- ክሳቸው ከሌሎች ተከሳሾች እንዲነጠልላቸው ጠየቁ
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በማባባስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍና የሐሰት ወሬዎችን በማውራት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ ለብይን ተቀጠረ፡፡
ዶ/ር መረራ በጠበቃቸው አማካይነት ዓርብ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች፣ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ከአቶ ጀዋር መሐመድ ጋር አብሮ ለመከሰስ የሚያስችል ምንም ዓይነት ምክንያትም ሆነ የጋራ ነገር ስለሌለ ክሳቸው እንዲነጠልላቸው ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የተመሠረተባቸው ክስ የሽብር ወንጀል ክስ ባለመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እና ከ8 እስከ 12 ያሉት ድንጋጌዎች እንዲከበሩላቸውም በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ዋስትና ቢፈቀድላቸው የሚሸሽጉት፣ የሚያባብሉትና የሚያጠፉት እንደሌለ፣ ወይም ከአገር ወጥተው ይጠፋሉ የሚባሉ እንዳልሆኑ የገለጹት ጠበቃቸው፣ እሳቸው ሰላማዊና በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ የፖለቲካ ትግል የሚታወቁ መሆኑን ችሎቱም ሊገነዘብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር መረራን ዋስትና ከልክሎ ማሰር ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ እንደሚያደርገው የተናገሩት ጠበቃቸው፣ ዶ/ር መረራ ‹‹ገነት›› ውጭ አገር የለም እንጂ ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያን የሚያስበልጡና ከአገራቸው መውጣት እንደማይፈልጉ የተመሰከረላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ስለዶ/ር መረራ የተናገሩት የቀድሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ተቃዋሚዎች ሲናገሩ ዶ/ር መረራን እንደ ሞዴል መውሰድ አለባቸው ማለታቸው፣ ዶክተሩ ምን ያህል የአገርን ፖለቲካ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መታገል እንደሚችሉ ጠቋሚ መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ዶ/ር መረራ ካለባቸው የስኳር ሕመም አኳያ በቤታቸው ሆነው የቤተሰቦቻቸውን ክትትል በማግኘት ክርክራቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲፈቅድላቸው በቃልና በጽሑፍ ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በቀረበለት የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በጽሑፍ ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ላይ ዓቃቤ ሕግ ምላሹን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ የክስ መቃወሚያን በሚመለከት በዕለቱ ቀጠሮ እንደሚሰጥ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
