በ2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የቀን ገቢ ግምት ጥናት ከተካሄደ በኃላ 8,651 ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የታክስ ሥርዓት መግባት መቻላቸው ተገለጸ፡፡
በከተማዋ ለዓመታት በነጋዴዎች ዘንድ ጥያቄ ሲያስነሳ የነበረውን ፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት ችግር መስመር ለማስያዝ በ2009 ዓ.ም. በተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ጥናት፣ የአዲስ አበባ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባት መቻሉ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ከተማ የታክስ ፕሮግራምና ሥርዓት ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ዓርብ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጥናቱ መሠረት ከስምንት ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ወደ ታክስ ሥርዓቱ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የገቢ አቅም በዓመት ከ40 ቢሊዮን በላይ እንደሆነና የገቢ አቅም ጥናት ከመቀጠር የሚገኝ ገቢን ካካተተ ደግሞ በየዓመቱ ከ52 ቢሊዮን በላይ መሰብሰብ እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ታክስና ፕሮግራም ልማት ሥራዎች የደንበኞች አገልግሎትና ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ቶሊ ፊጤ ናቸው፡፡ ከከተማው የገቢ አቅም አኳያ የ2008 ዓ.ም. የገቢ አሰባሰብ መነሻ ተደርጎ ሲወሰድ ከዝቅተኛው 40 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር መሰብሰብ የተቻለው 52.7 በመቶ፣ ከከፍተኛው የገቢ አቅም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ መሰብሰብ የተቻለው 40.6 በመቶ ብቻ መሆኑን አቶ ቶሊ ተናግረዋል፡፡
የ2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ዕቅድ 22.109 ቢሊዮን፣ አሰባሰቡ 92.5 በመቶ ነበር ተብሏል፡፡ ከእያንዳንዱ የታክስ ዓይነት የነበረው ድርሻ ሲታይ ከመቀጠር የተገኘው 37 በመቶ፣ ከንግድ ትርፍ ግብር 22 በመቶ፣ ከኪራይ ገቢ 4.55 በመቶና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደግሞ 2.33 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ቻርተር መሠረት አዲስ አበባ ከተማ ከፌዴራል መንግሥት የሚሰጣት ድጎማ የለም የከተማዋ የመደበኛና የካፒታል ወጪ የሚሸፈነው በዋነኛነት ከታክስ ከሚገኝ ገቢ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ወደ ንግድ ሥርዓቱ ቢገቡም ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያልገቡ በመኖራቸው፣ የቀን ገቢ ግምት መረጃ ባለመሰብሰቡ፣ የታክስ ሕጉ ክፍተት የነበረበት በመሆኑ፣ ዘርፍ የጨመሩ ግብር ከፋዮች በብዛት በመኖራቸውና ወቅታዊውን የብር የመግዛት አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ የቀን ገቢ ግምት ጥቅም ላይ ለማዋል ሲባል የዘንድሮውን የቀን ገቢ ግምት መረጃ መሰብሰብ ተገቢ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
የቀን ገቢ ግምት ማድረግ ያስፈለገበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የግብር ከፍዮች ደረጃ ላይ ለውጥ የተደረገ መሆኑ የተገለጹ ሲሆን፣ ለአብነት ያህልም ደረጃ ‹‹ሐ›› የግብር ከፋዮች በቀድሞው አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 286/1994) እስከ 100,000 ብር ሲሆን በአዲሱ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 979/2008) ደግሞ እስከ 500,000 ብር ድረስ ከፍ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡
የ2009 ዓ.ም. የቀን ገቢ ግምት ሲከናወን ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሙ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ መካከል በገቢው መሥሪያ ቤት በኩል በፍጥነት አለመገመት፣ የሚገመቱ መደብሮችን መረጃ በአግባቡ አለማጥራት፣ አለማየትና የኢንስፔክሽን ኮሚቴ በአግባቡ መረጃ መሰብሰብ አለመቻሉ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በግብር ከፋዩ በኩል ደግሞ ዕቃ ማሸሽ፣ መረጃ ለመስጠት አለመፈለግ፣ መረጃ አሳንሶ መስጠት፣ የንግድ መደብር መዝጋት፣ ውክልና የሌለው ሰው ማስቀመጥ፣ ግምት እንዳይገመት እስከ መጨረሻ ዘግቶ መጥፋት፣ የራሱን ዕቃ ካሸሸ ሌላውም እንዲያሸሽ መገፋፋት የሚሉት ዋነኛ ችግሮች እንደነበሩ ወ/ሮ ነፃነት አስረድተዋል፡፡
ጥናት የተደረገው በነጋዴው ላይ ታክስ ለመጨመር ነው ወይ? ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ወ/ሮ ነፃነት ሲመልሱ፣ ‹‹ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ የቀን ገቢ ግምት የተካሄደው በነጋዴው መካከል ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲፈጠር እንጂ ታክስ ለመጨመር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ የንግድ እንቅስቃሴ ያላቸውን በዚህ ሥርዓት እንዲያልፉ ለማድረግ ሲባልም፣ የቀን ገቢ ግምት ሥራው በሌሊት ሳይቀር መከናወኑ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የገቢ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በከተማዋ ሕገወጥ ነጋዴዎች በስፋት ያሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ገማች ኮሚቴዎች ከነጋዴው ጋር የጥቅም ግንኙነት ፈጥረው ታይተዋል፣ ይህንን እንዴት ገመገማችሁት ተብለው ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ ነፃነት፣ ይህ ጉዳይ ቀደም ተብሎ ከግምት ውስጥ የገባና የራሱ መመርያ የተዘጋጀለትና ‹‹መመርያ ቁጥር 123/2009 የገማች ኮሚቴ የዲሲፒሊን ሥርዓትና ሒደቱን የሚከታተል ተደርጎ እንደተሠራ አስረድተው፣ በሒደቱ ጉድለት የተገኘባቸው ገማቾች በሕግ እንዲጠየቁና ከሥራቸውም እንዲባረሩ መደረጉን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
