በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛው ማስተር ፕላን፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማስተር ፕላኑ ከመፅደቁ በፊት የወረዳ፣ የክፍላተ ከተማና ማዕከል የሚገኘው ዋናው ምክር ቤት ጋር በጋራ እንዲወያዩበት ማድረጉን ገልጿል፡፡
ታኅሳስ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው ውይይት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ወይም 25 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ማስተር ፕላን ይዘትና ይዟቸው የሚመጣቸው ተስፋዎች ላይ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ አስፋው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በ130 ዓመት ታሪኳ ዘጠኝ ማስተር ፕላን አስተናግዳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጠናቀቀው አሥረኛው ማስተር ፕላን ከሌሎች ዘጠኝ ማስተር ፕላኖች ጋር ሲነፃፀር በስፋትም በጥልቀትም የተለየ ነው ተብሏል፡፡
ዘጠነኛውና አሥረኛው ማስተር ፕላን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች፣ የተቀሩት ስምንት ማስተር ፕላኖች ደግሞ በውጭ አገር ባለሙያዎች የተዘጋጁ ናቸው፡፡
አቶ ማቴዎስ በዘጠነኛውና በአሥረኛው ማስተር ፕላን ዋነኛ ተዋናይና መሪ ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ የአሥረኛው ማስተር ዝግጅት በመጠናቀቁ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል፡፡
አዲሱ ፕላን ኮሚሽን ማስተር ፕላኑ በአግባብ መተግበሩን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
አቶ ማቴዎስ ቅዳሜ ታኅሳስ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት ቀጣዩ የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ዕድገትና የኢኮኖሚ እምርታ ሊያስተናግድ በሚችል ደረጃ፣ የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ መቀመጫ መሆኗን በሚገባ በምታረጋግጥበት መንገድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ወደ ጎን ስትለጠጥ ቆይታ ያላትንም 54 ሺሕ ሔክታር መሬት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ግንባታ ያካሄደችበት አዲስ አበባ፣ ‹‹በአዲሱ ማስተር ፕላን ወደ ጎን መለጠጧን አቁማ ወደ ላይ ከፍ ማለት ትጀምራለች፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት አራት ሚሊዮን በተጨማሪ፣ 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ አዲስ ነዋሪ ሆኖ እንደሚመዘገብና ይህ ሁሉ ሕዝብ በመሀል ከተማ እንደሚሰፍር አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ዕቅድ መሳካት መሃል ከተማው (ዞን አንድ) ውስጥ በርካታ ቤቶች የሚገነቡ ከመሆኑ በላይ፣ አራት ደረጃ በወጣላቸው ዞኖች ውስጥ ማንኛውም ባለሀብት የሚገነባው ሕንፃ መኖሪያ ቤቶችን ማካተት ይጠበቅበታል፡፡
አቶ ማቴዎስ እንዳሉት ከመንግሥት ተቋማት፣ ከደኅንነትና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከሆስፒታሎች፣ ከእምነት ተቋማት፣ ከሆቴሎችና ከትምህርት ቤቶች ግንባታ በስተቀር በሚካሄዱ ማናቸውም ሕንፃዎች መኖሪያ ቤቶችን ማካተታቸው የግድ ነው፡፡
በዞን አንድ 30 በመቶ፣ በዞን ሁለት 40 በመቶ፣ በዞን ሦስት 50 በመቶ፣ በዞን አራት 60 በመቶ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መካተት አለበት ተብሏል፡፡
‹‹በመሀል ከተማ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ የማስፈር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህን ልናደርግ የምንችለው ነባርና ያረጁ ግንባታዎችን አፍርሰን ነው፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ዞን አንድ ላይ ማለትም (ፒያሳ፣ ብሔራዊ፣ ሜክሲኮና ለገሃር አካባቢዎች) የሚገነቡ ሕንፃዎች በአንድ ሔክታር 150 ቤቶች መያዝ ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉም አቶ ማቴዎስ ቀጣዩን አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ሒደት ግን የአንድ መኖሪያ ቤት ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በተካሄደው ማሻሻያ አንድ መኖሪያ ቤት ዝቅተኛው የሚያርፍበት ቦታ 30 ካሬ ሜትር የነበረው፣ በአዲሱ ማስተር ፕላን 90 ካሬ ሜትር እንዲሆን ተደርጓል፡፡
‹‹በከፍተኛ ጥግግት አዲስ አበባን አየር ላይ ገንብተን ሕዝብ የተሸለ ኑሮ እንዲኖር እናደርጋለን፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡
አሁን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መሠረታዊ በሚባል ደረጃ ይቀይራል የተባለው ማስተር ፕላን በመሬት አጠቃቀም፣ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በአረንጓዴ ቦታዎች ልማት፣ በቅርስ አጠባበቅ፣ ወዘተ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ያለውን ዕቅድ ይዞ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ የጤና ተቋማትና የአፍሪካ ባህል ማዕከልን ለመገንባት ታቅዷል፡፡
በማሻሻያ ደረጃም ለከተማው ነዋሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታ በፈጠሩት በቀላል ባቡር መስመሮችና በቀለበት መንገድ ላይ ተጨማሪ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች ለመገንባት ታስቧል፡፡
በ1994 ዓ.ም ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በ2006 ዓ.ም የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል፡፡ አሥረኛው ማስተር ፕላን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር አቀናጅቶ ለማካሄድ በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በመቅረቡ እንዲቀር ተደርጓል፡፡
በዚህ ምክንያት ባለፉት አራት ዓመታት አዲስ አበባ ይፋ ማስተር ፕላን ሳይኖራት ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሥራዎቹ በመጠናቀቃቸው ለምክር ቤቱ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡