በጎንደር ከተማ ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡20 ሰዓት አካባቢ ከከተማው አውቶቡስ ተራ ወረድ ብሎ በተለምዶ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ፣ ከ400 በላይ የንግድ መደብሮች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ታወቀ፡፡
ረጅም ዕድሜ ማስቆጠራቸው የተገለጸው የአገር ባህል አልባሳት፣ የብረታ ብረትና የቅመማ ቅመም መሸጫ መደብሮች ሙሉ በሙሉ በቃጠሎው የወደሙ ቢሆንም፣ የእሳቱ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልታወቀ የጎንደር ከተማ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ አዳነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እሳቱ የተነሳው ባለመደብሮቹ ዘጋግተው ከሄዱ በኋላ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የከተማው ፖሊስና የሚመለከታቸው የፀጥታ ሠራተኞች እያጣሩ በመሆኑ፣ የወደመውንም ንብረት ዋጋ ለማወቅ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ችግሩ ከደረሰባቸው የንግድ መደብሮቹ ባለቤቶች ጋር ዓርብ መስከረም 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ውይይት ማድረጉን ገልጸው፣ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በመለየት፣ የከተማ አስተዳደሩ ለመርዳት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አቶ ሲሳይ አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ ምን መሆን እንዳለበት በውይይቱ ወቅት ስምምነት ላይ መደረሱንም አክለዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት ሁለት የከተማ አስተዳደሩ እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎችና የጎንደር ኤርፖርት የእሳት አደጋ መከላከል ተሽከርካሪዎች ባደረጉት የማጥፋት ጥረት እሳቱ ወደሌላ ሳይዛመት ባለበት እንዲቆም ማድረጋቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የንግድ መደብሮቻቸው በእሳት ቃጠሎው ከወደመባቸው መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለንብረቶች (ስማቸው እንዲገለጽ አልፈለጉም) እንደገለጹት፣ እሳቱ ሆን ተብሎ የተለኮሰ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በመደብሮቹ አካባቢ ሻይ ሲፈላ፣ ከሰል ሲቀጣጠልና የካውያ ሥራ ሲሠራ ምንም ደርሶ እንዳልነበር እየታወቀ መደብሮቹ ከተዘጉና ባለንብረቶቹ ከአካባቢው ከራቁ በኋላ ሊቃጠሉ የሚችልበት ምክንያት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
በእያንዳንዱ መደብር በትንሹ ከ200 ሺሕ በላይ የሚገመት ንብረት ሊኖር እንደሚችል የተናገሩት ባለንብረቶች በዝቅተኛ ግምት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል፡፡ በጎንደር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በመደብሮቹ ላይ ዘረፋ ይካሄዳል የሚል ሥጋት እንደነበራቸው ባለንብረቶቹ ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ሸዋ ዞን መቂ አካባቢ በሚገኙ የጨፌ እርሻ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዘረፋና ውድመት በሚሊዮኖች ብር የሚገመቱ የቲማቲም ምርቶች መውደማቸውን አልሚዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ በዚህም ሳቢያ በተከሰተ ግጭት አንድ ሰው ሲሞት በተወሰኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል፡፡ በመቂ አካባቢ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ሥጋት እየገባቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሰሞኑን ከእርሻዎቹ ወደ ዋና መንገድ የሚወስዱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በመቆፈር ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ምርታቸውን ለመላክ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
