Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የኢንተርኮንቴኔንታል ሆቴል ባለቤት ፍርድ ቤቶች በሰጡት ትዕዛዝ ስላልተፈቱ በድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጠ

$
0
0
  • የተሰጣቸው አመክሮ እንዲነሳ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ የተፈረደባቸው የእስራት ቅጣት ከተጠናቀቀ በኋላ ከእስር እንዲፈቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጡ ቢሆንም፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ትዕዛዙን ተግባራዊ ባለማድረጉ ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከታክስና ከገቢ ግብር ጋር በተገናኘ አቶ ስማቸውንና ድርጅታቸውን ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥፋተኛ ብሎ፣ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በስድስት ዓመታት እስራትና ድርጅታቸው በ100 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ፍርድ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አቶ ስማቸው ከአራት ዓመታት በላይ በእስር ስለቆዩ የተፈረደባቸውን የእስራት ቅጣት ሁለት ሦስተኛውን በማጠናቀቃቸውና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 202(1ሀ እና ለ) ሥር የተደነገገውን በማሟላታቸው በማረሚያ ቤት በተደረገው ግምገማ ብቁ ሆነው መገኘታቸውን ማረሚያ ቤቱ ገልጾ፣ ሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ በትዕዛዙ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ፍርደኛው የእስር ጊዜያቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ማረሚያ ቤቱ በምስክርነት ካረጋገጠ በኋላ፣ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከእስር እንዲፈታቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ማረሚያ ቤቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝን ተግባራዊ ባለማድረጉ የአቶ ስማቸው ጠበቆች አቤቱታ በማቅረባቸው፣ ፍርድ ቤቱ በዘጋው መዝገብ ላይ እንደገና ተሰይሞ ሌላ ትዕዛዝ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. አስተላልፏል፡፡ የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በተሰየሙበት ችሎት፣ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከበረና ፍርደኛውን ከእስር ያልፈታበትን ምክንያት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ሌላ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀርበው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ያልፈጸሙበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ቀርበው እንዳስረዱት፣ አቶ ስማቸው በዚያው ችሎት ከሙስና ወንጀል ነፃ ከተባሉ በኋላ በብይኑ ደስተኛ ያልሆነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱና ለሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በመቅጠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን አቶ ስማቸው በሥር ፍርድ ቤት ነፃ የተባሉበት የሙስና ወንጀል፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋስትና ማስከልከል አለማስከልከሉን በሚመለከት ላቀረቡት ማመልከቻ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ሁለት ጊዜ ለማረሚያ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ይግባኝ የተባለባቸው ጉዳይ ከእስር እንዳይፈቱ እንደማይከለክላቸው ገልጾ ቢለቀቁ የማይቃወም መሆኑን መግለጹን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ገና እየመረመረው መሆኑን በመጥቀስ፣ የዓቃቤ ሕግን አስተያየት ሳይጠይቅ የተሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን በመግለጽ እንዲታረምለት ለሰበር ሰሚው ችሎት አቤቱታውን፣ በሙስና ወንጀሎች ዓቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መዝሙር ያሬድ ፊርማ አቅርቧል፡፡

ሰበር ችሎቱ የቀረበለትን አቤቱታ ተመልክቶ በሰጠው ትዕዛዝ አቶ ስማቸው የተከሰሱት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411 (1ሐ እና 2)ን በመተላለፍ ማለትም፣ ‹‹የመንግሥት ሥራ በማያመች አኳኃን መምራት፣ በጠቅላላው በሥራው ሥልጣን መሠረት በአደራ የተሰጠውን ወይም ሊጠብቀውና ሊከላከለው የሚገባውን የሕዝብ ወይም የመንግሥት ጥቅም የሚጎዳ ተግባር፣ በማንኛውም ዘዴ የፈጸመ እንደሆነ፤›› የሚለውን በመተላለፍ መሆኑን ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ማቅረቡን ጠቁሞ፣ መጣራት እንዳለበት ማመኑን በመግለጽ ያስቀርባል ብሏል፡፡

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎችም ይህንኑ በመግለጽ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ማረሚያ ቤት ለአቶ ስማቸው የሰጠው አመክሮ እንዲነሳለት መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ ዓቃቤ ሕግ የሥር ፍርድ ቤቶቹን ትዕዛዝ ተቃውሞ ለሰበር ሰሚው ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ‹‹ያስቀርባል›› ቢባልም፣ ፍርደኛው (አቶ ስማቸው) ከእስር እንዳይለቀቁ የሚከለክል እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለአቶ ስማቸው ማረሚያ ቤቱ የሰጠው የአመክሮ ጊዜ እንዲነሳለት የጠየቀ መሆኑን አስታውሶ፣ የተሰጣቸው አመክሮ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት መሆኑን በማስረዳት፣ ያቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ሰበር ሰሚው ችሎት እስከ ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. 11፡30 ሰዓት ድረስ አቶ ስማቸው እንዳይለቀቁ የሰጠውን ትዕዛዝ እንዲያቀርብ፣ ወይም አቶ ስማቸውን ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት በመፍታት ውጤቱን እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡        

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles