Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

አወዛጋቢ ሆኖ የቀጠለው 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ለመግዛት የወጣው ጨረታ ታገደ

$
0
0

ዳዊት እንደሻው

የመንግሥት ግዥዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሦስት ኩባንያዎች ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት፣ በመንግሥት ግዥዎችና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ለመግዛት ሲከናወን የነበረውን የጨረታ ሒደት በጊዜያዊነት አገደ፡፡

ከአሁን ቀደም በጨረታው ላይ ተሳትፈው የነበሩ ስድስት ኩባንያዎች ለአገልግሎቱ ቅሬታ  አቅርበው ነበር፡፡ አገልግሎቱ ግን ቅሬታቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዜድቲኢ፣ አይ ላይፍ፣ ቴክኖ፣ ሲምቦ ሪሶርስ፣ ሌኖቮና መስቴክ አፍሪካ የተባሉት ድርጅቶች ውጤቱን እንደማይቀበሉትና ጉዳያቸው እንደገና በአገልግሎቱ እንዲታይ አመልክተው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በመከተል በአገልግሎቱ ውሳኔ ያልተደሰቱ ሦስት የጨረታው ተሳታፊ ኩባንያዎች ቅሬታቸውን ወደ ኤጀንሲው ወስደዋል፡፡ ባለው የሕግ አግባብ መሠረት በተገለጸው ውጤትና በአገልግሎቱ ውሳኔ ተጫራቾች ደስተኛ ካልሆኑ፣ ቅሬታቸውን ወደ መንግሥት ግዥዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ መውሰድ ይችላሉ፡፡

ኤጀንሲውም ቅሬታቸው አሳማኝ ሆኖ ካገኘው ብቻ ቅሬታቸውን የማየት ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሠረት ከስድሰቱ ተጫራቾች ቴክኖ፣ ሲምቦ ሪሶርስና ሌኖቮ የተባሉ ተጫራቾች ቅሬታቸውን ለኤጀንሲው ባለፈው ሳምንት አቅርበዋል፡፡

ከአሁን ቀደም አገልግሎቱ የአሜሪካው ባክ ዩኤስና የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያዎች ወደ ቀጣዩ የፋይናንስ ግምገማ ዙር እንዲያልፉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጨረታ ቴክኖ ሞባይል እንደ አገር ውስጥ ተጫራች ተወዳድሯል፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሥራውን የጀመረው ቴክኖ የተለያዩ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ዲጂታል ታብሌቶችን ያቀርባል፡፡ የኩባንያው ዋና መቀመጫ ሆንግ ኮንግ ነው፡፡

‹‹ጨረታው ለአገር ውስጥ ተጫራቾች ብቻ መውጣት ነበረበት፤›› ሲሉ የቴክኖ ፓርትነር  አቶ ሌቪ ግርማ ይገልጻሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጨረታ ሲጀመር አገር ውስጥ ያሉ 14 አቅራቢ ድርጅቶች የተጠየቁዋቸው መሥፈርቶች እንደሚያሟሉ ተጠይቀው ካላሟሉ ነበር ጨረታውን ወደ ዓለም አቀፍ ጨረታ መሄድ የነበረበት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ሌቪ ድርጅታቸው ስላቀረበው ቅሬታ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ለኤጀንሲው በቀረበው ቅሬታ መሠረት ጨረታው እንዲታገድ የታዘዘ ሲሆን፣ አገልግሎቱም የቀረቡት ቅሬታዎች ላይ መልስ እንዲሰጥ ታዟል፡፡

በዚህም መሠረት አገልገሎቱ በዚህ ሳምንት ሌኖቮ በተባለው ኩባንያ ለቀረበው ቅሬታ መልስ መስጠቱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት አገልገሎቱ ከዚህ ቀደም ሌኖቮ የተባለው ኩባንያ ወደ ቀጣዩ ዙር እንዳያልፍ የሰጠውን ውሳኔ ትክክለኛ ነው ብሎ በአቋሙ መፅናቱ ታውቋል፡፡

ሌኖቮ ተቀማጭነቱን በአሜሪካና በቻይና ያደረገ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ የተለያዩ እንደ ታብሌት፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ እንዲሁም ኮምፒዩተሮች በማምረትና ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡

ሌኖቮ ካቀረበው ቅሬታ በተጨማሪም ሁለቱ ኩባንያዎች ያቀረቡት ቅሬታ ላይ  አገልግሎቱ መልስ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው ውስን ጨረታ 18 ድርጅቶች ተጋብዘው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ ብቻ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

ይኼ ውጤት የመጀመሪያው የቴክኒክ ግምገማ ከተሰረዘ በኋላ የመጣ ነው፡፡ የተሰረዘውም የታብሌቶቹ ዝርዝር ዓይነት መሻሻል በማስፈለጉ እንደነበር ተገልጿል፡፡

መጀመሪያ በነበረው ጨረታ የታብሌቶቹ ባትሪ ዓይነት ተቀያሪ እንዲሆኑ ቢፈለግም፣ ነገር ግን ይኼ ተጫራቾችን የሚጋብዝ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚህም ምክንያት ጨረታው ሊደገም ችሏል፡፡

ከአሁን ቀደም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች ጨረታው ለመሰረዙ ሌሎች ምክንያቶችን ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጨረታ ከተደረገ በኋላ የተጫራቾች የቴክኒክ ሰነድ ውጤት በተጫራቾች መገኘቱን እንደ ምክንያት ይገልጻሉ፡፡

አጨቃጫቂ ሆኖ የቀጠለው የጨረታው የቴክኒክ ግምገማ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ በተወጣጡ ባለሙያዎች መደረጉ ይታወሳል፡፡

ታብሌት ኮምፒዩተሮቹ በግንቦት 2009 ዓ.ም. ግዢያቸው ተጠናቆ ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በተፈጠረው የጨረታ መዘግየት አቅርቦቱ በአንድ ወር ተራዝሟል፡፡

የሕዝብ ቆጠራውን የሚያካሂደው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለሕዝብ ቆጠራው በአጠቃላይ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ ታብሌቶቹ ደግሞ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ያስወጣሉ ተብሏል፡፡

ግዥው ከተፈጸመ በኋላ ታብሌቶቹ በአውሮፕላን ተጓጉዘው የሚገቡ ሲሆን፣ የሕዝብ ቆጠራው ከተደረገ በኋላ ደግሞ ለሌሎች ተመሳሳይ ቆጠራዎች ይውላሉ፡፡

ለደኅንነትም ሲባል ባትሪያቸው እስከ 30 በመቶ ብቻ እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ ከአሁን ቀደም ኤጀንሲው ለዋናው የሕዝብ ቆጠራ ዝግጅት እንዲረዳው የሙከራ ቆጠራ ባለፈው ዓመት የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም 220 የሚሆኑ የተመረጡ ቦታዎች በታብሌት ኮምፒዩተሮች የታገዘ ቆጠራ ተደርጎላቸዋል፡፡

በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ብሔራዊ ቆጠራ ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ከዚህ በፊት የመጨረሻውንና ሦስተኛውን ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡ በዚህም ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 73.8 ሚሊዮን መድረሱ ይታወሳል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ 100 ሚሊዮን ይጠጋል እየተባለ ነው፡፡

 ድርጅቶቹ ያቀረቡት ጨረታ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በሚመራው የቅሬታ አጣሪ ቦርድ ይታያል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles