- የቀብር ሥርዓቱ በልደቱ ቀን ተፈጸመ
ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከቤተሰቦቹ ጋር በመኖር ላይ የነበረው የ32 ዓመት ጣሊያናዊ ወጣት፣ የካቲት 18 ለ19 አጥቢያ 2009 ዓ.ም. በመዝናናት ላይ እያለ ባልታወቁ ሰዎች ተገደለ፡፡
መኖሪያቸውንና የሥራ ቦታቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉትን ወላጆቹን ለመጠየቅ ከጣሊያን መጥቶ እዚሁ የቀረው ሟች ጃማ ካርሎስ ጉላ ይባላል፡፡ ወጣቱ ዘወትር እንደሚያደርገው የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለመዝናኛ የመረጡት ቦታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ፍሬንድሺፕ ሆቴል ኤቪ ናይት ክለብ እንደነበር፣ ሪፖርተር ከቤተሰቦቹና ከፖሊስ ባገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡
ሟች እስከ ሌሊቱ 9፡30 ሰዓት ድረስ ከጓደኞቹ ጋር በሰላም እየተዝናና እያለ ስልክ ተደውሎለት ወደ ውጭ ለማነጋገር በወጣበት ወቅት፣ በአንድ ተሽከርካሪ ውስጥ ከነበሩና ከማይታወቁ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ መውደቁን እንደሰማ ፖሊስ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት ሰው እንደሚፈልገው ጠርታው ሲወጣ በተተኮሰ ጥይት እንደተመታም እየተነገረ ነው፡፡ ፖሊስ ለጊዜው አብረውት የነበሩትንና በቅርበት ነበሩ የተባሉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ስለግድያው የተለያዩ መላምቶች ተሰምተዋል፡፡ አንደኛው ግድያው የተፈጸመው በሴት ምክንያት በተነሳ ግጭት ነው የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተገናኘ ነው የሚባል ያልተጣራ ወሬ ነው፡፡ ነገር ግን ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉትን ግለሰቦች ለመያዝ ክትትል እያደረገ ከመሆኑ ውጪ ምንም የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ ፖሊስ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የሟች ታላቅ ወንድም አቶ ሳቬሪዮ ጉላን ለሪፖርተር እንደተናገሩት ሟች የእሳቸው ተከታይ ነው፡፡ የተወለደውና ያደገውም ጣሊያን ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ አምስት ዓመቱን ያከብር ነበር፡፡ ነገር ግን የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. 32ኛ ዓመቱን ያከብር ነበር፡፡ የልደት ቀኑ የቀብሩ ቀን ሆኗል ብለዋል፡፡ ከቤተሰብ ጋር አብሮ የሚሠራና ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ ገብቶ ስለማያውቅ፣ የተፈጸመበት የግድያ ወንጀል እንዳስደነገጣቸው ወንድምየው ገልጸዋል፡፡ ዘወትር እንደሚያደርገው ለመዝናናት ብሎ ከጓደኞቹ ጋር ወጥቶ መገደሉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በግድያው ሥፍራ ስለተፈመጸው ድርጊት ጠይቀው እንደተረዱት፣ ወንድማቸው በመዝናናት ላይ እያለ ከውስጥ ተጠርቶ ሲወጣ ተመትቶ እንደሞተ ከመስማታቸው ውጪ አሁን ፖሊስ ምን እያደረገ እንደሆነ እንደማያውቁም ገልጸዋል፡፡
ወንድማቸው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆኑ ለገሃር አካባቢ በሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፀሎተ ሥርዓት ተደርጎለት፣ የቀብር ሥርዓቱ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጄኔራል ዊንጌት የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ፊት ለፊት በሚገኘው የካቶሊካውያን መካነ መቃብር መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡
