Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live

ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪና ለወጣቶች ፈንድ 18.2 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ፀደቀ

$
0
0

ለ2009 ዓ.ም. የሚውል የ18.2 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ፀደቀ፡፡ መንግሥት ያቀረበውን የተጨማሪ በጀት አዋጅ ፓርላማው በመጀመሪያ ንባብ ማክሰኞ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. አፅድቆታል፡፡ በዚህም መሠረት የ2009 ዓ.ም. አጠቃላይ በጀት 229.2 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጁን ይዘት ለምክር ቤቱ ያብራሩት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ኤዴታው አቶ አማኑኤል አብርሃ ናቸው፡፡ አቶ አማኑኤል እንዳብራሩት፣ ተጨማሪ በጀቱ አስፈላጊ ከሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል መንግሥት ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች ተግባራዊ የሚያደርገው የደመወዝ ጭማሪ በዋነኝነት ይገኝበታል፡፡

መንግሥት ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነው የደመወዝ ጭማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ከክልሎችና ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ለደመወዝ ጭማሪው ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ በጀት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህም በላይ ተጨማሪ በጀቱ ለወጣቶች የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀውን የተዘዋዋሪ ፈንድ ለማቋቋም ለሚያስፈልገው ወጪ የሚውል እንደሆነ አቶ አማኑኤል ገልጸዋል፡፡

ይኼንን ፈንድ ለማቋቋም አሥር ቢሊዮን ብር እንዲመደብ በመንግሥት መወሰኑንና ፈንዱን ለማቋቋም አዋጅ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀሪዎቹ ስድስት ወራት የፈንዱን ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገው ወጪ አምስት ቢሊዮን ብር በልዩ ልዩ ወጪዎች በጀት እንዲያዝ ሆኖ በተጨማሪ በጀቱ እንዲደገፍ ቀርቧል፡፡ ቀሪው አምስት ቢሊዮን ብር ደግሞ በ2010 በጀት ዓመት ለፈንዱ የሚከፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2009 ዓ.ም. በልማታዊ ሴፍቲኔት የተያዘው በጀት በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ 1.5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት፣ የድርቅ አደጋውን ለመከላከልና ቀሪ ግዴታዎችን በመወጣት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አንድ ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው መጠባበቂያ በጀት ሥራ ላይ በመዋሉ 1.41 ቢሊዮን ብር በመጠባበቂያ በጀትነት እንዲውል፣ ተጨማሪ በጀት ማፅደቅ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ለቀረበው 18.26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በገቢነት የተጠቀሰው ከነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ የሚገኘው ነው፡፡ በዚህም መሠረት 10.18 ቢሊዮን ብር ከነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ እንደሚገኝ፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ ገቢ ደግሞ 6.56 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ፣ እንዲሁም 1.23 ቢሊዮን ብር ከዘቀጠ ትርፍ (ከመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ኢንቨስትመንቶች የሚገኝ የተጣራ የትርፍ ክፍያ) እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በመሙላት ረገድ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ አሁን ለቀረበው ተጨማሪ በጀት ትልቁ የገቢ ምንጭ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም መሠረት የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ የመንግሥትን የገቢ ፍላጎት በመሙላት ረገድ ለሦስተኛ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ በዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋና በብሔራዊ የነዳጅ ማከፋፊያ ዋጋ መካከል የሚገኝን ልዩነት የሚጠቅም ፈንድ ሲሆን፣ ዓላማውም የነዳጅ ዋጋ ለማረጋጋት የሚውል ነው፡፡ ፓላማው የቀረበለትን የበጀት ጥያቄ ከአስቸኳይነቱ አንፃር በመጀመሪያ ንባብ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

 

Standard (Image)

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከኃላፊነት ሲነሱ የሚያገኟቸው ጥቅሞችና መብቶች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

$
0
0

ከኃላፊነት የሚነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኟቸው መብቶችና ጥቅሞችን የሚወስነው አዋጅ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥቅማ ጥቅም ከፍ ሊል ነው፡፡

እነዚህን ጥቅማ ጥቅምና መብቶች በተሻለ ሁኔታ ለማስከበርም በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡ ከማሻሻያው ረቂቅ አዋጅ ጋር የተያያዘው አባሪ ሰነድ በተግባር ላይ በነበረው አዋጅ አማካይነት ከኃላፊነት የተነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ዳኞችና የምክር ቤት አባላት ከኃላፊነት ሲነሱ ከችግር የራቀ ኑሮ እንዲኖሩና ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ማድረጉን፣ የእነዚህን ከፍተኛ ባለሥልጣናት እውቀትና ልምድ ለመጠቀም አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዴሞክራሲያዊው ዕድገትና ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለበት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነት የሚለቁ አመራሮችን በሁለት ምድብ በመክፈል ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያው ምድብ የአገርና የመንግሥት መሪዎች ንዑስ ምድብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምድብ ነው፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ለአገርና ለመንግሥት መሪዎች (ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አፈ ጉባዔና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት) ያስጠበቃቸው መብቶችና ጥቅሞች ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥቅሞችና መብቶች ጋር በአንፃራዊነት ሲታይ የተሻለ በመሆኑ፣ በማሻሻያው እንዳልተካተተ አባሪ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም በነባሩ አዋጅ ላይ የተደረጉት ማሻሻዎች ከኃላፊነት የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የተመለከተ ነው፡፡

ለእነዚህ ባለሥልጣናት በአዋጁ ውስጥ የተጠበቁ መብቶች ቢኖሩዋቸውም የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንበት ክፍያ፣ የቤት አበልና የተሽከርካሪ አገልግሎትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ማስፈለጉን ይገልጻል፡፡ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የመቋቋሚያ አበል ለመጀመሪያው የአንድ ዓመት አገልግሎት የሦስት ወራት ደመወዝ ሆኖ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ላለው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአንድ ዓመት አገልግሎት የአንድ ወር ደመወዝ እንዲታሰብ፣ በአጠቃላይ ግን ክፍያው ከአሥራ ስምንት ወራት ደመወዝ የማይበልጥ የነበረው እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለመጀመሪያው የአንድ ዓመት አገልግሎት የስድስት ወራት ደመወዝ ሆኖ፣ ለተጨማሪ ዓመታት በእያንዳንዱ የአንድ ወር ደመወዝ እየታከለ በአጠቃላይ ግን ከ24 ወራት ደመወዝ እንዳይበልጥ በማሻሻያው ቀርቧል፡፡

የስንብት ክፍያ በሚል አርዕስት ደግሞ ለአንድ ዓመት አገልግሎት መነሻው የሦስት ወራት ደመወዝ ሆኖ፣ ተጨማሪ አገልግሎት ለሰጠ ደግሞ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ ዓመት የአገልግሎት ዘመኑ የመጨረሻ ወር ደመወዝ አንድ ሦስተኛ እየታከለ ሲከፈል የነበረው ተሸሽሏል፡፡ በዚህም መሠረት የሦስት ወራት የሚለው የደመወዝ ክፍያ የስድስት ወራት እንዲሆን፣ አንድ ሦስተኛ የሚለው ደግሞ ሁለት ሦስተኛ እንዲሆን በማሻሻያው ቀርቧል፡፡

የመኖሪያ ቤትን በተመለከተ በአንድ ሚኒስትር በአንድ የምርጫ ዘመን ወይም ግማሽ ያህሉን አገልግሎ ከኃላፊነት ከተነሳ፣ የስድስት ወራት ሙሉ የቤት ኪራይ አበልና ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ ካገለገለ ደግሞ ለእያንዳንዱ ዓመት የአንድ ወር የቤት ኪራይ ሁለት ሦስተኛው ይታከል የነበረው እንዲሻሻል ቀርቧል፡፡

በማሻሻያውም ለሚኒስትር የዘጠኝ ወራት የቤት ኪራይ ሙሉ ወጪና ከአንድ ምርጫ ዘመን በላይ ላለው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ አገልግሎት የአንድ ወር ክፍያ አንድ ሁለተኛው እንዲታከል ቀርቧል፡፡

ማሻሻያው ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡            

 

Standard (Image)

ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የሥነ ምግባር ደንቡ ቅድመ ሁኔታ አይደለም አለ

$
0
0

- መድረክና ሰማያዊ ተሳታፊ ናቸው

- ኢዴፓ ተቃዋሚዎች በቅንጅት እንዲደራደሩ ጥሪ አድርጓል

ኢሕአዴግ ሰላማዊና ሕጋዊ እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡ ከፓርቲዎቹ ጋር የሚደረገው ድርድር ቅድመ ውይይት ረቡዕ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በውይይቱ አካሄድና አጀንዳዎች ላይ ይከናወናል፡፡

በምርጫ ሕጉ አፈጻጸም ዙሪያ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት ገዥው ፓርቲንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማወያየት ኃላፊነት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 መሠረት በተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ካልሆኑ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማድረግ፣ ኢሕአዴግ ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ ይገልጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 21(9) ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ ሲቀረፅ በልዩ ልዩ ምክንያት ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን የጋራ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ መፈረም ይኖርባቸዋል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

በቅርብ በተካሄዱ ምርጫዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ድምፅ ያላቸው መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ ድርድር ለማድረግ ጥሪ በማቅረብ፣ ስምምነቱን አንፈርምም በማለት የምክር ቤቱ አባል ሳይሆኑ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡  

በዚህም መሠረት ኢሕአዴግ የሥነ ምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹የሥነ ምግባር ደንብን መፈረም አለመፈረምን ጨምሮ ምንም ዓይነት መሥፈርት አልተቀመጠም፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ለውይይቱ ጥሪ ያደረገላቸው አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለውይይቱ ጥሪ እንደደረሳቸው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡን ሳይፈርሙ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር መቻላቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ፍላጎት ስላልነበረው ነው እንጂ መፈረምና አለመፈረም ያን ያህል ወሳኝ ጉዳይ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡

በቅድመ ውይይቱ የውይይቱ አካሄድና አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የተገለጸ ቢሆንም፣ ፕሮፌሰር በየነ ግን በውይይቱ ላይ የእርስ በርስ መተማመን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነና በዋነኝነት ለውይይቱ አስፈላጊ የሆነ ምኅዳር ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጅነር) እና በቅርብ በተመረጡት አቶ የሺዋስ አሰፋ መካከል ያለው የይገባኛል ጥያቄ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተመረመረ እንደሚገኝ ሪፖርተር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ ሪፖርተር ከቦርዱ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ይህ በቅርቡ እልባት ያገኛል፡፡

አቶ የሺዋስ ቅድመ ውይይቱን በሚመለከት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በሰማያዊ ፓርቲ ዕይታ ውይይቱ የድርድሩን አካሄድ ለመወሰን፣ ይህም በማን እንደሚመራ፣ መቼ እንደሚካሄድና እንዴት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ለመወሰን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ለመያዝ እንደሆነ እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል በመሆን ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ዕድል የነበረው ኢዴፓም በቅድመ ውይይቱ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣውና ለሪፖርተር የተላከው የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ፣ ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ፓርቲውን ለውይይት መጋበዙን ያረጋግጣል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ የወቅቱ የውይይትና የድርድር ጥሪ ካለፉት የይስሙላ ድርድሮች በተለየ ምን ያህል ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚለው ጥያቄ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ያቀረበውን የወቅቱን የድርድር ጥሪ ኢዴፓ እንደ አንድ በጎ ጅምር በማየት ተቀብሎታል፤›› በማለት በቅድመ ውይይቱ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡

ኢዴፓ በመግለጫው ኢሕአዴግ የሚካሄደው ድርድር እንዳለፉት ድርድሮች ለይስሙላና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ በሚያስችል ውጤት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እንዲደራደር ጥሪ አቅርቧል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በድርድሩ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተበታተነና ባልተቀናጀ ሁኔታ ከኢሕአዴግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር የታሰበውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ተገንዝበው፣ ድርድሩን በተቀናጀ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል የጋራ ምክክር እንዲያካሂዱም አሳስቧል፡፡

ኢዴፓ ‹‹የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት›› ያለው ሕዝብም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ፓርቲዎቹ በአገራዊ የኃላፊነት ስሜት ለድርድሩ ራሳቸውን እንዲያስገዙ የበኩሉን ግፊትና ጫና እንዲያደርግም ጥሪውን አቅርቧል፡፡  

Standard (Image)

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት የተጠረጠሩ የቡና ነጋዴዎች ታሰሩ

$
0
0

በተለያዩ ሰዎች ስም የቡና ላኪነት የንግድ ፈቃድ በማውጣትና ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር መንግሥትን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማሳጣትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ፣ አምስት የቡና ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ታሰሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በርሔ ገብረ መድኅን፣ ዳንኤል ይህደጎ፣ መሰሉ ተፈራ፣ ፋንታሁን ስሜና ሳድቅ ሸደምሴ ረዲ ናቸው፡፡ ሁሉም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች  መንግሥትን የተጠቀሰውን ያህል የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገዙትን ቡና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ደብቀው በመገኘታቸው መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ፖሊስ ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው በርሔ ገብረ መድኅን፣ ዳንኤል ይህደጎና መሰሉ ተፈራ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በተለያዩ ግለሰቦች ስም የቡና ላኪነት ፈቃድ አውጥተዋል፡፡ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋርም በመመሳጠር ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት በጀት ዓመቶች ውስጥ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 1,992.1 ቶን ወይም 19,921 ኩንታል ኤክስፖርት የሚሆን ቡና ገዝተዋል፡፡ ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ሳይልኩ በመቅረታቸውና በመደበቃቸው አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 7,531,200 ዶላር ወይም 147,209,795 ብር የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል፡፡ ፋንታሁን ስሜ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ በ2006 በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 445.5 ቶን ወይም 4,455 ኩንታል ኤክስፖርት የሚሆን ቡና ገዝተዋል፡፡ የገዙትን ቡና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ደብቀው በመገኘታቸው አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 1,491,800 ዶላር ወይም 505,036,808 ብር የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ሳድቅ ሸደምሴ ረዲ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ ከግብር አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር በ2000 በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 178.5 ቶን ወይም 1,785 ኩንታል ቡና የገዙ ቢሆንም፣ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ደብቀው መገኘታቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን 500,700 ዶላር ወይም 5,292,899 ብር የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ማድረጋቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው መሆኑን እንደደረሰበት ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቶ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

 

Standard (Image)

ምርት ገበያ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በኤሌክትሮኒክ ግብይት ማስተናገዱን አስታወቀ

$
0
0

- በክልሎች ሰባት የግብይት ማዕከላትን እንደሚከፍት ገልጿል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከሰባት ዓይነት የግብርና ምርቶች ግብይት 10 ቢሊዮን 108 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ግብይት ማከናወኑን አስታወቀ፡፡ በመንፈቅ ዓመቱ ከ246,652 ሜትሪክ ቶን ምርት አገበያይቷል፡፡

የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በስድስት ወራት ውስጥ የተከናወኑት ግብይቶች 89 በመቶው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መካሄዳቸውን፣ የተቀሩት ግን እንደ ቀድሞው ድምፅን በማስተጋባት በግብይት መድረኩ ተካሂደዋል፡፡

በስድስቱ ወራት ውስጥ የተካሄደው ግብይት በምርት መጠን ሲታይ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የስድስት ከመቶ ቅናሽ ቢያሳይም፣ የምርት ገበያውን ዕቅድ 96 በመቶ ያሳካ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ በምርት ዋጋ በኩልም የዕቅዱን 94 ከመቶ እንደተገበረ ተገልጿል፡፡

ምርት ገበያው ቡና፣ ሰሊጥ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ በቆሎ፣ ማሾና ስንዴ በማገበያየት ላይ ሲሆን፣ ካገበያያቸው ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ የቡና 15 በመቶ እንዲሁም የነጭ ቦሎቄ ግብይት መጠን በ23 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አቶ ኤርሚያስ አብራርተዋል፡፡ በግብይት ዋጋ ረገድ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ19 በመቶ ጭማሪ ከመገኘቱ ባሻገር የቡና ግብይት 35 በመቶ እንዲሁም የነጭ ቦሎቄ ግብይት በ82 በመቶ ዕድገት ማሳየታቸውም ተጠቅሷል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው ውጤት ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ሲተገበር ከቆየው የኤሌክትሮኒክ ግብይት ዘዴ አኳያ አመርቂና ዕድገቱም ጤናማ የሚባል ነው ያሉት አቶ አርሚያስ፣ ምርት ገበያው ገዥና ሻጭ በድምፅ እያስተጋቡ የሚገበያዩበት አሠራር ቀስ በቀስ እየቀረ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡

ተወያዮች ድምፅ እያወጡ በማስተጋባት የሚያካሂዱት ግብይት በርካታ ግድፈቶች፣ ሆን ተብሎም ሆነ በስህተት የሚፈጸሙ የግብይት ሕግ ጥሰቶች ሲስተናገዱበት መቆየቱን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ አዲሱ በኮምፒዩተር የተደገፈ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ግን በተገበያዮች መካከል ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖር ከማድረግ ባሻገር፣ ገዥና ሻጭ እነማን እንደሆኑ የማታወቅበት አሠራር በመሆኑ የግብይት ተዓሚነትን ይበልጥ እንደሚያሰፍን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ አልሳም ጨለለቅ ሕንፃ ላይ የሚገኘው የምርት ገበያው ብቸኛ የግብይት መድረክ ነው፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ በሐዋሳ፣ በነቀምት እንዲሁም በሑመራ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከሎች እንደሚከፈቱ ያስታወቁት አቶ ኤርሚያስ፣ ከሦስቱ በተጨማሪ በጂማ፣ በአዳማ፣ በጎንደርና በኮምቦልቻም ተመሳሳይ የግብይት ማዕከሎች ይፋ እንደሚደረጉና ለገበሬው በቅርብ ሆነው ግብይት ለማካሄድ እንዲቻል እንደሚያግዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በየቀኑ ከ200 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ግብይት እንደሚፈጽም ያስታወሱት አቶ ኤርሚያስ፣ በግብይት ሒደቱ ምንም ዓይነት የውል ጥሰት ችግሮች ሳያስመዘግብ እንደዘለቀ ጠቅሰው፣ ይሁንና በኮንትሮባንድና በመሰል ችግሮች ምክንያት ወደ ምርት ገበያው መግባት ያለባቸው ምርቶች እንዳይገቡ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የስትራቴጂ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ኃይለ ሚካኤል ኃይሌም በኮንትሮባንድ ምክንያት ቀይ ቦሎቄና ማሾ ወደ ምርት ገበያው መምጣት በሚገባቸው መጠን ልክ እየገቡ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ ገበያዎች መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት ለማጥበብ በማሰብ ሲሠራበት የነበረውና ከአራት ዓመታት በፊት የተቋረጠው አሠራር በቡና ላይ በድጋሚ ሊተገበር እንደሚችል አቶ ኤርሚያስ፣ እንዲሁም የምርት ገበያው የኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በኃይሉ ንጉሤ ተናግረዋል፡፡

የመጋዘን አሠራር ከምርት ገበያው ውጭ ከተደረገ በኋላ በመጣው አዲስ አሠራር በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን አቶ ኤርሚያስ ቢገልጹም በምርት ጥራት፣ በጉቦ የምርት ደረጃን ከፍና ዝቅ ለማስደረግ ከቡና ቀማሾች ጋር መደራደር፣ ወዘተ. ያሉት ችግሮች በምርት ገበያው ላይ የሚቀርቡ ስሞታዎች እንደሆኑ በመጥቀስ ጋዜጠኞች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም በላይ ምርት ገበያው ለዓመታት በጥቂት ምርቶች ላይ ብቻ ተወስኖ መቆየቱ ለምን እንዳልተለወጠና አጠቃላይ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ ላይ ዕድገት ይታይበት እንደሆነ ጥያቄዎች ለምርት ገበያው ኃላፊዎች ከቀረቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ባለፈው ዓመት በምርት መጠንና በዋጋ በኩል ምርት ገበያው ከፍተኛ የተባለውን ግብይት ማከናወኑን ያስታወሱት አቶ ኤርሚያስ፣ 632 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምርቶች ተገበያይተው ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ግብይቶች መፈጸማቸው የምርት ገበያውን ጤናማ የዕድገት ጉዞ እንደሚያመላክቱ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምርት ጥራት ቁጥጥር፣ በቡና እርጥበትና በመሳሰሉት ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አብራርተው፣ በቡና ቀመሳ ወቅት በተለይ ቡናው የማን እንደሆነ በማይታወቅበት አሠራር ደረጃ እንደሚወጣ፣ የሚቀርቡ ስሞታዎችም ከእውነታው የራቁ ናቸው በማለት አጣጥለዋቸዋል፡፡ ማጥጥርከማደክቱ

Standard (Image)

የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት መጓተታቸው ተገለጸ

$
0
0

በአገሪቱ ሊካሄዱ የታሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በገንዘብ ዕጦት ምክንያት መጓተታቸውን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ የተቋማቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ለሕዝብ ቀን  ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንዳይሠሩ የሚያደርጉ ጥቃቅን ችግሮች መኖራቸው፣ የፕሮጀክቶችና የሌሎች ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

በዋናነት ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የበጀት እጥረት ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይካሄዱ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ግን የፕሮጀክቶች መጓተት በፋይናንስ ችግር ብቻ እየተሳበበ እንዳይቀጥል፣ ተቋሙ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የሚፈለግበትን እንዲያደርግ መመርያ ሰጥቷል፡፡ 

መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ በውጭ ባለሀብቶችና በመንግሥት ትብብር እንዲገነቡ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 13,699 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የታቀደ ሲሆን፣ 7579 ሜጋ ዋት ከውኃ ኃይል ለማመንጨት ታስቧል፡፡ ከዚህም ውስጥ 3,758 ሜጋ ዋት የሚሆነው በግል ባለሀብቶች እንዲገነባ ተወስኗል፡፡

ከፀሐይ ኃይል 5,200 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የታቀደው ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም 3,600 ሜጋ ዋት የንፋስ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

ይህንን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለበርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጨረታ ያወጣ ቢሆንም፣ ወደ ትግበራ መግባት አልቻለም፡፡ ያወጣቸው ጨረታዎች 2,000 ሜጋ ዋት ከውኃ ኃይል ለማስገኘት ሲሆን፣ የግል ባለሀብቶች በራሳቸው ገንዘብ አልምተው ለመንግሥት እንዲሸጡ የሚጋብዙ ናቸው፡፡ በጨረታው የተሳተፉ ውስን መሆናቸውንና ሒደቱም ሰፊ ድርድርን የማይጠይቅ መሆኑን ለማወቅ ተትችሏል፡፡

ከውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችንም የግል ባለሀብቶች አልምተው የኤሌክትሪክ ኃይል ለመንግሥት እንዲሸጡ ጨረታ ቢወጣም፣ እስካሁን ወደ ስምምነት መድረስ የተቻለው ከአንድ የጣሊያን ኩባንያ ጋር ብቻ ነው፡፡

Standard (Image)

በአነስተኛ ካፒታል የተቋቋሙ የልማት ድርጅቶች ካፒታላቸው ሊያድግ ነው

$
0
0

- ለተጓተቱ ፕሮጀክቶች ጥፋተኛው ተለይቶ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቢያ ተሰጠ

በአነስተኛ ካፒታል የተቋቋሙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ካፒታላቸውን ለማሳደግ ዕቅድ ተያዘ፡፡ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚቆዩ ነገር ግን በአነስተኛ ካፒታል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ካፒታል በማሳደግ ምርታማነታቸው እንዲጨምር ለማድረግ መታቀዱ ታውቋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትሩ አቶ ግርማ አመንቴ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ አነስተኛ ካፒታል ያላቸውን የልማት ድርጅቶች ካፒታላቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ ግርማ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

አነስተኛ ካፒታል ካላቸው የልማት ድርጅቶች መንግሥት ጠቀም ያለ ፋይናንስ እንዲያገኙ አድርጎታል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ጎልተው የወጡት የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች መዘግየት ናቸው፡፡

እነዚህ ከ15 በላይ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ላይ መንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢያፈስም፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቀቃቸው መጠነ ሰፊ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት በርካታ ምክንያቶች ቢነሱም በዋናነት የቀረቡት ግን፣ በቂ ፋይናንስና የመንገድ አውታር ሳይኖር ወደ ሥራ መግባት፣ የቦታ አመራረጥ ስህተትና በተገቢው መንገድ የአዋጭነት ጥናት አለማካሄድ ናቸው፡፡  

አቶ ግርማ እንደገለጹት፣ ለእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠያቂው ማነው በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኖቹ? ወይስ ግንባታውን የሚያካሂዱ ኮንትራክተሮች ናቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

አቶ ግርማ ጨምረው እንደገለጹት፣ የሚካሄደው ምርመራ ሲጠናቀቅ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘው አካል ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከነባር ስኳር ፋብሪካዎች በተጨማሪ 11 ስኳር ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከአዳዲሶቹ ስኳር ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ በደካማ የሥራ አፈጻጸም ሒደት ውስጥ የሚገኙና እጅግ የተጓተቱ ናቸው፡፡ ከስኳር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ ተብለው የተጀመሩት የማዳበሪያ ፋብሪካዎችም ግንባታ በጣም መዘግየቱ ይታወሳል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በስኳርና በማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ ለታየው ከልክ ያለፈ መጓተት ተጠያቂ አካላት ተለይተው ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

 

Standard (Image)

ተሸናፊው የጋምቢያው መሪ ዕውቅና መነፈጋቸውን ኢትዮጵያ ደገፈች

$
0
0

- የአፍሪካ ኅብረት አዲሱን ተመራጭ አዲስ አበባ ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ሊጋብዛቸው ነው

ባለፈው ወር በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን ለማስረከብ አሻፈረኝ ያሉትን የጋምቢያ መሪ፣ የምዕራብ አፍሪካ አገሮችና አፍሪካ ኅብረት ዕውቅና አንሰጥም ማለታቸውን ኢትዮጵያ ድጋፏን ቸረች፡፡

በምዕራባዊቷ አፍሪካዊ አገር ጋምቢያ በታኀሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የተቃዋሚው መሪ አዳማ ባሮው፣ አገሪቱን ለ22 ዓመታት ያስተዳደሯትን ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህን ሳይጠበቅ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ በምርጫው ማግሥት ፕሬዚዳንቱ ጃሜህ መሸነፋቸውን በመግለጽ ለተተኪው ሥልጣን በአግባቡ ለማስረከብ ፈቃደኝነታቸውን ቢያሳዩም፣ ከቀናት በኋላ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት እንዲደገም ጠይቀዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ያህያ ጃሜህን ወዲያው በማውገዝ ሥልጣናቸውን ለአሸናፊው እንዲያስረክቡ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ)፣ ወታደራዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አገሮቹ አስታውቀዋል፡፡

ሐሙስ ጥር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በኒውዮርክ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤኮዋስ ለጃሜህ ዕውቅና አለመስጠቱን በሙሉ ድምፅ የደገፈው ሲሆን፣ ቅድሚያ ግን በዲፕሎማቲክ ጥረት ጃሜህን እንዲለቁ ማድረጉ ይበጃል ሲልም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ለፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ቋሚ ያልሆነ ውክልና አግኝታ የተመረጠችው ኢትዮጵያም የኤኮዋስን ዕርምጃ በተመለከተ ድምፅ በመስጠት፣ የማኅበረሰቡን ዕርምጃ በመደገፍ ለአዲሱ ተማራጭ ፕሬዚዳንት ባሮው ድጋፏን አሳይታለች፡፡

የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመሄዳቸው በፊት አፋጣኝ ዕርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት ሊፈቀድ አይገባም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ በበኩላቸው ተማራጩ ባሮው በጎረቤት አገር ሴኔጋል በሚገኘው የጋምቢያ ኤምባሲ ቃለ መሀላ መስጠታቸውን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኮሚሽነሯም አዳማ ባሮው ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ በሚጀምረው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንዲገኙ፣ ከሌሎች የአኅጉሪቷ መሪዎች ጋር ትውውቅ እንዲያደርጉ እንደሚጋብዟቸውም ገልጸዋል፡፡

የቀጣናው አገሮች ኤኮዋስ በጋምቢያ ለሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ሴኔጋልን በፊታውራሪነት የመረጡ ሲሆን፣ የሴኔጋል ጦር ባለፈው ሐሙስ ከቀትር በኋላ የጋምቢያን ድንበር አልፎ በመግባት ወደ ዋና ከተማዋ ባንጁል መቃረቡን የሴኔጋል መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ግን ጦርነትና ኃይል የመጠቀምን አማራጭ አልደገፈም፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሐሙስ ቀትር ላይ ሥልጣን እንዲያስረክቡ ቢጠበቁም፣ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም በፓርላማቸው አማካይነት የሦስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ በሥልጣን እንደሚቆዩ ገልጸዋል፡፡

ኤኮዋስ እስከ ዓርብ ቀትር ድረስ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን በማስረከብ አገሪቱንም እንዲለቁ ጊዜ የሰጣቸው ሲሆን፣ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ጃሜህ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ተስማምተዋል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረትና አባል አገሮች በተጨማሪ፣ አሜሪካና ሌሎች የምዕራብ ኃያላን አገሮች ጃሜህ መልቀቅ እንዳለባቸው በመጠየቅ ለአዲሱ ተመራጭ ዕውቅናቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

Standard (Image)

ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ስምምነት ፈረመች

$
0
0

በኢትዮጵያና በታንዛኒያ መንግሥታት መካከል ሲካሄድ የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ድርድር ተጠናቆ፣ ከረቡዕ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በታንዛኒያ አሩሻ ከተማ ሲካሄድ ከቆየው የምሥራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር ጉባዔ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነቱ ተፈረመ፡፡

ታንዛኒያ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከጂቡቲና ከሶማሌላንድ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት የተፈራረመች አምስተኛ አገር ሆናለች፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአንድ ኪሎ ዋት 11 የአሜሪካ ሳንቲም ክፍያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡

በስብሰባው ለመካፈልና የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነቱን ለመፈረም የተጓዘውን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የመሩት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕላኒንግ ዳይሬክተር አቶ መኩሪያ ለማን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ለመሆን እየሠራች የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ለታንዛኒያ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ያቀደችው በኬንያ በኩል ነው፡፡

ከደቡብ ክልል ወላይታ ዞን (ሶዶ ከተማ) ጀምሮ እስከ ኬንያ ድረስ 400 ኪሎ ቮልት መሸከም የሚችል ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር እየተገነባ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የሚለቀቀውን ኃይል ታንዛኒያ ከኬንያ ድንበር እንደምትቀበል ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከቡሩንዲ፣ ከሩዋንዳና ከየመን ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማ የተለያዩ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ቀጣዩ ስትራቴጂ በጂቡቲ በኩል የመንን አቋርጦ ለሳዑዲ ዓረቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ፕሮጀክት መጀመር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከውኃ ብቻ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት፡፡ 

Standard (Image)

ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ስምምነት ከግብፅ ጋር አለመፈጸሟን አስታወቀች

$
0
0

ደቡብ ሱዳን ሰሞኑን ከግብፅ ጋር ባደረገችው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚጎዳ የሴራ ስምምነት ፈጽማለች ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ሐሰት መሆኑን ገለጸች፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታ ሞርጋ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት የተለመደው የሁለትዮሽ የወዳጅነት ግንኙነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ረዳት አተም ደንግ ዋለዋለ በበኩላቸው፣ ‹‹በደቡብ ሱዳን የውጭ ግንኙነት ላይ ማንም ሊያዝ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

የተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች በስም ያልተጠቀሱ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣንን እንደ ምንጭ በመጠቀም ባወጡት ዘገባ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በካይሮ ተገናኝተው ‹‹‹አግባብ ያልሆነ ስምምነት›› መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስምምነት ግብፅ በደቡብ ሱዳን በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አደጋ መጣል እንድትችል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ እንዳይረጋጋ ለማድረግ መስማማታቸውን ዘግበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በሰጡት ቃለ ምልልስ ግን ይኼንን ዘገባ መሠረተ ቢስ ብለውታል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ባለፈው ሳምንት ግብፅን ሲጎበኙ በይፋ በወጣው መረጃ መሠረት፣ ግብፅ የደቡብ ሱዳን መንግሥትን በተለያዩ ዘርፎች ለመርዳትና ወቅታዊ የደቡብ ሱዳን ቀውስን ለመፍታት እንደምትሠራ አሳውቃለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵም ሆነ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀጣና ፈተና መሆኗን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በተቃዋሚዎቹ መካከል የሰላም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፣ ይህንን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል የኢጋድ አባል አገሮችም ሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋናዮች የተለያየ አቋም መያዛቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትም በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን፣ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በደቡብ ሱዳን ሁኔታ ላይ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡  

 

Standard (Image)

በአቶ ይልቃል የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ ቡድን ኢሕአዴግ ከጠራው የፓርቲዎች ውይይት እንዲወጣ ተደረገ

$
0
0

ኢሕአዴግ ለቅድመ ውይይት ከጠራቸው 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በአቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ ቡድን የተገኘ ቢሆንም፣ በውይይቱ ላይ መሳተፍ የቻለው እስከ ሻይ ዕረፍት ድረስ ብቻ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ የሰማያዊ ፓርቲ ትክክለኛ መሪ ማን እንደሆነ በትክክል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ማለትም የተወሰኑ አባላት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መሆናቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ አቶ ይልቃል ጌትነት መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ለቅድመ ውይይት ባለቀ ሰዓትም ቢሆን እንዲገኙ ጥሪ ያቀረበላቸው ለእነ አቶ ይልቃል መሆኑን፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

በውይይቱ ላይ እስከ ሻይ እረፍት ድረስ መሳተፋቸውን የገለጹት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት አቶ ስለሺ ፈይሳና አቶ ይድነቃቸው አዲስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እነሱን ጨምሮ በውይይቱ ላይ 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፡፡

ነገር ግን ለሻይ እረፍት ወጥተው ሲመለሱ፣ እነ አቶ ስለሺ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ መጠራታቸውን፣ አቶ ሽፈራው ጠርተዋቸው ሕጋዊ የሰማያዊ ፓርቲ መሪ ማን እንደሆነ ሲጠይቋቸው፣ እነሱ የሚያውቁትና በምርጫ ቦርድም የሚታወቁት አቶ ይልቃል ጌትነት መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ተወካዮቹ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲ በመደበኛ ጉባዔ የተመረጠ መሪ እንዳለው አቤቱታ ቀርቦላቸው፣ ከምርጫ ቦርድ ሲያረጋግጡ ትክክል መሆኑን ስለተረዱ ከሻይ ዕረፍት በኋላ መሳተፍ እንደማይችሉ ተገልጾላቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እያለ ኢሕአዴግ የሚፈልገውንና የሚስማማውን የፓርቲ መሪ እሱ የሚወስን መሆኑንና ይኼ ደግሞ በእነሱ የተጀመረ ባለመሆኑ ብዙም እንዳልገረማቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ እንደ አገር ተገቢ አለመሆኑንና ሕግ ሊከበር እንደሚገባም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውን የገለጹትና ስለሰማያዊ ፓርቲ ማብራሪያና አቋማቸውን መግለጻቸውን የተናገሩት ሌላው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አገርና ሕዝብን የማረጋጋት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጥሪ ማቅረባቸውን ለሪፖርተር ተልጸዋል፡፡ በአቶ የሺዋስና በአቶ ይልቃል መካከል ያለውን ‹‹እኔ ነኝ ሊቀመንበር›› ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ምርጫ ቦርድ እያጠናው መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢሕአዴግ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ቅድመ ውይይት ላይ የተገኙት 22 ፓርቲዎች፣ የየራሳቸውን ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማስገባት መስማማታቸው ታውቋል፡፡ አራት የተስማሙባቸው ነጥቦችም ቀጥሎ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች በማን እንደሚመሩ፣ በውይይቱ ላይ እነማን በታዛቢነት እንደሚሳተፉ፣ ውይይቱ ምን ዓይነት የአካሄድ፣ የአጀንዳና የንግግር ሥርዓት እንደሚኖረውና ከውይይትና ከድርድር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እንዴት እንደሚሰጡ የሚገልጹ መሆኑም ታውቋል፡፡      

Standard (Image)

የግል ባንኮች ውህደት አይቀሬ መሆኑ ተገለጸ

$
0
0

የግል ባንኮች ወደፊት በሚቀመጥላቸው የጊዜ ገደብ የካፒታል መጠናቸውን ማሟላት የማይችሉ ከሆነ፣ ወደ ውህደት ማምራታቸው የማይቀር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ገለጹ፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ባንኮች እንዲጠናከሩ ከዚህ በኋላ ካፒታላቸውን ማሳደግና አገልግሎታቸውን ማስፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ካፒታል ማሳደግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው የተገለጸላቸው መሆኑን ያስታወሱት ገዥው፣ ከዚህ በኋላ ካፒታላቸውን ምን ያህል ማድረስ እንደሚገባቸው በመንግሥት ውሳኔ መሠረት እንደሚገለጽ አመልክተዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውን ካፒታል በምን ያህል ጊዜ ማሟላት እንዳለባቸው ጭምር ከታወቀ በኋላ፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚጠቀሰውን የካፒታል መጠን ካላሟሉ እንዲዋሀዱ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም ለመፍጠር ከተፈለገ ውህደት የማይቀር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹አዲስ እየተጠና ያለው ጥናት ከተጠናቀቀና ውሳኔ ከተሰጠው በኋላ ውህደት ግዴታ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ከአገሪቱ ባንኮች አፈጣጠር አኳያ አንዱን ከአንዱ ማዋሀድ እንዴት ይቻላል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ እነዚህን የፋይናንስ ተቋማት የሚያውቃቸው እንደ አንድ አትራፊ ሼር ኩባንያ ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አንፃር፣ ባንኮች የያዙት ገንዘብም የሕዝብ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ባንኮች በአሁኑ ወቅት በቁጠባ የሰበሰቡት ገንዘብ ከ467 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የመንግሥትም ሆነ የግል ባንኮች በድምሩ ያላቸው ካፒታል 30 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የካፒታል ገንዘብ ሲቀነስ ቀሪው 437 ቢሊዮን ብር የሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ገንዘብ በተገቢው መንገድ እንዲሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና መንግሥት ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

መንግሥት ወደዚህ ዕርምጃ ሊገባ የሚችለው ግን አዲስ በተጠናው ጥናት መሠረት፣ ባንኮቹ ሊደርሱበት ይገባል ተብሎ የሚወሰነውን የካፒታል መጠን በተቀመጠው ጊዜ ማሟላት ካልቻሉ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ባንኮች ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ አለባቸው የተባለ ሲሆን፣ ለዚህ ግን ቀነ ገደብ አልተቀመጠም፡፡ በአዲሱ ጥናትም ባንኮች መድረስ የሚገባቸውን የካፒታል መጠን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ይሁን አይሁን አቶ ተክለወልድ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ሆኖም አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ውህደት ይኖራል ተብሏል፡፡ የውጭ ዜጎች፣ የውጭ ኩባንያዎች፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲገቡ ሊፈቀድ የሚችል ቢሆንም፣ ጊዜው አሁን አለመሆኑን ከአቶ ተክለወልድ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በ10.5 ቢሊዮን ብር ሊገነቡ ነው

$
0
0

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በአዲስ አበባና ጂማ ከተሞች በ10.5 ቢሊዮን ብር ሊገነባ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ ፓርክ በቦሌ ለሚ በ3.5 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፣ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ ነው፡፡ የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና ለአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ልማት የተመደበ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ግንባታ የሚያከናውነው ‹‹ሲጂሲኦሲ›› የተሰኘ የቻይና ኮንትራክተር ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አማካሪ ዶዋ የተባለ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚካሄደው በአቃቂ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ አካባቢ ነው፡፡ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ የሚለማበት ሲሆን፣ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች የሚፈበረኩበት ይሆናል፡፡ በ5.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ12 ወራት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡

ግንባታውን የሚያካሂደው ‹‹ሲቲሲኢ›› የተባለው የቻይና ኮንትራክተር ሲሆን፣ ዶዋ የተባለው የኮሪያ ኩባንያ ፕሮጀክቱን እንዲቆጣጠር ተመርጧል፡፡ ሦስተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገነባው በጂማ ከተማ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ የተኮረ ነው፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነው በኢትዮጵያ ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን የሚያካሂደው ‹‹ሲሲሲሲ›› የተሰኘው የቻይና ኮንትራክተር ነው፡፡ ‹‹ኤምኤች›› ኢንጂነሪንግ የተባለው አገር በቀል አማካሪ ኩባንያ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ እንዲሆን ተመርጧል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሦስቱን ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ ውል ከሦስቱ የቻይና ኩባንያዎች ጋር ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ የቦሌ ለሚ ሁለትና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የሚካሄደው፣ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ158 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ የዓለም ባንክ የግዢ ሥርዓትን መከተሉን ተናግረዋል፡፡ የጂማ ኢንዲስትሪ ፓርክ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መንግሥት በመደበው በጀት የሚካሄድ በመሆኑ፣ የመንግሥት የግዢ ሥርዓትን ተከትሎ እንደተካሄደ አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት አቶ ሲሳይ፣ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ አምራች የሰው ኃይል የሚፈልግና የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በመቀጠልም ለፋርማሲቲካል፣ ለኬሚካል፣ ለብረታ ብረትና ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሲሳይ በቀጣይ ለሚለሙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚውል ብድር ከቻይና ኤግዚም ባንክና ከአውሮፓ ልማት ባንክ ሊገኝ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

በየተራ አጠር ያሉ ንግግሮች ያሰሙት የሦስቱ ቻይና ኩባንያዎች ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማልማት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የወጪ ንግዱ ለማሳደግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው የተሰጣቸውን ፕሮጀክት በከፍተኛ ጥራትና በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ አንድና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በከፍተኛ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመቐለ፣ የኮምቦልቻ፣ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ላይ ነው፡፡ አቶ ሲሳይ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀመር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ 

Standard (Image)

የጅሃድ ጦርነት ለማወጅ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው

$
0
0

- የግንቦት ሰባትን የትጥቅ ትግልን ሊቀላቀሉ ሞክረዋል የተባሉ ተከሰሱ

ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው አክራሪ የሽብር ቡድን ጋር ከተገናኙና ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የጅሃድ ጦርነት ለማወጅ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል የተባሉ ተከሳሾች ከአራት ዓመት በላይ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡

ፍርደኞቹ ጃፋር መሐመድ፣ መሐመድ ኑር፣ ሐጂ መሐመድ ታሚ፣ አንዋር ቲዳኔና ሼህ ጀማል ያሲን፣ መሐመድ አባቢያና ሼህ ጀማል አባ ጨቦ ናቸው፡፡ የአክራሪነት ሥልጠና ለመውሰድ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው አክራሪ ቡድን በተጨማሪ ወደ ሶማሊያ በመሄድ ከአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋርም መሠልጠናቸውን፣ የቅጣት ውሳኔ የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ገልጿል፡፡

ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የአክራሪነት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ሌሎች አባላትን መመልመላቸው፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰው ማስረጃዎች ማረጋገጡን ውሳኔው ያሳያል፡፡ ፍርደኞቹ በጅማ አካባቢ በሚገኙ ጫካዎች አዲስ ለተመለመሉ አባላት ሥልጠና ከሰጡ በኋላ፣ ለተጨማሪ ወታደራዊ ሥልጠና ወደ ሶማሊያ በመሄድ አልሸባብን ለመቀላቀል የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማዘጋጀት ላይ እያሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም፣ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃው ማረጋገጡን ውሳኔው ይጠቁማል፡፡

ፍርደኞቹ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ስላስረዳባቸው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ቢሆንም፣ ባቀረቡት ማስረጃ ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው የውሳኔው ሰነድ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም መሐመድ ኑር፣ ሙዲን ጀማልና ሼህ ጀማል አባ ጨቦ እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ጃፋር መሐመድ፣ መሐመድ አባቢያና አንዋር ቲዳኔ ደግሞ እያንዳንዳቸው በአራት ዓመታት ከአምስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነው አቶ መልካሙ ገበየሁና ምሥራቅ ጐጃም እንደሚኖሩ የተገለጸው አቶ አንሙት ታሞ፣ አቶ ሲመሽ አስማሴና አቶ ባዬ ደሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል በመሆን የድርጅቱን የትጥቅ ትግል ለመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን ተመልምለውና ሌሎችን በመመልመል በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ሌሎች ነዋሪዎችን ለመቀስቀስና ድርጅቱ የሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ይዘው እንዲቀርቡና ጠበቃ ለማቆም አቅም የሌላቸው መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ለጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጥሮአቸዋል፡፡ 

Standard (Image)

የጥጥ ምርትን በወቅቱ ኤክስፖርት ማድረግ እንዳልተቻለ ተገለጸ

$
0
0

- ኤክስፖርት እንዲፈቀድ ተጠየቀ

ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ግብዓት የሆነው የጥጥ ምርት ለገበያ በሚቀርብበት በዚህ ወር፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሠራተኞች ስብሰባ በመግባታቸውና ከተሃድሶ ከወጡ በኋላም የመመርመሪያ ላቦራቶሪው በመበላሸቱ ግብይቱ መስተጓጐል ገጠመው፡፡

ያመረቱትን የጥጥ ምርት ለገበያ ያቀረቡ ባለሀብቶች በወቅቱ መሸጥ ባለመቻላቸው፣ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ስለሆነ ኤክስፖርት ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ጠየቁ፡፡

በጥጥ አቅራቢዎችና በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መካከል ያለውን የጥጥ ግብይትን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ግብይት የሚፈጸምበትን 510 ሚሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አግኝቷል፡፡

ነገር ግን ይህንን ግብይት ለመፈጸም ተዳምጦ መጋዘን የገባውን ጥጥ ደረጃ የሚያወጣለት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ሠራተኞችን በሙሉ ይዞ ስብሰባ በመቀመጡ፣ ከስብሰባ ከተወጣም በኋላ የመመርመርያ መሣሪያዎች የቴክኒክ ብልሽት ስለገጠማቸው፣ ባለሀብቶች ያስገቡትን ጥጥ በወቅቱ መርምሮ ማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋወሰን አለነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግብይት ለመፈጸም የግድ የኢንስቲትዩቱ የምርመራ ውጤት ያስፈልጋል፡፡

‹‹ባለፈው ዓርብ ጀምሮ የመመርመርያ ላብራቶሪው መበላሸቱ ተገልጾልኛል፡፡ ነገር ግን ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. መመርያ ማሽኑ እንደተጠገነ ተገልጾልኛል፤›› ሲሉ አቶ አስፋወሰን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዘመናዊ የመመርመርያ መሣሪያ ባለቤት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዘመናዊ መመርመርያ ማሽን የቴክኒክ ብልሽት የሚገጥመው በመሆኑና ብልሽቱን ለመጠገን በቂ ባለሙያዎች ስለሌሉ ባለሀብቶች እንደሚመረሩ ይናገራሉ፡፡

የኢንስቲተዩቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ ለሪፖርተር፣ ‹‹የቴክኒክ ብልሽት በየጊዜው ያጋጥማል፡፡ ጥገናውን ለማካሄድ የተወሰኑ ቀናት ወስደውብናል፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ያሰፋው ለስምንት ቀናት የ‹ጥልቅ ተሃድሶ› አካል ነው የተባለው ስብሰባ ላይ ስለነበሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢንስቲትዩቱ ያለው ማሽን በሚፈለገው ደረጃ ምርመራ ማካሄድ የሚችል ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ መሰለ ማሽኑ፣ ማክሰኞ ግን ተጠግኖ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በማሽን ብልሽትና በስብሰባ ምክንያት በአግባቡ አገልግሎት አላገኘንም ካሉ ባለሀብቶች መካከል አቶ አብረሃለይ ይደግ ይገኙበታል፡፡

አቶ አብረሃለይ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ማክሰኞ ጥር  16 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ለመሸጥ ያስገቡት 826,215 ኩንታል ጥጥ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥጡ ተመላሽ እንዲሆንላቸው የጠየቁበትን ምክንያት አቶ አብረሃላይ ሲገልጹ፣ ያስገቡት ከዛሬ ነገ ‹አልተመረመረም›፣ ‹ማሽን ተበላሸ›፣ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እየተባለ እሳቸው በማይመለከታቸው ጉዳይ መጉላላታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ እንግልትና ጉዳት ደርሶብኛል፤›› ሲሉ በደብዳቤ የገለጹት አቶ አብረሃለይ፣ ‹‹አሁን ግን ሠራተኞቼ ክፍያ ልፈጽምላቸው ባለመቻሌ የተሰበሰበውን ምርትና ካምፑን ለማቃጠል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፤›› ሲሉ ምርቱ እንዲመለስላቸውና በርካሽም ቢሆን ለሌላ ገበያ ለማቅረብ መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅዶቹን ለውይይት ባቀረበበት ወቅት፣ የጥጥ ግብይት መመርያ እየተሻሻለ መሆኑንና ሲበላሽ የቆየው ላብራቶሪም እንደተሠራ ገልጾ ነበር፡፡

ነገር ግን ችግሩ በየወቅቱ እያጋጠመ በመሆኑ ሌሎች አማራጮች እንዲታዩላቸው ባለሀብቶቹ እየጠየቁ ነው፡፡ አገር ውስጥ በሥርዓቱ ግብይት መፈጸም ካልተቻለ ኤክስፖርት ማድረግ ሊፈቀድ ይገባል ሲሉ፣ ባለሀብቶች ለመንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡

Standard (Image)

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የገቢ አፈጻጸም አሽቆለቆለ

$
0
0

 

ባለፉት ስድስት ወራት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የወጪ ንግድ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ማሽቆልቆሉ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው 349 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሊገኝ የቻለው 198.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጿል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት የስድስት ወራቱ የገቢ አፈጻጸም 56.5 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው መገኘት የተቻለው 55.5 በመቶ ያህሉ ብቻ ሲሆን፣ ይኼም ካለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በ0.5 በመቶ ቅናሽ ያሳየ መሆኑን፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች የገቢ ዕቅድ የተገኘው 50.4 በመቶ ካለፈው ዓመት 7.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ከሥጋ የወጪ ንግድ የገቢ ዕቅድ ሊገኝ የተቻለው 61.6 በመቶ ያህሉ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ5.1 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የወጪ ንግድ ገበያ መቀዛቀዝ በቆዳ ዘርፍ ለታየው የኤክስፖርት አፈጻጸም ጉድለት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተመሳሳይ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያትና የተሻለ ትርፍ ፍለጋ የአገር ውስጥ ገበያ ላይ በማተኮሩ የገቢ አፈጻጸም ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰጠው አስተያየት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢንቨስተሮች ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ማበረታታትና የበለጠ ምርት በመላክ የተገኘውን ገበያ መጠቀም እንዳለበት አሳስቧል፡፡ 

Standard (Image)

ገቢዎችና ጉምሩክ አራት ተከሳሽ ድርጅቶች በመንግሥት ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም አለ

$
0
0

ሚሌ ላይ ተመርጠው ፍተሻ ሳይደረግባቸው እንዲያልፉ የተደረጉ አራት ድርጀቶች ማለትም የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ከተማ ከበደ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የአቶ ጌቱ ገለቴ ጌትአስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሱት ጉዳት እንደሌለ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

ድርጅቶቹ ጉዳት እንዳላደረሱ ወይም ሳይከፍሉ የቀሩት ታክስና ቀረጥ፣ እንዲሁም የመንግሥት ገቢ እንደሌለ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያስታወቀው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡                        

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141356 ውስጥ ተካተው በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት አራቱ ድርጅቶች፣ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከሚሌ ፍተሻ ጣቢያ ሳይፈተሹ እስከ መዳረሻ አቃቂ ቃሊቲና ለገሐር ጉምሩክ ድረስ ታክስ ሳይከፍሉ ቀርተው፣ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሱት ጉዳት መኖር ለመኖሩን አጣርቶ ማስረጃ እንዲያቀርብ ባለሥልጣኑ መታዘዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ደብዳቤ በችሎት ተነቧል፡፡ ባለሥልጣኑ ባደረገው ምርመራ ድርጅቶቹ ያልከፈሉት ታክስና ግብር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ባለሥልጣኑን ምላሽ ከሰጠ በኋላ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ተቃውሞ ዓቃቤ ሕግ የተጠየቀውን ማብራሪያ በሚመለከት ክስ ሳያቀርብ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት እንደሌለበት ተናግረው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በትዕዛዙ መሠረት ድርጅቶቹ ጉዳት አድርሰዋል ቢባል እንኳን ባልተከራከሩበት ጉዳይ እንዴት ብይን ሊሰጥባቸው እንደሚችልም በማንሳት አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ለፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ ትዕዛዙ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾ ምላሽ መስጠቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

 

Standard (Image)

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የመጨረሻ ዙር ውይይት እየተካሄደ ነው

$
0
0

 

   - በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፀድቃል ተብሏል

ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ላይ ከወረዳ አመራሮች ጋር የመጨረሻ ዙር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽነር አቶ ማቴዎስ አስፋው እንደገለጹት፣ አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን በቀናት ውስጥ ፀድቆ በይፋ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት 116 ወረዳዎች እያንዳንዳቸው 25 አመራሮች አሏቸው፡፡ በአጠቃላይ 2,900 ከሚሆኑት እነዚህ የወረዳ አመራሮች ጋር በአራት ዙር ከሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ከክፍላተ ከተሞች ጋር በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡ በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ 28 ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከ28 ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት በባለሙያ የሚመራ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ 27 አመራሮች አሉት፡፡ በድምሩ 270 ለሚሆኑ አመራሮችና በማዕከል ከሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የወረዳ፣ የክፍላተ ከተሞችና የማዕከል ምክር ቤቶችና የተለያዩ ፎረሞች በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ መድረኮች ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች እየተገባደዱ በመምጣታቸው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ማስተር ፕላኑ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡

‹‹አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ ገልጸው፣ ‹‹ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ሰዎች ማስተር ፕላን የመሐንዲሶች ጉዳይ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ነገር ግን የማስተር ፕላን ዝግጅት የብዙ ባለሙያዎችንና ፖለቲከኞችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፤›› ሲሉ በተለይ የወረዳ አመራሮች ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በውይይቱ ወቅት አሳስበዋል፡፡

በማስተር ፕላን ዝግጅቱ ወቅት በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቦርዱ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡

አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር ሲካሄድ ቆይቶ፣ በተነሱ አለመግባባቶች ማስተር ፕላኑ በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

አዲሱ ማስተር ፕላን በነባሩ የአዲስ አበባ መዋቅር ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ለማድረግ አስገድዷል፡፡ አቶ ማቴዎስ እንደገለጹት አሥሩ ነባር ክፍላተ ከተሞች ወደ 13 ከፍ እንዲሉ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ነባሮቹ 116 ወረዳዎች ወደ 120 ወረዳዎች ከፍ ይላሉ፡፡

ይህ ማሻሻያ የሚደረገው በተለይ ቦሌና አቃቂ ክፍላተ ከተሞች ከሌሎቹ ክፍላተ ከተሞች ጋር ሲነፃፀሩ የቆዳ ስፋታቸው በእጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ፣ ለአስተዳደራዊ ሥራዎች ባለመመቸታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

አዲስ አበባ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን ጊዜ ወደ ጐን ስትለጠጥ ቆይታለች፡፡ በአዲሱ ማስተር ፕላን ግን ወደ ጐን መለጠጧን አቁማ ወደ ላይ ከፍ ማለት እንደምትጀምር አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ካላት 54 ሺሕ ሔክታር መሬት 30 በመቶውን ለአረንጓዴ ልማት፣ 30 በመቶውን ለመንገድ አውታር ግንባታ፣ ቀሪውን 40 በመቶ ለተለያዩ ሕንፃዎች ግንባታ እንደምታውለው ተገልጿል፡፡

ይህ መሠረተ ልማት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት አራት ሚሊዮን በተጨማሪ፣ 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚያስተናግድ ታሳቢ ተደርጐ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ይህንንም ለማሳካት ከተወሰኑ ልዩ ባህሪ ካላቸው ግንባታዎች በስተቀር የሚገነቡ ሕንፃዎች አፓርትመንቶችን አካተው እንደሚገነቡ፣ ጥግግቱም እንዲጨምር ተደርጐ ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ የነበረው የመኖሪያ ቤቶች የወለል ስፋት 30 ካሬ ሜትር ወደ 90 ካሬ ሜትር እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ አዲሱ ማስተር ፕላን አዲስ አበባ ከተማ በቂ የመኖሪያ ሥፍራ፣ የመሥሪያ ቦታና የመዝናኛ ቦታ እንዲኖራት የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ የአፍሪካ መዲና መሆኗንም የሚያረጋግጡ ግንባታዎችን ታካሂዳለች ተብሏል፡፡

በውይይቱ ወቅት የወረዳ አመራሮች ላቀረቧቸው ጥያቄዎች አቶ ማቴዎስና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባው አማካሪ አቶ ተወልደ ገብረተንሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

Standard (Image)

የግል ባንኮች በግማሽ ዓመት 3.4 ቢሊዮን ብር አተረፉ

$
0
0

በአገሪቱ በሥራ ላይ ያሉ 16 የግል ባንኮች በ2009 ግማሽ በጀት ዓመት ወደ 3.4 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሲያገኙ፣ ሁለት ባንኮች ደግሞ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋቸው ታወቀ፡፡

የባንኮቹን የስድስት ወራት ክንውን የሚያመላክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያስመዘገቡት ግርድፍ የትርፍ መጠን፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ470 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

ባለፈው ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ሁሉም የግል ባንኮች 2.92 ቢሊዮን ብር አትርፈው እንደነበር በንፅፅር የተቀመጠው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ሙሉ በጀት ዓመት ደግሞ ከ6.05 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋቸው የሚታወስ ነው፡፡

ባንኮቹ በአገሪቱ ውስጥ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በአፈጻጸማቸው ላይ ችግር ይፈጥራል ተብሎ የተሠጋ ቢሆንም፣ ያስመዘገቡት ትርፍ ግን ከሥጋቱ ጋር የማይነፃፀር ሆኗል፡፡ ሁሉም ባንኮች በአትራፊነታቸው የቀጠሉ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

ሆኖም ከ16 የግል ባንኮች አምስት ባንኮች ብቻ በ2008 ግማሽ በጀት ዓመት አግኝተውት ከነበረው የትርፍ መጠን በተወሰነ ደረጃ ቅናሽ ቢታይባቸውም፣ ሁሉም ባንኮች በዘንድሮው ግማሽ በጀት ዓመት ካለፈው ግማሽ ዓመት የበለጠ ትርፍ አግኝተዋል፡፡

እንደ መረጃዎች ከሆነ የግል ባንኮቹ በጥቅል ያስመዘገቡት ትርፍ እያደገ ከመምጣቱም በላይ፣ ሁለት ባንኮች በ2009 ዓ.ም. ግማሽ የበጀት ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ችለዋል፡፡

የአንድ የግል ባንክ የግማሽ በጀት ዓመት ትርፍ ግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ ባያውቅም፣ በ2009 በጀት ዓመት ግን አዋሽና ዳሽን ባንኮች ለመጀመሪያ ጊዜ በግማሽ በጀት ዓመት የትርፍ መጠናቸውን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል፡፡

በግማሽ በጀት ዓመቱ የተገኘው የሁለቱ ባንኮች የትርፍ መጠን፣ ምናልባትም በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ላይ እያንዳንዳቸው ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ዓመታዊ ትርፍ ያገኛሉ የሚለውን ግምት አሳድሯል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት አዋሽ ባንክ አግኝቶ የነበረው ጥቅል ትርፍ ከ450 ሚሊዮን ብር ያነሰ ሲሆን፣ ዳሽን ባንክ ደግሞ ከ400 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡

በ2008 በጀት ዓመት አዋሽ ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.04 ቢሊዮን ብር በማትረፍ፣ በአንድ በጀት ዓመት የትርፍ መጠኑን አንድ ቢሊዮን ብር በማድረስ ቀዳሚ የግል ባንክ መሆን መቻሉን ባለፈው በጀት ዓመት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ከሁለቱ ባንኮች በተጨማሪ በግማሽ በጀት ዓመቱ ስድስት የግል ባንኮች ከ211 እስከ ሚሊዮን 300 ሚሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡

የግል ባንኮቹ በግማሽ በጀት ዓመቱ አስመዝግበዋል ከተባሉት ትርፍ ባሻገር ባሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብና ብድር መጠንም ዕድገት የታየባቸው ሲሆን፣ በ2009 ግማሽ በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን ከ170.06 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል፡፡ ይኼም ካለፈው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ደርሰውበት ከነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ጋር ሲነፃፀር ከ39.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

በ2008 ግማሽ በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኮቹ ደርሰውበት የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 130.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2008 ሙሉ በጀት ዓመት ደግሞ 146.2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ዓመቱን ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡

በብድር አሰጣጥ ረገድም ባንኮች የብድር ክምችታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ባንኮች በጥቅል የነበራቸው የብድር ክምችት 93.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ደግሞ የብድር ክምችታቸው 88.07 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2009 ግማሽ የበጀት ዓመት ግን ይህ የብድር መጠናቸው 116.17 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡ ይህም በግማሽ በጀት ዓመቱ ያበደሩት ብድር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የግል ባንኮች በ2008 የመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት የነበሯቸውን 1,728 ቅርንጫፎች፣ በ2009 ግማሽ በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 2,355 ማድረስ ችለዋል፡፡

 

Standard (Image)

ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበጀት ዕጥረትና የዕዳ ጫና ፈተና ውስጥ መሆኑን ይፋ አደረገ

$
0
0

   -  የዕዳ ክምችቱ 102.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል

   -  የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኪሳራ 1.8 ቢሊዮን ብር ነው

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የፋይናንስ እጥረትና የብድር ግዴታ ክፍያዎች የ2009 ዓ.ም. ፈተናዎች እንደሆኑበት፣ በይፋ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጸው፣ ለበጀት ዓመቱ 60.276 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ፍላጎት ውስጥ 10.5 ቢሊዮን ብር ወይም 31 በመቶው ብቻ ምንጩ እንደታወቀ ገልጿል፡፡

ለበጀት ዓመቱ የገንዘብ ፍላጎት ታሳቢ የተደረጉት 25.9 ቢሊዮን ብር ወይም 43 በመቶ ከውጭ አገር የፋይናንስ ምንጭ በብድር፣ ቀሪውን 34.3 ቢሊዮን ብር ወይም  57 በመቶ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሰብሰብ ነበር፡፡

ከውጭ ብድር ይገኛል የተባለውን እስካሁን አለማግኘቱን እንዲሁም ከአገር ውስጥ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 10.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ከየት ሊገኝ እንደሚቻል መታወቁን ገልጿል፡፡

ለተለያዩ የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮግራሞች ከተለያዩ አገሮች የተወሰደው ብድር ክምችቱ ከፍ ማለቱንና የብድር ወለድ መክፈል መጀመሩም ጫና ውስጥ እንደከተተው ገልጿል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ የሚመሩት ተቋም ያለበትን ሁኔታ ይፋ ቢያደርጉም፣ በዚያው ልክ ከተገባበት ፈታኝ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚወጣ እርግጠኝነታቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ዕዳ ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቅ ነበር ያሉት ዶ/ር ጌታቸው፣ ‹‹እንደዚህ ያለ ፕሮጀክት ውስጥ ደፍረን የገባነው መውጫ እንፈልጋለን በሚል መርህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የባቡር ሥራ ግም ባለ ቁጥር ችግር መጣ ብሎ የሚሮጥ ማኔጅመንት›› እንደሌለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ፕሮጀክቱ መፍትሔ ለመስጠት የተዘጋጀ አቅም ባለው ማኔጅመንት መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለዚህ ዓይነት ችግር ብቻ ሳይሆን ከዚህ በላይ ለሚመጡ ችግሮች ምላሽ የመስጠት በቂ አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከውጭ አገር ባንክ የተወሰደ ብድር ክምችት ከነበረበት 71.2 ቢሊዮን ብር ወደ ብር 76.37 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡

ከአገር ውስጥ ባንክ በቦንድ ሽያጭ የተወሰደ የረዥም ጊዜ ብድር በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 15.4 ቢሊዮን ብር ወደ 17.6 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱንም መረጃው ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ የዕዳ ክምችት በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረበት 95.97 ቢሊዮን ብር ወደ 102.52 ቢሊዮን ብር ማደጉን መረጃው ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የወለድና የግዴታ ክፍያ በየዓመቱ ለውጭ ባንኮች እየከፈለ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክትና ለተበደረው 2.5 ቢሊዮን ዶላር የወለድና የግዴታ ክፍያ መክፈል የጀመረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ግን ወደ ሥራ አለመግባቱ ይታወቃል፡፡

በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. 35.47 ሚሊዮን ዶላር ወይም 784 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ይገልጻል፡፡   

በጥር ወር 2009 ዓ.ም. 45 ሚሊዮን ዶላር ወይም 1.06 ቢሊዮን ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ይኼንን ግዴታውን ለመወጣት የውጭ ምንዛሪውም ሆነ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች በግልጽ አለመታወቁን መረጃው ያመለክታል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ የወሰደው 439 ሚሊዮን ዶላር ወለድና የዋና ብድር ክፍያ ከሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መክፈል የጀመረ ሲሆን፣ 28.93 ሚሊዮን ዶላር ወይም 685.46 ሚሊዮን ብር መክፈሉን መረጃው ያስረዳል፡፡ በጥር ወር ለዚሁ ብድር ወለድና የዋና ብድር ክፍያ 29.24 ሚሊዮን ዶላር ወይም 692.7 ሚሊዮን ብር መክፈል ያለበት ቢሆንም፣ የዚህ ገንዘብ ምንጭ እስካሁን አልታወቀም፡፡

በተመሳሳይ ለአዋሽ ወልዲያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ከቱርክ ኤግዚም ባንክ፣ እንዲሁም ከክሬዲት ስዊዝ የተገኘው 1.165 ቢሊዮን ዶላር ብድር የወለድና ግዴታ ክፍያ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. መክፈል ተጀምሯል፡፡ በተጠቀሰው ወርም 18.73 ሚሊዮን ዶላር ወይም 413.66 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ሲሆን፣ በጥር ወር ውስጥ ሁለተኛው ክፍያ 22.41 ሚሊዮን ዶላር 530.92 ሚሊዮን ብር መክፈል እንዳለበት ሲጠበቅ ምንጩ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡

በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በጥር ወር መክፈል የሚገባው የብድርና ዋና ወለድ ክፍያ 96 ሚሊዮን ዶላር ወይም 2.2 ቢሊዮን ብር የሚጠበቅበት ሲሆን፣ የዚህ ግዴታ የዶላርም ሆነ የብር ምንጩ ባለመታወቁ ከፍተኛ ሥጋት በኮርፖሬሽኑ ላይ መፍጠሩን መረጃው ያመላክታል፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ለቋሚ ኮሚቴው በዕዳ ጫናው ዙሪያ በሰጡት ምላሽ መፍትሔ እንዳላቸው በእርግጠኝነት የተናገሩ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. 2017 ፈተና እንደሚሆንባቸው ግን አልሸሸጉም፡፡

‹‹የ2018 መውጫ መንገድህ ምንድን ነው ካላችሁ የባቡር መስመሩን ከቱሪዝምና ከመሳሰሉት እሴት የሚጨምሩ ቢዝነስ ሥራዎች ጋር እናቀናጀዋለን፤›› ብለዋል፡፡

በምሳሌነትም መንግሥት ፖሊሲውን እንዲቀይር በማድረግ የደረቅ ወደብ ባለቤት መሆን እንደሚቻል፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚያልፍባቸው መስመሮች ላይ ተጓዳኝ ቢዝነሶችን በማልማት መወጣት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የከፋ ነገር ቢመጣ ደግሞ የኮርፖሬሽኑን የተወሰነ ድርሻ ለውጭ ኢንቨስተሮች በመሸጥ የዕዳ ጫናውን መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ያደነቀ ሲሆን፣ ያልተጠናቀቁ ቀሪ ሥራዎች በጂቡቲ መስመርና በቀላል ባቡር መስመር ላይ በፍጥነት እንዲያልቁ አሳስቧል፡፡

ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን የገንዘብ ችግሩ መፈታት እንዳለበትም እንዲሁ አሳስቧል፡፡ 

Standard (Image)
Viewing all 1275 articles
Browse latest View live