በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ድርቅ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ባለፈው ሳምንት በተጀመረው ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ ከ20,000 በላይ ኩንታል እህል ለድርቁ ተጎጂዎች ተገኝቷል፡፡ የማሰባሰቡ ሥራ አሁንም መቀጠሉን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተጀመረውን የወገን ለወገን ድጋፍ ማሰባሰብ የመሩት የደምበል ሲቲ ሴንተር ባለቤት አቶ የምሩ ነጋና አቶ ሰዒድ ዳምጠው መሆናቸውን፣ ከአቶ አዲሱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህ ድጋፍ ውስጥ ከተሳተፉት ታዋቂ ባለሀብቶች መካከልም የአሊሊ ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ፣ አቶ የምሩ ነጋና አቶ ሰዒድ ዳምጠው እያንዳንዳቸው 1,200 ኩንታል እህል መለገሳቸው ታውቋል፡፡
የአልሳም ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ሳቢር አርጋው 1,200 ኩንታል፣ የአቶ ጌቱ ገለቴ ድርጅት ጌታስ ትሬዲንግ 1,200 ኩንታል፣ የኤም ኤች ኢንጂነሪንግ ባለቤት ዶ/ር መሰለ ኃይሌ 400 ኩንታል እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሌላ ቡድን በተካሄደው ድጋፍ የማሰባሰብ ሒደት ታዋቂው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎች ባለቤት አቶ ፀጋዬ አበበ በማስተባበር መሳተፋቸውን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ኃይላንድስ አበባ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አቶ ፀጋዬ አበባ ባስተባበሩት ድጋፍ ማሰባሰብ አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ራሳቸው አቶ ፀጋዬ 100 ሺሕ ብር ድጋፍ ሲያደርጉ፣ የሉና ኤክስፖርት ቄራ ባለቤት አቶ ተስፋልደት ሐጎስ በተመሳሳይ 100 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
የበላይነህ ክንዴ አስመጪ ድርጅትና የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ 200 ሺሕ ብር፣ የሆራይዘን ፕላንቴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ 200 ሺሕ ብር፣ የአምደይሁን ጄኔራል ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ናስር ጀማል 200 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም አቶ ዓሊ አብዱራህማን 100 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጋቸቸውን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን የትግራይና የአማራ ክልላዊ መንግሥታት በተመሳሳይ የምግብና የመጠጥ ውኃ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ፀጋዬ አበበ በእሳቸውና በአቶ የምሩ ነጋ አስተባባሪነት ይመራ የነበረው ድጋፍ የማሰባሰብ ሒደት ዓላማው አንድ በመሆኑ እንዲዋሀድ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት አቶ የምሩ ነጋ በአስተባባሪነት እየሠሩ መሆኑን፣ ባንኮችንና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጭምር ያካተተ ሰፊ ዘመቻ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህ ጥረት ባለሀብቶቹ በራሳቸው የጀመሩት እንጂ በመንግሥት ጥያቄ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የድርቅ ተጎጂ ለነበሩ 1.6 ቢሊዮን ብር መለገሱን አስታውሰዋል፡፡
