በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል በሦስት መዝገቦች ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ መላኩ ፈንታ፣ በመዝገብ ቁጥር 141352 ከቀረቡባቸው 93 ክሶች ውስጥ በስድስት ክሶች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ የተሰጠ ቢሆንም፣ ውሳኔውን የተቃወመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠየቀ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ በሰውም ሆነ በሰነድ ሊያስረዳባቸው እንዳልቻለ በመግለጽ ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ በተወሰኑ ክሶች፣ አቶ ስማቸው ከበደና አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ከተጠረጠሩበት የሙስና ክስ ሙሉ በሙሉ፣ አቶ ከተማ ከበደ የባንክና የፋይናንስ ተቋማት ሥራን በመተካት አራጣ የማበደር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ከመሠረተባቸው ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም፣ ኅዳር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ያቀረበው ስድስት የመቃወሚያ አቤቱታዎችን ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ተከሳሾች በተጨማሪ አቶ መርክነህ ዓለማየሁ፣ አቶ እሸቱ ግረፍ፣ አቶ አስፋው ሥዩም፣ የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ማርያም፣ አቶ ጌቱ ገለቴ (በሌሉበት)፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬና አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤልም ላይ የይግባኝ አቤቱታ አቅርቧል፡፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ የመቃወሚያ አቤቱታ ያቀረበው በጂኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ ላይ ነው፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ አቶ ስማቸው በ2003 ዓ.ም. ለሆቴል አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ አስገብተዋል፡፡ ነገር ግን ዕቃዎቹን ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እየተገለገሉበት የተገኙ ቢሆንም፣ ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረዋህድ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት የፈጸሙት ተግባር ሕገወጥ መሆኑ በኦዲት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ምርመራና ክስ እንዳይጀመርባቸው መደረጉን ዓቃቤ ሕግ ለሥር ፍርድ ቤት ማስረዳቱን በአቤቱታው ገልጿል፡፡ የሰነድና የሰው ምስክሮችም ቢያሰማም፣ አቶ ስማቸው ፈጽመውታል ተብለው የተጠረጠሩበት ወንጀል፣ በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 163 መሠረት በአስተዳደራዊ ቅጣት የሚታይ መሆኑንና ወንጀል መሆኑ ቀሪ እንደሆነ የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው መግለጹን፣ ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው ጠቁሟል፡፡ በተጠቀሰው አዋጅ ከአንቀጽ 166 እስከ 174 ድረስም በጉምሩክ ወንጀልነት ከተፈረጁትም ውስጥ አለመካተቱንም የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው ማስቀመጡንም አክሏል፡፡
በተጨማሪም የሥር ፍርድ ቤት አዲስ የወጣውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006ን መሠረት አድርጎ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና በወንጀል ሕግ ቁጥር 5(2) ድንጋጌ መሠረት ክሱ እንዲቋረጥ ማድረጉን ዓቃቤ ሕግ በመቃወም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ተከላከሉ እንዲባልለት ሰፊ ዝርዝር የይግባኝ አቤቱታውን ለይግባኝ ሰሚው ችሎት አቅርቧል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ ደረጃ የይግባኝ አቤቱታ ያቀረበባቸው በአቶ ገብረዋህድ፣ በአቶ አስመላሽ፣ በአቶ መላኩ፣ በአቶ ነጋ፣ በአቶ ጌቱ፣ በአቶ ገብረ ሥላሴና በአቶ ወልደ ሥላሴ ላይ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው ያቀረበው ተቃውሞ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ ከገባ ሲሚንቶ ጋር በተያያዘ ክስ ላይ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ የሥር ፍርድ ቤት መስጠቱን በመግለጽ ነው፡፡
የሲሚንቶን እጥረትና ዋጋ ለማረጋጋት ለቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ታስቦ ወደ አገር ውስጥ ከቀረጥ ነፃ የገባ ሲሚንቶ ለሦስተኛ ወገን በማስተላለፍ፣ መንግሥት ከቀረጥና ታክስ ክፍያ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከ21.6 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳጣታቸውን በሰውና በሰነድ ማስረዳቱን ጠቁሟል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ግን እንዳላስረዳ በመግለጽ፣ በአግባቡ ሳይመረምር ተከሳሾቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ የሰጠው ውሳኔ አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ተከሳሾቹ ተከላከሉ እንዲባሉለት ሰፋ ያለ አቤቱታ ለይግባኝ ሰሚው ችሎት አቅርቧል፡፡
አቶ ገብረዋህድ፣ አቶ መርክነህ፣ አቶ እሸቱና አቶ አስፋው በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ላይ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም በሦስተኛ ደረጃ አቤቱታ ያቀረበው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ አዋሽ መቅረጫ ጣቢያ ላይ ማንነቷ ካልታወቀች ግለሰብ ላይ ከተያዙ ኮንትሮባንድ ካሜራዎች ውስጥ ሦስት ሶኒ ዲጂታል ካሜራዎች ጋር በተያያዘ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ካሜራዎቹ መወሰዳቸውን የሰነድና የሰዎች ማስረጃዎችን አቅርቦ ያስመሰከረ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ አድርጎ በነፃ ማሰናበቱ ተገቢ ባለመሆኑ ተከላከሉ እንዲባልለት ዝርዝር አቤቱታውን አቅርቧል፡፡
አቶ ገብረዋህድና ባለቤታቸው በተከሰሱበት በሕገወጥ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመሰል ወንጀልን በሚመለከት የሥር ፍርድ ቤት ኮሎኔል ሃይማኖት የተከሰሱበትን የሕግ አንቀጽ በመለወጥ፣ ተከላከሉ የተባሉበትን ውሳኔም ዓቃቤ ሕግ ተቃውሟል፡፡ በክሱ ባቀረበው ዝርዝር ሁኔታ በማስረጃዎች ማረጋገጡን ገልጾ፣ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ተከሳሾቹ በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘው ንብረትና ገንዘብ በሕገወጥ የተገኘ መሆኑን ማስመስከሩ ተረጋግጦለት ተከላከሉ እንዲባልለት በዝርዝር አቤቱታውን አቅርቧል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በመጨረሻ ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ በኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ ላይ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው እንዳስረዳው፣ አቶ ከበደ በአዋጅ ቁጥር 83/1986 አንቀጽ 59(1)ሸ መሠረት ለባንክና የፋይናንስ ተቋማት የተሰጠን ሥልጣን በመተላለፍ፣ በሕገወጥ መንገድ የባንክ ሥራን ሲሠሩ መገኘታቸውን በመጥቀስ ክስ ማቅረቡን አስታውሷል፡፡ በሰነድና በሰው ምስክሮችም ማረጋገጡን ጠቅሶ በአቤቱታው አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ አቶ ከተማ የባንክ ሥራን ተክተው አለመሥራታቸውንና የአራጣ ማበደር ወንጀል እንዳልፈጸሙ በመግለጽ በነፃ ያሰናበታቸው በመሆኑ፣ ውሳኔውን እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔም ውድቅ ተደርጎ ተከላከሉ እንዲባልለት ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የዓቃቤ ሕግ ይግባኝን ያስቀርባል በማለት፣ ተከሳሾቹ በይግባኙ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
