ከ60 ዓመት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በነዳጅ ማከፋፈል ሥራ የተሰማራው ቶታል ኢትዮጵያ፣ በዱከም ከተማ በ270 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ ዘመናዊ የነዳጅ ዴፖ ገነባ፡፡
ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የዱከም ከተማ በ5.5 ሔክታር ቦታ ላይ በ270 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የሆነ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ መገንባቱን አስታውቋል፡፡ አዲስ የተገነባው የነዳጅ ዴፖ ስምንት ሚሊዮን ሊትር የተለያዩ የነዳጅ ዓይነቶችንና 200,000 ሊትር ቡታ ጋዝ የማጠራቀም አቅም እንዳለው ኩባንያው ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ዴፖው ዘመናዊ የኤታኖል ነዳጅ ማደባለቂያ ማዕከልና በኤሌክትሮኒክስ የሚሠራ የቡታ ጋዝ ሲሊንደር መሙያ ማሽን እንዳለው ተገልጿል፡፡
የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው የእሳት አደጋ ማንቂያና መከላከያ ማዕከል፣ የነዳጅ ፍሰት መጠቆሚያና አጠቃላይ የነዳጅ ዴፖውን እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ የኮምፒዩተር መሠረተ ልማት የተገጠመለት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ አገር ተገዝተው የተገጠሙት የነዳጅ ፍሰት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ደኅንነትን ለማስጠበቅና አካባቢን ከብክለት ለመከላከል እንደሚያስችሉ ተገልጿል፡፡
የነዳጅ ዴፖው ከፍተኛ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት፣ በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደርና የቶታል ኩባንያ ኃላፊዎች በተገኙበት መስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚመረቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1950 የተመሠረተው ቶታል ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባሉት 173 የነዳጅ ማደያዎች በ500 የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ በዓመት 700 ሚሊዮን ሊትር የነዳጅ ውጤቶች ያከፋፍላል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ካለው የነዳጅ ዴፖ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ቦሌ፣ መቐለና ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ኤርፖርቶች የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖዎች ባለቤት ነው፡፡
