አቀፍ የሥሌት ቀመር እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ሒሩት፣ በዚህ ሥሌት መሠረት 872 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተመሳሳይ የመጀመርያው ሩብ ዓመት ውስጥ ከ300 ሺሕ በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ ፓርኮችን ድንበር ከመከለል አንፃር ተቋማቸው ምን እየሠራ እንደሆነ የተጠየቁት ሚኒስትሯ፣ አገሪቷ ካሏት ስምንት ብሔራዊ ፓርኮች መካከል የስድስቱ ድንበር በድጋሚ ተከልሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን አውስተዋል፡፡
ድንበሮቹን በድጋሚ መከለል ከክልሎች መሬትን የመጠቀም መብት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ፣ የስድስቱ ፓርኮች ድንበርም ከክልሎች ጋር በተደረገ ጥልቅ ውይይትና መግባባት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
የኦሞና የነጭ ሳር ፓርኮች ከአንድ በላይ ክልሎችን ወሰን የሚነኩ በመሆናቸው የበለጠ ጥንቃቄ፣ በፓርኮቹ ውስጥ የሠፈሩትን ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወርና መጠለያ መገንባትም የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱም ፓርኮች አዲስ ድንበር በ2009 ዓ.ም. እንደሚከለል አስረድተዋል፡፡
