Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ጥብቅ የሆነ የቡና ምርት ግብይት ሕግ ፀደቀ

$
0
0
  • ዕለታዊ የአገር ውስጥ ቡና ዋጋ በመንግሥት ይተመናል
  • ከመስመር ውጪ ቡና ያጓጓዘና ይዞ የተገኘ እስከ አሥር ዓመት በእስር ይቀጣል

ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ገበያ የምትታወቅበት የቡና ምርት በበቂ ሁኔታ እንዳይቀርብ ያደረጉ ውስብስብ የአገር ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል እምነት የተጣለበት እጅግ ጥብቅ የሆነ አዋጅ ፀደቀ፡፡

አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁጥር 602/2000 በማሻሻል የሚተካ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ዓርብ ሰኔ 30 ቀን በፓርላማ ሲፀድቅ፣ አዋጁን በተጓዳኝ ለመደገፍ ያስችላል የተባለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅን የሚያሻሽል አዋጅም ራሱን ችሎ በፓርላማው ፀድቋል፡፡

የቡና ግብይት ጥራትና ቁጥጥርን እንደ አዲስ ለመደንገግ የተፈለገበት ምክንያት መንግሥት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመመካከር የለያቸውን ውስብስብ ችግሮች በመፍታት አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት በመጠን፣ በጥራትና እሴት በመጨመር የሁሉንም ተዋናዮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ የአዋጁ አባሪ ሰነድ ያስረዳል፡፡

የአገር ውስጥ የቡና ምርት የግብይት ሥርዓት ውስብስብ ያደረጉ አሥራ አንድ ነጥቦች ተለይተዋል፡፡ እሴት በማይጨምሩ የግብይት ሰንሰለቶች መራዘም፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቅልጥፍናና በውጤታማነት ያለመሥራት፣ የቡና ጥራት ማሽቆልቆልና የቡና ገበያ ተገማችና የተረጋጋ አለመሆን ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት አዋጁ እሴት የማይጨምሩ የግብይት ሰንሰለቱ ተዋናዮች እንዲወጡ፣ ቡና አልሚ ባለሀብቶች ከአርሶ አደሮች ጋር በትስስር እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ ቡና በመቁላትና አቀነባብሮ በማዘጋጀት እሴት ለሚጨምሩ ሕጋዊ ፈቃድ መስጠትና ልዩ ድጋፍ ማድረግን በመፍትሔነት አካቷል፡፡

ቡና ላኪዎች በአገር ውስጥ የቡና ገበያ ዋጋ መናር የተነሳ የኤክስፖርት ደረጃ ቡና ሕግን በመጣስ ለአገር ውስጥ እስከማቅረብ በመድረሳቸው፣ በአገር ውስጥ የቡና ገበያ ላይ ልዩ ቁጥጥር ማድረግም በረቂቁ ተካቷል፡፡

በዚህም መሠረት የአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ አማካይ ዕለታዊ የዋጋ ገደብ እንዲደረግበት ማካተቱን ማብራሪያው ያስረዳል፡፡

አዋጁ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና ከአምራች ገዝቶ ለማቅረብ፣ ወደ ውጭ ለመላክ፣ እሴት ጨምሮ ለማቀነባበር፣ እንዲሁም በችርቻሮ ለመሸጥ  አግባብ ያለው የቡና ንግድ ፈቃድ ማግኘት ይጠይቃል፡፡

ለአብነት ያህል ‹‹የአገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ጅምላ ነጋዴ›› እና ‹‹የአገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ችርቻሮ ነጋዴ›› የሚል የተለዩ የንግድ ፈቃዶችን ያልያዘ በአገር ውስጥ የቡና ንግድ ውስጥ መሳተፍ አይችልም፡፡

የአገር ውስጥ ቡና ጅምላ ነጋዴ ለውጭ ገበያ የማይውል ቡናን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመግዛት በተፈቀደለት አካባቢ ብቻ ለሚገኙ ቸርቻሪዎች ብቻ ማከፋፈል ይኖርበታል፡፡ በተመሳሳይም ቡና ቸርቻሪ ነጋዴ ከጅምላ አቅራቢ ነጋዴው ወይም ከአገር ውስጥ ቡና ቆዪ ብቻ በመግዛት በችርቻሮ ለመሸጥ፣ ንግድ ፈቃድ በወሰደበት መቸርቸሪያ ሱቅ ወይም ቦታ መሸጥ ይኖርበታል፡፡

በቡና ንግድ ዘርፍ ለመሰማራት ከሚፈቀዱ የንግድ ዓይነቶች መካከል ‹‹የአገር ውስጥ ቡና ቆዪ›› እና ‹‹የውጭ ቡና ቆዪ›› ዘርፎች ተካተዋል፡፡ የውጭ ቡና ቆዪ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ከራሱ ማሳ ወይም በሌሎች የግብይት አማራጮች ቡና በመግዛት ቆልቶ ወይም ቆልቶና ፈጭቶ ለውጭ ገበያ በሚመጥን ደረጃ አዘጋጅቶ መላክ ይኖርበታል፡፡ የአገር ውስጥ ቡና ቆዪ ደግሞ ለአገር ውስጥ የሚውል ቡና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ በመግዛት ቆልቶ ወይም ቆልቶና ፈጭቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

አዋጁ ቡናን በምግብነት ወይም በመጠጥነት አዘጋጅቶ የመሸጥ አገልግሎት ሰጪዎች ላይም ጥብቅ ግዴታዎችን ጥሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በልዩ ሁኔታ ካልፈቀደ በስተቀር፣ ከአገር ውስጥ ቡና ጅምላ ነጋዴ ወይም ቸርቻሪ ወይም ቆልቶና ፈጭቶ አከፋፋይ ውጪ እንዳይገዙ ግዴታ ይጥላል፡፡ በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ካልፈቀደ በስተቀር የውጭ ገበያ ደረጃ ያለውን ቡና መግዛት፣ ማጓጓዝ ወይም ይዞ መገኘት አይችሉም፡፡

ከውጭ ገበያ የሚቀርብ ልዩ ቡና (Specialty Coffee) ትርጓሜና የግብይት ሒደትም በሕጉ ተካቷል፡፡

‹‹ልዩ ቡና›› ማለት በአመራረቱ፣ በአዘገጃጀቱና በጥራቱ የተለየ ስለመሆኑ በመሥፈርት አግባብ ባለው አካል ተመስክሮለት ከሌሎች የቡና ምርት ዓይነት በተሻለ ዋጋ የሚሸጥ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ለሽያጭ የሚቀርብበት ሥርዓትም በልዩ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጪ እንደሚካሄድ ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይም ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል፣ ዋነኛውም የልዩ ቡና የግብዓት ሒደትን የተመለከተ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የልዩ ቡና ምርትን ዱካና ባለቤት ማንነት የሚያረጋግጥ የገበያ ሥርዓት መዘርጋት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ከዚህም የገበያ ሥርዓት ዋነኛው ልዩ ቡናው ከተሽከርካሪ ሳይወርድ ግብይቱ እንዲከናወንና በቀጥታ እንዲላላ የሚያስችል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ምርቱን ለጫኑ ተሽከርካሪዎች ጥብቅ ማቆያ ሥፍራ ያዘጋጃል፡፡

በሌላ በኩል ቡና የማጓጓዝ አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉ ተሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ደረጃ እንደሚወጣባቸው በቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጅ ላይ ተካቷል፡፡

በተጨማሪም ቡና ከመጫኑ በፊት ቡናው በአዋጅ መሠረት ለመጓጓዝ የተዘጋጁና ሕጋዊ መሆኑን፣ እንዲሁም ቡና ጭኖ ሲጓዝ ብልሽት ያጋጠመው ወይም ወንጀል የተፈጸመበት እንደሆነ በአካባቢው ለሚገኝ ሥልጣን ላለው አካል ወዲያውኑ የማሳወቅ ግዴታን በአሽከርካሪው ላይ ወይም በባለቤቱ ላይ ይጥላል፡፡

ከመሸጫ ጣቢያ ሕጋዊ ቡና ጭኖ ወደ ተሸኘበት መዳረሻ ሳይደርስ ቡናው እንዲሰወር ወይም ሆን ብሎ መጠኑ እንዲቀንስ ወይም እንዲጨምር፣ እንዲሁም ጥራትና ዓይነቱ እንዲቀየር ያደረገ ማንኛውም አጓጓዥ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ፅኑ እስራትና ከ100 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር መቀጮ ይጣልበታል፡፡

ከተፈቀደለት ቡና ውጪ በተሽከርካሪው የትኛውም አካል ላይ ተጨማሪ ቡና ወይም ቡና ያልሆነ ሌላ ጭነት አዳብሎ የጫነ፣ በተጨማሪነት የተጫነው ጭነት እንደሚወረስና እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራትና ከ10 ሺሕ ብር እስከ 40 ሺሕ ብር  የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል፡፡    

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles