እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ እንዲሆን ታስቦ ለውይይት የቀረበው የሰብዓዊ ድርጊት መርሐ ግብር አፈጻጸምን የሚከታተልና መንግሥት የሚወከልበት ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 26 እና 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርጊት ጋር በመርሐ ግብሩ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በርካቶቹ የቀረበውን የድርጊት መርሐ ግብር ተግባራዊነት በመጠራጠር ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ከጌዲዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የተወከሉት አሌሳ መንገሻ፣ ‹‹ዛሬ ጥያቄው የተግባር ነው፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት በቃል እስከ ዛሬ ከተነገረው በላይ በተግባር እንዲሆን ይፈለጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በበኩላቸው የድርጊት መርሐ ግብሩ የዘገየ ቢሆንም መዘጋጀቱን ተቀብለው አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር አፈጻጸም ምክር ቤት›› እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብሩ አጥጋቢ ሆኖ እንዳላገኙት የጠቀሱት ደግሞ ከሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ የተወከሉት አቶ ሉምባ ደምሴ ናቸው፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በአጠቃላይ የሚመነጨው አገሪቱ ከምትከተላቸው ፖሊሲዎች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኢኮኖሚ መብቶች ጥሰት የሚመነጨው አገሪቱ በምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለማሳያነትም በድርጊት መርሐ ግብሩ ላይ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትን በተመለከተ ቢታቀድም፣ ይህ ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ ሊሳካ የሚችለው የመሬት ፖሊሲው መከለስ ሲችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዝግ የሆነ የመሬት ፖሊሲ ተይዞ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ለመመለስ መጣር የሚጋጭ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ከሊዝ ነፃ ዜጎች መሬት የማግኘት መብት ሲያገኙ ነው የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት የሚከበረው እንጂ ስለኮንዶሚኒየም በማቀድ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው፣ የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዱን ሙሉ ለሙሉ እንዳነበቡት ጠቁመው፣ ‹‹የማነበው ግን ስለሌላ አገር ነው የመሰለኝ፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹የምናወራው ስለሌላ አገር ካልሆነ በስተቀር በ150 ገጾች ተዘርዝሮ የቀረበውን የድርጊት መርሐ ግብር ሊያስፈጽም የሚችል ተቋም አለ ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የሲቪክ ማኅበራት በተዘጉበትና የዴሞክራሲ ተቋማት በተዳከሙበት፣ ነፃ ፕሬስ በሌለበት ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን በራሱ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚዳርግ በመሆኑ በተጋላጭነት ከሚጠቀሱት ሴቶችና ሕፃናት ቀጥሎ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚል እንዲካተትላቸው ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የድርጊት መርሐ ግብሩ አፈጻጸም ክትትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ ጠቃሚ የሚባሉትን ነጥቦች በሰነዱ ለማካተት እንደሚጥሩ አስረድተዋል፡፡
በፓርላማ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በተመሳሳይ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች ከውይይቱ እንደተገኙ ገልጸው፣ መታረም አለበት ያሉትንም ጠቁመዋል፡፡ ይኸውም በዋናው የውይይቱ አጀንዳ ላይ ሐሳብ ከመሰንዘር ይልቅ የፖለቲካ ክርክር ውስጥ መግባት የመፈለግ አዝማሚያ መቅረት እንዳለበት፣ ምክንያቱም ለፖለቲካ ክርክር ራሱን የቻለ መድረክ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
