የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ አወጣጥና መንግሥትን በመቆጣጠር ተግባሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሊያሳትፍ ነው፡፡
የሚሳተፉት ፓርቲዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀሩ እንደሚሆኑና የታደሰ የምርጫ ቦርድ ምዝገባ ሠርተፊኬት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተቀምጧል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ሲቪክ ማኅበራትን በሕግ አወጣጥና በመንግሥት ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር ለማሳተፍ የሚያስችለውን ʻማኑዋልʼ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ፣ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብረሃ ተናግረዋል፡፡
በመተዳደርያ ደንባቸው መሠረት ጉባዔ ያላካሄዱ ፓርቲዎች በዚህ የፓርላማ ውይይት ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ የገለጹት አቶ አማኑኤል፣ የሚሳተፉትም የታደሰ ሠርተፊኬት ሊያመጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህም ማለት ምርጫ ቦርድ በሕጉ መሠረት ጉባዔ የማያካሂዱ ፓርቲዎችን ይሰርዛል ማለት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ፓርላማው ቢያንስ በዓመት ሦስት ጊዜ ከፓርቲዎቹ ጋር እንደሚወያይ፣ ነገር ግን ትልልቅ ጉዳዮች በሚኖሩበት ጊዜ ጥሪ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚደረገው ውይይትም ፓርላማው ዓመታዊ ሥራውን ሲጀምር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግማሽ ዓመት ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ እንዲሁም በመጨረሻ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሚያቀርበው በኦዲት ግኝትና በበጀት ላይ እንደሚሆን አቶ አማኑኤል አስረድተዋል፡፡
