በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመገንባት ላይ ለሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 1,600 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲቀርብ መንግሥት ወሰነ፡፡
መንግሥት በተለያዩ ክልሎች እያስገነባቸው ለሚገኙ ዘጠኝ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 1,600 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲቀርብ ውሳኔውን ያሳለፈው ብሔራዊ የኢኮኖሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ለሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲከፋፈል የተወሰነው 1,600 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ካላት 4,288 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም 37 በመቶ እንደሚሆን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
መንግሥት ለዘመናት የቆየውን የአገሪቱን ኋላቀር የኢኮኖሚ መሠረት በመቀየር ወደ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚ ለማሸጋገርና ወደፊትም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን አቅዷል፡፡
ይህንን የተለጠጠ ዕቅድ ዕውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን ሀብት ለማሰባሰብ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱን የዕዳ ሰነድ በአውሮፓ ገበያዎች በመሸጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡
ይህ ገንዘብ ከሞላ ጎደል ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማለትም የሐዋሳ፣ የመቐለና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው ዓመት ተመርቆ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ የተወሰኑ የውጭ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎችን በማስገባት ማምረትና ኤክስፖርት ማድረግ ጀምሯል፡፡
በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተጨማሪ አምስት ቢሊዮን ዶላር በመመደብ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና አግሮ ፕሮሰሲንግ (የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያዎችን) ለመገንባት መንግሥት ማቀዱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስተሮች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ርካሽ የሼዶች የኪራይ ዋጋ፣ የካፒታል ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት፣ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ የታክስ እፎይታ፣ ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ይገኙበታል፡፡
መንግሥት በወሰነው መሠረት 1,600 ሜጋ ዋት ኃይልና ከዚህ በላይ መሸከም የሚችሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያዎች በፍጥነት እንዲገነቡ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መታዘዙንና በጥድፊያ ሥራ ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡
እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስም ለሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ 85 በመቶ መድረሱን፣ እንዲሁም ለተቀሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተጀመሩ የመስመር ዝርጋታዎች ከ54 በመቶ በላይ መሆናቸውን እንዲሁ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሚመነጨው 4,288 ሜጋ ዋት ኃይል በተጨማሪ፣ 8,800 ሜጋ ዋት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡
