Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል ያሉ የቂሊንጦ ተከሳሾችን ጉዳይ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ታዘዘ

$
0
0

 

‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸው ሳይሆን የማረሚያ ቤቱን ስም ለማጥፋት ነው››

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር 

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቂሊንጦ የተከሳሾች ማቆያን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አቃጥለዋል ተብሎ ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ 38 ተከሳሾች፣ ማረሚያ ቤቱ የሰብዓዊ መበት ጥሰት እንደፈጸመባቸው ለፍርድ ቤት አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማረሚያ ቤት ድረስ ሄዶ በማጣራት ውጤቱን እንዲልክ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል 23 ክሳቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ እስረኞች መሞታቸውንና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ለውድመት መዳረጉ፣ ለዚህም ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 38 እስረኞች መከሰሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ በተለያዩ ጊዜያት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ እየመረመረው ለሚገኝው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ከርመዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥ ባዘዘው መሠረት፣ ማረሚያ ቤቱ የተለያዩ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤቱ የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለፍርድ ቤቱ በራሳቸውና በጠበቃቸው አማካይነት እንደገለጹት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27(2) መሠረት የምርመራ ቃላቸው በግዳጅ የተሰጠ በመሆኑ በማስረጃነት እንዳይቀርብና ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ከ38ቱ ተከሳሾች ለ24ቱ ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ ማረሚያ ቤቱ በደንበኞቻቸው ላይ እያደረሰ ስለሚገኘው የመብት ጥሰት ለፍርድ ቤት  ደንበኞቻቸው በማረሚያ ቤት ውስጥ ድብደባ ደርሶባቸዋል፣ በጨለማና ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ ተደርገዋል፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኙ የሚደረገው ለ30 ደቂቃ ብቻ መሆኑንና የታሸገ ውኃ እንዲጠቀሙ እንደማይፈቀድላቸው በጽሑፍ ማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና አበበ ኡርጌሳ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ በሌላ የክስ መዝገብ ጥፋተኛ ሆነው ቅጣት እንደተወሰነባቸው አስታውሰው፣ በጽኑ እስራት የተቀጡ በመሆናቸው ከቀጠሮ እስረኞች ተለይተው በሌላ ቦታ ሊቀመጡ እንደሚገባም ማመልከታቸውን ፍርድ ቤቱ ያስረዳል፡፡  

ሚስባህ ከድር የተባለው ተከሳሽ ደግሞ በካቴና ታስሮ እንደሚያድርና ሌሎቹም ተከሳሾች በማረሚያ ቤቱ አያያዝ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆናቸው በማረሚያ ቤቱ በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ማስረዳታቸውንም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ መስጠቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ የ24 ተከሳሾች ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ያቀረቡት አቤቱታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጿል፡፡ በጠባብ ክፍል ውስጥና በጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል መባሉና በ24 ሰዓታት ለ30 ደቂቃ ብቻ የፀሐይ ብርሃን እንደሚያገኙ የተገለጸው፣ ከእውነት የራቀና ስህተት መሆኑን ማረሚያ ቤቱ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ አስፍሯል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በሌላ መዝገብ ፍርደኛ ቢሆኑም በአዲሱ መዝገብ ሌላ የክስ ሒደት እየተከታተሉ በመሆኑ፣ ወደ ሌላ ፍርደኞች ማዕከል ማዛወር እንደማይችል ማረሚያ ቤቱ ምላሽ መስጠቱንም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡ የሌላው ተከሳሽም ተመሳሳይ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ምግብ እንዳይገባላቸው መከልከላቸውንም በሚመለከት ምንም የተከለከሉት ነገር እንደሌለም ማረሚያ ቤቱ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የቤተሰብ ግንኙነትም እንዳልተከለከሉና የታሸገ ውኃን በሚመለከት በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከሚገኙ ሱቆች ገዝተው መጠቀም የሚችሉ በመሆናቸው ተከልክለናል ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ማረሚያ ቤቱ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አካቷል፡፡ ሌሎችም ተከሳሾች በሌላ መዝገብ ፍርደኛ ቢሆኑም፣ በተያዘው መዝገብ በቀጠሮ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ወደ ሌላ ማዕከል ማዛወር እንደማይቻል ማረሚያ ቤቱ አጽንኦት ሰጥቶ ምላሽ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ሚስባክ ከድር የተባለው ተከሳሽ በካቴና ታስሮ የሚያድር መሆኑን በሚመለከት፣ አለመታሰሩን ማረሚያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ማሳወቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ምንም ዓይነት ድብደባ፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት እንዳልተከሰተ፣ እንዲያውም መብቶቻቸው ተከብረውላቸው ሁሉም በየቋንቋቸው እኩል የሚከበሩበት ተቋም መሆኑን፣ ማንኛውም ዓይነት የፖሊስ ምርመራ የማይደረግባቸው እንደሆነና በአጠቃላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደሌለ ማረሚያ ቤቱ መግለጹን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የማረሚያ ቤቱን ስም ሆን ብለው ለማጥፋት ያቀረቡት ከመሆኑ ውጪ፣ የተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሌለ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ማረሚያ ቤቱ እንደገለጸው በማረሚያ ቤቱ ላይ በደረሰው ቃጠሎ ከመጠርጠራቸው ውጪ፣ ምንም ዓይነት ድብደባና ምርመራ እንዳልተደረገባቸውም በተደጋጋሚ ማስረዳቱን አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች አቤቱታና ምላሽ አግባብነት ካላቸው ሕግጋት ጋር በማገናዘብ፣ መርምሮ ትዕዛዝ መስጠቱን አስረድቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 ሥር እንደተደነገገው፣ በጥበቃ ሥር ያሉ ወይም በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው መጠበቅ እንዳለበት ፍርድ ቤቱ ገልጾ በማረሚያ ቤቱ በሚቆዩበት ጊዜ ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አባታቸው፣ ከሕግ አማከሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ መደንገጉን አስረድቷል፡፡

የሕግ መንግሥቱን ድንጋጌ ለማስፈጸም ወይም ተፈጻሚ እንዲሆን ለማድረግ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በአዋጁ ቁጥር 365/95 መቋቋሙንና አዋጁን ለማስፈጸም፣ የፌዴራል ታራሚዎች አያያዝ ደንብ ቁጥር 138/99 ወጥቶ ሥራ ላይ መዋሉን ፍርድ ቤቱ አስታውሷል፡፡ አዋጁና ድንቡ ታራሚዎቹ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በብሔር ብሔረሰብ አገልግሎት ልዩነት ሊደረግባቸው እንደማይገባ መድንገጉን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የታራሚዎቹ አኗኗር ሁኔታን በተመለከተም ምግብ፣ ሕክምናና መጠለያ ሊቀርብላቸው እንደሚገባም በዝርዝር መቀመጡን ጠቁሟል፡፡ በፍርድ ቤት በቀጠሮ ላይ ያሉና ያልተወሰነባቸው ታራሚዎች፣ ከተወሰነባቸው ታራሚዎች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው በግልጽ በአዋጁና ማስፈጸሚያ ደንቡ ላይ መቀመጡንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር የማረሚያ ቤቱ ኮሚሽን በሥሩ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች መሠረት፣ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት ባስጠበቀ ሁኔታ መያዝ እንዳለበት ከማቋቋሚያ አዋጁና ከማስፈጸሚያ ደንቡ መገንዘብ እንደሚቻል ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹና ማረሚያ ቤቱ በተከራከሩበት ጉዳይ ማረሚያ ቤቱ መመርያው በሚፈቅደው መንገድ እየሠራ መሆኑን ቢገልጽም፣ ተከሳሾቹ ደግሞ ሰብዓዊ መብታቸው እንደተጣሰ እየገለጹ መሆኑን ጠቁሞ፣ በደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 16(1ለ) ሥር እንደተገለጸው አንድ ታራሚ በዲሲፕሊን ምክንያት ሲቀጣ ለአንድ ወር በማንኛውም ጎብኚ እንዳይጎበኝ እንደሚደረግ ፍርድ ቤቱ አስታውሷል፡፡ በመሆኑም ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መልስ ላይ በደንቡ መሠረት ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋል ከማለት ውጪ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ያልገለጸ በመሆኑ፣ በግልጽ ሊያሳውቅ እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ ስምምነት ላይ መድረሱን አስቀምጧል፡፡

በሌላ መዝገብ የተቀጡ ፍርደኞች ከተመላላሽ እስረኞች መለየት እንዳለባቸው በአዋጁና ደንቡ ላይ የተደነገገ ቢሆንም፣ በአዲስ መዝገብ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ከመሆኑ አንፃር፣ በተለያየ ቦታ ሆነው ሊከታተሉ ይገባል የሚል በአዋጁም ሆነ በደንቡ ባለመገለጹ፣ ፍርድ ቤቱም በተለያየ ቦታ ሆነው ይከታተሉ በማለት የተሰጠው ሥልጣን ስለሌለ መልስ የሚሰጥበት ጉዳይ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27(2) መሠረት ለፖሊስ የሰጡት ቃል ማስረጃ እንዳይሆንና ውድቅ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ በሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 23 መሠረት በተከሳሽ የተሰጠ የእምነት ቃል ተቀባይነት ያለው የእምነት ቃል ነው፡፡ በተያዘው ክርክር ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ የሌላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ የእምነት ቃል በፈቃደኝነት ያልሰጡና እየተከራከሩ በመሆኑ ‹‹የእምነት ቃልን መቼ ነው መቃወም የሚቻለው›› የሚለውን ምላሽ መስጠት ተገቢ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዳመነበት ገልጿል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ በ27(2) መሠረት የተሰጠ የእምነት ቃል ተቃውሞ ሲቀርብበት በየትኛው መንገድ እንደሚቀርብ  ወይም መፍትሔ እንደሚያገኝ የሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚለው ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ነገር ግን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 146 መንፈስ፣ በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠ እምነት ቃል በመደበኛ ፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃል ተጠይቆ፣ ማስረጃ የመሰማት ሒደት በሚጀመርበት ጊዜ መገንዘብ እንደሚቻልና ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንደሚሰጡበት መመልከቱን (መጠቀሱን) ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች የሰጡት ቃል ተገደው መሆኑን በቀጣይ ክርክር ግራ ቀኙ በሚያቀርቡት ድምዳሜ ላይ እንደሚደረስ ገልጾ፣ ክርክሩ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት ተከሳሾቹ አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ማረሚያ ቤቱ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተፈጸመ በመግለጹ፣ በሦስተኛ ወገን ሊጣራ እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ተገኝቶና አጣርቶ፣ የደረሰበትን ውጤት ለፍርድ ቤቱ እንዲልክ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም፣ ጥፋተኛም አይደለንም›› በማለት በመስጠታቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ከግንቦት 14 ቀን እስከ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያሰማ ትዕዛዝ በመስጠት ችሎቱን አጠቃሏል፡፡              

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles