Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የብረት ታሪፍ ጉዳይ ውዝግብ ቀሰቀሰ

$
0
0

በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተደራጅተው ሚስማር የሚያመርቱ ማኅበራት፣ ከግዙፎቹ ብረት አስመጪዎችና ሚስማር ፋብሪካ ባለቤቶች ጋር ተወዛገቡ፡፡

የውዝግቡ ማጠንጠኛ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ሚያዚያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥር ማኢ-30147/13 ባደረገው የታሪፍ ማሻሻያ፣ የአገር ውስጥ ሚስማር አምራቾች ግብዓቱን ከውጭ ሲያስመጡ ይሰጥ የነበረውን የሁለተኛ ስኬጁል ታሪፍ ማበረታቻ ማንሳቱ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ ታሪፉ በመነሳቱ ትርፋቸው በመቀነሱና በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር ፈጥሯል በሚል ምክንያት መንግሥት በድጋሚ የታሪፍ ማሻሻያ እንዲያደርግ ለመጠየቅ እርስ በእርሳቸው መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ባለሀብቶቹ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች የታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ለመንግሥት የሚቀርበውን ጥያቄ እንዲቀላቀሉና እንዲደግፉ ለማግባባት ሞክረዋል፡፡

ነገር ግን ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶቹ የባለሀብቶቹን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ይልቁኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ችግር በሚገባ እንዲያጤነው በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡

መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የብረት ገበያ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው አቶ ዮሐንስ አባዲ፣ አቶ ቢንያም ብርሃኔ እና አቶ ዘነበ ፍሬው ወጣቶቹን ሚስማር አምራቾች ስብሰባ ጠርተው ነበር፡፡

እነዚህ ታዋቂ የቢዝነስ ሰዎች ብረት ከማስመጣት በተጨማሪ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ሲሆኑ፣ ይህንን ስብሰባ የጠሩት ለሚስማር ማምረቻ የሚሆነው ስታፋ ብረት ላይ የተጣለው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እንዲነሳ ለመንግሥት በ48 የፋብሪካዎች ስም ያለፊርማና ማኅተም ያቀረቡት ጥያቄ ባለቤት ያስፈልገዋል ስለተባሉ፣ ለዚህ ጥያቄ ባለቤትነት ለመስጠት እንደሆነ ታውቋል፡፡

ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ታሪፍ እንዲነሳ ከተደረገ የአገር ውስጥ ስታፋ አምራቾች ይህንን ምርት በመተው ወደሚያበረታታው ወይም የታሪፍ ከለላ ያለው የአርማታ ብረት ብቻ ስለሚያመርቱ፣ ‹‹የእኛን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል፣ እኛ ከአገር ውጭ ስታፋ አምራቾች እየገዛን ሚስማር የምናመርት በመሆኑና ከውጭ የምናስመጣበት የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ስለሌለን እንጎዳለን፤›› በማለት ጥያቄውን ሳይቀበሉ መቅረታቸውን ዓለማየሁ ጥላሁን ብረትና የብረታ ብረት ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ጥላሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹እኛ ባለን መረጃ የስታፋ ብረት አቅርቦትን የሚያጠናክሩ ፋብሪካዎች ወደ ምርት እየተሸጋገሩ ነው፡፡ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲም የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚደግፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹ አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች መንግሥት በብረት ዘርፍ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እንዲያጤን ጠይቀዋል፡፡ ድርጅቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ለስድስት መንግሥታዊ ተቋማትና ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ማኅበር ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ስብሰባ በእኛ ስም ቀጥታ ያለቀለት ስታፋ ብረት ከውጭ እያመጡ ለሚነግዱ አስመጪዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን በመገንዘባችንና የእኛንም ህልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ስለሚከት፣ እኛና ሠራተኞቻችንን ከሥራ በማፈናቀል ሜዳ ላይ የሚጥል በመሆኑ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ለማሳወቅ ተገደናል፤›› በማለት አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶቹ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስቲሊ አርኤምአይን ጨምሮ ሦስት ፋብሪካዎች ስታፋ ብረት ያመርታሉ፡፡ ሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች በዓመት 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶንና በኢስት ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የተቋቋመው ሼንዠን ስቲል ፋብሪካ በዓመት 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስታፋ ብረት የማምረት አቅም አላቸው፡፡

መንግሥት በአገር ውስጥ ስታፋ ብረት መመረት እንደጀመረ ቀደም ሲል ከውጭ ሲገባ ይሰጥ የነበረውን የታሪፍ ከለላ አንስቷል፡፡ ይህ የታሪፍ ከለላ በመነሳቱ ከውጭ ስታፋ ብረት በማስገባት ሚስማር ሲያመርቱ የቆዩ ፋብሪካዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡

ከውጭ ስታፋ ብረት አስገብተው ሚስማር ሲያመርቱ የቆዩ ባለሀብቶች በተለያዩ ጊዜያት ለመንግሥት ያቀረቡት ቅሬታ በተለይ ስቲሊ አርኤምአይ አስመን የተባለ ሚስማር የሚያመርት እህት ኩባንያ ያለው በመሆኑ፣ ሞኖፖሊ ይፈጥራል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ያንፀባርቃሉ፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ኢንስቲትዩት የግብይት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ካሳ ይህንን ሥጋት አይቀበሉትም፡፡ ይልቁኑም መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾችን የበለጠ ማበረታታት እንዳለበትና በንግድ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊገቡ እንደሚገባ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ከካንትሪ ሚስማር ፋብሪካና ከሰኒ ሚስማር ፋብሪካ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡           

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles