Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የመቐለና የኮምቦልቻን ጨምሮ ለአራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ 650 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉ ተገለጸ

$
0
0
  • 190 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው መቐለና ኮምቦልቻ ባለሀብቶችን ይጠብቃሉ

በሳምንቱ መጨረሻ ግንባታቸው ተጠናቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመረቁት የመቐለና የኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ የሐዋሳና የቦሌ ለሚ አንድ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት፣ እስካሁን 650 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ እንደተደረገባቸው ተገለጸ፡፡

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ እሑድ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ከመቐለ መሀል ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ በ75 ሔክታር መሬት ላይ ተገብንቶ መጠናቀቁን የሚዘክር ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በሥነ ሥርዓቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ለተገነባው ቦሌ ለሚ አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጣው 110 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኮምቦልቻ 90 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ ለአራቱ ፓርኮች ግንባታ ብቻ በጠቅላላው 650 ሚሊዮን ዶላር መንግሥት ማውጣቱን የጠቆሙ አቶ ሲሳይ፣ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

አቶ ሲሳይ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ75 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈና 15 የማምረቻ ሼዶች የተገነቡበት ነው፡፡ አምስት የውኃ ጉጓዶች የተቆፈሩለት የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ 30 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ ለ20 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡  

ይሁንና በሐዋሳ እንደተገኘው ባይሆንም እስካሁን ሦስት ዋና ዋና አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እንደሚገቡ ተጠቁሟል፡፡ ሚኒስትር አርከበ እንደገለጹት፣ በመቐለ ቬሎቺቲ የተባለው የዱባይ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያን ጨምሮ የኔዘርላንድስ ኩባንያ የሆነው ደች ብራንድ ማኔጅመንት (ዲቢኤም)፣ እንዲሁም ካልዜዶኒያ የተባለው የጣልያን አልባሳት አምራች ኩባንያ ዋና ዋናዎቹ ወደ ፓርኩ ሊገቡ እንደሚችሉ የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ቬሎቺቲ ቀደም ብሎ በመግባት በመቐለ ምርት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በትዕምት (ኤፈርት) ጥረት አማካይነትም ሌሎች ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ሊገቡ እንደሚችሉ ሚኒስትር አርከበ አስታውቀዋል፡፡

ሆኖም ሦስት ዋና ዋና ሥራዎች እንደሚቀሩ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በመጀመሪያው ሥራ ምርጥ ኢንቨስትመንቶች ከተለያዩ አገሮች መሳብና ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ለማድረግ የ15/85 (የ15 በመቶ የገንዘብ ወይም የዓይነት መዋጮ ለሚያቀርቡ የ85 በመቶ የባንክ ብድር መንግሥት ይሰጣል) የብድር አቅርቦት፣ እንዲሁም በአምስት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅና የውጭ ባለሙያዎችን የሚያካትት የሥልጠና ወጪዎች ድጋፍ ማድረግና ሌሎችም ድጋፎች ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀናጀና አንድ ወጥ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የመቐለ ከተማ በውኃና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደመገኘቷ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩም የእነዚህ አቅርቦቶች ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ወጣት ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እንዲገቡ የማድረግ ፈተና ይጠብቀናል ብለዋል፡፡ ከመቐለ  በተጨማሪ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ75 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈና የመቐለን ያህል ለ20 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የውጭ ኩንባዎችን መምጣት በጉጉት መጠባበቅ ግድ ሆኖበታል፡፡

 የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ያካሄደው የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ አንድ ሺሕ ሔክታር ድረስ እንደሚስፋፋ ተገልጿል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ማስፋፊያ ደሴን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎችን የሚያካትት የኢንቨስትመንት ኮሪደር ልማት ጥናት መሠረት እንደሚከወናወን ሚኒስትር አርከበ አስታውቀዋል፡፡ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክም በመጪው ዓመት ሚያዝያ ወር እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ 13 የማምረቻ ሕንፃዎች ግንባታ ተደርጎለት ለሥራ ዝግጁ ሆኗል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles