Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ለኢትዮ ቴሌኮም የማስፋፊያ ፕሮጀክት ታዋቂ የጃፓን ኩባንያ ፉክክሩን ተቀላቀለ

$
0
0

 

  • የሞባይል ካርድ ዕጥረት የውጪ ምንዛሪና አከፋፋዮች የፈጠሩት ችግር ነው ተብሏል
  • በአገር ውስጥ ለማምረት የመንግሥት ውሳኔ ይጠበቃል

ኢትዮ ቴሌኮም ጨረታ ባወጣበት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት አራት ኩባንያዎችን ለድርድር ሲመርጥ፣ የጃፓን ኤንኢሲ (ዩኒፖን ኤሌክትሮኒክስ) ኩባንያ ከቻይና ሁለት ግዙፍ ኩባንያዎችና ከአንድ የስዊድን ኩባንያ ጋር ፉክክር ውስጥ መግባቱ ታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሥር ኩባንያዎች በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም ለድርድር አራት ኩባንያዎች ተመርጠዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ የተመረጡት አራት ኩባንያዎች ሁለቱ የቻይናዎቹ ዜድቲኢና ሁዋዌ፣ የስዊድኑ ኤሪክሰንና የጃፓኑ ኤንኢሲ ናቸው፡፡ የጃፓኑ ኤንኢሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚሳተፍ መሆኑን ዶ/ር አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡

ከተመረጡት ድርጅቶች ጋር ድርድር የተጀመረ መሆኑን፣ ሁሉም ድርጅቶች ዝርዝር ዕቅዳቸውን በተመለከተ መረጃ ይልካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡ ተፎካካሪዎች በሚያቀርቡዋቸው መረጃዎችና ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሊያቀርቧቸው በሚችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች መሠረት ድርድሩ የሚቀጥል መሆኑን፣ በፋይናንስ ጉዳይና ስምምነት ማዕቀፍ ላይም የመጨረሻ ድርድር እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

በድርድሩ ላይና በኩባንያዎቹ በኩል ስለሚኖሩ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮች ለጊዜው መናገር ከጨረታ ባህሪ አንፃር የማይቻል መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ውጤቱ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ እንደሚገለጽም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በአገሪቱ የተስተዋለውን የባለ አምስት ብርና የባለ አሥር ብር የሞባይል ካርድ አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶ/ር አንዱዓለም በሰጡት ምላሽ፣ የእጥረቱ ዋነኛ መንስዔ አከፋፋዮች ካርዱን ሆን ብለው በመያዛቸው ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ሰው ሠራሽ እጥረት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ውጭ አገር የሚያሳትማቸውን ካርዶች የሚፈለገው ጊዜ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠመውም ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮ ቴሌኮም በራሱ መጋዘን የሞባይል ካርዶች ባይኖሩም፣ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ካርዶች በአከፋፋዮች እጅ በመኖራቸው በአገር ደረጃ እጥረቱ ተከስቶ እንደነበረ ዋና ሥራ  አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

‹‹በወቅቱ በእኛ መጋዘን ውስጥ ካርዱ አለመኖሩን የተረዱ አከፋፋዮች እጥረት ሊፈጠር ይችላል ብለው ካርዱን በመያዝ፣ በገበያ ውስጥ እጥረት እንዲፈጠር አድርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሆን ብለው ምርቱን አስረው አቆይተዋል በተባሉ አከፋፋዮች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ቢገልጹም፣ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ስለተባሉት አከፋፋዮች በዝርዝር አልገለጹም፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዳቸው 140 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ባለ አምስትና አሥር ብር ካርዶች፣ በመላው አገሪቱ በፖስታ ቤቶችና በቻርተርድ አውሮፕላኖች የተሰራጩ ስለሆነ እጥረቱ ተቀርፏል ሲሉም አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ከካርድ ችግር ጋር በተገናኘ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት በአገር ውስጥ ለማምረት ስማቸው ካልተጠቀሱ ኩባንያዎች ጋር ድርድር መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ድርድሩን የያዘው ኢትዮ ቴሌኮም ራሱ ባለመሆኑ ዝርዝር ጉዳይ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ አገር ውስጥ የማምረት ሥራ እንደሚጀመር ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተለይ ተቋሙን እየተፈታተነው ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እልባት እንደሚያስገኝላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለእኛ የሞባይል ካርድ የደም ሥራችን ነው፡፡ ካርድ የለንም ማለት ሕይወታችን ቀጥ አለ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles