የዳኝነት ነፃነትን ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጹ፡፡
አቶ ዳኜ የ11 ወራት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ነፃነትን ማስጠበቅ ለፍትሕ ሥርዓቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንንም ለመተግበር እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተቋማዊ ነፃነትን ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች አንዱ የሆነው የፍርድ ቤቶችን የበጀት ፍላጎት ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ መላቀቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች ከአስፈጻሚው አካል የበጀት ጥገኝነት ተላቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጀት እየተፈቀደላቸው የሚንቀሳቀሱበት አሠራርን ለመፍጠር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የፍርድ ቤቶች ተቋማዊ አሠራር ብቻ ሳይሆን የዳኞችም ግለሰባዊ ነፃነት መጠበቅ እንዳለበት አክለዋል፡፡ የተሽከርካሪ አቅርቦቶች አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሟሉ ማድረግን ጨምሮ፣ የመኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለዳኝነት ዘርፉ ነፃነትና ውጤታማነት መጎልበት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ደመወዝ እንዲስተካል መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ የዳኞች ገለልተኝነት ችግር አሁንም እንዳለ አምነዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ድንገተኛ የችሎቶች ቅኝት መጀመሩንና የመዝገብ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም. 236 ጊዜ ድንገተኛ የችሎቶች ቅኝትና 1,570 መዛግብት ላይም ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምርመራ ገለልተኛ ሆነው ያልተገኙ ዳኞች መኖራቸውንና ጉልህ የገለልተኝነት ችግር በታየባቸው ላይ ከሥራ እስከማሰናበት ዕርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡
ፓርላማው የፕሬዚዳንቱን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በገለልተኝነት ዙሪያ በስፋት መሠራት እንዳለበት፣ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የሕዝብ መገልገያዎች (እንደ መፀዳጃ ቤት ያሉ) እንዲስተካከሉ አሳስቧል፡፡
