Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የኦሮሚያን የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀደቀ

$
0
0

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ላይ ‹‹የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› በማለት ተደንግጎ ይገኛል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በሕገ መንግሥቱ እንዲሰፍር ያደረጉት የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ መላው የአገራችን ሕዝቦች ናቸው፡፡ የመረጡት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች መንግሥታት እንደሚኖሩ የሚደነግግ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነች ከተማ መመረጥ ስለነበረበትም የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ መላው የአገራችን ሕዝቦች በኦሮሚያ ክልል እንብርት ላይ ያለችውን አዲስ አበባ ከተማን የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ አድርጎ መርጠዋታል፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ እንዲሰፍር አድርገዋል፤›› ያለው ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣውና በኢሕአዴግ ይፋዊ የፌስቡክ ድረ ገጽ ላይ የታተመው መግለጫ፣ ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ሕግ መመለስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የሕገ መንግሥቱን መንፈስ ተከትሎ ዝርዝሩ እንዲሠራ መደረጉን ያመለክታል፡፡

ዝርዝሩን ለመሥራት ግብዓት እንዲሆን በክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦሕዴድና በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተው በመጨረሻ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ በዝርዝር ታይቶ የመንግሥት ሕጋዊ ተቋማት መክረውባቸው ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የተወሰኑ ጉዳዮችን ተመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክሮበት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ውሳኔ ማሳለፉም ተገልጿል፡፡ እነዚህም ሦስት ጉዳዮች ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ያስቀመጣቸው ማለትም 1ኛ/ ከአገልግሎት አቅርቦት ልዩ ጥቅም አኳያ፣ 2ኛ/ ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ልዩ ጥቅሞች አኳያ፣ 3ኛ/ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ያለው ልዩ ጥቅምን ማስጠበቅ ሲሆኑ፣ ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲቀረፁና እንዲካተቱ መደረጉን አስገንዝቧል፡፡

መግለጫው ስለአዲስ አበባ ሲናገር፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ የምትገኝ ከኒዮርክና ከጄኔቫ ቀጥላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስተኛ ማዕከል የሆነች፣ የአፍሪካውያን የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መዲና የሆነች . . . የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫና ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት በሽግግር ወቅትም የክልል 4 ዋና መዲና፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀም በኋላ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ሆና እየገለገለች ያለች ናት፤›› ብሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅ የሚወጣው ሕግም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪያዎችን መብቶችና ጠቅሞች በምንም መልኩ የማይሸራርፍ፣ ይልቁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በመጠበቁ ምክንያት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ሕጋዊ መስመር ይዞ እንዲጠናከር የሚያደርግና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እንደሚሆን መግለጫው አትቷል፡፡

በመግለጫው በረቂቅ አዋጁ የሚካተቱ የአገልግሎት አቅርቦት ጉዳዮች ተካተዋል፡፡  ከእነዚህም መካከል ከትምህርት አኳያ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የአርሶ አደሩ ልጆችን እንዲሁም አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ ምክንያት ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ በአፋን ኦሮሞ፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማደራጀት እንዳለበት መቀመጡን ጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያለው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ አብዛኛውን አገልግሎቱን በተለይም የሆስፒታል አገልግሎቶችን ከከተማዋ የሚያገኝ በመሆኑ፣ አዲስ አበባ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በዕቅዷ ውስጥ ማካተት እንደሚኖርባትም ይገልጻል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲሆን መደረጉንም አስታውሷል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የአገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎቱ እንዲቀርብ ከአማርኛ በተጓዳኝ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንደሚያገልግልም ተመልክቷል፡፡

ከተማዋ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ፣ እንዲሁም አገራዊና የከተማ ነዋሪዎችን ለማገልገል ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቁ አሻራዎች በከተማዋ ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከክልሉ ሕዝብ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ስም መታሰቢያዎች እንዲኖሩ አመቺ የሆኑ እንደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሠፈሮችና የመሳሰሉት ቦታዎች እንዳስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የከተማዋ አስተዳደር የኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባህልና ታሪክ ማዕከላት፣ የቴአትር፣ የኪነ ጥበባትና የመዝናኛ ማዕከላት የሚነገቡበትንና የሚተዋወቁበትን ሁኔታዎች እንደሚመቻችም ተመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የከተማዋ መጠሪያዎች ‹‹ፊንፊኔ›› እና ‹‹አዲስ አበባ›› በሕግ ፊት እኩል ዕውቅና እንደሚኖራቸውም ተገልጿል፡፡ መሠረታዊ ነገሩን የሚቀይር ባይሆንም የስሞቹን አጠቃቀም ዝርዝር በደንብ እንደሚወሰንም አስቀምጧል፡፡ አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን፣ በቂ ካሳ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገልግሎቶችን እንዲያገኝ እንደሚደረግም አመልክቷል፡፡ አርሶ አደሩ በልማቱ ማስፋፋት ምክንያት ተጎጂ ሊሆን በጭራሽ ስለማይገባ ለወደፊቱ በቂ ካሳና በዘላቂነት የሚቋቋምበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ከዚህ በፊት የተሠራውም ሥራ ተፈትሾ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ እነዚህን ሥራዎች የሚያስተባብር የሚመራና የሚያስፈጽም ጽሕፈት ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ እንዲካተት መደረጉን አመልክቷል፡፡ ነገር ግን መግለጫው በአዲስ አበባ ነዋሪ ዜጎች ላይ በብሔር ልዩነት ምክንያት የተለየ ጥቅም እንደማይቀርብ ግንዛቤ ሊያዝበት እንደሚገባ ያሰምርበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውኃ የሚያገኘው በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር መገኛዎች በመሆኑ፣ ከዚህ አኳያ ጉድጓዱ የሚቆፈርበት፣ ግድብ የሚለማበት ወይም የውኃ መስመሩ አቋርጠው የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞችኛና ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ወጪ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ  እንዲሆኑ እንደሚደረግም ተቀምጧል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር በመተባበር የማኅበራዊ ቤቶች የሆኑትን የኮንደሚኒየም ቤቶች አስገንብቶ ከእነዚህ ውስጥ በከተማው ላሉ የመንግሥት ሠራተኞትና ሴቶች በኮታ በዕጣ ውስጥ ገብተው እንዲወዳደሩ እንደሚደረግ ያስታወሰው መግለጫው፣ በተመሳሳይ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኛ ሆነው በከተማው ውስጥ ለሚኖሩትም ተመሳሳይ ዕድል እንዲሰጥ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ገልጿል፡፡

ከከተማው መሠረተ ልማት አቅርቦት፣ ከመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዘ በተፈጥሮ ሀብት ላይና በአየርና ውኃ ላይ የሚደርስ ብክለት እንዳይኖር የሚያደርግና ይህንን መብት የማስጠበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ተገልጿል፡፡

በረቂቅ አዋጁ በአዋጁ ውስጥ የተጠቀሱትንና ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ክልሉና አስተዳደሩ የሚወያዩበትና የሚወስኑበት ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት የሆነ ከአስተደደሩና ከክልሉ ምክር ቤት የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተመልክቷል፡፡ የምክር ቤቱ ዋና ዓላማውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) መሠረት የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ከልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዚህ አዋጅ የተዘረዘሩትን ልዩ ጥቅሞች በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መከታተል፣ መገምገምና ለአፈጻጸሙ ቅልጥፍና ድጋፍ ማድረግ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታን ያገኘው ይኼ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መመራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles