- የትምህርት ቤቶቹ ባለሀብቶች ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ንክኪ እንደሌላቸው እየገለጹ ነው
በኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት ሲንቀሳቀሱ የቆዩትንና በቱርክ መንግሥት አሸባሪ ከተባለው የጉለን ንቅናቄ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የቱርካውያን ባለሀብቶች ትምህርት ቤቶችን፣ ለቱርክ መንግሥት አሳልፎ እንደሚሰጥ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንት ሙላቱ በቱርክ ለአምስት ቀናት በነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት ወቅት ከቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶዋን ጋር በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥታቸው ከጉለን እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ ያላቸውን ትምህርት ቤቶች አሳልፎ እንደሚሰጥና ከቱርክ መንግሥት ጋር እንደሚተባበር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከቱርክ ጎን በመቆም ሽብርተኝትን ለመታገል ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፉን እንደሚሰጥ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት የቱርካውያን ትምህርት ቤቶች ማሪፍ ፋውንዴሽን ለተባለው መንግሥታዊ የቱርክ ተቋም ተላልፈው እንደሚሰጡ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
የቱርክ መንግሥት በሐምሌ ወር ለተቃጣበት የግልበጣ ሙከራ ቀንደኛ ተጠያቂ ያደረጋቸው፣ በአሜሪካ በስደት የሚኖሩትንና የጉለን ንቅንናቄ ወይም የሂዝመን ንቅናቄ መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ሞሐመድ ፌቱላህ ጉለንና ተከታዮቻቸውን ነው፡፡ የጉለን ንቅናቄ አባላትና ደጋፊዎች፣ በግልበጣ መኩራው ሳቢያ ለ248 ሰዎች መሞትና ለ2,000 ተጎጂዎች ተጠያቂ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡ የንቅናቄው አራማጆችና አባላት በመላው ዓለም ከሚንቀሳቀሱባቸው መንገዶች መካከል በንግድ፣ በትምህርት ተቋማትና በሌሎችም መስኮች ተፅዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል በማለት የቱርክ መንግሥት ሲወነጅል ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ከቱርክ መንግሥት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች በሙሉ ንክኪ አላቸው በማለት የሚወነጅላቸው ትምህርት ቤቶችንም ሆኑ የንግድ ተቋማትን እንዲዘጉለት ሲወተውት ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያም ይህ ጥያቄ ከቀረበላቸው አገሮች መካከል ትመደባለች፡፡ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጦ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ፕሬዚዳንት ሙላቱ እነዚህ ትምህርት ቤቶች እንደሚዘጉና ለቱርክ መንግሥት ተላልፈው እንደሚሰጡ በቱርክ ጉብኝታቸው ወቅት ይፋ አድርገዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን ንግግር በቱርክ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ካሰራጨ በኋላ ሪፖርተር የመንግሥትን ይፋዊ አቋም ለማረጋገጥ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ኢንተርናሽናል በመባል የሚጠሩት ትምህርት ቤቶች መሥራች ግን ፕሬዚዳንቱ ስለተናገሩት ጉዳይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ፣ የፕሬዚዳንቱን ንግግር መተርጎም እንደማይፈልጉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አስተባባሪና ትምህርት ቤቶች በሚያስተዳድረው የካይናክ የትምህርትና የሕክምና መሣሪያዎች ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሴሊል አይዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋማቸው በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተቋቋመ፣ በመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት የአገሪቱን ሕግጋት አክብሮ የሚሠራ የትምህርት ተቋም እንጂ አሸባሪ አይደለም፡፡
‹‹ከቱርክ ተቋማትና ከቱርክ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም፤›› ያሉት አይዲን፣ የቱርክ መንግሥት ላቋቋማው ማሪፍ የትምህርት ፋውንዴሽን ተላልፈው ይሰጣሉ በማለት ፕሬዚዳንት ሙላቱ በተናገሩት ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ጠቁመው፣ ይልቁንም በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ላይ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ በዓለም ገና እንዲሁም በመቀሌ ከተማ ቅርንጫፎች ያሏቸው የቱርካውያኑ ትምህርት ቤቶች፣ የተለያዩ አገሮች ዜግነት ያሏቸውን ከ1,700 በላይ ተማሪዎች ተቀብለው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት በምን አኳኋን ትምህርት ቤቶቹ ለማሪፍ ፋውንዴሽን ተላልፈው እንደሚሰጡ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
‹‹ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የግል ሀብታችንን ኢንቨስት አድርገን ትምህርት ቤቶቹን መሥርተናል፤›› የሚሉት አይዲንና አጋሮቻቸው፣ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ንክኪ እንደሌላቸው፣ መንግሥት የጉለን አሸባሪ ቡድን ከሚላቸውም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው እየገለጹ ነው፡፡
