የቀድሞው የጤና ጥበቃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች፣ ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚያደርጉት ፉክክር የፊታችን ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በጄኔቫ ፍፃሜ ያገኛል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ለመወዳደር ያነሳሳቸው ለሙያው ያላቸው ፍቅር፣ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያካበቱት ልምድ፣ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ክህሎታቸውና ለዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ዕይታ ለማምጣት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
አሁንም የምረጡኝ ቅስቀሳቸው የቀጠለ ሲሆን፣ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ለሚያደርጉት ውድድር በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ማኅበራት ድጋፋቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡
ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ማኅበራቱ በኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ አማካይነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር ገመቺስ እንደገለጹት፣ ዶ/ር ቴድሮስ የአገር ውስጥ የጤና አገልግሎት ሥርዓትንና ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅትን የመለወጥና በአገሮች መካከል መግባባትን የመፍጠር በቂ ልምድ አላቸው፡፡
ለሰባት ዓመታት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ወቅት በአገሪቱ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ያስታወሱት ዶ/ር ገመቺስ፣ 3,500 የጤና ማዕከላትና 16 ሺሕ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጤና ባለሙያ ማሠልጠኛ ማዕከላትን ከሦስት ወደ ሠላሳ ሦስት ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የነበሩትን 16,500 የጤና ባለሙያዎች በሰባት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸው የጤናውን ዘርፍ የመምራት አቅማቸውን የሚያሳይ በመሆኑ፣ በዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ቢመረጡ በዓለም ላይ በጤናው መስክ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ የሕፃናት ሞትን በሁለት ሦስተኛ፣ በወባ የሚከሰት ሞትን በ45 በመቶ፣ በኤችአይቪ የሚሞቱትን በ70 በመቶ፣ እንዲሁም በሳንባ ነቀርሳ የሚሞቱትን 64 በመቶ መቀነስ እንደቻሉ ተገልጿል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዶ/ር የቴድሮስ ተጠቃሽ ስኬታቸው እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህ መስክም ከ38 ሺሕ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሠልጥነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረጋቸው አንዱ ለስኬት የሚያበቃቸው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ወቅትም ግሎባል ፈንድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የመሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ኢቦላን ለመከላከል በተደረገው ዘመቻ ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንድታበረክት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በመወዳደር ላይ ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውሷል፡፡ እንደ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከሆነ፣ የአፍሪካ ካሪቢያንና ፓስፊክ ቡድን አባል አገሮች ሙሉ በሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ አባል አገሮች ድምፅ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ በሚካሄደው ምርጫ አንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀና በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የአተት በሽታ በአገሪቱ ተከስቶ ይፋ እንዳላደረጉ ኒውዮርክ ታይምስ ሰሞኑን ዘግቧል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዶ/ር ገመቺስ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በዚህ ላይ መልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመጡ ኃላፊዎች ሊመልሱት እንደሚችሉ ዕድሉን ቢሰጡም መልስ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጋር በተያያዘ ከሳምንት በፊት ወደ ግብፅ አቅንተው የነበረ ሲሆን፣ ካይሮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግብፅ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ በመሐመድ ኢድሪስ በኩል፣ ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ ለዓለም ጤና ድርጅት ለምታደርገው ውድድር ግብፅ ድጋፍ እንደምትሰጥ መናገራቸውን የግብፅ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ግብፅና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያልተፈቱ ጉዳዮች በመካከላቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስትወዳደር ድምፅ ከነፈጓት አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ሲነገር ነበር፡፡ የዶ/ር ቴድሮስ ወደ ግብፅ ማቅናትም ይህንን ጉዳይ አለዝቦ ግብፅ ድምጿን ለኢትዮጵያ እንድትቸር ለመጠየቅ እንደሆነ ግምት አለ፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከሚወዳደሩ የመጨረሻ ዕጩዎች መካከል አንዱ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ሲሆኑ፣ በጤናው ዘርፍ የአርባ ዓመት ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ በተለያዩ ቦታዎች ስኬታማ ሥራዎችን እንደሠሩና ከእነዚህም መካከል ኢንፍሌዌንዛን መከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ኢቦላን መከላከል እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተመድ ውስጥ የዋና ጸሐፊውንና የ2030 ዘላቂ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ አማካሪ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡
ሦስተኛ ተወዳዳሪዋ ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ሲሆኑ፣ በአገራቸው ከ15 ዓመታት በላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በኃላፊነት እንዳገለገሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
