- የክስ ሒደቱ ለአንድ ዓመት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ተሰጠ
ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተገናኘ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ከተመሠረተባቸው 121 ተከሳሾች መካከል 21 ተከሳሾች ዳኞችንና ዓቃቢያነ ሕግን በችሎት ተሳድበዋል፣ ለድብድብም ተጋብዘዋል የተባሉ ‹‹ችሎት በመድፈር ወንጀል›› ጥፋተኛ ተብለው የአንድ ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡
ተከሳሾቹ ቁጥራቸው በመብዛቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን በሦስት ከፍሎ ጉዳዩን ማየት ጀምሯል፡፡ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ችሎቱ የቀረቡት 21 ተከሳሾች የአብሥራ ብርሃኑ፣ ቴዎድሮስ ዳንኤል፣ ብሥራት አበራ፣ አርጋው ሞገስ፣ ያሬድ ሁሴን፣ ዳዊት በላይነህ፣ ገብረ ሚካኤል ገብረ ሥላሴ፣ ያዕቆብ ይስሀቅ፣ ሔኖክ ወሰኑ፣ ኪዳኔ ክብሮም፣ ታምራት ፀጋዬ፣ ውብአንተ ሙጬ፣ አመሐ ካሳሁን፣ ዮናስ ሳሙኤል፣ አቤል አበባሉ፣ ታሪኩ ሼልቶ፣ ተመስገን አበበ፣ አወት ገብረ መድኅን፣ ሔኖክ ተሾመ፣ ወርቁ ጉርሙና ሚልኪያስ ከበደ ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ መቅረባቸውን አረጋግጦ የዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ፣ የቀረበባቸውን ክስ በንባብ ሊያስማ ሲዘጋጅ ሁሉም ተከሳሾች ‹‹ክሱ አይነበብም›› በማለት ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል፡፡
የተወሰኑ ተከሳሾች የተሰጣቸውን ክስ ወደ ዓቃቤ ሕግና ወደ ዳኞች በመወርወር፣ ‹‹ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች ጅቦች፣ ውሾች፣ ቆሻሾች፣ ሆዳሞች ናችሁ›› በማለት ዓቃቤ ሕግን ለመደብደብ ሲንቀሳቀሱ ፖሊስ ከልክሏቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ ጣቶቻቸውን ወደ ዳኞችና ዓቃቤ ሕግ በመጠቆም ምራቃቸውን በመትፋት (የተወሰኑት) ያልተገባ ድርጊት መፈጸማቸውን፣ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ገልጿል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ተከሳሾች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 449(ሀ) ሥር የተደነገገውን ማለትም ‹‹ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለን ዳኛ በማናቸውም መንገድ የሰደበ፣ ያወከ ወይም ያፌዘና የዛተ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ቀላል እስራት ይቀጣል፤›› የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍ፣ ፍርድ ቤት የመድፈር ወንጀል መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡ በሕጉ የተቀመጠውን የመጨረሻ ጣሪያ ማለትም እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
የክስ ሒደቱም የቅጣት ውሳኔው እስከሚፈጸም ድረስ መቋረጡን አስታውቆ፣ ማረሚያ ቤት ቅጣቱን ሲጨርሱ ፍርድ ቤት እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ውሳኔው የተሰጠው በአብላጫ ድምፅ ሲሆን አንድ ዳኛ በሐሳብ ተለይተዋል፡፡
ዳኛዋ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን በሁለቱ ዳኞች እንደተገለጸው ንግግሩ በተከሳሾቹ የተባለ ቢሆንም፣ በመዝገቡ የተከሰሱት 21 ተከሳሾች ከመሆናቸው አንፃር ሁሉም ድምጽ ሲያሰሙ ስለነበር የትኛው ተከሳሽ እንደተናገረ ባልተረጋገጠበት ጉዳይ ዝም ብለው የተቀመጡትን ተከሳሾች የሚጎዳ ቅጣት መወሰኑ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ተበድለናል አዳምጡን፡፡ ጉዳት ደርሶብናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ክስ የመስማት አቅም የለንም፤›› በማለት ተከሳሾች መግለጻቸውን ዳኛዋ ተናግረዋል፡፡
ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢ ጊዜ የሚፈልግና ምናልባትም ላቀረቡት አቤቱታ ተገቢ መልስ ሊያገኙ ቢችሉ አለመግባባቱን ሊተው ይችሉ እንደነበርም የልዩነት ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የሚጣልባቸውን ቅጣት እንደሚቃወሙና ክሱ መቀጠል እንዳለበት በመግለጽ ከሁለቱ ዳኞች መለየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
