Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live

‹‹የኛ›› ፕሮጀክት ዕርዳታው የተቋረጠበት በፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን በእንግሊዝ የውስጥ ፖለቲካ ነው አለ

$
0
0

‹‹የኛ በተሻለና በላቀ ደረጃ ይቀጥላል›› ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ

የኛ ፕሮጀክት ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዲፊድ (DFID) ያገኝ የነበረው ድጋፍ የተቋረጠው በፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን፣ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት በመውጣቷ ምክንያት እየተንፀባረቀ ባለው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ተፅዕኖ ሳቢያ መሆኑን፣ የየኛ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡

አሁን ባለው የእንግሊዝ ፖለቲካ እንደ የኛ ያሉ ማብቃትንና ማስቻልን ዓላማ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ሳይሆን፣ እንደ አስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ያሉ የነፍስ አድን ድጋፎች ላይ ማተኮር ይመረጣል ብለዋል፡፡ ‹‹ከመነሻውም የኛ አስቻይ መሆኑን ተናግረናል፡፡ የኛ ተደብድባ ዓይኗ የጠፋ ሴት የምትገባበት መጠለያ እንዲኖር ሳይሆን፣ ዓይኔ አይጠፋም የምትል ሴት መፍጠር ነው፤›› በማለት ወ/ሮ ሰሎሜ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በወቅታዊው የፖለቲካ ተፅዕኖ የኛ ቀዳሚ ዒላማ እንደሆነ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

ዕርዳታ መስጠት የመቀነስና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የሚያደርገው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ በአውሮፓም በአሜሪካም እየተንፀባረቀ ቢሆንም፣ የኛ ያነገበውን ዓይነት ዓላማ ከሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነቱን እንደሚያጠናክር የገለጹት ወ/ሮ ሰሎሜ፣ የኛ በተሻለና በላቀ ደረጃ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ አብሯቸው ሊሠራ የሚችል ዓለም አቀፍ ተቋም መኖሩን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰሎሜ፣ የተቋሙን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ እስካሁን ከተቋሙ ባገኘው ድጋፍ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራትና ከዚያም በላይ እንደሚዘል ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ትልቁ ነገር በውጭ ዕርዳታ መንቀሳቀስ ሳይሆን በራስ አቅም መሥራት በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ፈንድ ማግኘትንም እንደ ሌላ አማራጭ እንደሚመለከቱት ጠቁመዋል፡፡ የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትንሹም ቢሆን እየታየ መሆን በዚህ ረገድ ተስፋ እንደሆነም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት (ዲፊድ) ለየኛ የሚሰጠውን ድጋፍ ማቋረጡ፣ በቀጣይ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመመሥረት የሚፈልገው አጋርነት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው እንደሆነ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የተነሳላቸው ወ/ሮ ሰሎሜ፣ ውሳኔው በዚህ ረገድ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለው እንደሚምኑ አስረድተዋል፡፡

የየኛ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል አየር ላይ ውለዋል፡፡ ዲፊድም በእነዚህ ጊዜያት በሠራቸው ዓመታዊ ግምገማዎች የኛ በእያንዳንዱ “A”  ማግኘቱን ወ/ሮ ሰሎሜ ገልጸዋል፡፡

የዲፊድ አጋር ገርል ኢፌክት (Girl Effect) ሲሆን፣ የኛ ደግሞ አንዱ የገርል ኢፌክት ፕሮግራም ነው፡፡ የዲፊድ የአሁኑ ውሳኔም ሙሉ በሙሉ የገርል ኢፌክትን በጀት ማቋረጥ ነው፡፡ ሪፖረተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ውሳኔ ድንገተኛ በመሆኑ ሊደረግ ይገባ እንደነበረው አጥኚ ቡድን መጥቶ ሁኔታውን ገምግሞ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይህም የፕሮግራሞቹን ሽግግር አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል፡፡

ዲፊድ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ይሰጥ ከነበረው ዕርዳታ ከፍተኛውን መቀነሱም ይታወሳል፡፡

የኛ በመባል የሚታወቀው ፕሮጀክት በገሃዱ ዓለም ውስጥ ታዳጊ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ማለትም ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጥቃትና የትምህርት ክልከላ በድራማና በሙዚቃ አማካይነት በሴቶች ልጆች ላይ የሚንፀባረቀው አመለካከት እንዲቀየርና ሴቶች ልጆችም ስለራሳቸው የነበራቸውን አስተሳሰብ ለመለወጥ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህም ሚሊዮኖች ዘንድ በመድረስ በአዎንታዊ ጎኑ መነጋገሪያ መሆን የቻለ ፕሮጀክት ነው፡፡    

Standard (Image)

በአንድ ሕፃን ላይ በተፈጸመ የሕክምና ስህተት ሳቢያ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ተፈረደ

$
0
0

ዮሐንስ ዘውዱ ዓይናለም የተባለ የአራት ዓመት ሕፃን ለቀዶ ሕክምና ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በየካቲት ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ገብቶ በተፈጠረ የሰመመን መድኃኒት አሰጣጥ ስህተት (ቸልተኝነት) ምክንያት፣ የአካል መጉደል እንዲደርስበት ማድረጋቸው የተረጋገጠባቸው ሆስፒታሉና የሕክምና ባለሙያው ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው፡፡

የሕፃን ዮሐንስ ዘውዱ ወላጆች አቶ ዘውዱ ዓይናለምና ወ/ሮ ጥሩወርቅ ገብረ መስቀል፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት የክስ አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ ልጃቸው የተወለደው ሐምሌ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ሕፃኑ ሲወለድ የሽንት መሽኛው ቀዳዳ በተፈጥሮ ሊገኝ የሚገባው ቦታ ላይ አልነበረም፡፡

በመሆኑም ከታኅሳስ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ የሽንት መሽኛ ቀዳዳውን በትክክለኛ ቦታ ለመመለስ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና ክፍል መግባቱን የክስ አቤቱታው ያስረዳል፡፡

የሕፃን ዮሐንስ ቀዶ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን በቅድሚያ የሰመመን መድኃኒት የ76 ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት የሕክምና ባለሙያ አቶ ዘውዱ ዳምጤ ከወጉት በኋላ፣ የመተንፈሻ ቱቦ በአየር ቧንቧ የመተንፈሻ አካሉ ውስጥ ለማስገባት ጥረት ሲደረግ በተፈጠረ የሕክምና ስህተት፣ የሕፃኑ አንጎል በቂ ኦክስጂን ማግኘት ባለመቻሉ ቀዶ ሕክምናው ሳይደረግ መቋረጡን ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የክስ አቤቱታ ይገልጻል፡፡

በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የገጠመው ችግር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳካት በሪፈራል የተላለፈው ሕፃን ዮሐንስ፣ ለ27 ቀናት በፅኑ ሕሙማን ክፍል እንዲቆይ ተደርጎ ከወጣ በኋላ፣ በሆስፒታሉ ሕፃናት ክፍል ለ14 ቀናት ቆይቶ እንዲወጣ መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡

የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ፈቃድ የሌላቸውንና መስማት የማይችሉ የሕክምና ባለሙያ እንዲሠሩ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ መቆጣጠሪያ የሌለው ኦክስጂን ለሕፃኑ እንዲሰጥ ማድረጉንም የሕፃኑ ወላጆች በክስ አቤቱታቸው አመልክተዋል፡፡

የመስማት ችግር ያለባቸው የ76 ዓመት የሕክምና ባለሙያ ያለረዳት ማደንዘዢያ በመስጠታቸው፣ ልጃቸው የኦክስጂን እጥረት ሲገጥመው በወቅቱ አፋጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው የከፋ ጉዳት ላይ ሊደርስ መቻሉንም ወላጆቹ ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉን ባለሙያው በፈጸሙት የሕክምና ግድፈት (ቸልተኝነት) በልጃቸው ላይ ከባድ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸውም ወላጆቹ አክለዋል፡፡

ሕፃኑ በተፈጠረበት የሕክምና ግድፈት ሁለት ዓይኖቹ እንደማያዩና ጆሮው መስማት እንደተሳነው፣ እጆቹና እግሮቹ ፓራላይዝድ በመሆናቸው መቆምና መቀመጥ እንደማይችል፣ የነርቭና የሚጥል ሕመም እንደያዘውና ሽንቱንም ሆነ ዓይነ ምድሩን መቆጣጠር እንደማይችል ወላጆቹ በዝርዝር በክስ አቤቱታቸው ላይ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ወላጆቹ በልጃቸው ላይ በደረሰው ከባድ ጉዳት ለሕክምናና ተያያዥ ችግሮች ከአቅማቸው በላይ መሆናቸውን አስረድተው፣ ፍርድ ቤቱ ተገቢ ካሳ ማለትም 5.6 ሚሊዮን ብር እንዲያስከፍላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ሆስፒታሉ የክስ ማስረጃ ደርሶት በሰጠው መልስ ሕፃኑ ለቀዶ ሕክምና መግባቱን አረጋግጦ፣ የደረሰበት ችግር የመተንፈሻው ቱቦ ወደ ውስጥ አለመግባት የሕፃኑ የተፈጥሮ ችግር እንጂ የባለሙያ ስህተት አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ የሕክምና ባለሙያውም ከ60 ዓመታት በላይ ያለምንም ስህተት ሲሠሩ የኖሩ ባለሙያ መሆናቸውንና ከተለያዩ ተቋማት የሙያ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያገኙ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን የምስክር ወረቀቶቻቸውን፣ የምግብ፣ ጤና ክብካቤና አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የሰረዘባቸው ቢሆንም ቀደም ብሎ የተሰጣቸው የሙያ ፈቃድ ግን እንደነበራቸው አክሏል፡፡

የሕክምና ባለሙያውም በሰጡት ምላሽ ሕፃኑ በተፈጥሮ የሽንት መሽኛ አካሉ ቀዳዳ ሊገኝ በሚገባው ቦታ አለመኖሩ፣ ሕፃኑ በትክክል የሰው አካል ቅርፅ ይዞ ያልተወለደና ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ባለሙያው ከ60 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው ገልጾ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፣ ባለሙያው ግን ከ40 ዓመታት በላይ የአገልግሎት ዘመን እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ አብረዋቸው የሠሩ ባለሙያዎች የምስክርና የምሥጋና ወረቀቶች የሰጡዋቸው ምሥጉን ሠራተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የመስማትና ማዳመጥ ችሎታም እንዳላቸውና ስላለመስማታቸው ማስረጃም እንዳልቀረበባቸው ገልጸዋል፡፡  

ተከሳሾቹ ዘርዘር ያለ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል መስማቱንም ገልጿል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የመተንፈሻ አካል ውስጥ የመተንፈሻ ቱቦ የማስገባት ችግር የተከሰተው በሕፃኑ የተፈጥሮ ችግር ነው? ወይስ የሕክምና አሰጣጥ ስህተት? በሕክምና ስህተት ነው ከተባለ ንፁህ አየር ማጣት የሚጥል በሽታን ያስከትላል? ወይስ አያስከትልም? ተከሳሾቹ ኃላፊነት አለባቸው? ወይስ የለባቸውም? አለባቸው ከተባለ ምን ያህል የጉዳት ካሳ ሊከፈል ይችላል የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን በውሳኔው መዝገብ ላይ አስፍሯል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሁሉንም የክርክርና የማስረጃዎችን ከተገቢው ሕግ ጋር በማገናዘብ ከመረመረ በኋላ፣ በሕፃኑ ላይ የተከሰቱ በሽታዎችና ችግሮች በተፈጥሮ የመጡ ሳይሆኑ፣ በሆስፒታሉና በሕክምና ባለሙያው ስህተት መሆኑን በማረጋገጥ፣ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች 3,002,452 ብር ካሳ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ድርጊቱ የወንጀል ኃላፊነትንም ስለሚያስከትል በወንጀል ተከሰው ጉዳዩ በሒደት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

 

 

Standard (Image)

በጋምቤላ በሕገወጥ የመሬት ግብይት የተጠረጠሩ 13 ግሰለቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

$
0
0

በጋምቤላ ክልል በሕገወጥ የመሬት ግብይትና በመሬት ዘርፍ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ከተባሉ 21 ተጠርጣሪዎች ውስጥ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

የጋምቤላ ክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 13 ተጠርጣሪዎች ከጋምቤላ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦንጋ ከተማ በሚገኝ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

‹‹የተቀሩትን ስምንት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፀጥታ ኃይል ተሰማርቷል፤›› ሲሉ አቶ ኡቶው ገልጸዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አራቱ በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ የጋምቤላ የመሬት አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ፣ የአቦቦ ወረዳ ምክትል አስተዳደርን ጨምሮ አመራሮችና ባለሙያዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በመሬት ድለላ፣ በሕገወጥ የመሬት ግብይትና በብልሹ አሠራር ተጠርጥረው መሆኑን አቶ ኡቶው ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የበላይነት በጋምቤላ ክልል በሚገኙ አኙዋ፣ ኑዌርና ማጃንግ ዞኖችና በሥራቸው በሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና አንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ 623 ባለሀብቶች ላይ በተካሄደ ጥናት፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ለተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ዋናው ባለቤት የክልሉ አመራር መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሕገወጥ ደላሎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈጥሩት አሻጥር በክልሉ ግብርና ኢንቨስትመንት ቀውስ መፍጠሩ ተገልጿል፡፡

ይህ ጥናት በቀረበበት ወቅትም የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት፣ ችግር የተፈጠረው በክልሉ አመራር ድክመት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ለጋምቤላ ክልል ግብርና ኢንቨስትመንት የተወሳሰበ ችግርን ከፈጠሩ ሁኔታዎች መካከል ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖሩና የሚሰጡ አገልግሎቶች በግለሰቦች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን ተጠቃሽ ነው፡፡ የአንዱን ባለሀብት ይዞታ ለሌላ መሰጠት፣ የሕግ የበላይነት አለመኖር፣ የፍትሕ አካላት አድሎአዊ አሠራር፣ የተጠያቂነት ሥርዓት አለመኖር ከሚጠቀሱ ተጨማሪ ምክንያቶች ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከፈቃድ አሰጣጥ እስከ መሬት ማስተላለፍ ድረስ የሚሰጡ አገልግሎቶች በጉቦ የሚከናወኑ መሆናቸውና የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ በደላላ የተተበተበ መሆኑም ተጨማሪ ችግር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ባለሀብቱ በግሉ ወይም በደላላ ጥቆማ መሠረት መሬት ሲያቀርብ ይተላለፍለታል፤›› የሚለው ይህ ጥናት፣ በአንድ ውል ለሁለትና ለሦስት ባለሀብቶች አንድ መሬት ሲሰጥ መቆየቱንና ይህም አሠራር በክልሉ ለተፈጠረው ችግር ምክንያት እንደሆነም ይደመድማል፡፡

ይህ አሠራር የክልሉን የግብርና መሬት አስተዳደር ውስብስብና ለሙስና ተጋላጭ ያደረገው መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉትና በመፈለግ ላይ ያሉት ተጠርጣሪዎች ከእነዚህ ችግሮች ጀርባ እጃቸው አለበት የተባሉ ናቸው፡፡ 

Standard (Image)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል በ26 ቢሊዮን ብር የሚያሳድግ የቦንድ ሽያጭ ሕግ ሊወጣ ነው

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የተከፈለ ካፒታል ወደ 40 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ፣ የ26.5 ቢሊዮን ብር የመንግሥት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) ሽያጭ እንዲጀመር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

የመንግሥት ዕዳ ሰነድ አዋጅ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ረቂቅ ሰነዱ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ያለውን 13.5 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ 40 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡

በመሆኑም የባንኩን ካፒታል ወደተጠቀሰው ደረጃ ከፍ ለማድረግ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር 26.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግሥት ዕዳ ሰነድ እንዲያወጣ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡

የተጠቀሰው የዕዳ ሰነድ ለሽያጭ የሚቀርብ ቢሆንም ወለድ እንደሚያስፈልገውና የአምስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ፣ በ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል፡፡

ከረቂቅ አዋጁ ጋር አባሪ የተደረገው ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ የባንኩ ዕዳ (ተቀማጭ ገንዘብና የመሳሰሉት) በከፍተኛ ደረጃ ያደገ ቢሆንም በተነፃፃሪ ግን ካፒታሉ በተመጣጣኝ አላደገም፡፡

የባንኩ ዕዳ መጨመር ማለትም ተቀማጭ ሒሳብ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2015 ወደ 241.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከሕጋዊ መጠባበቂያ (Legal Reserve) ጋር ሲተያይ 4.4 በመቶ እንደሆነና በእጅጉ ያልተመጣጠነ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

በተጨማሪም እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ በነበሩ አምስት ዓመታት የባንኩ ብድር ከካፒታል ጋር ያለው ንፅፅር ከ409 በመቶ ወደ 837 መቶ ማደጉን ሰነዱ ያብራራል፡፡ በዚህ ላይ የዕዳ ሰነዶች ከተጨመሩ ደግሞ ንፅፅሩ እጅግ በጣም አድጎ እ.ኤ.አ. በ2009 በነበረበት 913 በመቶ ምጣኔ በ2015 ሰኔ ወር ላይ ወደ 2,016 በመቶ ምጣኔ እንደደረሰ በየደረጃው ያሳያል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የባንኩ የሀብት ተመላሽ ንፅፅር 96 በመቶ መድረሱን፣ ይህም ከአገር አቀፍም ሆነ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል፡፡

ለዚህ ያልተለመደ የሀብት ተመላሽ ንፅፅር መጨመር ምክንያቱ የባንኩ ካፒታል ዝቅተኛ መሆን ሊሆን እንደሚችልም ያመለክታል፡፡ ይህም ማለት የባንኩ ሀብትና ከባንኩ የዕዳና ንብረት ማሳያ (Balance Sheet) ውጪ የሚታዩ ባንኩ ሊከፍላቸው የሚገቡ ግዴታዎች፣ በባንኩ ተመጣጣኝ የካፒታል ዕድገት ያልተደገፉ መሆናቸውን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ብድሮችና የዕዳ ሰነዶች ከአጠቃላይ ተቀማጭ ጋር ያላቸው ንፅፅር እ.ኤ.አ. በ2015 ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ 114 በመቶ እንደደረሰም ይገልጻል፡፡

በመሆኑም የካፒታል ጭማሪ የባንኩን የካፒታልና የጠቅላላ ንብረት ንፅፅር ምጣኔ የሚያሳድገው መሆኑን፣ እንዲሁም የባንኩ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት የውጭ ባንኮች ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ሰነዱ ያስረዳል፡፡

የባንኩ ካፒታል በ26.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበው የመንግሥት የዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከፈለ ካፒታል ገንዘብ ፈሰስ ሳይደረግ በ26.5 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሎ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡   

Standard (Image)

​‹‹ከፍተኛ አመራሩ ተጠያቂ ያልሆነው ማስረጃ ስለሌለ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

$
0
0

-  ማስረጃ ከተገኘ የትኛውንም አመራር አንተውም ብለዋል

-  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት የሚያጣድፍ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መደበኛውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ ሁለት ዓመት ገደማ ሆኖታል፡፡ ባለፈው ሰኞ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. የግሉን ፕሬስ ጨምሮ ለውጭ ጋዜጠኞች በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉት መካከል የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋልና አለመጠየቅ፣ በአጥፊዎች ላይም ዕርምጃ ሲወሰድ የላይኛውና የታችኛው አመራር ቢባልም ዝቅተኛውና መካከለኛ አመራሩ ብቻ እንደሚጠየቅ፣ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅምን በተመለከተና በወልቃይት የወሰን ጥያቄ ምላሽ አሰጣጥ፣ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ መነሳትን በተመለከተ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞቹ ለቀረቡት ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡

Standard (Image)

በበርሃሌ በ331 ሚሊዮን ብር የጨው ፋብሪካ ሊገነባ ነው

$
0
0

ደናክል ኢንዱስትሪያል የተሰኘ አገር በቀል ኩባንያ፣ በ331 ሚሊዮን ብር ወጪ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአፋር ብሔራዊ ክልል በርሃሌ ከተማ ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

ደናክል ኢንዱስትሪያልን ያቋቋመው ቲቲኬ ኢንዱስትሪያል የተባለ በገላን ኢንዱስትሪያል ዞን የዲተርጀንት ፋብሪካ ባለቤት ነው፡፡ የደናክል ኢንዱስትሪያልና ቲቲኬ ኩባንያ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ደናክል ኢንዱስትሪያል በበርሃሌ ከተማ የሚገነባው የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የኢንዱስትሪ ግብዓት የከብቶች መኖ ለገበታ የሚሆን ጨው ያመርታል፡፡ በበርሃሌ ወረዳ ከፍተኛ የአሞሌ ጨው ክምችት የሚገኝ ሲሆን፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ በባህላዊ መንገድ ለዘመናት ሲያመርት ኖሯል፡፡

አቶ ሳሙኤል እንደተናገሩት ፋብሪካው የአካባቢው ማኅበረሰብ ሃመዴላ በተባለ አካባቢ የሚያመርተውን ጥሬ የአሞሌ ጨው በማነቀባበር፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ ፋብሪካው በወር 500,000 ኩንታል ጨው የማምረት አቅም እንደሚኖረው ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ የኢንዱስትሪ ግብዓት፣ 20 በመቶ የእንስሳት መኖ፣ 50 በመቶ የገበታ ጨው ነው፡፡

ፋብሪካው የሚገነባው ከአዲስ አበባ 890 ኪሎ ሜትር ሰሜን ምሥራቅ ርቃ በምትገኘው በርሃሌ ከተማ ሲሆን፣ ደናክል ኢንዱስትሪያል ከከተማዋ መስተዳድር 20,000 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል፡፡ የፋብሪካው የተለያዩ ዘመናዊ የጨው ማቀነባበሪያ ማሽኖች ከህንድና ከስፔን ለመግዛት ከአቅራቢዎቹ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ በአገር በቀል ኮንስትራክሽን ኩባንያ እንደሚካሄድና የማሽን ተከላው ሥራ በማሽን አቅራቢዎቹ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ የመሬት ማስተካከል ሥራ ከሁለት ሳምንት በኋላ ተጀምሮ፣ ግንባታው በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ምርት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

ደናክል ኢንዱስትሪያል ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ጨው ለአገር ውስጥ ቆዳ ኢንዱስትሪ፣ ለዲተርጀንትና ለኬሚካል ፋብሪካዎች እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ‹‹በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማራን በመሆኑ በአገር ውስጥ የኢንዱስትሪያል ጨው እጥረት እንዳለ እናውቃለን፡፡ በገላን ኢንዱስትሪያል ዞን የዲተርጀንት ማምረቻ አለን፡፡ ለፋብሪካችን የኢንዱስትሪ ጨው በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያለውን ችግር ስለምናውቅ ለምን ራሳችን አናመርትም ብለን ነው የተነሳነው፤›› ብለዋል አቶ ሳሙኤል፡፡

ደናክል ኢንዱስትሪያል ለእንስሳት መኖ የሚሆነውን ጨው በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለማቅረብ አቅዷል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የገበታ ጨው በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

‹‹መጀመሪያ የአገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት ካሟላን በኋላ ወደ ውጭ መላክ እንጀምራለን፡፡ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ጨው በተመሳሳይ የአገር ውስጥ ፍላጎት ካማሏን በኋላ ለውጭ ገበያ እናቀርባለን፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ የፋብሪካውን ምርቶች ተረክቦ ለውጭ ገበያ እንዲያከፋፍል ሊጎ ኢንተርናሽናል ከተባለ የዱባይ ኩባንያ ጋር መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

በማዕድን ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኬሚካል ሶሳይቲ የተሠራ ጥናት በደናክል ዝቅተኛ ቦታ 1,200 ካሬ ሜትር መሬት በጨው የተሸፈነ እንደሆነ ያሳያል፡፡ የአሞሌ ጨው ክምችቱ አንድ ቢሊዮን ቶን እንደሚገመት፣ ይህም ከዓለም ትልቁ የጨው ክምችት እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ጥናቱ የአሞሌው ጨው ጥራት ያለው መሆኑን ገልጾ፣ ለምግብነት ለማዋል ግን በፋብሪካ ሊቀነባበር እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡

የጨው ክምችቱ በዝርዝር ተጠንቶ ባለሀብቶች በዘመናዊ የጨው ማምረት ዘርፍ እንዲሰማሩ አስፈላጊው የማስተዋወቅ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ ጥናቱ ያሳስባል፡፡ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የጨው ክምችት በአገር ውስጥ እያለ አገሪቱ አሁንም ጨው በውጭ ምንዛሪ የምታስገባ በመሆኑ፣ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ሊበረታቱ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡

አቶ ሳሙኤል የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ሙቀት ባለው በረሃ የእጅ መሣሪያዎችን በመጠቀም አነስተኛ መጠን ያለው አሞሌ ጨው እንደሚያመርት፣ የሚያገኘውም ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሙቀቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ በመሆኑ በዓመት የተወሰኑ ወራት ነው ማምረት የሚችሉት፡፡ በገንዘብ ብዙ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በከፍተኛ ስቃይ ያመረቱትን አሞሌ ጨው በግመል ጭነው በዚያ ከፍተኛ ሙቀት ከሃመዴላ በርሃሌ ድረስ 60 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ይጓዛሉ፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ደናክል ኢንዱስትሪያል በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ሥልጠና እንደሚሰጥ፣ ማሽነሪዎችንና የትራንስፖርት አገልግሎትን ለአካባቢው ኅብረተሰብ በማቅረብ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ደናክል ኢንዱስትሪያል የሚገነባው የጨው ፋብሪካ ለ250 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ከዚህ በላይ ግን ለአካባቢው ጨው አምራቾች ሰፊ ገበያ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብና ሽማግሌዎች ጋር ለረጅም ጊዜ መወያየታቸውንና ኅብረተሰቡም ኢንቨስትመንቱን መቀበሉን፣ ሦስት የጨው አምራች ማኅበራት ለፋብሪካው አሞሌ ጨው ለማቅረብ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፋብሪካችን በጣም በተሻለ ዋጋ አሞሌ ጨውን ከአምራች ማኅበራት ይገዛል፡፡ በማሽነሪና በትራንስፖርትም እገዛ እናደርግላቸዋለን፤›› ብለዋል አቶ ሳሙኤል፡፡

የአፋር ክልል መንግሥት ለኩባንያቸው ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካው ምርት ከጀመረ በቀጣይ የጨው ከረጢት ፋብሪካ ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡ ማዳበሪያው ለራሱ ለደናክል ፋብሪካና በክልሉ ለሚገኙ ሌሎች ጨው አምራቾች እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

የደናክል ኢንዱስትሪያል እህት ኩባንያ የሆነው ቲቲኬ ከስድስት ዓመት በፊት በ35 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ በገላን ኢንዱስትሪ ዞን ሳሙና፣ ሻምፑና ሌሎች የፅዳት ኬሚካሎች በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ኩባንያው ካፒታሉን ወደ 120 ሚሊዮን ብር በማሳደግ በቅርቡ ለሳሙናና ሻምፑ ማሸጊያ የሚውል ፕላስቲክ ማምረቻ ገንብቶ የሙከራ ምርት ጀምሯል፡፡

‹‹ቀጣዩ የመንግሥት የልማት አቅጣጫ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ እኛም ኢንቨስት ማድረግ የምንፈልገው በዚሁ ዘርፍ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ጥረታችንን ተመልክቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገልን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

የግብፅ መንግሥት ዜጎቹ ከኢትዮጵያ መለቀቃቸውን አወደሰ

$
0
0

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ለወራት አስሯቸው የነበሩትን ሦስት ግብፃውያንን ከለቀቀ በኋላ፣ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዕርምጃውን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ስኬት ነው በማለት አወደሱ፡፡

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ሁከት በተከሰተበት ወቅት ሦስቱ ግብፃውያን በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን፣ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ግብፃውያኑ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ማግሥት በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ችሎት ቀርበው እንደነበር፣ የግል ጠበቃም መቅጠራቸውን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

ነገር ግን ክስ ሳይመሠረትባቸው የግብፅ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ፣ በስለላ ሥራ ተሠማርተዋል የተባሉት ሦስቱም ተጠርጣሪዎች ከሦስት ወራት በኋላ ተለቀዋል፡፡

‹‹የዜጎቻችን መለቀቅ የሁለቱ ወዳጅ አገሮች ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ውጤት ነው፤›› ሲሉ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ከእስር የተለቀቁት ሦስቱ ግብፃውያን ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ካይሮ አቅንተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ ተለቀቁ የተባሉት ግብፃውያን በኢትዮጵያ የሚገነቡ ሆቴሎችን ያስተዳድሩ እንደነበር ግን ታውቋል፡፡    

በኢትዮጵያ ተቀስቅሶ ከነበረው አመፅ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ መንግሥት በዝርዝር ያልገለጻቸው የተለያዩ የግብፅ ተቋማት አመፁን ለማባባስ፣ ለኢትዮጵያ ፀረ ሰላም ኃይሎች ድጋፍ ሲሰጡ ነበር ማለቱ ይታወሳል፡፡

ይህንንም በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሹን እንዲሰጥ መጠየቁን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ የግብፅ መንግሥት በበኩሉ ለማንኛውም የኢትዮጵያ አማፂ ቡድን ምንም ዓይነት ዕርዳታ አለማድረጉም መግለጹ አይዘነጋም፡፡ 

Standard (Image)

ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክን ከ276.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝበር የተጠረጠሩ ኃላፊዎች ታሰሩ

$
0
0

  በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የፋይናንስ የሥራ ሒደት ዳይሬክተርና የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር የሥራ ሒደት ዳይሬክተር፣ ባንኩን ከ276.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝበር ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

          ተጠርጣሪዎቹ የባንኩ ኃላፊዎች አቶ ሳሙኤል ግርማ ደሴና አቶ በለጠ ዋቅቤካ ሂርጳ ናቸው፡፡ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው በባንኩ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ላይ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በቅርንጫፉ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት በቅርንጫፉ ‹አካውንት ሪሲቨብል›፣ ‹ኤክስፖርት ሴትልመንት አካውንት› የሚባል ሒሳብ ከባንኩ ዕውቅና ውጪ በመክፈትና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ 276,675,572 ብር ባንኩ እንዲመዘበር ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመራቸው እንደሚገኝ ፖሊስ በማስረዳት፣ የወንጀል አፈጻጸሙ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

 

 

Standard (Image)

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ብሔራዊ ባንክንና የፋይናንስ ድርጅቶችን ከሰሱ

$
0
0

 

- አክሲዮኖቻቸው ባሉበት እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ዕግድ ሰጥቷል

በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንግድ ባንኮችም ሆነ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የአክሲዮኖች ባለቤት መሆን እንደማይችሉ በወጣው መመርያ ምክንያት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷብሔራዊ ባንክን፣ ኅብረት ባንክንና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያን ከሰሱ፡፡

በካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆኑትና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሪት ሶፊያ በቀለ በጠበቃቸው አቶ ዮሴፍ ኪሮስ አማካይነት ብሔራዊ ባንክን፣ ኅብረት ባንክንና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ከሰዋል፡፡

ግለሰቧ ብሔራዊ ባንክን የከሰሱት ባወጣው መመርያ ኅብረት ባንክና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ያላቸውን አክሲዮን እንዲመልሱ፣ ካልመለሱ ግን መንግሥት እንደሚወርሰው በመግለጽ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ማድረጉን በመቃወም ነው፡፡

ከሳሽ የኅብረት ኢንሹራንስ መሥራች የነበሩት አባታቸው እያንዳንዳቸው 1,000 ዋጋ ያላቸው 288 አክሲዮኖችንና እንዲሁም ከኅብረት ባንክ (መሥራች ናቸው) 4,066 አክሲዮኖችን በውርስ እንደተላለፈላቸው በክሳቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ የአክሲዮኖቹን ድርሻ ያገኙት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካላቸው አባታቸው መሆኑን የገለጹት ከሳሽ፣ ማንኛውም ሰው በስሙ ተመዝግቦ የሚገኝን ንብረት የመጠቀምና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ለፈለገው ሰው ያለክፍያና ያለምንም ገደብ የማስተላለፍ መብት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) እና በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1205(2) መደንገጉንም አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን መሠረታዊ መብት የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መመርያው ከመውጣቱ በፊት በውርስና በተለያዩ መንገዶች የተላለፉና በከሳሽ ስም የተዘዋወሩ አክሲዮኖች ወደ ኋላ ተመልሰው ሊፈጸሙ እንደማይገባቸውም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘው የአክሲዮን ድርሻ ላይ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም እንዲባልላቸው፣ በጠበቃቸው በኩል ክሳቸውን አቅርበዋል፡፡ በሕግ የተከበሩላቸውን አክሲዮኖች ለፈለጉት ሰው የማስተላለፍ መብታቸውን ተጠቅመው፣ አክሲዮኖቻቸውን ማስተላለፍ እንዲችሉ እንዲወሰንላቸውም አመልክተዋል፡፡

ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ብሔራዊ ባንክ፣ ኅብረት ባንክና ኅብረት ኢንሹራንስ መልስ እንዲሰጡና በከሳሽ ስም የሚታወቁ አክሲዮኖች ባሉበት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ክስ ለመስማት ለየካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

በርካታ ባለድርሻዎች በተለያዩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ክስ መመሥረታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

ግሎባል ፈንድ በኢትዮጵያ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

$
0
0

ግሎባል ፈንድ በመባል የሚታወቀው ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ድርጅት ሀብትን በሚገባ ለመጠቀም፣ ግሎባል ፈንድና እሱ የሚወክላቸው የሥራ ኃላፊው በነፃነት በኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ስምምነት ለማፅደቅ ሲሆን፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ ከሚጥላቸው ግዴታዎች መካከል ግሎባል ፈንድ የሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ማናቸውም ዕቃዎችን፣ መንግሥት ከማንኛውም ዓይነት ግብር ክፍያ ነፃ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል የግሎባል ፈንድ ሀብትና ንብረት የሆኑ ቁሳቁሶች በየትኛውም ቦታ በማንም ቢያዙ ድርጅቱ ያለውን በሕግ የመጠየቅ ከለላ ካላነሳ በስተቀር በሕግ ሒደት ከመያዝ ነፃ እንደሚሆኑ፣ እንዲሁም በየትኛውም ሥፍራ የሚገኙ የተቋሙ ንብረቶች ከመፈተሽና ከመወረስ ከለላ ይኖራቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በግሎባል ፈንድ ውስጥ የሚሠሩ የአባል አገሮች ተወካዮች በሥራ ወቅትና በጉዞ፣ እንዲሁም ጉባዔ በሚደረግበት ጊዜ ለስብሰባ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ ከመያዝና ከመታሰር የመጠበቅ መብት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም በሥራ ምክንያት የሚጠቀሙባቸው ንብረቶች እንዳይያዙና እንዳይበረበሩ፣ ሰነዶችና ደብዳቤዎችን በታሸገ ቦርሳ መቀበል እንዲችሉ፣ ሥራቸው ካበቃም በኋላ ቢሆን በሥራ ላይ እያሉ ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ላደረጓቸው ንግግሮችና ለጻፏቸው ጽሑፎች ከሕግ ተጠያቂነት ነፃ እንደሚሆኑ ይገልጻል፡፡ እንዲሁም በዚህ ምክንያት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ሊከለከሉ እንደማይችል ይገልጻል፡፡

የስምምነቱ መፅደቅ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ እያበረከተ ከሚገኘው አስተዋጽኦ አንፃር ከድርጅቱ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራትና መልካም ግንኙነት ለመፍጠር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር፣ ከረቂቅ አዋጁ ጋር የተያያዘው ሰነድ ይገልጻል፡፡

የረቂቁ የእንግሊዝኛ ቅጂ እንደሚገልጸው ደግሞ ግሎባል ፈንድ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ምንዛሪ፣ ወርቅና ፈንዶችን መያዝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በየትኛውም አገር ውስጥ ያለውን የውጭ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ፣ ወይም በኢትዮጵያ ገንዘብ የመቀየር መብት እንደሚኖረው ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ሙሉ በሙሉ የተቀበለች ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሕጎች መሠረት እንደሚሆን በመግለጽ ተአቅቦ አድርጋለች፡፡ ፓርላማው ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

 

Standard (Image)

የኢትዮ ቴሌኮምና የንግድ ባንክ ኃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ

$
0
0

በኢትዮ ቴሌኮም ሶርሲንግና ፋሲሊቲ ዲቪዥን ኃላፊና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም በተጠቀሰው ኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት አቶ አብርሃም ጓዴ ወርቁ የተጠረጠሩት፣ ከከረዩ ቱር ኤንድ ትራቭል ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር፣ ተቋሙ ከገባበት ውልና ስምምነት ውጪ በመሥራት በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ በማድረሳቸው መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣  ኢትዮ ቴሌኮም የሥሪት ዘመናቸው እ.ኤ.አ. ከ2000 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን እንዲያቀርብ፣ ከከረዩ ትራቭል ኤንድ ቱር ጋር ተዋውሏል፡፡ ነገር ግን የቀረቡት 69 ተሽከርካሪዎች የሥሪት ዘመናቸው እ.ኤ.አ. ከ2000 በታች ነው፡፡

አቶ አብርሃም ግን ተሽከርካሪዎቹ በተደረገላቸው የቴክኒክ ምርመራ እ.ኤ.አ. ከ2000 በላይ ናቸው ተብሎ በተዘጋጀላቸው ሐሰተኛ ሊብሬ ላይ ፈርመው ማሳለፋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር በመሆኑ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቁሞ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ቢጠየቅባቸውም፣ ፍርድ ቤቱ ግን አምስት ቀናት ብቻ ፈቅዶ ለጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሌላው በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ሲሆኑ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል በባንኩ ዕቃ አቅርቦትና አስተዳደር ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ ከዕቃ ግዢ ጋር በተገናኘ በመንግሥት ላይ ከ6.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳትና ኪሳራ አድርሰዋል የሚል ነው፡፡

አቶ ኤፍሬም እ.ኤ.አ. በ2012/2013 በጀት ዓመት ለግዢ አፅዳቂ ኮሚቴ 500,000 ማርከር እንዲገዛ ከማቅረባቸው በፊት፣ ከቀደምት አቅርቦት ጋር በተገናዘበ መንገድ እንዲገዛ አለማድረጋቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ አቶ ኤፍሬም በራሳቸው ውሳኔ ለግዢ ኮሚቴው አቅርበው ተገቢ ያልሆነ ግዢ በመፈጸም፣ በባንኩ ላይ የ6,962,090 ብር ጉዳትና ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረጋቸውን ፖሊስ አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡

አቶ ኤፍሬም ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለና ግዢውንም ያዘዙት ከኃላፊዎቻቸው በተሰጣቸው አቅጣጫ መሆኑን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን በማለፍ የተጠየቀውን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

Standard (Image)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አላና ፖታሽን በታክስ ማጭበርበር ወነጀሉ

$
0
0

-  አላና ፖታሽ ግን በሰላማዊ መንገድ ችግሩን እንፍታ ብሏል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አላና ፖታሽ የተሰኘውን በአፋር ክልል በፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ተሰማርቶ የነበረውን የካናዳ ኩባንያ በታክስ ማጭበርበር ወነጀሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አላና ፖታሽ የኢትዮጵያ መንግሥትንና አይሲኤል የተባለውን የእስራኤል ኩባንያ ማጭበርበሩን ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ የማዕድን ዘርፍ ስላለበት ሁኔታና እንደ አላናና አይሲኤል ያሉ የማዕድን ኩባንያዎች ሥራቸውን አቋርጠው መውጣት በዘርፉ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአላና ጉዳይ ከታክስ ስወራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የአላና ፖታሽ ጉዳይ ግብር ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኩባንያው ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር መክፈል ያለበት የግብር ዕዳ አለበት፡፡ ያንን ግብር መክፈል አለበት፡፡ መንግሥት ይኼን በሆነው መንገድ በሕግም ፈልጎ ያስከፍላል፤›› ብለዋል፡፡

በቶሮንቶ ስቶክ ገበያ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የቆየው አላና ፖታሽ፣ ‹‹አላና ፖታሽ አፋር›› የሚባል እህት ኩባንያ በማቋቋምም በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ሥራ ለስድስት ዓመታት ያህል ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ አላና ፖታሽ አፋር ለማዕድን ፍለጋ ሥራው 90 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱን፣ 3.2 ቢሊዮን ቶን የፖታሽ ክምችት ማግኘቱን በወቅቱ አስታውቋል፡፡

የፖታሽ ክምችቱን ለማልማት 750 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው፣ የፖታሽ ማምረቻ ፋብሪካውን ገንብቶ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ430 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የሚያስችል ዕቅድ ለመንግሥት አቅርቦ ይሁንታን አግኝቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የማዕድን ሚኒስቴር ለአላና ፖታሽ አፋር የከፍተኛ ማዕድን ማምረቻ ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡

ይሁን እንጂ በዓለም ገበያ የማዕድናት ዋጋ በመውደቁና አላና ፖታሽ የሚፈለገውን ካፒታል ማሟላት ባለመቻሉ፣ እስራኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ (አይሲኤል) ለተባለው ታዋቂ የማዳበሪያ አምራች የአክሲዮን ድርሻውን ሸጧል፡፡ አይሲኤል ቀደም ሲል የአላና ፖታሽ በቶሮንቶ ስቶክ ገበያ 16 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ገዝቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የተቀረውን 84 በመቶ በ140 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶታል፡፡

በወቅቱ የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስለሽያጩ ቀደም ብሎ አልተገለጸልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰሙ ቢሆንም፣ የአላና ፖታሽ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለሚኒስቴሩ አሳውቀናል ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

አላና ፖታሽን ከገዛ በኋላ አይሲኤል የአላና የማዕድን ማምረቻ ፈቃድ እንዲዛወርለት ለማዕድን ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ማመልከቻውን በመገምገም ላይ ሳለ የፖታሽ ፕሮጀክቱ ሥራ እንዳይቋረጥ አይሲኤል ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች አስገብቶ ሥራውን እንዲቀጥል መፍቀዱን የቀድሞው ሚኒስትር አቶ ቶለሳ ሻጊ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች አይሲኤል አስፈላጊዎቹን ሰነዶች አሟልቶ እንዲያቀርብ ጠይቀው ጉዳዩን በማየት ላይ ሳሉ፣ አይሲኤል (አላና ፖታሽ አፋር) ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በታክስ ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል፡፡ ባለሥልጣኑ በአላና ፖታሽ ሊከፈል የሚገባ የዊዝሆልዲንግና የቫት ክፍያ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ በአላናና በአይሲኤል መካከል በተፈጸመው ሽያጭ ውል መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን የካፒታል ዕድገት ግብር በአጠቃላይ 55 ሚሊዮን ዶላር ግብር እንዲከፈል ጠይቋል፡፡

የአይሲኤል ኃላፊዎች በበኩላቸው በአላና ሊከፈል የሚገባ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የዊዝሆልዲንግና የቫት ግብር ለመክፈል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ይህን ሊቀበል አልቻለም፡፡

በግብር ጥያቄው የተደናገጡት የአይሲኤል ኃላፊዎች ሥራቸውን አቁመው ከአገር ወጥተዋል፡፡ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. የአይሲኤል ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያሠራን ስላልቻለ በኢትዮጵያ የጀመርነውን ኢንቨስትመንት ለማቋረጥ ተገደናል፤›› ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን መሠረተ ልማትና የሕግ ማዕቀፍ ሊያቀርብልን ባለመቻሉ፣ የታክስ ባለሥልጣኑ አላና ፖታሽ አፋር ላይ ሕገወጥ የታክስ ጥያቄ በማቅረቡ የኩባንያው ሥራ እንዲቋረጥ ወስነናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ከለላ ውሎችን የጣሰ ነው፤›› ብሏል ቦርዱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሰጡት ምላሽ ከአይሲኤል መግለጫ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት አላና ፖታሽን እንጂ አይሲኤልን እንደማያውቀው ነው የተናገሩት፡፡

‹‹አይሲኤልን በተመለከተ አይሲኤል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደራደረው ነገር የለም፡፡ አላና ፖታሽ ከሚባል አንድ የፖታሽ ኩባንያ ጋር የኢትዮጵያ መንግሥትን ሳያሳውቁ ከበስተጀርባ ተደራድረው ነው የመጡት፡፡ እኛ አሁንም የምናውቀው አላና ፖታሽን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው እሱ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አይሲኤል ከበስተጀርባ ተደራድሮ ከበስተጀርባ እንደሄደ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እኛ የምናውቀው አላና ፖታሽን ነው፡፡ እኛ አገር ውስጥ ተመዝግቦ የሚሠራው አላና ፖታሽ ነው፡፡ ከቀጠለ ይቀጥላል፣ ካልቀጠለ ለሌላ ኩባንያ እንሰጣለን፡፡ ብዙ ፈላጊዎች ስላሉ ብዙ የሚያሳስበን ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አላና ፖታሽ አይሲኤልን እንዳጭበረበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ ‹‹አይሲኤል በራሱ በአላና ፖታሽ የተጭበረበረ መሆኑን አውቆ ነው የሸሸው፡፡ ምክንያቱም እኛ ግብር ይከፈል ስንል እነሱ ከጀርባ የተፈራረሙት ይህን ሁሉ ስለማያካትት፣ ከዚህ ተቋም ጋር መቀጠል አንችልም ብለው ነው የሄዱት፡፡ አሁንም ቢሆን መጥተው ግብሩ ከተከፈለ በኋላ ስማቸውን ለማዛወር ከፈለጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼን ቢሉም የቀድሞ አላና ፖታሽ ማኔጅመንትና ቦርድ አባላትና የአይሲኤል ኃላፊዎች በድብቅ የተደረገ ስምምነት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የቀድሞ የአላና ፖታሽና የአይሲኤል ኃላፊዎችን አስደንግጧል፡፡

ከአላና ፖታሽ አፋር መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ነጂብ አባቢያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰዎች ሳያሳስቷቸው እንዳልቀሩ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን እናከብራቸዋለን፡፡ ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅና፣ ከአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ አገር መሪ ናቸው፡፡ አላና ፖታሽን በተመለከተ ግን የቀረበላቸው መረጃ የተሳሳተ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚናገሩት በበታቾቻቸው በቀረበላቸው መረጃ ነው፡፡ እኔ የቀረበላቸው መረጃ የተሳሳተ ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ አላና ፖታሽንና አይሲኤልን በተመለከተ የተፈጸመው ውል የተመዘገበና በእኛና በመንግሥት እጅ የሚገኝ ለመሆኑ ሰነዶቹን በእርጋታ በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ብለዋል አቶ ነጂብ፡፡

አላና ፖታሽ ለአይሲኤል መሸጡ በገሃድ የተካሄደ እንደሆነ፣ በወቅቱ የአላናና የአይሲኤል ከፍተኛ ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከቀድሞ የማዕድን ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ጋር በመገናኘት አይሲኤል በኢትዮጵያ ለመሥራት ስላሰበው ሰፊ ኢንቨስትመንት ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ በወቅቱም መሪዎቹ ዕቅዱን በበጎ ሁኔታ መቀበላቸውንና ማበረታታታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በድብቅ የተደረገ ድርድር የተባለው እኔ አልገባኝም፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች በስቶክ ኤክስቼንጅ ለሕዝብ ለሽያጭ የቀረቡ በመሆናቸው ማንኛውንም መረጃ መደበቅ አይችሉም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ስላላቸው ለእነሱ እያንዳንዱን ነገር ማሳወቅ በሕግ ይገደዳሉ፡፡ ግዢውም ቢሆን በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሪፖርተርን ጨምሮ ዘግበውታል፡፡ ምኑ ነው ድብቅ?›› ብለዋል፡፡

አይሲኤል አላና ፖታሽን ከመግዛቱ ቀደም ብሎ ጀምሮ ከግብርና ሚኒስቴርና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በቅርበት ይሠራ እንደነበር የአይሲኤል ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአይሲኤል ዋና ባለድርሻና የእስራኤል ቁጥር አንድ ቱጃር የሆኑት ኢዳን ኦፋርና በወቅቱ የአይሲኤል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ሚስተር ስቴፋን ቦርጋስ፣ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በማዳበሪያ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚካሄዱ ፕሮግራሞች የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ቃለ መጠይቁ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ 600,000 ዶላር መለገሳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የታክስ ማጭበርበር ተፈጽሟል ስለተባለው አቶ ነጂብ አይሲኤል አላና ፖታሽን ከመግዛቱ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል አላና ፖታሽ ስላለው ንብረትና ዕዳ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የኢትዮጵያና የውጭ ባለሙያዎች ቀጥሮ ሰፊ የምርመራ ሥራ መሥራቱን፣ ባካሄደውም ጥናት አላና ያለበትን ዕዳ አብጠርጥሮ ማወቁንና ዕዳውንም ለመክፈል መስማማቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹እንኳን በዓለም ገበያ ላይ የተመዘገበ ኩባንያ ስትገዛ አይደለም አዲስ አበባ ውስጥ አንድ አነስተኛ ቤት ስትገዛ የባንክ ዕዳ አለበት ወይ? የአገር ውስጥ ገቢ አለበት ወይ? ክርክር አለበት ወይ? መንገድ ይወጣበታል ወይ? ብለህ ትጠይቃለህ፡፡ እንዴት ነው አይሲኤልን የሚያህል ግዙፍ ኩባንያ የሚገዛውን ኩባንያ ዕዳ ሳያጣራ ገንዘብ የሚከፍለው?›› ሲሉ በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ እንደሚጽፉ፣ ከተፈቀደላቸውም በአካል ቀርበው ለማስረዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንደምንፈታው አምናለሁ፡፡ ሁሉም ነገር በመዝገብ የተያዘ ነው፤›› ያሉት አቶ ነጂብ፣ አላና ፖታሽ ለማዕድን ፍለጋ ሥራው 90 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን፣ በወቅቱ ለ450 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ አብዛኛው ባለአክሲዮን ድርሻውን ከስሮ መሸጡን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የቀድሞ የአላና ፖታሽ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፈርሃድ አባጎቭ፣ ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ተመካክረው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አይሲኤል ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአላና ዕዳ የሆነ ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር (200 ሚሊዮን ብር) የታክስ ግብር ለመክፈል ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ 55 ሚሊዮን ዶላር የካፒታል ዕድገት ታክስ ጨምሮ እንዲከፍል በመጠየቁ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 4 ቀን 2016 አይሲኤል (አላና ፖታሽ አፋር) ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለማዕድን ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የዳሎል ፖታሽ ፕሮጀክቱን ዘግቶ ለመንግሥት ማስረከብ እንደሚፈልግ፣ አላና ፖታሽ አፋር የሚጠበቅበትን (ያለበትን) በሰነድ የተደገፈ ግብር እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ዕዳ ካለ ለመዝጋት ፍላጎት እንዳለው አሳውቋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመዝጋት የሚልካቸውን ባለሙያዎች ምንም ዓይነት ችግር እንደማይፈጠርባቸው ዋስትና እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ሪፖርተር ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ አይሲኤል ለጻፈው ደብዳቤ እስካሁን ከመንግሥት በጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ለአይሲኤል ኃላፊዎች በኢሜይል አድራሻቸው ለላካቸው ጥያቄዎች ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አላገኘም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የማዕድኑ ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል የገለጹ ቢሆንም፣ ኢኮኖሚው በማዕድን ዘርፉ ላይ ጥገኛ እንዲሆን መንግሥታቸው እንደማይፈልግ አስረድተዋል፡፡ 

Standard (Image)

በጎንደር ከተማ አመፅና ሁከት አስነስታለች የተባለች ግለሰብ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባት

$
0
0

በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር ከተማ በተለያዩ የዞን ከተሞችና በአዲስ አበባ ጭምር አመፅና ሁከት በማስነሳት፣ የአመፅ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በማስተባበር ከፍተኛ የሆነ የግልና የመንግሥት ንብረት ላይ ውድመት አድርሳለች የተባለች አንድ ግለሰብ ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በቅጽል ስሟ ይርገዱ እንደምትባል የተገለጸችው ንግሥት ይርጋ ተፈራ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ተልዕኮን በመቀበል፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አባላት የገንዘብ ድጋፍ በመቀበል፣ የተለያየ የጦር መሣሪያ እንዲገዛ በማድረግና በክልሉ በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች አመፅና ሁከት እንዲነሳ በማድረግና በመምራት መሳተፏን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ግለሰቧ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን ጋር ግንኙነት ካለው በካናዳ ነዋሪ መሆኑ ከተገለጸው ክንዴ ከሚባለው ግለሰብና በሰሜን ጎንደር ከሚንቀሳቀሰው የቡድኑ አባል ደጀኔ ማሩ ጋር ግንኙነት እንደነበራትም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ውስጥ በሚገኘው ደሳለኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈጠረው አመፅና ሁከት፣ 20 ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር በመግባትና በማስተባበር ሰዎችና ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ መንገድ ከማዘጋቷም በተጨማሪ በአመፁ የተሳተፉ ወጣቶችን በራሷ ግሮሰሪ ውስጥ በማሳደር ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዲደርስ ማድረጓን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

ደጀኔ ማሩ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ጋር ተገናኝታ በጎንደር ከተማ የተከሰተውን አመፅ መምራት እንዳለባት ከተወያዩ በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ አመጽ የሞቱት አራት ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሳይቆስል እንደቆሰለ በማስመሰልና ለመቀስቀሻ በ600 ብር ባነር አሠርታ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመፅ በማስነሳት፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም ማድረጓን ክሱ ይገልጻል፡፡

መንግሥትን በአመፅ ትግል መጣል እንዳለባቸው በመነጋገርና በመስማማት ሐምሌ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በመሰብሰብና አመፁን የሚያስቀጥሉ 15 ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ በመምረጥ ግንባር ቀደም የመሪነት ተሳትፎ እንደነበራትም አክሏል፡፡ ተከሳሿ ኮሚቴው እንዲቋቋም ካደረገች በኋላ ኮሎኔል ደመቀን ለመጠየቅ ጎንደር ማረሚያ ቤት በተገኘችበት ወቅት፣ ኮሎኔሉ ጠንክረው በመደራጀት ሥራቸውን እንዲሠሩ እንደ መከሯትና ከሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹እቴጌ ጣይቱ›› ብለው እንደሰየሟት ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በስልክ መናገሯን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በካዳና የሚገኝ የቡድኑ አባል ወደ ተከሳሿ በመደወል የትጥቅ ትግል ለማድረግ ከቆረጠች በውጭ ያሉ የቡድኑ አባላት ከሚያደራጇቸው አባላት ጋር እንደሚያገናኟት፣ አርማጭሆ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱት የቡድኑ አባላት ሰጠኝ አርጋውና ማሩ አረጋ ጋር መገናኘት እንዳለባት፣ በሥሯ የሚገኙ የቡድኑ አባላትን ከላከች ደግሞ እንደ ፕሮጀክት ይዘው ከውጭ ዕርዳታ እንደሚያደርጉላት፣ የጦር መሣሪያ እንደሚያስታጥቋቸውና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያደርጉላት ቃል ተገብቶላት እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ለቤት ማደሻ በሚል ከካናዳ ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተላከላትም አክሏል፡፡

በለጠ አዱኛ የተባለ ሌላው የጎንደር ከተማ አመፅ አስተባባሪ ለተከሳሿ ነሐሴ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ደውሎላት፣ የቡና ቤት ሴት አለባበስ በመልበስና በየመዝናኛ ቦታዎች በመሄድ ባለሥልጣናትን በወሲብ በማጥመድ የማስገደል ሥራ እንድትሠራ የተሰጣትን ተልዕኮ ለመተግበር እየተንቀሳቀሰችና ፎቶዎችን እያነሳች ለቡድኑ በመላክ ላይ እንደነበረች በክሱ ተገልጿል፡፡

‹‹ትግሉ ከሥርዓቱ ጋር እንጂ ከትግሬ ጋር እንዳልሆነ›› በማስታወቅ ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥርና የሚሞክሩ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተከሳሿ መናገሯን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሿ አመፁን እንድታስቀጥል ከውጭ ተደውሎላት መምህር ኤፍሬም በተባለ ግለሰብ በኩል 108,000  ብር እንደተላከላትም ክሱ አክሏል፡፡

ከንግሥት ይርጋ ጋር ተጠርጥረው የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ዓለምነህ ዋሴ ገብረ ማርያም፣ ቴዎድሮስ ተላይ ቁሜ፣ አወቀ አባተ ገበየሁ፣ በላይነህ ዓለምነህ አበጀና ያሬድ ግርማ ኃይሌ (ከአዲስ አበባ) ሲሆኑ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባልና አመራር ጋር በመነጋገር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ለኢሳት ቴሌቪዥን በጎንደር ከተማ ስለተከሰተው አመፅ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላትና አመራሮች ጋር በመነጋገር የሽብር ተግባር ለመፈጸም ትጥቅ ከታጠቁ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ በመቀበል፣ አመፁን በመምራትና በማስተባበር በግልና በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በስፋት በክሱ አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1 ሀ እና ለ)ን 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3፣ 4 እና 6ን በመተላለፍ ድርጊቱን እንደፈጸሙ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ለማየት ፍርድ ቤቱ ለጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

Standard (Image)

ወደ ግል ከተዛወሩ የልማት ድርጅቶች 2.2 ቢሊዮን ብር ዕዳ መሰብሰብ አልተቻለም

$
0
0

-  ሚድሮክ ከገዛቸው ድርጅቶች 1.7 ቢሊዮን ብር ይፈለጋል

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ባለፈው በጀት ዓመት ወደ ግል ካዛወራቸው ተቋማት መሰብሰብ የነበረበትን 2.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ መሰብሰብ የቻለው 611 ሚሊዮን ብር (25 በመቶ)  ብቻ ነው፡፡ ለሚኒስቴሩ ገቢ አሰባሰብ ደካማ መሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የሚድሮክ ኩባንያዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር አቶ ግርማ አመንቴ ከሳምንት በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የገዙ ባለሀብቶችንና ኩባንያዎችን ጠርተው፣ በወቅቱ ክፍያ በማይፈጽሙበት ምክንያት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መሰብሰብ ከነበረበት 2.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ሚድሮክ የገዛቸው ኩባንያዎች 1.7 ቢሊዮን ብር ባለመክፈል ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ከሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚድሮክ ብዛት ያላቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ ትልቁ ክፍያም የሚጠበቀው ከሚድሮክ ነው፡፡

‹‹ገቢ በመሰብሰብ ረገድ በአንድ በኩል ዝቅተኛ አፈጻጸም ቢኖረንም፣ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማኅበርን ከ11 ቢሊዮን ብር (510 ሚሊዮን ዶላር) በላይ በሆነ ዋጋ የአክሲዮን ሽያጭ ፈጽመናል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ችለናል፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ በሌላ በኩል ከፍተኛ ገቢ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቶቹና ኩባንያዎቹ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ እስከ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ማጠናቀቅ ነበረባቸው ተብሏል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሦስት ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ቢጠይቁም፣ በጭማሪ ጊዜው ውስጥም ክፍያ መፈጸም እንዳልቻሉ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የገዙ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ክፍያቸውን በወቅቱ መክፈል ያልቻሉበትን ምክንያት ሚኒስትሩ በጠሩት ውይይት ላይ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሽያጭ ቢፈጽምም የወሰን ማስከበር ሥራ ባለመከናወን፣ የይዞታ ካርታ አለመኖር፣ በምርት ሒደት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለመኖር፣ በጡረታ የሚገለሉ ሠራተኞችን ማስተናገድ አለመቻሉ፣ የውጭ ንግድ ገበያ እጥረትና አፈጻጸም ደካማ መሆን ተጠቃሽ ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡

አቶ ግርማ በመንግሥት በኩል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ፣ ገዢዎቹም ያሉባቸውን ችግሮች ፈተው በፍጥነት ከመንግሥት የሚፈለግባቸውን ገንዘብ እንዲያስገቡ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የይዞታ ካርታ ችግሮቻችንን ከክልሎች ጋር በጋራ የምንፈታው ነው፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተያዘው በጀት ዓመት 14 የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር አቅዷል፡፡ ከልማት ድርጅቶቹም 3.1 ቢሊዮን ብር ለማስገባት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

 

Standard (Image)

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በኋላ ከባንኮች መጠባበቂያ ገንዘብ እየሰበሰበ ብቻ ኢኮኖሚውን መቆጣጠር አይችልም›› አቶ ነዋይ ገብረ አብ፣ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ

$
0
0

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ሲጠቀምበት የነበረው የፖሊሲ መሣሪያ በቂ ስለማይሆን ተጨማሪ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው፣ ለዚህም ባንኮች ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

ይህንን የገለጹት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ነዋይ ገብረ አብ ናቸው፡፡ አቶ ነዋይ ለአገልግሎታቸው ዕውቅና ለመስጠት ሐሙስ ጥር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት በሒልተን ሆቴል በተሰናዳ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት አሁን ያለው የመጠባበቂያ ገንዘብ አሠራር በቂ አይደለም፡፡

‹‹ባለፉት 10 እና 12 ዓመታት በብሔራዊ ባንክ ድጋፍ በቂ የገንዘብ አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ነዋይ፣ በዚህ ረገድ ትልቅ ዕድገት ቢኖርም ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች መጠባበቂያ ገንዘብ እየሰበሰበ ብቻ ኢኮኖሚውን ሊቆጣጠር የማይችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ያለው የፖሊሲ መሣሪያ በጣም ውስን በመሆኑና ኢኮኖሚውንም ለመቆጣጠር የንግድ ባንኮች ከሚያስቀምጡት ገንዘብ ውጪ፣ አዳዲስ የፖሊሲ ማስፈጸሚያዎችን ሊተገብር ይችላል፡፡ ይህም የወለድ ምጣኔን ከፍና ዝቅ በማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የብሔራዊ ባንክም ሆነ የንግድ ባንኮች ሥራ ትልቅ ሙያ የሚጠይቅ፣ በብዙ ዳታ የሚገፋና የተወሳሰበ ስለሚሆን ባንኮች ከወዲሁ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር እስካሁን ባንኮች 15 በመቶ አሁን ደግሞ 10 በመቶ እንዲያስቀምጡ በማድረግ ሲሠራበት ከነበረው አሠራር በተጨማሪ፣ የወለድ ምጣኔን ከፍና ዝቅ ማድረግ፣ ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ሥልቶችን ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡

አቶ ነዋይ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ልዩ አማካሪነትና ከብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነት በጡረታ መገለላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ምሽት በተደረገላቸው የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለአቶ ነዋይ ዕውቅናና ማስታወሻ አበርክቶላቸዋል፡፡    

Standard (Image)

የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በ12.2 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

$
0
0

በቀድሞ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የኦፕሬሺን ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በትረወርቅ ታፈሰ፣ በመንግሥት ላይ የ12.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

አቶ በትረወርቅ ተጠርጥረው የተከሰሱበትን የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት፣ እ.ኤ.አ ኦገስት 17 ቀን 2012 ግብረ አበር መሆናቸው ተጠቅሶ ሁለተኛ ተከሳሽ ከሆኑትና ካልተያዙት አቶ ወንድወሰን መስፍን ጋር ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ በትረወርቅ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ወንድወሰን ሥራ አስኪያጅ ለሆኑበት፣ ትራንስ ናሽናል ኮምፒዩተር ከውጭ አገር ለሚያስመጣው “Annual Software Update and License of Support” ለተባለ አገልግሎት፣ በሐሰተኛ ሰነድ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) እንዲከፍቱ አድርገዋል፡፡ ኤልሲውን የከፈቱት ‹‹ለኤፌዴሪ ኢኮኖሚና ልማት ሚኒስቴር የሚሰጥ አገልግሎት ነው›› በማለት ያለምንም መጠባበቂያ ገንዘብ የ445,724 ዶላር ነው፡፡

አቶ በትረወርቅ የተጠየቀውን ኤልሲ ከባንኩ አሠራር ውጪ እንዲከፈት በማድረግ፣ ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ወንድወሰን ደግሞ ለተገለጸው አገልግሎት በተከፈተው ኤልሲ መሠረት ገንዘቡ ለላኪው ባንክ ያላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ በትረወርቅ በወቅቱ በባንኩ ውስጥ በነበራቸው ሥልጣን መሠረት ገንዘቡ እንዲተካ ወይም እንዲመለስ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው፣ ባለማድረጋቸው ገንዘቡ ለባንኩ አለመመለሱንም ክሱ ይጠቁማል፡፡ በወቅቱ ከባንኩ የተወሰደው 445,724 ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሪ 8,456,252 ብር ሲሆን፣ ወለድ 1,534,159 ብር እና የዘገየበት ቅጣት 2,222,166 ብር በድምሩ 12,222,166 ብር መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በመሆኑም ግብረ አበር ከተባሉት ሁለተኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 33፣ 411 (1ሐ)ንና (2)ን በመተላለፍ፣ የመንግሥትን ሥራ በማይመች አኳኋን መምራትና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሙስና ወንጀል፣ ክስ መመሥረቱን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የክስ ሰነድ ያስረዳል፡፡

Standard (Image)

በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 948 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ሪፖርት ቀረበ

$
0
0

የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፍ አጋር የረድኤት ድርጅቶች ማክሰኞ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉት የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ሪፖርት፣ በደቡብና በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ 5.6 ሚሊዮን ወገኖች፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ምግብና ምግብ ነክ ላልሆነ ዕርዳታ 948 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታወቁ፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ እንደተናገሩት፣ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ለጋሾችና የረድኤት አጋር ድርጅቶች እገዛ በታሪክ ትልቅ የሆነ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ ‹‹አዲስ በገጠመን ድርቅ ሳቢያ 5.6 ሚሊዮን ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ያ አጋርነት ዛሬ ያስፈልገናል፤›› ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2017 ለሚያስፈልገው ዕርዳታ በመጀመሪያ ዙር 47.37 ሚሊዮን ዶላር እንደመደበ አስረድተዋል፡፡

በህንድ ውቅያኖስ በተፈጠረ ድንገተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በደቡብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በተከሰተው አዲስ ድርቅ 5.6 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታ ፈላጊዎች አድርጓቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2017 የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ሪፖርት እንደሚያሳየው ውኃና ንፅህና፣ ግብርና፣ የምግብ ዕርዳታ፣ ጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ መጠለያና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታ ሥራዎች እንደ አንገብጋቢነታቸው ዕቅድ ወጥቶላቸዋል፡፡

በዕቅድ ከተያዘው 948 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 598 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ፣ ለተመጣጠነ ምግብ 105 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለውኃና ለንፅህና 86 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. የ2017 የዕርዳታ ፍላጎት ሪፖርት የተሰናዳው በኢትዮጵያ መንግሥት አመራር በርካታ የረድኤት ድርጅቶችን ያሳተፈ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ተመርኩዞ መሆኑን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሁና እዚያኮንዋ ኦኖቺ ተናግረዋል፡፡

ከኅዳር እስከ ታኅሳስ 2009 ዓ.ም. ለሦስት ሳምንት ሰፊ የመስክ ግምገማ መካሄዱንና 230 የመንግሥት፣ የተመድ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የለጋሾች ተወካዮች በድርቅ የተጎዱትን አካባቢዎች መጎብኘታቸውን ኦኖቺ ገልጸዋል፡፡ 

Standard (Image)

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቂሊንጦ ተከሳሾች ጉዳይ በዝግ ችሎት እንዲታይ ጠየቀ

$
0
0

የቂሊንጦ እስረኛ ማቆያን በማቃጠል የ23 ተከሳሾች ሕይወት በማጥፋትና 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት በማውደም ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ተከሳሾች ክርክር፣ በዝግ ችሎት እንዲሆንለት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤትን ጠየቀ፡፡

ፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው አቤቱታ ምስክሮቹ ዛቻና ማስፈራራት እየተደረገባቸው በመሆኑ፣ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/03እና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32(1) መሠረት፣ ጉዳዩ በዝግ ችሎት እንዲታይለት አመልክቷል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሠረተባቸው 38 ተከሳሾች ውስጥ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ ሆስፒታል በሕክምና ላይ በመሆናቸው በወቅቱ ቀርበው የተከሰሱበት ጉዳይ ሳይነበብላቸው ቆይቶ ነበር፡፡ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ዶ/ር ፍቅሩ ከሆስፒታል ወጥተው በቂሊንጦ ያሉና ጉዳያቸው በክርክር ሒደት የሚገኝ ተከሳሾች የሚለብሱትን ቢጫ ሸሚዝና ሱሪ ለብሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ስማቸውን፣ ማዕረጋቸውንና አድራሻቸውን ፍርድ ቤቱ ጠይቆ እንደጨረሰ፣ የተከሰሱበትን ጉዳይ በንባብ አሰምቷቸዋል፡፡ በተነበበላቸው ክስ ላይ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡም ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡

ሌሎቹ 37 ተከሳሾች ለጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ተቀጥረው የነበሩት በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ፣ ጠበቃ ካላቸው ማቆም የሚችሉ ከሆነ ይዘው እንዲቀርቡ ወይም አቅም ከሌላቸው ቃለ መሃላ ፈጽመው መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸውና የማረሚያ ቤት አስተዳደር ተከሳሾቹ ባቀረቡበት አቤቱታ ላይ ምላሽ እንዲያቀርብ ነበር፡፡

ቀደም ካሉ ችሎቶች በተለይ ከማረሚያ ቤት አያያዝ ጋር በተገናኘ ተከሳሾቹ ብሶታቸውን በተደጋጋሚ በማቅረባቸውና የችሎቱም የአሠራር ሥርዓት በአግባቡና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዳይሄድ አድርገዋል በሚል፣ ፍርድ ቤቱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ  ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በርከት ያሉ ፖሊሶች፣ የማረሚያ ቤት ፖሊሶችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከመገኘታቸውም በተጨማሪ፣ ወደ ፍርድ ቤቱ በሚገባ ማንኛውም ሰው ላይ ጠበቅ ያለ ፍተሻም ተስተውሏል፡፡ የማረሚያ ቤት ከፍተኛ ኦፊሰሮችም በርከት ብለው ተገኝተዋል፡፡

ችሎቱ እንደተሰየመ የተከሳሾች ጠበቆች ደንበኞቻቸውን አስመዘግበዋል፡፡ ከ38 ተከሳሾች ውስጥ የ26 ከሳሾች ጠበቃ ሆነው የቀረቡት አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ ለአንድ ተከሳሽ ደግሞ አቶ መሐመድ ኑር አብዱልከሪም ሲሰየሙ፣ ለአምስቱ ተከሳሾች ሌላ ጠበቃ ተሰይመዋል፡፡ ሦስት ተከሳሾች ያለ ጠበቃ መቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የክስ ቅድመ መቃወሚያ ማቅረባቸውን ሲጠይቅ፣ ከአንድ ተከሳሽ በስተቀር ሁሉም ተከሳሾች አለማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ ቀደም ባሉት ችሎቶች ያሰሙት የነበረውን የጋራ ተቃውሞና ተፈጸመብን የሚሉትን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሚመለከት፣ በዕለቱ ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ የፍርድ ቤቱን አካሄድ ተከትለው አንዳንዶቹ ጥያቄ ለማቅረብ ቢሞክሩም፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹አንቀበልም፣ በጽሕፈት ቤት በኩል አቅርቡ›› በማለት ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡ ጠበቆቻቸውም ሊያስረዱ ቢሞክሩም ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ምላሽ ለመስጠት፣ ቅድመ ክስ መቃወሚያ ለማቅረብና የማረሚያ ቤትን ምላሽ ለመስማት ለጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

 

Standard (Image)

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተሰማ

$
0
0

በግጭት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ከገባው ደቡብ ሱዳን በየጊዜው እየፈለሱ የሚገኙ ስደተኞች፣ በጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተሰማ፡፡

ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ብድር የተበደሩ 160 የሚጠጉ ባለሀብቶች በሚገኙበት ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ የስደተኞች ካምፕ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የስደተኞቹም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ በእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጫና እየደረሰ መምጣቱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሀብቶች ገልጸዋል፡፡

በስደተኞች መስፋፋት በደረሰባቸው ጫና ምክንያት የኢንቨስትመንት ሥራቸውን አቋርጠው የወጡና አቋርጠው ለመውጣትም የተዘጋጁ ባለሀብቶች መኖራቸው ተሰምቷል፡፡

ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል አቶ አደገ ንጉሤና አቶ ጌታነህ ጥላሁን ይገኙበታል፡፡ አቶ አደገ በ2002 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ ፑኩሞ ቀበሌ 2,000 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ እርሻ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

ለዚህ እርሻ ሥራ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 21 ሚሊዮን ብር ተበድረው ጥጥና የቅባት እህሎችን ሲያለሙ መቆየታቸውን፣ ነገር ግን አዲሱ ኑኝኒያል ስደተኞች ካምፕ የክልሉ መንግሥት በሰጣቸው የእርሻ መሬት ላይ እየተገነባ ስለሆነና፣ በቀረው መሬታቸው ላይም ያለሙት ምርት በስደተኞቹ ጉዳት እየደረሰበት በመሆኑ፣ የደከሙበትን ኢንቨስትመንት አቋርጠው ለመውጣት እያቅማሙ መሆኑን አቶ አደገ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕግና ሥርዓት ተጠብቆ የተሰጠ የእርሻ መሬት ላይ የስደተኞች ካምፕ ሊሠራበት አይገባም፤›› ያሉት አቶ ታደገ፣ ‹‹የፌዴራልና የጋምቤላ ክልል መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው ሊያዩት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አደገ እንደሚገልጹት ከአንድ ሺሕ ሔክታር በላይ ጥጥ አልምተዋል፡፡ ስደተኞቹ በጥጥ ማሳ መካከል የሚበቅሉ ዕፅዋትን ለምግብነት ስለሚጠቀሟቸው፣ የጥጥ እርሻ ውስጥ በጥልቀት ስለሚገቡ እርሻቸው እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጥጥ ተክል በብዙ ዓይነት ተባዮች የሚጠቃ በመሆኑ፣ ተባዮቹን ለመከላከል  የተለያዩ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ እርሻ ውስጥ ስደተኞች በብዛት የሚገቡ በመሆኑ ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል፣ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን መርጨት በማቆማቸው ምርት እያነሰባቸው መሆኑን አቶ አደገ ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው ላለፉት ሰባት ዓመታት የለፉበትን ሥራ ለማቋረጥ እያሰቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ጌታነህ የአቶ አደገን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ ጌታነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጋምቤላ ክልል አቦል ወረዳ ጃዊ ቀበሌ 500 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

አቶ ጌታነህ ከወሰዱት መሬት ውስጥ 200 ሔክታር ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በብዙ ድካም ለእርሻ ሥራ ባስተካከሉት መሬት ላይ የጃዊ ስደተኞች ካምፕ በመገንባቱ ሥራቸውን ጥለው መውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹የደረሰብኝን በደል ለክልሉ ባስታውቅም ምንም ምላሽ አልተሰጠኝም፤›› በማለት፣ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ያፈሰሱበት የእርሻ ኢንቨስትመንት ባዶ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ባለሀብቶች ካሳም ሆነ ተለዋጭ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን ለክልሉ ማስታወቃቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ምላሽ አልተሰጠንም ብለዋል፡፡

በተቀሩት ቦታዎች ላይ የእርሻ ሥራቸውን ለመቀጠል የፀጥታ ሥጋት እንዳለባቸውም አብራርተዋል፡፡

ኢታንግ ልዩ ወረዳ ብቻ ሦስት ካምፖች አሉ፡፡ በዚህ ዓመት በዚሁ ኢታንግ አንድ አዲስ ካምፕ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ‹‹በርካታ ትልልቅ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ነገር ግን ግንባታዎቹ በባለሀብት መሬት ላይ ስለመካሄዳቸው መረጃው የለኝም፡፡ ባለሀብቶቹ ቅሬታውን ለክልሉ ካረቀቡ ግን አጣርተን በአስቸኳይ ምላሽ እንሰጣለን፤›› በማለት የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ከስደተኞች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አቶ ኡቶው አክለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በጋምቤላ ክልል አራት ትልልቅ የስደተኞች ካምፖች ይገኛሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ግጭት ከመርገብ ይልቅ እየባሰ በመምጣቱ የስደተኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡

አቶ ኡቶው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ይጋራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን መረጋጋት የተሳነውና በቀውስ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በርካታ ስደተኞች ወደ ጋምቤላ እየፈለሱ ነው፡፡ ‹‹ጋምቤላ ክልል በአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሩ 306 ሺሕ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የስደተኞቹ ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኡቶው ስደተኞች በብዛት እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢፌዴሪ መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመ በመሆኑ ስደተኞችን ይቀበላል፡፡ በእርግጥ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በክልሉ ሀብት ላይ ጫና አሳድሯል፤›› በማለት መፍትሔ የሚሻ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

Standard (Image)

በአዲስ አበባ ከተማ 741 ቦታዎች ለዓመታት ታጥረው መቀመጣቸው ተጠቆመ

$
0
0

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን ለውይይት የቀረበ አንድ ሰነድ፣ በከተማው ውስጥ 741 ቦታዎች ለዓመታት ታጥረው መቀመጣቸውን ይፋ አደረገ፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ውስጥ 147 የሚሆኑት ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳልተካሄደባቸው ሰነዱ አመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 372 ዓይነት ሥር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ሰነዱ ለይቷል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል መሬትና መሬት ነክ የሆኑ ጉዳዮች ጎልተው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

ይኼ ሁሉ ቦታ ታጥሮ ያለ ሥራ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል ዕርምጃ አለመውሰዱ፣ ክትትልና ድጋፍ አድርጎ ወደ ሥራ አለማስገባቱ አግባብ አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት አለመኖሩ፣ የአመለካከት መዛነፍና ሙስና መንሰራፋቱ ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ ይህ አካሄድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ለከተማው ዕድገት መሰናክል እንደሚሆን በሰነዱ ላይ በግልጽ ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ተቋማት በሙሉ ለችግር የተጋለጡ መሆናቸውን የሚገልጸው አዲሱ ሰነድ፣ የመሬት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥም ብልሹ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ተገልጋዮችን ማወናበድ፣ ማመናጨቅ፣ ማጉላላት፣ መረጃ አለመስጠት፣ የይዞታ ባለቤት ካርታ ችግሮችን አለመፍታትና የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ አለማድረግ ተጠቃሽ ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

ለልማት ተነሽዎች ምትክ ቦታ አለማቅረብ በዘርፉ ለተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳንካ ሆነው ቀርቧል፡፡

በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ላይም መጠነ ሰፊ ችግሮች መኖራቸውን ሰነዱ አመልክቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ዘርፍ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ በርካታ የመዋቅር ለውጦችን አካሂዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት ለተፈጠረው ብልሹ አሠራርና ሙስና 210 አመራሮች ላይና 1,200 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰዱ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን አሁንም ዘርፉ ፀድቷል ተብሎ ባለመታመኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  አዲስ የመዋቅር ለውጥ ለማካሄድ ተወጥኗል፡፡

አዲሱ መዋቅር የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን እንዲቋቋምና የልማትና ዝግጅት ሥራዎችን እንዲያካሂድ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የክትትልና የግምገማ ሥራዎችን እንዲያካሂድ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ የተጠቀሱትን ችግሮች ይህ አዲስ መዋቅር እንደሚፈታው መታመኑ ተገልጿል፡፡

 

Standard (Image)
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live