በዳዊት እንደሻው
መንግሥት በግማሽ ቢሊዮን ብር ከተገዙ በኋላ የጥራት ችግር የተገኘባቸው ማዳበሪያዎች ላይ ማጣራት እያደረገ እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
መጠናቸው ከ70,000 እስከ 75,000 ቶን ይጠጋሉ ተብለው የተገመቱት ማዳበሪያዎች ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ተገዝተው እንደገቡ ተገልጿል፡፡
እነዚህ ማዳበሪያዎች አገር ውስጥ ከገቡና በየክልሉ ለሚገኙ የማዳበሪያ ማቀነበበሪያ ፋብሪካዎች ከተሠራጩ በኋላ የጥራት ችግር እንዳለባቸው እንደታወቀ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የጥራት ችግር ያለባቸው ማዳበሪያዎች ወደ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሲገቡ ችግር እንደነበረባቸው በዚህም ሳቢያ ፋብሪካዎቹ ጉዳት ላይ እንደወደቁ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የእንደርታ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር ያለው ፋብሪካ፣ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ጉዳት እንደደረሰበት የፋብሪካው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ አምስት ሺሕ ኩንታል የሚሆን የቦሮንና 37 ሺሕ ኩንታል የፖታሽ ማዳበሪያ ከመንግሥት መቀበላቸውን፣ የእንደርታ ኅብረት ሥራ ማኅበር ኃላፊ አቶ ጎይቶም ከሰተ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን በወቅቱ የተላኩት ማዳበሪያዎች በውስጣቸው ያለው ንጥረ ነገር ከሚፈለገው የመጠን ዓይነት በታች ሆኖ እንደተገኘና ገልጸዋል ማቀነባበሪያ ውስጥ ሲገቡም በመሣሪያዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
‹‹ማዳበሪያዎቹን የያዘው ከረጢት ላይ የተገኘው ዝርዝር መረጃና ውስጡ የተገኘው የተለያየ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲሉ አቶ ጎይቶም አክለዋል፡፡
እንደ አቶ ጎይቶም ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ችግር ያለባቸው ማዳበሪያዎች መጋዘን ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ከእንደርታ በተጨማሪ በአማራ ክልል ያለው መርከብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ እንዲሁም ደቡብ ክልል የሚገኘው ወሊሶ የኅብረት ሥራ ማኅበር የዚሁ ችግር ተጠቂዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዙ መርከብ በወቅቱ 8,000 ኩንታል ቦሮን ማዳበሪያ ከመንግሥት ወስዷል፡፡ ቦሮን ማዳበሪያ በታዋቂው የኖርዌይ የማዳበሪያ አቅራቢ ያራ ኩባንያ የቀረበ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያለው ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ማዳበሪያ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
‹‹ያቀረብነው ማዳበሪያ በተባለው የጥራት ደረጃና መጠን የቀረበ ነው፤›› ሲሉ የያራ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ሩዋን ቦዛርት ለሪፖርተር በላኩት የኢሜይል መልዕክት ገልጸዋል፡፡
‹‹በተወዳደርንባቸው ጨረታዎች ያቀረብናቸው ቦሮን ማዳበሪያዎች የተቀመጠላቸውን ጥራት የሚያሟሉ ናቸው፤›› ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ማዳበሪያዎቹ በቀድሞው የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ የተገዙ ሲሆን፣ ይህ ኢንተርፕራይዝ ከዓመት በፊት ወደ ኮርፖሬሽንነት አድጓል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ከችግሩ ጋር በተያያዘ ግንኙነት የነበራቸው ኃላፊዎች ከቦታቸው መነሳታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢንተርፕራይዙ ግብርና ግብዓት ገበያ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሽብሩ ደምሴ መነሳታቸው ታውቋል፡፡
‹‹ጉዳዩ በአሁኑ ጊዜ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እየታየ ነው፤›› ሲሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሃኑ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ዝርዝር ጉዳዮችን ለመናገር እንቸገራለን፡፡ ጉዳዩን በሁለት ሳምንት ውስጥ እንገልጻለን፤›› ሲሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ እያሱ አብርሃ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ ችግሩ አሁን ከተነሱት ኃላፊዎች ባለፈ ሌሎችንም ይነካል፡፡ በወቅቱ ውሳኔ የሰጡ የኢንተርፕራይዙ ኃላፊዎች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉም ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን በሕግ ለማየት የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከስምንት ዓመት ጀምሮ ከሚፈለገው መጠን በላይ ያላግባብ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ክፍያ የተፈጸመባቸው ማዳበሪያዎች ጉዳይም ማጣራቱ እንደሚያካትተው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለአሁኑ የምርት ዘመን ብቻ ኮርፖሬሽኑ ወደ 936 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ማዳበሪያ በ290 ሚሊዮን ዶላር መገዛቱ ይታወሳል፡፡
