በአራዳ ክፍለ ከተማ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ ስምንት ሠራተኞች የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል ብሎ ክስ የመሠረተባቸው፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ናቸው፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ዲዛይን ዋና የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ መዓዛ ታደሰ፣ የግዢና ጨረታ ውለታ ኦፊሰሮች ወይዘሪት ስምረት ኃይለ ሚካኤልና አቶ አበራ ልየው፣ የግንባታና ክትትል ቁጥጥር ኦፊሰር አቶ አዲስ ዘርጋው፣ የግንባታ ንዑስ የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ገብረ ንጉሥ፣ የግንባታ ውለታና ጨረታ ኦፊሰር አቶ ሙሉጌታ ከበደ፣ የጨረታና ውለታ ኦፊሰር ወይዘሪት ሕይወት ተስፋዬና የግዢና ጨረታ ውለታ ኦፊሰር አቶ ዘርፉ ፀጋዬ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ባቀረበው ክስ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡
ተከሳሾቹ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው የክፍለ ከተማው የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ከግንባታ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ያደረገውን ውል በመጣስ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው፣ ጽሕፈት ቤቱ ለየካቲት 12 ሆስፒታል የጄኔሬተር ቤት ለማስገንባት አርጂኤች ቢዝነስ ሴንተር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የውል ስምምነት ፈጽሟል፡፡ በክፍለ ከተማው ለወረዳ አምስት ባለሦስት ፎቅ የወጣቶች ማዕከልን ለማስገንባት ካቡ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የ2,105,882 ብር የውል ስምምነት ፈጽሟል፡፡
የወይዘሮ ቀለመወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይብረሪ ባለሁለት ፎቅ ለማስገንባት ደግሞ ፈጥኖ ለሥራ ኮንስትራክሽን ከሚባል ድርጅት ጋር ውል ፈጽሟል፡፡ ምዕራፍ ኮንስትራክሽን ከሚባል ድርጅት ጋር ደግሞ የቀበና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ባለአራት ፎቅ ለማስገንባት፣ እንዲሁም ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል እስከ ቀበና አደባባይ የከርቭ ስቶን አጥር ለማስገንባት ጨረታ አውጥቶ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አስፍሯል፡፡
ተከሳሾቹ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ጽሕፈት ቤቱ የገባውን ውል በአግባቡ ተከታትለው ማስፈጸምና የውል ግዴታውን በማይወጣው ድርጅት ላይ የተቀመጠውን የውል ግዴታ ማስፈጸም ሲገባቸው፣ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ በድምሩ የ848,264 ብር ጉዳት በመንግሥት ላይ በማድረሳቸው የሙስና ወንጀል ክስ መመሥረቱን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
