Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የነዳጅ ኩባንያዎች የትርፍ ሕዳግ እንዲጨመርላቸው ግፊት እያደረጉ ነው

$
0
0

-  ነዳጅ መቀየጥ አሳሳቢ ሆኗል

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የነዳጅ ውጤቶች አከፋፋይ ኩባንያዎች በነዳጅ ሽያጭ የሚታሰብላቸው የትርፍ ሕዳግ (ኮሚሽን) እንዲጨመርላቸው መንግሥትን እየጠየቁ ነው፡፡

እንደ ቶታል ኢትዮጵያ፣ ኖክና ኦይል ሊቢያ ያሉ ታዋቂ የነዳጅ አከፋፋዮች ለኩባንያዎችና ለሽያጭ ወኪሎች የሚከፈለው የአንድ በመቶ የትርፍ ሕዳግ አነስተኛ መሆን በመስኩ ያለውን ኢንቨስትመንት እንደማያበረታታ በመጥቀስ፣ መንግሥት የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመጎትጎት ላይ ናቸው፡፡ የቶታል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበር ኃላፊዎች ኩባንያው በዱከም ከተማ ያስገነባውን የነዳጅ ዲፖ ምርቃት በማስመልከት ሐሙስ መስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ መንግሥት የትርፍ ሕዳግ ክፍያ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ከማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቶታል አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ዤሮም ዴሻምፕስ በኢትዮጵያ ያለው የትርፍ ሕዳግ ከአፍሪካ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

የቶታል ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ላሲና ቱሬ በኢትዮጵያ ለኩባንያዎች የሚከፈለው የትርፍ ሕዳግ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጎረቤት ኬንያ፣ ኡጋንዳና ዛምቢያ ለነዳጅ ኩባንያዎች አሥር በመቶ የትርፍ ሕዳግ እንደሚከፈል ገልጸው፣ ቶታል ኢትዮጵያ በነዳጅ ሽያጭ ኮሚሽን ዙሪያ በዓለም አቀፍ ኩባንያ ጥናት አስጠንቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ለማዕድን ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርና ለንግድ ሚኒስቴር መላኩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን፡፡ በቅርቡ አንድ ዕርምጃ ይወስዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ሚስተር ዴሻምፕስ ቶታል ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጉን፣ ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ ኩባንያዎች በዲፖዎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና በነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ እያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ በአማካይ ለ30 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የነዳጅ ገበያውም ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ከ7 እስከ 10 በመቶ በማደግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የነዳጅ ገበያ ፍላጎት ለማሟላት ኩባንያዎች አዲስና ዘመናዊ ዲፖዎችና የነዳጅ ማደያዎች መገንባት እንዳለባቸው የገለጹት ዴሻምፕስ፣ አሁን ባለው ዝቅተኛ የትርፍ ሕዳግ ምክንያት ኩባንያዎች የሚያስፈልገውን ኢንቨስትመንት ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

የችግሩ መፍትሔ በመንግሥት እጅ መሆኑን የገለጹት ሚስተር ዴሻምፕስ፣ የነዳጅ ዋጋ በስምንት ሣንቲም ቢጨምር ወይም የትርፍ ሕዳጉ ወደ ሁለት ወይም ሦስት በመቶ ከፍ ቢል፣ ከአካባቢው አገሮች አማካይ የኮሚሽን ክፍያ ጋር ማመጣጠን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ይህ ከሆነ ኢንዱስትሪው በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 300 ማደያዎች በመገንባት ለ10,000 ዜጎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ነዳጅ መቀየጥ ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡ የቶታል ኢትዮጵያ ኃላፊዎች እንደተናገሩት አንዳንድ ሕገወጦች ነጭ ጋዝን ከቤንዚን ወይም ከናፍጣ ጋር ቀላቅሎ በመሸጥ በተሽከርካሪዎች፣ በኢንዱስትሪዎችና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ነጭ ጋዝ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በገጠርና በከተማ ለማብሰያነት የሚጠቀሙት በመሆኑ መንግሥት ድጎማ እንደሚያደርግለት ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ነጭ የጋዝ ዋጋ ከቤንዚንና ከናፍጣ በሊትር ሦስት ብር ቅናሽ ያለው በመሆኑ፣ ይህን ልዩነት ለመጠቀም ነጭ ጋዙን ከቤንዚንና ከናፍጣ ጋር በመቀላቀል እንደሚሸጥ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የነጭ ጋዝ እጥረት በተለያዩ ከተሞች መከሰቱን የገለጹት የቶታል ኃላፊዎች፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡

ወንጀሉ በተለያዩ ማደያዎች ጭምር እንደሚፈጸም ለማወቅ መቻሉን፣ ችግሩን ለመቆጣጠር ቶታል ኢትዮጵያ ‹‹የነዳጅ ዶክተር›› የሚል ፕሮግራም መጀመሩን አውስተዋል፡፡ የነዳጅ ጥራት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ ችግሩ በተገኘባቸው ማደያዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ እኛ በተናጠል የቶታል ማደያዎች ላይ ብቻ የምንሠራው ነው፡፡ እኛ እገሌ ይህን ያደርጋል ብለን መናገር አንችልም፡፡ ሌሎች ኩባንያዎች ተመሳሳይ ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ ችግሩን ለመንግሥት እናስረዳለን፡፡ አጠቃላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚችለው ግን መንግሥት ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ማሳወቅ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ በሚመጣ ነዳጅ ላይ የሚፈጸመው ሸፍጥ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፣ የዕርምት ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1950 የተመሠረተው ቶታል ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 173 ማደያዎች የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ በ500 የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ በዓመት 700 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንደሚያከፋፍል ተገልጿል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles