- የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተደጋጋሚ ትችታቸውን እያሰሙ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃውሞ ሠልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እየተጠቀመ መሆኑን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሰማንታ ፓወር ገለጹ፡፡
አምባሳደር ሰማንታ ፓወር በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አመራሮች ጋር ለመወያየት ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅት ለውጭ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ግልጽና ገለልተኛ በሆነ መንገድ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ እንዲመረመር ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በነፃነት የመሰብሰብ፣ ሐሳባቸውን የመግለጽና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የመግለጽ መብታቸውን መንግሥት ሊያከብር ይገባል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሰማንታ ፓወር የሰጡት አስተያየት ሰሞኑን በአሜሪካ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እየተገለጸ ካለው አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የሥራ ዘመናቸውን በቅርቡ ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሐስላክ፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውና መንግሥት የሁሉንም ድምፅ የመስማትና ተጠያቂ የመሆን ግዴታ አለበት ማለታቸውን ባለፈው እሑድ ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አያይዘውም በኢትዮጵያ ሕግን ያልተከተለ እስር ሊቆም እንደሚገባ፣ ኢትዮጵያ እንድትለማ ስኬታማና ጠንካራ እንድትሆን ሁሉም ድምፆች ተደማጭ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የሠራተኞች ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ቶም ማሊኖስኪ መንግሥት የዜጐቹን ደኅንነት መጠበቅ እንዳለበት እ.ኤ.አ. ኦገስት 21 ቀን 2016 በጻፉት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ማሰር፣ የሲቪክ ተቋማትን እንዳይንቀሳቀሱ በሕግ መገደብ፣ ሕዝብ ተቃውሞውን እንዳያነሳ እንደማያደርገው ይልቁንም መሪ የሌለው ተቃውሞን በመፍጠር መንግሥት የሚደራደረውና ቀውሱን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን ዕድል የሚያሳጣ ነው ብለዋል፡፡
